ከቁጥር አራት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
ባለፈው በክፍል አራት ጽሁፋችን የካህናትን አገልግሎት በሚመለከት ጽሁፍ እንመለሳለን ባልነው መሰረት እነሆ ዛሬ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት “‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ” ብለን በጀመርነው ርዕስ እንቀጥላለን፡፡
- ከመጽሐፉ ከገጽ 8 የተወሰደ ፦ ‹‹…ዛሬም በሰው ሥርዓት የተሸሙትን ምድራውያን ካህናት አልፈን በመምጣት እግዚአብሔር በሾመው ሰማያዊ ሊቀካህን እግር ሥር እንውደቅ፤ምሕረትም እናገኛለን፡፡››
- ከመጽሐፉ ከገጽ 12 የተወሰደ ፦ ‹‹…በመሆኑም በወንጌል ቃል ለተገለጠው እውነት ታማኝ ሊሆኑ ባልቻሉት በዘመናችን አሮኖችና ኤሊዎች መገልገልን ትተን በሰማያዊት መቅደስ እግዚአብሔር ወዳስቀመጠልን ወደታመነው ሊቀካህናት ወደ ኢየሱስ ዘንድ ልንኮበልል ያሰፈልጋል፡፡››
- ከመጽሐፉ ከገጽ 17 የተወሰደ ፦ ‹‹ከክርስቶስ ወደ ሐዋርያት ከሐዋርያት ወደ ተከታዮቻቸው እየተባለ ሲወርድ ሲዋረድ እስከ ዘመናችን የደረሰ የተለየ የክህነት መስመር የለም፡፡››
በማለት
ለጻፉት ክህደታቸው ምላሽ የሚሆኑትን የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት ፦
- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያዎቹን የአዲስ ኪዳን ሐዋርያትን(ደቀመዛሙርትን) እንደመረጠና ሥልጣን እንደሰጣቸው፦
- ማቴ.10፤1-8 ‹‹አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲያወጧቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው››…ድውዮችን ፈውሱ፤ሙታንን አስነሱ፤ለምጻሞችን አንጹ፤አጋንንትን አውጡ፡……፡፡››
- ማቴ.16፤18-19 ‹‹እኔም እልሃለሁ አንተ ጴጥሮስ ነህ ፤በዚህም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም ፡፡የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፡፡በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፤በምድር የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል፡፡››
- ማቴ.28፤16-20 ‹‹አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፡፡…..እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኳችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ከናንተ ጋር ነኝ፡፡››
- ዮሐ.21፤21 ‹‹ጌታ ኢየሱስም ዳግመኛ ሰላም ለናንተ ይሁን ፤አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካቸኋለሁ አላቸው፡፡ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡››
- ማቴ.10፤40፦ ‹‹እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡››
- የሐዋ.ሥ.1፤21-26 ‹‹…ሲጸልም የሁሉን ልብ የምታውቅ አንተ ጌታ ሆይ ይሁዳ ወደ ገዛ ራሱ ስፍራ ይሄድ ዘንድ በተዋት በዚህች አገልግሎትና ሐዋርያነት ስፍራን እንዲቀበል የመረጥከውን ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን ሹመው አሉ፡፤ ዕጣም ተጣጣሉላቸው ዕጣውም ለማትያስ ወደቀና ከአስራ አንዱ ሐዋርያት ጋር ተቆጠረ፡፡››
- የሐዋ.ሥ.6፤3 ‹‹ወንድሞች ሆይ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ ፤ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፡፡››
- የሐዋ.ሥ.14፤23 ‹‹በየቤተ ክርስቲያኑም ሽማግሌዎችን ከሾሙላቸው በኋላ ጦመውም ከጸለዩ በኋላ ላመኑበት ለጌታ አደራ ሰጡአቸው፡፡ ››
ታዲያ
እነዚህ ናቸው እውነት እንሰብካለን እያሉ ለራሳቸው ግራ ገብቷቸው ምዕመኑን ግራ የሚያጋቡት?ደግሞስ በማህበር ተሰብስበው በአደባባይ ሲዋሹና ሲያጭበረብሩ ትንሽ እንኳን አፈር አይሉም እንዴ? ብርሃን በርቶልናል፤እውነትን ይዘናል እያሉ በከንቱ ከሚመጻደቁትና እራሳቸውን ከሚያጸድቁት መካከል አንድ እንኳን የሚመክር የለም ? እውነት እነዚህ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ
ክርስቲያን ውስጥ ተወልደው ያደጉ ናቸው ለማለት ይቻላል?ከዚህም አልፈውና ተርፈው ደግሞ ቤተ ክርስቲያን እውቅና ትስጠን ማለታቸውስ አያስገርምም!? እኛም ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ባይነቅፉብን ኖሮ እነሱ በቅዠት መንፈስ የጻፏቸውን ፍሬ አልባና አጸያፊ ጽሁፎቻቸውን ሰብሰበን መልስ ለመሰጠት ባልደከምንም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ሰይጣናዊ ስራቸውን እያየንና እየሰማን፤የፈጣሪያችን እግዚአብሔር ቃል ሲዘበትበት፤እናታችን ጽዮን/ቤተ ክርስቲያን/ ስትሰደብ ዝም የምንልበት አንጀት ስለሌለን አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በፈቀደልን መጠን ይህንን የሐሰት ሥራቸውን እስከ መጨረሻው ደረስ እንቃወማለን፡፡እነሱ እንደሚሉት እንደ እስስት የሚለዋወጥ ብዙ ዓይነት ስልት ቢጠቀሙ፤ቁጥራችን በዛ እያሉ ወሬ ቢነዙ፤ ወ.ዘ.ተ. እውነትን እስካልያዙ ድረስ ከጥፋት በስተቀር የሚያተርፉት ነገር ስለሌለ ድካማቸው ከንቱ መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡
እንግዲህ አርባ ስምንት ገጾች ያሉት‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» መጽሐፋቸው በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ቀሎ የተገኘና ፍሬ የሌለው ገለባ መሆኑን ከላይ በስፋት ባቀረብነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ በቂ ዝንዛቤ እንዳገኛችሁ እንምናለን፡፡ለያንዳንዱ ሃሳብና አልባሌ ቃላት መልስ እንስጥ ብንል አንባቢን ማሰላቸትና ሥራ ማስፈታት ይሆናል በማለት አልፈነዋል፡፡ ዋናው አላማችንም ቤ/ክ እናድሳለን ባዮቹ ምን ያህል ከእውነት የራቁ እንደሆኑ ለማሳየትና የዋሁ ምዕመን በስህተት ትምህርታቸው እንዳይጠለፍ ለማስገንዘብ ሲሆን ተገቢውን እውቀት ለማገኘት ግን ወደ ሊቃውንት አባቶች እየቀረብን መማር ይኖርብናል፡፡
ለቀጣዩ
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሌላውን መጽሐፋቸውን እንመለከታለን፡፡
ለዛሬው
ይቆየን፡፡
No comments:
Post a Comment