እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!
በመዝሙር ስም ዘፈን! እስከ መቼ?
የተከበራችሁ የዚህ ድረ ገጽ ታዳሚዎች እንደምን ሰነበታችሁ?
ባለፈው ክፍል አምስት ጽሁፋችን ‹‹በቀጣይ ሌላውን የክህደት መጽሐፋቸውን እንመለከታለን›› ብለን በይደር እንዳቆየነው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ወደ ሌላው መጽሐፋቸው ከመሄዳችን በፊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናቸንን በእጅጉ እየተፈታተናት ስላለው የመዝሙር ሁኔታ ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በጻድቁ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ከፈጣሪዋ ከልዑል እግዚአብሔር ልዩ የሆነ የዜማ ጸጋ ተሰጥቷታል፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያዊው አባታችን ቅዱስ ያሬድ ከቅዱሳን መላእክት የተሰጠውን ሰማያዊ ዜማ ተቀብላ መላውን አገልግሎቷን ትፈጽማለች ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷንና ሥርዓቷን ከአባቶች ወደ ልጆች ለማስተላለፍ እንዲሁ በልማድ ብቻ መቀጠሉ በቂ ስላልሆነ ከ1960ዎቹ አመታት ወዲህ ወጣቶችና ህጻናት በዕለተ ሰንበት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው እየተሰበሰቡ ስለ ሃይማኖታቸው
እንዲማሩ ‹‹መንፈሳውያን ማሕበራት›› ተቋቋሙ /ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበትን ቃለ ዓዋዲ የ1970 እትም ይመልከቱ/፡፡ የእነዚህ መንፈሳውያን ማሕበራት ስያሜ ከጊዜ በኋላ ‹‹ሰንበት ትምህርት ቤት›› በሚለው ተተክቶ እስከ አሁን እንጠቀምበታለን ፡፡ ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግጥምና ዜማቸው በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተዘጋጁ የአማርኛና የግዕዝ መዝሙሮችንና እንዲሁም በዓመቱ ውስጥ ለሚከበሩት ዐበይት በዓላት ተስማሚ የሆኑትን መዝሙራት (ወረቦች) እንዲያጠኑ በማድረግ ወጣቱ ከያሬዳዊ ዜማ ሳይወጣ እውቀቱ በሚፈቅድለት መጠን ፈጣሪውን እንዲያመሰግንበትና እንዲማርበት ሲደረግ ቆይቷል፡፡እንዲሁም ከዚህም በተጨማሪ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን የሰርክ ጉባኤያትን በማዘጋጀት ለምዕመናን ከምታቀርበው የወንጌል ትምህርት ጎን ለጎን በነዚሁ መዝሙራት ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑ እያደረገች ነው፡፡