Wednesday, August 15, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ. ፯፥፲፮ (7፥16) ክፍል አርባ ሦስት

ከክፍል አርባ ሁለት የቀጠለ፦
የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት!
      ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡በዚህ ክፍል ደግሞ የዶግማና የቀኖና ጥሰትን በተመለከተ "www.emenetsion.blogspot.com"ከተባለው የጡመራ መድረከ ያገኘነውን በሦስት ክፍል የተዘጋጀ ጠቃሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክት በትዕግስት እንድትመለከቱት እንጋብዛለን፡፡
ጽሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማድረግ ውጪ የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡
መልካም ንባብ!

Tuesday, August 7, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ. ፯፥፲፮ (7፥16) ክፍል አርባ ሁለት

ከክፍል አርባ አንድ የቀጠለ፦
የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት!
       እንኳን በጉጉት ለምንጠብቃት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የፍልሰቷ መታሰቢያ ጾም በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን፡፡ሁላችንም እንደምናውቀው እመቤታችን በጥር ሃያ አንድ ቀን ባረፈች ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የከበረ ሥጋዋን በገነት ውስጥ በምትገኝ በዕፀ ሕይወት ዛፍ ሥር አኑረውት ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይቶ፤በነሐሴ አስራ ስድስት ቀን ልጅዋ ወዳጅዋ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋንና ነፍሷን አዋሕዶና አስነስቶ በቅዱሳንና በመላእክት ምስጋና ታጅባ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንድትገባ አድርጓታል፡፡ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ክብር ያላት እመቤታችን የአምላክ እናት እንደመሆኗ መጠን ትንሣዔ ዘጉባዔን መጠበቅ ሳያስፈልጋት ከሰው ልጆች ሁሉ ቀድማ መንግሥተ ሰማያት መግባቷ፤ በልጅዋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነትና በእርሷ አማላጅነት ለምንታመን ለሁላችንም የተጠበቀልን ታላቅ ተስፋ እንዳለን ያረጋግጥልናል፡፡ስለሆነም እኛም የእመቤታችን የአሥራት ልጆች፤በተለይም እትዮጵያውያን፤ ከአባቶቻችን ከሐዋርያት በተቀበልነው ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ እስከ ነሐሴ አስራ አምስት ቀን ጾመን በአስራ ስድስተኛው ቀን የእመቤታችን የትንሣዔዋንና የዕርገቷን መታሰቢያ እናከብራለን፡፡
       ይህንን ታሪክ በማስመልከት በዚሁ የጡመራ ገጸችን ክፍል ሃያ ስድስት "በሊቀ ጉባዔ ጌታሁን ደምፀ" የተዘጋጀ፤በአጭር አቀራረብ ብዙ ትምህርት የሚያሰጨብጥ ጽሁፍ አስነብበናችሁ ነበር፡፡አሁን ያለንበት ወቅት ስለ እመቤታችን ብዙ የምነማርበት፣ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በጾምና በጸሎት ተወስነን በቃል ኪዳኗ የምንማጸንበት ወቅት ላይ ስለሆንን ይህንን የሊቁን ትምህርት አንብበን መንፈሣዊ እውቀታችንንና ሕይወታችንን እንድናጎለምስ ስለሚረዳን በድጋሚ አቅርበነዋል፡፡