Saturday, February 21, 2015

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አራት

ከቁጥር ሦስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
ባለፈው በክፍል ሦስት ጽሁፋችን ‹‹እኔ  መንገድና  እውነት ሕይወትም ነኝ...›› በሚለው ርዕስ እንመለሳለን ባልነው መሰረት እነሆ ዛሬ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ካቆምንበት “‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ” ብለን በጀመርነው ርዕስ  እንቀጥላለን፡፡ 

1/ከመጽሐፉ ከገጽ 8 የተወሰደ ፦
‹‹አነ ውእቱ ፍኖትኒ ወጽድቅኒ ወሕይወትኒ አልቦ ዘይመጽእ ኀበ አብ ዘእንበለ እንተ ኀቤየ ›› ማለትም ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም ››በማለቱ በእርሱ መንገድነት ካልሆነ በቀር በሌሎች  መንገዶች ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የማይቻል መሆኑን አረጋግጧል/ዮሐ.14፤6 እዚህ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ‹‹መንገድ›› ብሎ ጠርቷል፤መንገድ በመንገደኛውና መንገደኛው በሚደርስበት ቦታ መካከል የተዘረጋ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ሰማያዊ መንገደኞች በሆንነው በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ ነው፡፡ ከእርሱም በቀር ሌላ መካከለኛ የለም፡፡›› በማለት ጽፈዋል፡፡
ከዚህ በላይ ያስነበብናችሁ ከመጽሐፋቸው ቃል በቃል የተወሰደ ሲሆን ሃሳቡን ጠቅለል በማድረግ በሁለት ከፍለን እናየዋለን፡፡ ይኸውም ፦
     ሀ/ ሐሰታቸውን እውነት ለማስመሰል የተጠቀሙበትን የግዕዙን ጥቅስ ከትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱስ አምጥተን፤ 
     ለ /‹‹መንገድ›› የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን ትርጉም የተወሰኑ ጥቅሶችን መሰረት አድርገን  እንመለከተዋለን፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነገር ሁሉ ማስተዋሉን ይስጠን፡፡


ሀ/ ዮሐ.14፤6 ከግዕዝ በቀጥታ ወደ አማርኛ ከተተረጎመው /ከትክክለኛው/ መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ
በግዕዝ‹‹አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት፤ወአልቦ ዘይመጽእ ኀበ አብ ዘእንበለ እንተ ኀቤየ፡፡››
በአማርኛ ‹‹የጽድቅና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡››
     ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን፤ ጌታችን ወደዚህ ምድር በሥጋ የመጣው አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ለማዳን እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡በመሆኑም እሱ በፈቃዱ ሊቀበለው ያለውን የቤዛነት ሥራውን በመስቀል ፈጽሞ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ እየተቃረበ በነበረበት ወቅት፤  ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ እሱን ብቻ ተስፋ አድርገው ሲከተሉት ለነበሩት ደቀ መዛሙርት የማጽናኛና የማበረታቻ ትምህርት ይሰጣቸው ነበር፡፡የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል ከምዕራፍ አስራ ሁለት እስከ ምዕራፍ አስራ ሰባት ድረስ ያለውን ስንመለከት ደቀ መዛሙርቱ በጊዜው ሊረዱት ያልቻሉትን ጥልቅና ረቂቅ የሆነውን የምሥጢረ ሥላሴና የምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርትና እንዲሁም የጸሎትን አስፈላጊነት እንዳስተማራቸው እንረዳለን፡፡
     በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.14 ከቁ.1 ጀምሮ ያለውን በማስተዋል ስንመለከተው ጌታችን ትምህርቱን ‹‹ ልባችሁ አይታወክ›› ብሎ የጀመረው የሁሉንም ልቡና መርምሮ የሚያውቀው አምላካችን የደቀ መዛሙርቱን መጨነቅና ግራ መጋባታቸውን ስለተረዳ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡በመቀጠልም ‹‹በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ…..ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ….ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፤….››እያለ በሚነግራቸው ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ እያሉ ጠየቁት፡፡
የቅዱስ ቶማስ ጥያቄ፦ ‹‹ጌታ ሆይ ወደምትሄድበት አናውቅም  እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?›› ዮሐ.14፤5.
የጌታችን መልስ ‹‹የጽድቅና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡›› ዮሐ.14፤6
የቅዱስ ፊልጶስ ጥያቄ ‹‹ጌታ ሆይ አብን አሳየንና ይበቃናል፡፡›› ዮሐ.14፤8
የጌታችን መልስ ‹‹እኔን ያየ አብን አይቷል እንዴትስ አንተ አብን አሳየን ትላለህ ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?….ዮሐ.14፤9-10
እንግዲህ በላይ የተጠቀሰውን ክፍለ ትምህርት ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው፦

  1. ጌታችን የተናገረው ቃል ስለ እምነት እንጂ ስለ ምልጃ ወይም መካከለኛነት አለመሆኑን እንገነዘባለን፡፡
  2. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮት፤በፈቃድ በህልውና፤በአገዛዝና በመሳሰሉት አንድ መሆናቸውን፤
  • ዮሐ. 5፤23 ‹‹ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ   አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፡፡ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም፡፡›› 
  • ዮሐ.10፤30 ‹‹እኔና አብ አንድ ነን ፡፡››በማለት በማያሻማ አምላካዊ ቃሉ አርጋግጦልናል፡፡ 

አሁን ‹‹መንገድ›› የሚለው ቃል  በመጽሐፍ ቅዱስ ያለውን የተለያየ  አተረጓጎም በአጭሩ እንመልከት፡፡
  1. ‹‹መንገድ›› በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት ማመን እንደሚገባን ለመግለጽ ሲነገር፦ ከዚህ በላይ በተመለከትነው ክፍለ ትምህርት/ዮሐ.141-6/ መሠረት ‹‹መንገድ›› የሚለው ቃል የሚያስተምረን ስለ ሃይማኖት እንጂ ስለ ምልጃ አይደለም፡፡ይህንንም ‹‹በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ››ብሎ በተናገረው አምላካዊ ቃሉ አረጋግጦልናል፡፡
  2. ‹‹መንገድ ››የቀደመችውን ሃይማኖት ለማመልከት ሲነገር፦
    በትን. ኤር. 616‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‹‹በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ ፤መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ፤በእርሷም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ››፤እነርሱ ግን ‹‹አንሄደባትም አሉ፡፡›› ይላል፡፡ በዚህም ኃይለ ቃል የምንማረው መንገድ የተባለችው ጥንታዊቷ ፤ቀደምቷ፤አንዲቷ ፤ሃይማኖት እንደሆነች የሚያጠራጥርም የሚያከራክርም ነገር የለውም፡፡
  3. ‹‹መንገድ›› የእግዚአብሔር ህግ እንደሆነ ሲነገር፦
    መዝ.26/27/11 ‹‹አቤቱ መንገድህን አስተምረኝ፤ስለ ጠላቶችም በቀና መንገድ ምራኝ ››
  4. ‹‹መንገድ›› ስለ ሰው ልብ ሲነገር፦
    ሉቃስ 8፤5  ‹‹ዘሪ ዘሩን ሊዘራ ወጣ፡፡ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ተረገጠም የሰማይ ወፎችም በሉት›› ይላል፡፡የምሳሌው ትርጉም ደግሞ ቁጥር 12 ‹‹በመንገድ ዳር ያሉት የሚሰሙ ናቸው፡፡ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ይመጣል፤አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል፡፡›› 
  5. ‹‹መንገድ›› የዘላለም ሕይወት ለመውረስ ህጉንና ትእዛዙን መጠበቅ እንደሚገባ   ለማመልከት ሲነገር፦
    ማቴ.7፤13-14 ‹‹ በጠበበው ደጅ ግቡ ፤ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጁ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ መንገዱም የቀጠነ ነውና፤የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው፡፡››
     እንግዲህ ከዚህ በላይ ከብዙው በጥቂቱ እንደተመለከትነው እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይህ ሆኖ ሳለ የበግ ለምድ ለባሾች /ተሐድሶ ነን ባዮቹ/ ግን‹‹መንገድ በመንገደኛውና መንገደኛው በሚደርስበት ቦታ መካከል የተዘረጋ እንደሆነ ሁሉ ክርስቶስም ሰማያዊ መንገደኞች በሆንነው በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለ መካከለኛ  ነው፡፡››በማለት በፈጣሪያቸው ላይ የድፍረት ቃል መናገራቸው ትዕቢታቸው እስከ ሰማይ ጥግ እንደደረሰ ያረጋግጣል፡፡  በዚህም አባባላቸው እስከ ዛሬ ከምናውቃቸው መናፍቃን በተለየና በከፋ መልኩ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ለይተው በፍጡር ደረጃ ከመመልከታቸውም አልፎ እራሳቸውን ከእርሱ አስበልጠው እነርሱ መንገደኞች እሱን መሄጃ እንደሆነ አድርገው ጽፈዋል፡፡ለመሆኑ ከመንገድና ከመንገደኛው ማንኛው ይበልጣል? ‹‹እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ!!!›› ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ሮሜ.1፤28 ‹‹እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ ሰጣቸው›› ብሎ የተናገረው ቃል ስለተፈጸመባቸው በፈጣሪ ሥራና በፍጡር ሥራ መካከል ያለው ልዩነት፤እንዲሁም በላይ በሰማይና በታች በምድር  የሚሰራው ሥራ ምን ዓይነት እንደሆነ መለየት እንኪሳናቸው ድረስ አእምሯቸው የተቃወሰ መሆኑን እኛ ሳንሆን የራሳቸው ሥራ ይመሰክራል፡፡ከፍሬያቸው/ከሥራቸው/ ታውቋቸዋላችሁ የተባለውም ይሄና የመሳሰለው ነው፡፡ 
የተከበራችሁ አንባቢያን ለቀጣዩ ከዚሁ መጽሐፍ የካህናትን አገልግሎት በሚመለከት ጽሁፍ እንመለሳለን:: 
ለዛሬው ይቆየን::

No comments:

Post a Comment