Sunday, May 10, 2015

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል ስምንት

በስም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከሐሰተኛው ‹‹መምህር›› ተጠበቁ!

የተከበራችሁ አንባብያን!

“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፡ ከእሾህ ውይን ክኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን ? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፡፡ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል፡፡”ማቴ.7፤15-18 የሚለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክፍለ ትምህርት መነሻ ርዕስ አድርገን ባቀረብነው ተከታታይ ጽሁፍ ፤ መናፍቃን /ተሐድሶ ነን ባዮች/ በውስጥም በውጭም ሆነው በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችን ላይ እየዘሩ ያሉትን የኑፋቄ እንክርዳድ በተመለከተ እያንዳንዱ ምዕመን ቢያንስ እራሱን ከስህተት ትምህርታቸው ለመጠበቅ የሚያስችለውን ያህል መጠነኛ ገንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረናል፡፡ወደፊትም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንቀጥላለን፡፡

ለዛሬው ስለ አንድ የውስጥ መናፍቅ የኑፋቄ ሥራ እንመለከታለን፡፡


ቁጥር--045/መሰ/04
ቀን--የካቲት 7 ቀን 2004 ዓ.ም

ለገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ኰኲሐ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት
ከየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል መልአከ ሰላም ሰንበት ት/ቤት
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፦ መረጃ መስጠትን ይመለከታል
በቅድሚያ መንፈሳዊ ሰላምታችንን እናቀርባለን፡፡

     የበግ ለምድ ለብሰው ውስጣቸው ግን ተኩላ የሆኑ መናፍቃን ባለንበት ዘመን በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተመሳስለው በመግባት ምዕመናንን ሲያታልሉ በተለያየ ጊዜ መያዛቸው የሚታወስ ነው፡፡ነገር ግን በአንድ አጥቢያ ቤ/ክ ሲጋለጡ ወደ ሌላ አጥቢያ ቤ/ክ በመሄድ የኑፋቄ ስራቸውን ማከናወን አላቋረጡም፡፡በዚህ መሰረት ሰሎሞን ዮሐንስ የሚባል ግለሰብ በእኛ ሰንበት ት/ቤትና በተለያዩ ቦታዎች ከቅድስት ቤ/ክ ትምህርት ውጪ አስተምሮ በመገኘቱ የታገደ ሲሆን ፤ዛሬም በናንተ ገዳም መሰል የኑፋቄ ስራውን ለማስፋፋት እንደቀረበ፤ይህንንም ለመግታት በእኛ ዘንድ የነበረውን ቆይታና የታገደበትን ምክንያት የሚገልጽ መረጃ እንድንሰጣችሁ ጠይቃችኋል፡፡
ስለሆነም ግለሰቡ ከሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 1999 ዓ.ም ጀምሮ እንግዳ ትምህርት በሰንበት ት/ቤታችን በማስተማሩ በጉባዔ ተመክሮ መታገዱን እያሳወቅን ፤ይህንንም የሚገልጽ መረጃ በዚህ ደብዳቤ ሸኚነት መላካችንን እንገልጻለን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ጸንተን ለመኖር ያበቃን፡፡
ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያንም እንቅስቃሴ ይጠብቀን፡፡
ከመንፈሳዊ ሰላምታ ጋር 
የየካ /ሣህል /ሚካኤል ሰንበት /ቤት ሊቀ መንበር
ፊርማ አለው፡፡


ከላይ በተጠቀሰው ደብዳቤ ላይ በዝርዝር ከቀረቡት የሰሎሞን ዮሐንስ ኑፋቄዎች ዋና ዋናዎቹ/በአጭሩ/

ሀ/ በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፦

1. ‹‹ወደ ክርስቶስ እንዳንቀርብ የሚከለክሉን /የሚጋርዱን/ገድልና ተአምራት ናቸው፤ቃል ኪዳናቸውም ውሸት ነው››
2. ‹‹የነገረ ደህነት ትምህርት የሚጀምረው ከማርያም ሳይሆን ከኢየሱስ ነው››
3. ‹‹ጸሎተ ፍትሐት አያድንም፤አያስፈልግም››
4. ‹‹ኢየሱስ የሚለው ስም ነው ወይስ ማርያም የሚለው ስም ነው ያዳነን?››
5. ‹‹በመጽሐፍ ቅዱስ ማርያም በሚለው ስም ስምንት ሰዎች ስለተጠሩበት የማርያም ስሟ ልዩ አይደለም››
6. ‹‹ኢየሱስ የሚለውን ስም ልዩ የሚያደርገው በዚህ ስም ሌላ ሰው ስላልተጠራበት ነው ››
7. ‹‹ሰንበታትን ማክበር አይገባም››
8. ‹‹የዳንኩት በጾም ሳይሆን በማመኔ ነው›› /ጾም አይጠቅምም/
9. ‹‹የዲቁና ሥልጣን /በአጠቃላይ ሥልጣነ ክህነት /በዝሙት ምክንያት አይፈርስም››
10. ‹‹የክርስቶስ ደም አሁንም ያስታርቃል›› /ክርስቶስ አሁንም ያማልዳል/
11. ‹‹ግሸን ማርያምንና የመሳሰሉትን በአጠቃላይ ገዳማትን በመሳለም ይገኛል ተብሎ የሚነገረው ቃል ኪዳን አይጠቅምም፤ውሸት ነው›› 
12. "‹‹ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ›› በማለት ፋንታ ‹‹ኢየሱስ››ብለን ብንጠራው ምን ችግር አለው?"
13. ‹‹ቅዱሳን መላእክት ውሱን ናቸው፡፡ሁለት ሰዎች በእኩል ሰዓት ቢጸልዩ ለአንዱ ሰው ሲገለጡ ለአንዱ ግን በረድዔት ይረዱታል፡፡››
14. ‹‹አንድ ሰው ርኩስ መንፈስ ሲያስጮኸው መጽሐፍ ቅዱስ ከማደረግ ይልቅ ገድልና ድርሳን ያደርጋሉ››
የሚሉና የመሳሰሉት የክህደት ትምህርቶች ሲሆኑ፤
15. ከላይ ለተዘረዘሩትና ለሌሎቹም የክህደት ትምህርቶቹ እንደ ምንጭ የሚጠቀምበት መጽሐፍ ‹‹የተቀበረ መክሊት›› የተባለ የተሐድሶ መጽሐፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ማስታወሻ - "የተቀበረ መክሊት" የተባለው መጽሐፍ አዘጋጁ አግዛቸው ተፈራ ሲሆን እሱም ድርጅቱም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዙ ናቸው፡፡የበለጠ ለመረዳት በ2007 ዓ.ም በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ የተዘጋጀውን መድሎተ ጽድቅ(የእውነት ሚዛን) የተባለውን መጽሐፍ ይመልከቱ፡፡ 

ለ/ በገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን

በመቀጠል የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ኰኲሐ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ከላይ የተጠቀሰውን ደብዳቤና እንዲሁም ሰሎሞን ዮሐንስ በዚሁ በገዳመ ኢየሱስ የሰራውን ስህተት የሚያሳይ የጽሁፍ፤የድምጽና የምስል መረጃና ማስረጃ ለገዳመ ኢየሱስ ቤ/ክ ሰበካ ጉባኤ በማቅረባቸው 9 የሰበካ ጉባዔ አባላትና 12 የሰ/ት/ቤት አባላት በተገኙበት በየካቲት 25 ቀን 2004 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ ጉዳዩ በጥልቀት ከተመረመረ በኋላ ግለሰቡ ከሥራ ታገዶ፤ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ግን ሥልጣኑ የሊቃውንት ጉባዔ በመሆኑ አለ የተባለው መረጃም ሆነ ማስረጃ በሙሉ ወደ ሊቃውንት ጉባዔ እንዲላክ፤ይህንንም ጉዳይ ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ሁለት ሰዎች ተመርጠው የእለቱ ስብሰባ ተጠናቋል፡፡ 

እንግዲህ በነዚህ በሁለቱ አድባራትና በሌሎችም የነበረው ሁኔታ ይህንን ሲመስል፤የሊቃውንት ጉባዔ ጉዳዩን አጥንቶ የግለሰቡን የእምነት ክህደት ቃሉን ተቀብሎ፤ስህተቱን ከልቡ አምኖ ከተቀበለ ተመክሮና ቀኖና ተሰጥቶት አገልግሎቱን እንዲቀጥል፤ስህተቱን ካላመነና ከልተጸጸተ ደግሞ ተወገዞ መለየት ሲገባው፤ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንዲት መሆ ተዘንግቶ ያንኑ የጥፋት ተልእኮውን እንደያዘ በደብረ ፍስሃ መካነ ሰማዕት ቅ/ቂርቆስ ቤ/ክ ‹‹በሰባኬ ወንጌልነት››ተመድቦ የተሰለፈለትን የምንፍቅና ሥራውን አጠናክሮ እየሰራ ይገኛል፡፡/በዚህ ደብር ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ/

ሐ/ በደብረ ፍስሃ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን

በዚህ ደብር እያደረገ ያለውን ሁኔታ ወደፊት የምናየው ሲሆን፤ይኸው ግለሰብ የጀመረውን የማጭበርበር ሥራ እንደልቡ ለመቀጠል እንዲመቸው በማያምንበት የአርቶዶክስ ተዋሕዶ ሥርዓተ ተክሊል በደብረ ናዝሬት ቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም የጋብቻ ሥርዓቱን አከናውኗል፡፡እዚህ ላይም ‹‹ከሚያገለግልበት›› ከቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ዮሴፍን ቤተ ክርስቲያን ለምን መረጠ የሚል ጥያቄ መነሳቱ የግድ ነው፡፡በዚህና በሌሎቹም ጉዳዮች ዙሪያ በሌላ ጊዜ እንመለሳለን፡፡

ለዛሬው ይቆየን፡፡

ይቀጥላል፡፡

No comments:

Post a Comment