Friday, April 10, 2015

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል ስድስት

እንኳን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣዔ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!!!
በመዝሙር ስም ዘፈን! እስከ መቼ?

የተከበራችሁ የዚህ ድረ ገጽ ታዳሚዎች እንደምን ሰነበታችሁ?

     ባለፈው ክፍል አምስት ጽሁፋችን ‹‹በቀጣይ ሌላውን የክህደት መጽሐፋቸውን እንመለከታለን›› ብለን በይደር እንዳቆየነው ይታወሳል፡፡ ሆኖም ወደ ሌላው  መጽሐፋቸው ከመሄዳችን በፊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናቸንን በእጅጉ እየተፈታተናት ስላለው የመዝሙር ሁኔታ ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ቅድሚያ ሰጥተናል፡፡  
    ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ / በጻድቁ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ከፈጣሪዋ ከልዑል እግዚአብሔር ልዩ የሆነ የዜማ ጸጋ ተሰጥቷታል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊው አባታችን ቅዱስ ያሬድ ከቅዱሳን መላእክት የተሰጠውን ሰማያዊ ዜማ ተቀብላ መላውን አገልግሎቷን ትፈጽማለች ፡፡
     ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷንና ሥርዓቷን ከአባቶች ወደ ልጆች ለማስተላለፍ እንዲሁ በልማድ ብቻ መቀጠሉ በቂ ስላልሆነ 1960ዎቹ አመታት ወዲህ ወጣቶችና ህጻናት በዕለተ ሰንበት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው እየተሰበሰቡ ስለ ሃይማኖታቸው እንዲማሩ ‹‹መንፈሳውያን ማሕበራት›› ተቋቋሙ /ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበትን ቃለ ዓዋዲ 1970 እትም ይመልከቱ/፡፡ የእነዚህ መንፈሳውያን ማሕበራት ስያሜ ከጊዜ በኋላ ‹‹ሰንበት ትምህርት ቤት›› በሚለው  ተተክቶ እስከ አሁን እንጠቀምበታለን ፡፡ ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን ግጥምና ዜማቸው በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተዘጋጁ የአማርኛና የግዕዝ መዝሙሮችንና እንዲሁም በዓመቱ ውስጥ ለሚከበሩት ዐበይት በዓላት ተስማሚ የሆኑትን  መዝሙራት (ወረቦች) እንዲያጠኑ በማድረግ ወጣቱ ከያሬዳዊ ዜማ ሳይወጣ እውቀቱ በሚፈቅድለት መጠን ፈጣሪውን እንዲያመሰግንበትና እንዲማርበት ሲደረግ ቆይቷል፡፡እንዲሁም ከዚህም በተጨማሪ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን የሰርክ ጉባኤያትን በማዘጋጀት ለምዕመናን ከምታቀርበው የወንጌል ትምህርት ጎን ለጎን በነዚሁ መዝሙራት ፈጣሪያቸውን እንዲያመሰግኑ እያደረገች ነው፡፡

     ከነዚህም ቀደምት መዝሙሮች ውስጥ ገና 1970ዎቹ አመታት ጀምሮ እስከ አሁን የምናመሰግንባቸውን ለምሳሌ እንደ ቸርነትህ ፣ጌታ ሆይ፣ የሲና ሐመልማል እና የመሳሰሉትን ቀደምት መዝሙራትና እንዲሁም በየጊዜው የሚያዘጋጇቸውንውን ለምሳሌ እንደ ፀምር ዘጌዴዎን ፣ለከ ኃይል፣አንቺ አንቺ ቀራንዮ፣እንዲህ አለው ጴጥሮስ፣ የተቀመጣችሁ ተነሱ፣ ያከብርዋ ለሰንበት፤ በሞት ጥላ ወድቀን ..የመሳሰሉትን ግጥምም ሆነ ዜማቸው የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖት ሥርዓት ትውፊትና ያሬዳዊውን ዜማ የጠበቁ መዝሙሮች በማዘጋጀት  በካሴትም ሆነ በመሳሰለው ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ የተለያየ ፈተና በበዛበት ዘመን ትውልዱ እንዲጠቀምባቸው ያደረጉ ጥቂት አባቶቻችን፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም ማህበራት ቢኖሩም ከተገልጋዩ ምዕመን ብዛትና ፍላጎት አንጻር ሲታይ ቁጥራቸው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ይህንን የመዝሙር አገልግሎት 1972 . ጀምሮ ግጥምና ዜማቸው የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የተከተሉ መዝሙራትን በማዘጋጀት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እስከ አሁንም ድረስ የሚያገለግለን ወንድማችን ሊቀ መዘምራን ኪነጥበብ /ቂርቆስ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህ አገልጋዮች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባለውለታዎች ናቸውና በደሙ የመሠረታት ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድርም በሰማይም መልካሙን ዋጋቸውን ይክፈልልን፡፡
      እንግዲህ መዝሙር ምሥጋናን፤ ንስሃንና ልመናን ወደ እግዚአብሔር የምናቀርብበት ከመሆኑ በተጨማሪ ቃለ ወንጌልን ለማስተማር አንደኛው መንገድ ነው፡፡ ሆኖም በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚኖረውና ተፈላጊውን መልእክት ማስተላለፍ የሚችለው የቤተ ክርስቲያናችንን እምነትና ሥርዓት ጠብቆ በማስተዋልና በተመስጦ ሆኖ ሲዘመር ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም እንደምናየውና እንደምንሰማው ከጠባቧ የተዋሕዶ መንገድ ከመሄድ ይልቅ ሰፊውን የዓለም መንገድ የመረጡ ክፍሎች በግልም ሆነ በማህበር በመደራጀት ከላይ የገለጽነውን ትክክለኛውን የመዝሙር አገልግሎት በሚቃረን መልኩ እያዘጋጁ፤ በሽፋናቸው ላይ ግን በኢ//// እምነትና ሥርዓት መሠረት የተዘጋጀ የሚል ማስመሰያ እየለጠፉ የሚያቀርቧቸውን "መዝሙሮች" ሁኔታ ስንመለከት እጅግ በጣም አሳዛኝ ሆኖ እንገኘዋለን፡፡ይህንን ችግር የፈጠሩት የተለያየ ዓላማ ያላቸው ክፍሎች ቢሆኑም፤ለጥፋቱ በር ከፍተውና እውቅና ሰጥተው በቤ/ አውደ ምህረትም ሆነ በየሰንበት ትምህርት ቤቱ እንዲዘመርና እንዲሸጥ ትብብር የሚያደርጉ የቤ/ ሃላፊዎችና ምንነቱን ሳይመረምሩ የቀረበላቸውን ሁሉ በገንዘባቸው እየገዙ የሚጠቀሙ ምዕመናንም የጥፋቱ ተጨማሪ አካል መሆናቸው ችግሩ የበለጠ እንዲወሳሰብ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሁሉ በደሉ….›› እንዳለው፡፡ መዝ.523
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንቀጥላለን፡፡

ለዛሬው ይቆየን፡፡

1 comment:

  1. መልካም የሆነ ጀሮ ያለውባለአዕምሮ ሁሉ ሊሰማውና ሊያስተውልበት የሚችል መልእክትና ትምህርት ነውና በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ገላጭነት ሳትፈሩ "መንገዴ በሬ" እየተባሉ የክርስቶስን ክብርና አምላክነት የሚያቃልሉና የሚሳደቡ ግጥም ተብየ ጥርቅሞችን ሁሉ በማብራራት ትምህርትና ግንዛቤን መስጠት እንድትበረቱ። ዘማሪዎች በማወቅም ይሁን ገን ለማግኘት ሲሉ በድምጽ ቢሰሩትም ግጥሙን የሚያዘጋጀው ግን ባላማ ቀምሮ ነውና ምእመናን ከእንዲህ አይነት ስጋዊና ክህደት ካዘሉ መዝሙር ተብየዬ እንዲጠበቁ አንቋቸው። ይህ ብቻም አይደለም ዛሬ እንዘምራለን ግጥምም እንገጥማለን የሚሉ ግለሰቦች ስለራሳቸው የሚዘምሩና እንደተጣለው ሳጥናኤል ክብርን ለራሳቸው የሰጡና ዘወትር የተሰወ(በሐሳብ ከሚሰሩት) ሐጢያት እንሿን ያልነካቸው መስለው የሚመፃደቁ ነው ሆነው ዘመርን ብለው የሚያወሩት። ይህም ብቻ አይደለም በአንድ ወቅት የቤተክርስቲያ አውደምህረት ቤተክርስቲያን ለምታውቃቸውና እንዲቆሙበት ለፈቀደችላቸው ነው ሲባለ ስምህን እንዳልጠራ ከለከሉኝ ተብሎ ይዘመር ነበር። ስሙን መጥራት በደረቁ ማመንም መመስከርም ማምለክ መዳንም አይደለም። ክርስቶስም ኢየሱስ ኢየሱስ የሚለኝ ሁሉ የሚድን እንዳልሆነ ተናግሯል። ይህ ማለት ደግሞ ስሙን ከመጥራት ባለፈ ሌላ መፈፀም ያለብን የእምነት ተግባር እንዳለ ያመላክታል። እና እባካችሁ በዚህ ጉዳይ በስፋት ስሩበት። የእግዚአብሔር ቸርነት አይለያችሁ።

    ReplyDelete