Wednesday, August 15, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ. ፯፥፲፮ (7፥16) ክፍል አርባ ሦስት

ከክፍል አርባ ሁለት የቀጠለ፦
የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት!
      ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡በዚህ ክፍል ደግሞ የዶግማና የቀኖና ጥሰትን በተመለከተ "www.emenetsion.blogspot.com"ከተባለው የጡመራ መድረከ ያገኘነውን በሦስት ክፍል የተዘጋጀ ጠቃሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክት በትዕግስት እንድትመለከቱት እንጋብዛለን፡፡
ጽሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማድረግ ውጪ የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡
መልካም ንባብ!

የዶግማና የቀኖና ጥሰት በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ክፍል አንድ
       እንደሚታወቀው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ አሁን እኛ አለንበት ዘመን ላይ የደረሰችው፤ ዘመን ከሚወልደው ሥርዓተ ማህበር ጋር እየተለዋወጠች ሳይሆን ከፈጣሪዋ በተሰጣት በማይናወጥ እምነት ጸንታ በመቆየቷ ነው፡፡ለእምነቷ መጠበቅ ደግሞ የሥርዓቷ (የቀኖናዋ) አጥርነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡አጥር የሌለው ቤት የእንስሳውም የአራዊቱም መፈንጫ እንደሚሆን ሁሉ፤ የሥርዓት (የቀኖና) መፋለስም በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ የእምነት ተፋልሶን ያስከትላል፡፡ ቀደም ባሉት የአገራችን የኢትዮጵያ ታሪኮች የአገሪቱ መሪዎች እራሳቸው ክርስቲያኖች ስለነበሩና ሀገር የመምራቱንም ሥልጣን የሚረከቡት፤ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ቃለ መሐላ ፈጽመው ስለነበር፤ሥጋ ለባሽ እንደመሆናቸው የተለያየ ስህተት ቢሰሩም ቤተ ክርስቲያኒቱን አክብረውና አስከብረው ኖረዋል፡፡
       1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከ አሁን ያሉት የአገሪቱ መሪዎች ግን እራሳቸው ሃይማኖት የለሾች ከመሆናቸው ሌላ፤ "መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው" የሚል ህግ ቢያወጡም መንግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡በአንጸሩ ደግሞ እንደ ወንጌሉ ቃል "ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባናል" ብለው ለቤተ ክርስቲያኒቱን እምነትና ሥርዓት መጠበቅ እራሳቸው ጸንተው ምእመናኑን መጠበቅና በሃይማኖት ማጽናት የሚገባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ከተልእኳቸው ውጪ የመንግሥት ፈቃድ አስፈጻሚ እስከ መሆን ደርሰው እንደነበር እራሳችን እያየነው ስለሆነ ሌላ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡
       ከነዚህም ችግሮች ውስጥ አንዱ፤ በ1983 ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው ወርደው ወደ አሜሪካ አገር እንዲሰደዱና በምትካቸው ሌላ ፓትርያርክ እንዲሾም መደረጉ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና አብረዋቸው የተሰደዱት ጳጳሳት "ምንም በስደት ላይ ብንሆንም በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ህጋዊው ሲኖዶስ የእኛ ነው፤ ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ መሾም የለባችሁም " ሲሉ፤ በአገር ቤት ያለው ሲኖዶስ ደግሞ "ፓትርርኩም ሆኑ ሌሎቹ ጳጳሳት በግል ይሰደዱ እንጂ "ሲኖዶስማ አይሰደድም ህጋዊዎቹ እኛ ነን" እያሉ በመወዛገብና በመወጋገዝ ወደ 26 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ከዚህም ሌላ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ አህጉር የሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ በዘርና በምንፍቅና ምክንያት ያለው ልዩነት ሳይቆጠር በሦስት ተከፍለው ቆይተዋል፡፡አንዱ ክፍል በውጭው(በስደተኛው) ሲኖዶስ የሚመራ፣አንዱ በአገር ውስጥ ሲኖዶስ የሚመራና ሦስተኛው ከሁለቱም ያልሆነ ገለልተኛ አቋም ይዞ የሚያገለግል ነበር፡፡በዚህ ኢ-ክርስቲያናዊ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኒቱን  ምእመናን በተለይ በውጭ ሀገር ያሉት  እጅጉን ተፈትነዋል፡፡
       ከላይ በመግቢያው በጥቂቱ እንደተገለጸው፤ ለአቡነ መርቆሬዎስ መሰደድ ትልቁ ምክንያት በጊዜው የነበረው የመንግሥት ተጽእኖ ቢሆንም፤ቤተ ክርስቲያኒቱ የተፈጠረውን ችግር ተቋቁማ በራስዋ ህግና ሥርዓት መሠረት ተገቢውን ነገር ማድረግ ሲገባት፤ከመንግሥት ጋር ተባብራ ወይም ቀኖና ጥሳ፤ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ከአንድም የሁለት ፓትርያርኮች ሹመት ፈጽማለች፡፡አሁን ሰሞኑን በተደረገው ውይይት ግን ከላይ የተጠቀሰው ድርጊት የቀኖና ጥሰት ያስከተለ መሆኑ በሁለቱም በኩል ባሉት አባቶች ስለታመነበት፤ 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ መንበራቸው እንዲመለሱና  በሁለት ተከፍሎ የነበረው ቅ/ሲኖዶስ  ወደ አንድነት እንዲመጣ በመደረጉ፤ ከእኛ ከቤተ ክርስቲያኒቱ  ልጆች  አልፎ በእምነት ከእኛ ጋር አንድነት የሌላቸው ክፍሎች ሳይቀሩ የደስታችን ተካፋይ ሆነው ስንብተዋል፡፡
 የተከበራችሁ አንባብያን! ይህ በሰፊው እንድንወያይበት ወደመረጥነው ርዕስ ዝርዝር ሃሳብ ከመግባታችን በፊት፤ ከ"ሐራ ተዋሕዶ " የጡመራ መድረክ ያገኘነውን  "የዕርቀ ሰላም ስምምነት" ሙሉ ቃል እንድትመለከቱ እንጋብዛለን፡፡
"ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ስምምነት"
1. ስለ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፤
 በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የመንግሥት ለውጥ የተነሣ አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለሁለት ተከፍላ በሁለት ፓትርያርኮች የሚመሩ አንድ ሲኖዶስ ለሁለት ሲኖዶሶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። በዚህም የተነሣ አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በስደት ዓለም መቆየታቸው ይታወቃል። ስለኾነም የሁለቱን ቅዱሳን ፓትርያርኮች ቀጣይ ኹኔታ በተመለከተ በሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶሶች የተወከሉት የሰላም ልኡካን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትና ሰላም በአደረጉት የጋራ ስብሰባ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ እንደሚከተለው በአንድ ድምፅ ወስነዋል።
 ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፓትያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት አገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ/እንዲገቡ፤
 ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አገር ቤት ኢትዮጵያ ሲመለሱ በክብር የሚያርፉበትን የመኖሪያ ቦታ በተመለከተ ደረጃውን የጠበቀ በመንበረ ፓትርያርክ ግቢ ውስጥ ቦታ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤
 ሐ/ የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
 1.1/ ስለ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤
 ሀ/ በሕገ ቤተ ክርቲያን መሠረት የአስተዳደር ሥራውን በመሥራት ቅድስት ቤተ ክርስቲንን እንዲመሩ፤
 ለ/ ጸሎት እና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
1.2/ የሁለቱም ቅዱሳን ፓትርያርክ አባቶቻችን ስም በቅደም ተከተል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአለችበት ዓለም ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ፤
 1.3/ ሁለቱ ቅዱሳን ፓትርያርኮች በሕይወተ ሥጋ እስከ አሉ ድረስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በእኩልነት የአባትነት ክብራቸውን ጠብቃ እንድትይዝ፤
 1.4/ይህ ስምምነት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ፣ የአገር ቤትና የውጭ አገር ሲኖዶስ የሚለው ስም ቀርቶ አንዲት ቤተ ክርስቲያንና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንዲኾን፤
 2. ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፤
 ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት የተነሳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈተና ላይ ወድቃለች። ይህም ይታወቅ ዘንድ ሁለተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት እንደ ተፈጸመ በልኡካኑ ታምኖበታል። ስለኾነም ለአለፉት ዘመናት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መብትና ክብር በመጠበቅና በማስጠበቅ በውጭም ኾነ በውስጥ በአገር ቤት የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉና ከጊዜው ጋራ አብሮ በመሔዱ፣ ስለተፈጸመው ጥፋትና ለዘመናት በቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየት የተነሣ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልጆች ያለፉትንም ኾነ ዛሬ ላይ ያሉትን በጋራ ይቅርታ እንዲጠይቅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።
 ስለኾነም ከሁለቱም ሲኖዶስ መዋሐድ በኋላ ያለፈው የቀኖና ጥሰት ስሕተት ለወደፊቱ እንዳይደገም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ሉዓላዊነት ተጠብቆና ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረገ ደንብ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲዘጋጅ የልኡካኑ ጉባዔ በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል።
 3. ስለ ነባር ሊቃነ ጳጳሳት፤
 ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትን በተመለከተ በሁለቱ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት በጋራ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተፈቶ ስማቸውና ክብራቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት እንዲመደቡና እንዲያገለግሉ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል።
 4. ከልዩነት በኋላ ስለተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳት፤ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፤
 ከልዩነት በኋላ በሁለቱም ወገኖች የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ፦ ስማቸውን እንደያዙ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀበላቸውና በውጭ ዓለምም ኾነ በሀገር ቤት በሀገረ ስብከት ተመድበው እንዲያገለግሉ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ተስማምቶአል። ስም አጠራራቸውንም አስመልክቶ እንደ ሹመት ቅደም ተከተላቸው ቀዳማይ፣ ካልዓይ፣ ሣልሳይ… ወዘተ እየተባሉ እንዲጠሩ ጉባዔው በአንድ ድምፅ ወስኖአል።
 5. ስለ ቃለ ውግዘት፤
 በተፈጠረው ችግር ምክንያት በሁለቱም ሲኖዶስ ቃለ ውግዘት እንደ ተላለፈ ይታወቃል። ስለሆነም ከዚህ ስምምነት በኋላ ቃለ ውግዘቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንዲነሣ የሰላም ልዑካኑ በአንድ ድምፅ ወስኖአል።
 6. በውጭ ዓለም በስደት የምትገኘውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ ያገናዘበ መዋቅራዊ አስተዳደርን ስለማዘጋጀት፤
 እንደሚታወቀው በዘመናችን በየትኛውም ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በአሉበት ሁሉ ተስፋፍታ ትገኛለች። ይኹን እንጂ በውጭ ዓለም የምትገኝ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋራ አንድነቷን፤ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክብሯን ጠብቃ መኖር እንዳለባት ጉባዔው አምኖበታል።
 ስለኾነም የየሀገሩን ሕገ መንግሥት መሠረት ያደረገ የቃለ ዐዋዲውና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ገዥነት የሚረጋገጥበት መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያዘጋጅ ልኡካኑ በአንድ ድምፅ ወስኗል። እንዲሁም በውጭ ዓለም የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና በመዋቅራዊ አስተዳደር መሠረት ከአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በመቀበል በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንድትመራም ወስኖአል።
 በተጨማሪም በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል የተደረገውን የዕርቀ ሰላም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግና የሁለቱንም ሲኖዶስ መዋሐድ ፍጹም ለማድረግ እንዲሁም በስደት የሚገኙ ብፁዓን አባቶች ወደ እናት አገራቸው ተመልሰው፥ የቀደመውን ሰላምና አንድነት አጽንተው፥ ሁሉም በአንድ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተዳደሩበትን ቅድመ ኹኔታ የሁለቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡካን እንዲያዘጋጁና እንዲከታተሉ የሁለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ልኡክ በአንድ ድምፅ ወስኗል።
 ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም.
ዋሽንግተን ዲሲ
       የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ከላይ በመግለጫው ከሰፈሩት ሃሳቦች ውስጥ አጽንኦት ስጥተን ልንወያይባቸው ይገባል የምንላቸውን ሃሳቦች እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣዩ ክፍል ይዘን እንቀርባለን፡፡ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሔ የሚገኘው በጾምና በጸሎት ጭምር ስለሆነ መልካሞቹን ቀኖች ለማየት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤
ክፍል ሁለት
       የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ፤ ለዚህ ጸሁፉ መነሻ ያደረገው፤የእርቅ ስምምነቱ በተካሄደበት በአሜሪካ አገር ዋሽንግተን ዲሲ ላይ፤ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ለአንድነቱ ማብሰሪያ የሆነው "ሲኖዶሳዊው የዕርቀ ሰላም ስምምነት"ን ነው፡፡ዓላማውም በስምምነቱ ላይ ከሰፈሩት ሃሳቦች ውስጥ የቤ/ክ ልጆች የሆንን ሁሉ አጽንኦት ስጥተን ልንወያይበትና ካህን ምእመን ሳይባል ከጾምና ጸሎት ጋር ከልብ በመሥራት፤ በአባባይ ሲዘበትባት የኖረችውን ቤተ ክርስቲያናችንን  ወደ ነበረችበት ልንመልሳት ይገባል ብሎ ያመነበትን ፍሬ ሃሳብ ለማቅረብ ነው፡፡   መግለጫው በስድስት ነጥቦች ተከፍሎ የተቀመጠ ሲሆን ለዛሬው ውይይታችን የፈለግነው በተራ ቁ.2 "ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት" ከሚለው ርዕስ ውስጥ ፤
ሀ/ "የቀኖና ጥሰት...ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን"
ለ/ "ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን አለመወጣቱ"
መ/ "በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቤ/ክ ልጆች…ይቅርታ እንዲጠይቅ" …..በሚሉት ላይ ሃሳቦች ላይ ሲሆን፤ በቅደም ተከተል ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡
       ወደ ዋናው ሃሳብ ከመግባታችን በፊት ስለ ፓትርያርክ ሹመት፤ የህግና የሥርዓት ባለጸጋ የሆነችው ቅድስቲቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን፤ "ፍትሐ ነገሥት" በተባለው የሥርዓት መጽሐፍ፤ ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አራት ላይ፤ "በአንድ ዘመን በአንድ ወንበር ሁለት ሰዎች ሊሾሙ አይገባም…..በአንድ ሀገር ሁለት ሰዎች ተሹመው ቢገኙ አስቀድሞ ለተሾመው ሰው ትጽናለት" የሚለውን ቁልጭ ያለና የማያሻማ ቃል በአንክሮ ልንመለከተው ይገባል፡፡
 ሀ/ "የቀኖና ጥሰት"
       ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን የፍትሐ ነገሥቱን ህግ ይዘን ወደ ዕርቀ ሰላም ስምምነቱን ሃሳብ ስንሄድ፤ በአንድ በኩል 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከመንበራቸው መሰደዳቸውና እሳቸው በሕይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ በመሾሙ የቀኖና ጥሰት ስለተፈጸመ እሳቸው ወደ መንበራቸው ተመልሰው ቡራኬ እየሰጡ እንዲቀመጡ ሲወሰን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ቀኖና ተጥሶ ለተሾሙት 6ኛው ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ማትያስ ተገቢው ቦታ መስጠት ፋንታ ፓትርያርክነታቸውን እንደያዙ ቡራኬ መስጠቱንና የአስተዳደሩን ሥራ እንዲሰሩ የሚል ውሳኔ አሳልፎዋል፡፡ይህ አካሄድ ደግሞ "ተጣሰ"ተባለውን ቀኖና የሚያስተካክል ሳይሆን በሁለቱም በኩል ያለውን ፍላጎት ጠብቆ እርቁን እንደምንም ለመጨረስ ብቻ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ ቀድሞ በነበረው ላይ ሌላ የቀኖና ጥሰትን አስከትሏል፡፡በእውነት ቀደም ብሎ የተጣሰውን ቀኖና ለማስተካከል ታስቦ ቢሆን ኖሮ፤ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ በእድሜም መርዘምም ሆነ በሕመም ምክንያት መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የፓትርያርኩ እንደራሴ ሆነው ይሰሩ እንደነበረው፤ዛሬም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ተገቢውን ሥራ ለማከናወን የማይችሉ ቢሆን እንኳን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሁን የሚሰሩትን ሥራ በፓትርያርክነት ሳይሆን በእንደራሴነት እንዲሰሩ መደረግ ነበረበት፡፡
       በሌላ በኩል  ደግሞ ምንም እንኳን ሁላችንም እርቁ በተከናወነበት ጊዜና ቦታ ባንገኝም፤ በህሊናችን እነሱ ወደ ነበሩበት ቦታ ተጉዘን ስንመለከተው፤ ስምምነቱን የፈጸሙት አባቶችና በአሸማጋይነት የተላኩት የኮሚቴ አባላት እርቁን እውን ለማድረግ፤ ከነበሩበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ስንመለከተው በጊዜው ከዚህ የተሻለ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ አይጠበቅባቸውም፡፡ምክንያቱም፤
አንደኛ/ የእርቁ ጉዳይ ለብዙ ጊዜያት ተሞክሮ ሳይሳካ በመቆየቱና፤ አሁንም በሁለቱም በኩል ያለውን ፍላጎት የሚያሟላ ውሳኔ ካልተወሰነ በስተቀር ጉዳዩ ሊሰምር አይችልም የሚል ስጋት በሁሉም ዘንድ ስለነበረ እንደምንም አቀራርቦ ለመጨረስ ሲባል፤
ሁለተኛ/ ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ የቤ/ክ አባቶችን "እናንተ ሰላምና አንድነት ፍጠሩና ለእኛም አርአያ ሁኑን" እያሉ ባለማሰለስ ሲያሳስቡ ቆይተው( የአባቶች ልብ ወደ ልጆች ስለ ዞረ) በመጨረሻም ስምምነቱን ለመፈጸም ሲኖዶሱን ወክለው ወደ አሜሪካ የሄዱትን አባቶችና የሽምግልና ኮሚቴ አባላቱን እርቁን በአጭር ጊዜ እንዲፈጽሙ በሰጡት ጠንከር ያለ መመሪያ ስለነበረ፤
ሦስተኛ/ በመጨረሻ እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርቁ በተፈጸመበት ሳምንት ለሥራ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ሄደው ስለነበር ሲመለሱም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስንና ሌሎቹንም ጳጳሳት አብረዋቸው እንዲመጡ ስለወሰኑ፤…ወዘተ፡፡
      አሁን እየሆነ ያለውን ነገር በዚህ ሚዛናዊ በሆነ አስተሳሰብ ተመልክተን፤ የአንድ ጎልማሳ ሰው እድሜ ያስቆጠረ ችግር ቅጽበታዊ በሆነ ሁኔታ ሊስተካከል ስለማይችል ሁሉንም በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል፤አባቶቻችንም ሁኔታዎች ሲረጋጉ ለዚህ መፍትሔ ያመጡልናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡በተቃራኒው ይህንን ተስፋችንን የሚያጨልሙና የተሰራውን ስህተት ትክክል የሚያስመስሉ ሃሳቦች መንጸባረቅ ጀመሩ፡፡ሁላችንም እንዳየነው ይህንን ሰላምና አንድነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማብሰር ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም  በሚሊኒየም አዳራሽ የተደረገውን ዝግጅት፤ወደ አዳራሹ ለመግባት እድሉን ያገኘው ከሃያ ሺህ በላይ የሆነ ሕዝብ፤ በቦታው መገኘት ያልቻሉትና ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉት ሁሉ ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮት ሲከታተሉት ነበር፡፡(በቤ/ክ ታሪክም ተመዝግቦ የሚቀመጥ መሆኑን ልብ ይሏል)
       በዚህ መካከል ከመርሐ ግብር መሪው "ታሪክ እራሱን ይደግማል፤ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ አብርሃና አጽብሃ የተባሉት ወንድማማች ነገሥታት በአንድ ዙፋን ነግሠው አገሪቱን ሲመሩ እንደነበር፤ ዛሬም ቤተ ክርስቲያናችን በአንድ መንበር ሁለት ፓትርያርኮች እንዲመሩ አድርጋለች፡፡" የሚል ጆሮ ጭው የሚያደርግ ንግግር ተሰማ፡፡ይህንን የእርቁን ስምምነት በፈጸሙት አባቶችና በአሸማጋዮቹ የመወሰን አቅም ማጣት የተነሳ የተሠራውን ስህተት፤ ከጉዳዩ ጋር የማይገናኝ ምሳሌ በማቅረብ ትክክለኛ አስመስሎ ለማሳየት መሞከር "በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ" እንደሚባለው የቀደመው የቀኖና ጥሰት በአግባቡ ሳይስተካከል አሁን ደግሞ ሌላ ያልነበረ ሕግ ቤ/ክ ላይ ተጫነበት ማለት ነው፡፡
       ምናልባት ሃሳቡ የተናጋሪው የግል ምልከታ ነው ቢባል እንኳን፤ ይህንን ትልቅ ጉባኤ እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው፤ በግል ሙያውም በቤ/ክ ታሪክ ተመራማሪነቱ የሚታወቅና ብዙ መጻሕፍትን ጽፎ ያበረከተ የሥነ ጽሁፍ ባለሙያ በመሆኑ፤ የንጉሥና የፓትርያርክ ልዩነት ይጠፋዋል ተብሎ ስለማይታሰብ፤ ማንም ሰው ሃሳቡን ስህተት ነው ብሎ ሊጠራጠር አይችልም፡፡እንግዲህ ይህ እንደ ዘበት የተነገረ እንግዳ ትምህርት በጊዜው ካልታረመ፤ ትውልዱ ለወደፊትም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በቤ/ክ በአንድ ዘመን ሁለትም ሦስትም ፓትርያርክ መሾም ይቻላል የሚል ትምህርት ይዞ ይቀርና ለቤ/ክ ሌላ ትልቅ የቤት ሥራ ተቀመጠላት ማለት ነው፡፡ከዚህም በተጨማሪ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እሳቸውና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲመተ ጵጵስናቸውን ከ3ኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት የተቀበሉት በአንድ ቀን መሆኑን በማውሳት፤ አሁንም ሁለቱም ፓትርያርክነታቸውን እንደያዙ ቤተ ክርስቲያንን መምራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ 
    እንግዲህ ይህንን ሁሉ ሁኔታ "ብልጥ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል" እንደሚባለው፤ቢያንስ የሲኖዶሱን አንድ መሆን እንደ ቀላል የሚታይ ስላልሆነ፤ ይህንን እያመሰገንንና ለሚቀረው ደግሞ እያለቃቀስን ብንነተወው እንኳን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በየትኛው የአስተዳደር ተሞክሮዋቸው ነው የአስተዳደሩን ሥራ የተረከቡት? መላዋን የኢትዮጵያን ቤ/ክ ይቅርና ልዩ ሀገረ ስብከታቸው የሆነውንና በመንበረ ፓትርያርኩ የተወሰነ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤትን እንኳን በአግባቡ መርተዋል ወይ? ቀደም ብለው የነበሩት የአ.አ.ሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ በሥራቸው ያሉትን የዋና ክፍል ሃላፊዎችን ጨምሮ ቤተ ክርስቲያን በምትጸየፋቸውና በምታወግዛቸው እንደ ሌብነት፣ዘረኝነት፣ምንፍቅናና በመሳሰሉት አስነዋሪ ድርጊቶች ተዘፍቀው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሌቦች፣የወንበዴዎችና የመናፍቃን  ዋሻ ሲያደርጓት፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህግ የሚዳኝ አባት ጠፍቶ፤ ካህናትና ምእመናን ለመንግሥት ባቀረቡት አቤቱታ ሥራ አስኪያጁና ግብረ አበሮቻቸው ሳይወዱ በግድ ከሃላፊነታቸው የተነሱት በመንግሥት ህግ ተገደው አይደለም ወይ? አሁን ደግሞ ከሲኖዶሱ አንድነት ወዲህ ሀገረ ስብከቱ ሰፍቶ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደሚያጠቃልል ይታወቃል፡፡እናም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  የአመራር አቅም ይዘለቃል ወይ ብለን ስናስብ፤ ለዚህ እረኛ አጥቶ እዚህም እዚያም ለተበተነው ምእመን ልዑል እግዚአብሔር የሚበጀውን ያምጣ ብሎ ከመጸለይ በስተቀር አማራጭ የለንም፡፡

የዶግማና የቀኖና ጥሰት በኢ/ኦ/ ተ/ ቤተ ክርስቲያን፤
 ክፍል ሦስት
       ባለፉት ሁለት ክፍሎች በስፋት እንደተመለከትነው፤በተደጋጋሚ "የቀኖና ጥሰት" እየተባለ የሚነገረው "ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም" በሚለው ዙሪያ ይሁን እንጂ፤ (እሱም ተወራለት እንጂ መፍትሔ አላገኘም) የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን መሠረተ እምነቷንና ሥርዓቷን ትውፊቷን ሳይቀር የሚሸረሽሩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች፤ዓይነታቸውና ብዛታቸው  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ከላይ የተመለከትነው የአባቶቻችን መግለጫ፤ "…..ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ተላልፈው ለሞት ከተሰጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን…" በማለት እውነታውን ፍንትው አድርገው አሳይተውናል፡፡እንደሚታወቀው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ 2ኛው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ እንደሆኑ፤ይህንን የፓትርያርክነት ሹመት ያገኙት በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ፤ ከዚያም ንጉሣዊውን ሥርዓተ መንግሥት በጉልበቱ አስወግዶ ሀገሪቱን በተቆጣጠረው ደርግ በተባለው ሃይማኖት የለሽ መንግሥት በግፍ ታፍነው እንደተገደሉ ታሪክ መዝግቦ አስቀምጦታል፡፡ቤተ ክርስቲያንም ምንም ዓይነት የፍትሕ ጥያቄ አለማቅረቧ ብቻ ሳይሆን ፤ቢያንስ አስከሬናቸው በተገቢው ሥፍራ በክብር እንዲያርፍ ሳታደርግ እንዲሁ "እንደ ንጉሡ አጎንብሱ" እንደሚባለው ሆኖ የደርግ መንግሥት እስከሚወድቅ ድረስ የከበረ አስከሬናቸው የነበረበት ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡
       እንግዲህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን  ለ40 ዓመታት ያህል ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷን ሥርዓቷን የሚያፋልሱ ብዙ ጥፋቶች እንደተፈጸሙባት ከታመነ፤ለማስተካከያውም ቅዱሳን አባቶች በሙሉ ኃይል በመነሳት፤በመጀመሪያ ችግሮቹን ነቅሶ ማውጣት፤ከዚያም ከራሳቸው ጀምሮ ታች እስካለው ምእመን ድረስ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ መንገዱን ማመቻቸት አለባቸው ማለት ነው፡፡የዚህ ጸሁፍ አዘጋጅ ዋና ዓላማ "በሽታውን የደበቀ መድኃኒቱ አይገኝለትም" እንደሚባለው፤የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በመጠኑ ለማሳየትና ሁላችንም እንደ ቤ/ክ ልጅነታችን አቅማችን የፈቀደውን እንድናደርግ ማሳሰብ ስለሆነ፤ በደርግ ዘመን የነበረውን ሰፊ ችግር ለማውሳት ርዕሳችን ስለሚያግደን፤ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ያለውን ችግር ብዙውን አንድ እያልን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
በውጪው( በስደተኛው) ሲኖዶስ በኩል፤
       ለስደተኛው ሲኖዶስ መመሥረት ዋናው መንስኤ፤ 4ኛው የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ወደ አሜሪካ አገር መሰደድ ነው፡፡አንዳንድ ሰዎች አቡነ መርቆሬዎስ በጎቻቸውን በትነው መሄድ አልነበረባቸውም እዚሁ መከራ መቀበል ነበረባቸው ሲሉ ይደመጣል፡፡ሆኖም ማንም ሰው መከራ የሚቀበለው እንደአቅሙና የእግዚአብሔርም ፈቃድ ሲጨመርበት  ስለሆነ፤ደግሞም ተወልደው ካደጉበት ተሹመው ከከበሩት (ያውም በቤተ ክርስቲያን) ሀገር ወደማያውቁት ሀገር መሰደድ እራሱ ሰማዕትነት ስለሆነ ለምን ይህን አላደረጉም ተብሎ ሊወቀሱ አይገባም፡፡የውጭውን ሲኖዶስ ሲመሩ የነበሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በግላቸው፤ በአፍም ሆነ በመጽሐፍ ይህን አደረጉ ተብሎ በጉልህ የሚነገር ችግር አልተሰማም፡፡(ምንልባት እኛ ያልደረስንበት ነገር ካልኖረ በስተቀር) ሆኖም እሳቸውን ተገን በማድረግ የቤ/ክ እምነትና ሥርዓትን የሚያፋልሱ አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ለመጥቀስ ያህል፤
1/ የተለያዩ መናፍቃን (ተሐድሶ)መሸሸጊያ መሆኑ፤
       ቤ/ክ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ከውስጥም ከውጭም በሚነሱ ሃይማኖት ለዋጮች ስትፈተን ኖራለች፡፡ቀደም ያለውን ችግር ለታሪክ ጸሐፊዎች ትተን አሁን እኛ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆንበት ጊዜ ወዲህ ያለውን ስንመለከት፤በመናፍቃኑ የተመረጠው ዘመን አመጣሹ ተዋሕዶ ቤ/ክንን ገዝግዞ የመጣያው ስልት፤ ከቤ/ክ ውጭ ሆኖ ምእመኑን ወደ ተለያየ አዳራሽ ከመጥራት ይልቅ ቤ/ክ ውስጥ ሆነው የራሳቸውን የኑፋቄ ትምህርት በድብቅ በማስተማር ጥንታዊውን የቤ/ክ ትምህርት ቀሰ በቀስ መቀየር ነው፡፡ይህም የጥፋት ተልእኮ የሚያራምደው ኃይል እራሱን ኦርቶዶክስ ተሐድሶ ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው፡፡ ብዙዎቹ የዚህ ዓላማ አራማጆች እዚህ አገር ውስጥ ባለችው ቤ/ክ ውስጥ ውስጡን ሲበርዙና ሲከልሱ ኖረው ሲታወቅባቸው፤ከመወገዛቸው በፊት ሾልከው ሄደው የሚጠለሉት በውጭው ሲኖዶስ ሥር ነው፡፡ከዚያም አልፎ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፕሮቴስታንቱ ድርጅት ገብተው እስከ ፓስተርነት ደረጃ የደረሱት ሳይቀሩ፡፡እነዚህ ሃሳውያን የውጪው ሲኖዶስ ለም መሬት ስለሆነላቸው የያዙትን የጥፋት ዓላማ እንደያዙ፤የቅስናና የመሳሰሉት የክህነት ማዕርጋትን፤ ከዚህም በላይ እጅግ በጣም የጎላ የሃይማኖት ህጸጽ ያለባቸውን ስመ መነኮሳት ጵጵስና እስከመሾም ደርሰው፤ይኸው አሁንም በእርቁ ሳቢያ አገር ውስጥ ገብተው አዲሱን ምደባ እየጠበቁ ነው፡፡
2/ ቤ/ክ ለአገልግሎት ከምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች ውጪ መጠቀማቸው
       ቤ/ክ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የምትጠቀምባቸው የዜማ መሣሪያዎች ይታወቃሉ፡፡ቀደም ሲል በቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ በኦርጋንና በፒያኖ እንዲዘመር ያደረጉት አባት (ጳጳስ) አሁን እዚያው ስደተኛው ሲኖዶስ ውስጥ ናቸው፡፡አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ ይህ መሣሪያ የዘፈን በመሆኑ በ1986 ዓ.ም ከቤ/ክ አውጥቶ ጥሎ ከዚያም በኋላ በየትም ቤ/ክ አገልግሎት እንዳይሰጥበት ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎዋል፡፡እዚያ ግን በማናለብኝነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡
አገር ውስጥ ባለው ሲኖዶስ በኩል
       ቤተ ክርስቲያን ማለት በጥምቀትና በቅ/ቁርባን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች የሆኑ ሁሉ በአንድነት የሚኖሩባት በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ስትሆን ፓትርያርኩን፣ ጳጳሳንት፣(ሲኖዶስን) ካህናትን፣ ዲያቆናትን፣ ምእመናንን አጠቃላ የያዘች ነች፡፡የምትመራበትም ራሱን የቻለ ህግና ሥርዓት አላት፡፡ቤ/ክ በበላይነት የመምራት ሙሉ ሃላፊነቱ የቅ/ሲኖዶስ መሆኑ ባይካድም፤አገልግሎቱ ሊሰምር የሚችለው ሁሉም በተፈቀደለት ሥርዓት መሠረት የየድርሻውን መወጣት ሲችል ነው፡፡ካህናት ከሌሉ ቤ/ክ እንደማትከፈት ሁሉ ምእመናንም ከሌሉ ቅዳሴ እንደማይቀደስ ማለት ነው፡፡
       ወደ ተነሳንበት ርዕስ እንመለስና፤ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ከውጪው ሲኖዶስ አንጸር ሲታይ፤ ሀገረ ስብከቱ ሰፊ ከመሆኑ አንጻር የአገልግሎቱ ደካማም ሆነ ጠንካራ ጎኖቹ የዚያኑ ያህል የሰፉ ናቸው፡፡በመሆኑም የዚህ ጸሁፍ አዘጋጅ ዓላማ፤ችግሮቹን ዓይነትና ብዛት ተመልክተን እርስ በርስ እየተተቻቸንና አንዳችን በሌላችን እያሳበብን እንድንኖር ሳይሆን፤ ለተፈጠሩት ችግሮች ይብዛም ይነስም የሁላችንም አስተዋጽኦ እንዳለበት አውቀን፤( ለምሳሌ መናፍቃኑ የሚያዘጋጇቸውን መዝሙሮች በገዛ ገንዘባችን እየገዛን ችግሩን ያስፋፋነው እኛ ምእመናን መሆናችን መዘንጋት የለብንም፡፡) ለመፍትሔውም የየራሳችንን ድርሻ ለመወጣት እንድንዘጋጅ ለማሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥለን ቀደም ሲል የነበሩትንና አሁንም ያሉትን ችግሮች በመጠኑ እንመለከታለን፡፡
1/ በ1988 ዓ.ም በፓትርያርኩ በአቡነ ጳውሎስ ትእዛዝና በሌሎች ጳጳሳትና መምህራን አዘጋጅነት  ምሥጢረ ሥላሴን፣ምሥጢረ ሥጋዌን፣ነገረ ማርያምንና የመሳሰሉትን ትምህርቶች የሚያፋልስ መጽሐፍ ታትሞ ለህዝብ እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡
2/ ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ (1600 ዓመታት ያህል) በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት በውግዘት ከተለየቻቸው የካቶሊክና የሁለት ባሕርይ አምላኪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፤በሥርዓተ ጸሎታቸውና በማዕዳቸው በመሳተፍ ቤ/ክ የማትፈቅደውን ተግባር ፈጸመዋል፡፡ከሳቸው ጀምሮ እስከ አሁን ባሉት አባቶችም በእኛና በካቶሊክ መካከል ያለው ልዩነት ትንሽ ነው እየተባለ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡
3/ በ1988 ዓ.ም፤ /ክ ለብዙ ዘመናት ስትመራበት የነበረውን ህገ ቤ/ክ ሽረው፤ የሲኖዶሱ ጸሐፊ ብሎም አጠቃላይ ሲኖዶሱ ተጠሪቱ ለመንፈስ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ ለፓትርያርኩ እንዲሆን የሚያደርግ ህግ አውጥተዋል፡፡
 4/ ጥር አንድ ቀን 1989 ዓ.ም በአዲስ አበባ ደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ክ ዓመታዊ በዓል ላይ ፓትርያርሁ አቡነ ጳውሎስና ሌሎችም ጳጳሳት በተገኙበት ዓውደ ምሕረት በታቦት ፊት አንድ ባህታዊ በፓትርያርኩ አጃቢ ሲገደል በዚያ በዓል ላይ የተገኙት በርካታ ምእመናን ተደብድበዋል፡፡በዚሁ ትርምስ ታቦቱን የተሸከሙት ካህን በመደንገጣቸው መቆም ስላልቻሉ፤ ሌላ ካህን ታቦቱን ተቀብሎ በሴቶች በር ይዞ በመግባት፤ምእመኑ ያለ ጸሎትና ያለ ቡራኬ እንባውን እየተራጨ ተመልሷል፡፡ለተገደለውም ሰው ቢያንስ በኢትዮጵያዊነቱ ፍትህ የጠየቀ የለም፡፡ስለሆነም ደሙ እንደ አቤል ደም እየጮኸ ይኖራል፡፡
5/ ምንም ዓይነት የቤ/ክ እውቀት ሳይኖራቸው፤ አንዳንዶቹ ገንዘብ ለመሰብሰብ ብቻ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሆን ብለው እምነታችንንና ሥዓታችንን ለማፋለስ፤ የሚያዘጋጇቸው ለቁጥር የሚታክቱ መጻሕፍትና መዝሙሮች እየታተሙ በቤ/ክ ስም ሲሰራጩ ለማስቆም ቀርቶ ለመከላከል ባለመሞከሩ፤የቤ/ክ እምነትና ሥርዓትን ከሌሎቹ እምነቶች  ለመለየት እስከማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡
6/ ከላይ በገለጽነው በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ አራማጆችና በሌብነት ሥራ በተሰማሩ ሃላፊዎች ምክንያት ሃይማኖታችን፣ሥርዓታችን ተበላሸ፣የቤ/ክ ሃብትና ንብረት የግለሰቦች መጠቀሚያ ሆነ ብለው የጠየቁና የተከራከሩ ካህናት፣ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ተገድለዋል፣ታስረዋል፣ከሥራ ተፈናቅለዋል…..ወዘተ፡፡ምሳሌ ቢባል በአዲስ አበባ ብቻ፤ በደብረ ናዝሬት ቅ/ዮሴፍ፣ በልደታ ለማርያም ፣በሰዓሊተ ምሕረት ፣በብሔረ ጽጌ ማርያም ፣በቅ/ኡራኤል፣በገርጂ ጊዮርጊስ፣በቀራንዮ መድኃኔዓለም፣ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤ/ክ…ወዘተ፡፡
7/ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላማ አራማጆች የጥፋት ተልእኮ በተመለከተ፤እኩይ ሥራቸውን ለሃይማኖታቸው ቀናእያን የሆኑ የቤ/ክ ልጆች እተከታተሉ፤ የሊቃውንት ጉባዔ ድረስ ማስረጃ ሲያቀርቡ፤ ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ በመስጠት ፋንታ በሌላ ደብር እየተመደቡ ችግሩ የበለጠ እንዲስፋፋ ተደርጓል፡፡ከዚህም በላይ ጥያቄ አቅራቢዎቹን የተዋሕዶ ልጆች አክራሪ፣ጽንፈኛ፣ሽብርተኛ፣አሳዳጅ….የሚል ስም እየተሰጣቸው በገዛ ቤ/ክናቸው እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ በማድረግ፤በአንጻሩ ደግሞ መናፍቃኑ ከአጥቢያ ቤ/ክ ጀምሮ እስከ መንበረ ጵጵስናው ድረስ ባለ ሙሉ መብት እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
8/ የፈለጉትን ያህል አጥፍተው መስሎ ማጭበርበሩ ሲሰለቻቸው በገዛ ፈቃዳቸው የወጡትም ሆነ  በግድ ተወግዘው የተለዩት የውስጥ መናፍቃን (ተሐድሶዎች) የቤ/ክ የማዕረግ ስም (ዲያቆን፣መምህር፣አባ፣ቀሲስ..)እየተባሉ፤ የአገልግሎት አልባሳት (ካባ፣ ቆብ፣ቀሚስ፣ ነጠላ፣መስቀል..)እንደለበሱ የማጭበርበር ሥራ ሲሰሩ የጠየቃቸው የለም፡፡
9/ እውነተኞቹ ሊቃውንትና አገልጋዮች እየተገፉ፤ ጉቦ መስጠት የሚችሉ፣ በዘርና በጎሳ የተሳሰሩ አፈ ጮሌ የሆኑ እውቀትና ሃይማኖት አልባዎች ወሳኙን የሥልጣን ደረጃ እንዲይዙ መደረጉና ፍትህ በመታጣቱ ለአቤቱታ ወደ መንግሥት አካልና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እስከ መሄድ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
10/ የቤ/ክ መምህራንን ቀጥራ፣ልብስ ቀለብ ችላ፣ትምህርቴን ተምረው የዘመኑን ትውልድ በፈሊጥ ያስተምሩልኛል ብላ ትልቅ ተስፋ የጣለችባቸው በእጣት በሚቆጠሩ መንፈሳዊ ኮሌጆች ከሚማሩ ተማሪዎች ውስጥ አንዳንዶቹ፤ ከክትትልና ከቁጥጥር ማነስ የተነሳ በድብቅ በሚሰጡ የመናፍቃን ሥልጠናዎች እየተበረዙ፤ወደ ኮሌጅ ሲገቡ መንፈሳውያን የነበሩት ተምረው ሲወጡ መናፍቃን ሲሆኑ ለዚህ ያበቃቸው ችግር ተጠንቶ መፍትሔ ባለመሰጠቱ ችግሩ ከዕለት ዕለት እየጨመረ ነው፡፡ከዚህም አልፎ መናፍቃኑ እግራቸውን አስረዝመው በተለያዩ የአብነት ጉባዔ ቤት በመግባት፤ በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ፤ያውም "ቋርፍ" የተባለ መራራ የዛፍ ሥር እየበሉ በሚኖሩበት በዋልድባ ገዳም ሳይቀር ገብተው የቅሰጣ ስራ እየሰሩ መሆኑ ከራሳቸው ሰነድ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡  
11የቤ/ክ ህንጻ በአጸራረ ሃይማኖተኞች በግሬደር ሲፈርስ፣ በእሳት ሲቃጠል፣ ቅርሶቿንና ንዋያተ ቅድሳቷን ሲዘረፉ፣የጥምቀትና የደመራ ማክበሪያ ቦታዎችዋ ሲወረሱ ተከራካሪዎቹ ምእመናን ብቻ ናቸው፡፡አገራችን ለዱር እንስሳት እንኳን ፓርክ ተዘጋጅቶ መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ስትሆን፤ ዓለም በቃን ብለው ጫካ የገቡ፤እንደ ሌላው ዜጋ የመብራት፣የውሃ የስልክና የመሳሰሉትን ፍጆታዎች የማይፈልጉ፤ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ቅጠል እየቀመሱ፤ እንደ ዋልድባ በመሳሰሉት ታላላቅ ገዳማት የሚኖሩ መናንያን በጫካ እንኳን የመኖር መብት ተነፍጓቸው ገዳማቸውን ለቀው እንዲሰደዱና እንዲበተኑ ከዚያም አልፎ እንዲታሰሩ ተደርጓል፡፡
12/ በአጠቃላይ እነዚህና የመሳሰሉት የውስጥና የውጪ ችግሮች በጋዜጣና በኢንተርኔት ለዓለም በመሰራጨታቸው ቤ/ክ ለመናፍቃንና ለአሕዛብ መሳለቂያ ስትሆን የሚመለከቱ ምእመናን የማይጠገን የልብ ስብራት አድርሶባቸዋል፡፡      
ለ/ ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን አለመወጣቱ
       ቅዱስ ሲኖዶስ ከእግዚአብሔር በተሰጠው አደራ የወንጌልን ቃል ለዓለም ሁሉ ማዳረስ፤ያላመኑትን በማሳመንና ያመኑትንም እስከ መጨረሻው ጸንተው እንዲኖሩ ማበረታታት፤ በተለያየ ኃጢአት የተሰነካከሉትን በንስሃ በማደስ ሁሉንም የዘለዓለም ሕይወት ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻልና፤ በአጠቃላይ ከቀደሙት አባቶቻችን የተረከብናት የተዋሕዶ ሃይማኖት ሳትበረዝና ሳትከለስ ለቀጣዩ ትውልድ እንድትተላለፍ ማድረግ ነው፡፡እንግዲህ ከላይ ለተመለከትናቸው የተለያዩ ችግሮች የተጋለጥነው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ሲሆን፤ለዚህም ከዋነኞቹ ምክንያቶች አንዱ የቤ/ክ መሪዎች በየጊዜው የሚለዋወጠው ዓለማዊ አስተዳደር (መንግሥት) ጥገኛ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ  ማትያስ ጥቅምት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. 34ኛውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔን የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ  የተናገሩትን ስንመለከት ከላይ ያለውን ሃሳብ ያረጋግጥልናል፡፡
       "…..ባህርን አቋርጦ፣ድንበርን ተሻግሮ፣እስከ ጽንፈ ምድር ተጉዞ አስተምሮና ያላመነውን አሳምኖ የቤ/ክ ልጅ ማደርጉ ይቅርና በሀገሩ ውስጥ ያሉትን ወገኖች ቤ/ክ ውስጥ አጠራቅሞ ምዕመናንን ማበዛቱ የቱና ያህል የተሄደበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ከሁሉ በላይ የሚያስቆጨው ደግሞ ትናንት ቤ/ክ ሀብተ ውልድና ስመ ክርስትና ሰጥታ በሃላፊነት የተቀበለቻቸውን ልጆቿ ዛሬ እናት ቤ/ክ እየከዱ ወደ ሌላ ጎራ የመቀላቀሉ ጉዳይ እጅግ በጣም እየናረ መምጣቱ ነው፡፡የምዕመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምስጢር ምንድነው? የሚለው ጥያቄ ቤ/ክ በአንክሮ ልታጤነው ይገባል፡፡…….ይኸውም ምዕመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዷችንን ከመቅረታችን በፊት ለተለያየ ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል እንነሳ፡፡….."
       እንዲሁም በቅርቡ የአ.አ.ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት መምህር ይቅርባይ፤ይህንን የቤ/ክ መጠነ ሰፊ ችግር ቁጭት በተሞላው አነጋገር እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፤
"….አሁን የምናየው ኹኔታ ከዚህ ፈጽሞ የተለየም ብቻ ሳይኾን፣ ፍጹም ተቃራኒና ከመንፈሳዊ አባቶችና ወንድሞች ቀርቶ ከሰብአ ዓለም እንኳ የማይጠበቅ ተግባር በመኾኑ፣ እያንዳንዳችን እንደየአቅማችን ዋጋ እየከፈልን እንገኛለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንንም ዋጋ እናስከፍላታለን፡፡"……"በኑፋቄአቸው አወናብደው ከወሰዱብን ይልቅ፣ በመጥፎ ሥነ ምግባራችን ዕንቅፋት ኾነን ያባረርናቸውን ዓለም ይቁጠራቸው፡፡ ስለዚህ በጋራ ኾነን ብልሹ አሠራርን አርመን ወደ መልካም አስተዳደር እናምጣ፡፡"
(ማስታወሻ፤ መምህር ይቅርባይ የአ.አ.ሀ.ስብከት ሥራ አስኪያጅነቱን ሃላፊነት በተረከቡት ዕለት ለሥራችን መቃናት በሃሳብም በጸሎትም አግዙን ማለታቸው አይዘነጋም፡፡እኛም ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ የጋራችን እስከሆነ ድረስ በተሰጠን የቤት ሥራ መሠረት ቤ/ክ ከገባችበት አዘቅት እንድትወጣ ከጸሎትና ከጾም ጋር በሁሉም ነገር መትጋት ይጠበቅብናል፡፡)
ሐ/ በጥልቅ ኃዘን ልባችው የተሰበረውን የቤ/ክ ልጆች…..ይቅርታ እንዲጠይቅ
       ይቅርታ መጠየቅ ወይም ይቅርታ ማድረግ የሚባለው ነገር የሚመጣው በሁለት ሰዎች ወይም ቡድኖች መካከል፤አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ለመታረቅ የሚችሉት ደግሞ ምናልባት የተበደለው አካል ይቅርብኝ ብሎ ካልተወው በስተቀር የበደለው አካል ለተበዳዩ የቀማውን መልሶ የበደለውን ክሶ ሲሆን እርቁ ከልብ የመነጨ ይቅርታ የሚያሰጥ ይሆናል፡፡እንዲሁም ሰው ኃጢአት ሰርቶ ከፈጣሪው ሲጣላ ከፈጣሪው ለመታረቅ በመጀመሪያ ስለ ሰራው ኃጢአት መጸጸት፤በመቀጠልም እንደ ቤ/ክ ሥርዓት ለንስሃ አባቱ መናዘዝ ይጠበቅበታል፡፡በኑዛዜው መሠረት ካህኑ የሰጠውን ቀኖና ሲጨርስ በካህኑ አማካይነት(ይቅርታ) ሥርየተ ኃጢአት ያገኛል፡፡
       እንደዚሁ ሁሉ ከላይ በመግለጫው እንደተመለከትነው በአባቶቻችን አለመግባባትና ከዚያ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት እኛ ልጆቻቸው፤ ከፍተኛ የልብ ስብራት እንደደረሰብን አባቶቻችን ከተረዱልን፤ "ከቁስል ሁሉ የልብ ቁስል ይከፋል" እንደሚባለው፤ ይህ የልብ ስብራት ሊጠገን የሚችለው በነዚህ አስከፊ ጊዜያት የተፈጠሩትን ስህተቶች ማረም ሲቻልና ቤ/ክ ወደ ቀደመ ክብርዋ ስትመለስ እንጂ ጉዳዩ እንደ ቀላል ነገር ታይቶ፤አጥፍተናል ይቅር በሉን በማለት ብቻ የሚቋጭ መሆን የለበትም፡፡


No comments:

Post a Comment