በመዝሙር ስም ዘፈን! እስከ መቼ ?
“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” በሚለው ዋና ርዕሳችን ሥር ‹‹በመዝሙር ስም ዘፈን! እስከ መቼ?›› በሚለው ንዑስ ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል መግቢያውን ተመልክተን በይቀጥላል አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በ‹‹መዝሙር›› ስም ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሠርጎ ስለገባው ስህተት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ከብዙው በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
እነዚህ የተለያዩ የጥፋት መልእክተኞችና እኩይ ሥራቸው ቁጥራቸው ከመብዛቱ የተነሳ እያንዳንዳቸውን በዝርዝር ለማየት አስቸጋሪ በመሆኑ ብዙዎቹን ችግሮች አንድ እያልን በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍለን እናያቸዋለን፡፡ምንም እንኳን ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የወጡ እነዚህን ‹‹መዝሙሮች›› ‹‹መዝሙር›› ብለን መጥራት ባይገባንም፤ለጊዜው የምንግባባው በዚሁ ቃል በመሆኑ እኛም ይህንኑ ቃል ተጠቅመን ጽሁፋችንን እንቀጥላለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ማስተዋሉን ይስጠን !ሀ/ ቤተ ክርስቲያናችንን በመዝሙር ስም የዘፈን መድረክ ያደረጓት ክፍሎች
1/የተለያዩ የመናፍቃን ድርጅቶችን ዓላማ አስፈጻሚዎች /ተሐድሶዎች/
እነዚህ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ምዕመናንን የሚያሳስቱት መስለውና ተመሳስለው ስለሆነ የማስመሰያ ለምዳቸው ተገፎ ተለይተው እስኪወጡ ድረስ የተዋሕዶውንም የፕሮቴስታንቱንም መዝሙር እያቀላቀሉ ነው የሚዘምሩትና የሚያዘምሩት፡፡ በዝማሬ የሚተላለፍ ትምህርት ደግሞ በሰዎች ልቡና ውስጥ በቀላሉ ሰርጾ የመግባት ኃይል ስላለው ምዕመኑም በቀላሉ ስህተቱን መለየት ስለማይችል በዚሁ ግርግር ስህተታቸውን ይቀበላል፡፡ያጠናል፡፡ተኩላዎቹ ይህንን እኩይ ስራቸውን የሚቃወማቸው ከሌለ በስተቀር፤የቀደመ ዓላማቸው ማለትም የተዋህዶውን እምነት፤ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም ሰማያዊውን ያሬዳዊ ዜማ ቀስ በቀስ እየሸረሸሩ በማጥፋትና በመዝሙሮቻቸውም ግጥሞች በሚያስተላልፉት የስህተት ትምህርት ምዕመኑን ወደ ሌላ አዳራሽ መውሰድ ሳያስፈልግ እዚሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለ ተሐድሶ /ፕሮቴስታንት/ የማድረግ ዓላማቸው ተሳካ ማለት ነው፡፡
ይህ ሰይጣናዊ ዓላማቸው ይሳካላቸዋል የሚል ስጋት ባይኖረንም በየተገኘው አጋጣሚ ወደ ጥፋቱ ጎዳናቸው የሚነጉደውን ወጣትና ምዕመን ለማዳን፤ያወቅነውን ያህል ለሌሎች በማሳወቅ ስህተቱን እንዲገነዘብና በወንጌሉ ቃል መሰረት እራሱንና ሌላውንም በመጠበቅ፤ በእውነተኛይቱ የተዋሕዶ ሃይማኖቱ እስከ መጨረሻው ጸንቶ እንዲኖር አጥብቀን ለማሳሰብ ነው ዓላማችን ፡፡
2/ለግል ጥቅማቸው ገንዘብ የመሰብሰብ ዓላማ ይዘው የተሰማሩ
እነዚህ ክፍሎች አብዛኛዎቹ ስለ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትም ሆነ ስለ ያሬዳዊ ዜማ በቂ እውቀትና ችሎታውም ጭምር ሳይኖራቸው ለራሳቸው ደስ ያላቸውን ግጥምና ዜማ በአንድ ጀምበር አዘጋጅተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም አሳትመው መሸጥ ይጀምራሉ፡፡እነዚህኞቹ ከዋነኛው ዓላማቸው ገንዘብ ከመሰብሰብ በስተቀር እንደ ተሐድሶዎቹ ቤተ ክርስቲያንን የማጥፋት ዓላማ ይዘው የተነሱ ባይሆንም የሥራቸው ውጤት የሚያስከትለው ጥፋት ግን ከተኩላዎቹ የተለየ አይደለም፡፡ከዚህም ሌላ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር በመሆኑ ጠቀም ያለ ገንዘብ ካገኙ ወደ መናፍቃኑ ጎራ ለመቀላቀል የሚከለክላቸው ነገር አይኖርም፡፡
3/አርቲስቶች/ ዘፋኞች/
እነዚህ ክፍሎች ዘፈን ኃጢአት መሆኑን አውቀው ወደ ሃይማኖታዊ መስመር መምጣታቸው በጣም አስደሳች ነው፡፡ሆኖም የራሳቸውን ሕይወት በንስሃ አድሰው በቤተ ክርስቲያኒቱ ህግና ሥርዓት እራሳቸውን መምራት ሲገባቸው፤ጥሩ የተፈጥሮ ድምጽ ስላላቸው ብቻ ገና የዘፈኑ ቅላጼ ከውስጣቸው ሳይወጣ በዚያው በለመዱት በዘፈኑ ዜማ የ‹‹መዝሙር›› ካሴት ማዘጋጀትና መሸጥ፤በየአውደ ምህረቱ ‹‹መዘመር››ይጀምራሉ፡፡በዘፈን ያጡትን ገቢ በዚሁ ያካክሱታል፡፡ ምዕመኑም ያው እንደተለመደው በእልልታና በጭብጨባ እያጀበ አብሯቸው ‹‹ይዘምራል››፡፡ከዚህም ሌላ አርቲስቶቹ የዘፈኑን መንገድ ትተው ‹‹ዘማርያን›› መሆናቸው እንደ ትልቅ መሥዋዕትነት ተቆጥሮ በየደረሱበት ታሪካቸውና ‹‹ገድላቸው››ይነገርላቸዋል፡፡ቢሳሳቱ እንኳን ከዚህ ተመለሱ የሚላቸው ባለመኖሩ በጥፋት ላይ ጥፋት ይደራረባል እንጂ እርምት አይደረግበትም፡፡ እንግዲህ ከላይ ከብዙው በጥቂቱ ለመግለጽ እንደሞከርነው እነዚሁ የተለያዩ የጥፋት ክፍሎች፤በአሁኑ ጊዜ ያለውን የምዕመናን ፍላጎትና ደካማ ጎን፤በቤተ ክርስቲያኒቱ ሃላፊዎች በኩል የሚታየውን የቸልተኝነት ክፍተት በመጠቀም በማናለብኝነት ‹‹ጸጋው የበዛለት/የበዛላት‹‹ታዋቂ ዘማሪ /ዘማሪት/›› የዲቁና ማዕረግ ይኑራቸውም አይኑራቸውም ‹‹ዲያቆን›› ‹‹ሊቀ ዲያቆናት›› የሚል ‹‹የማዕረግ››ስም ይሰጣቸዋል፡፡ በወርሃዊም ሆነ ዓመታዊ በዓላት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እየተዘዋወሩ፤ካህናት በቤተ መቅደስ በተቀደሰው የማህሌት አገልግሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ እነሱ አስቀድመው ባስጠኑት ‹‹ዝማሬያቸው›› ምዕመኑን ከመንፈሳዊ ተመስጦ ውጪ በሆነ ስሜታዊነት ‹‹ሲያዘምሩ›› ይውላሉ ያመሻሉ፡፡ምዕመኑም በየዓውደ ምህረቱም ሆነ በየመዝሙር ቤቱ በሚደረግ ከፍተኛ ቅስቀሳ እየተታለለ ‹‹መዝሙሮቸቸውን››እየገዛ ይወስዳል፡፡በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀ ‹‹መዝሙር››ግጥሙንም ሆነ ዜማውን በቀላሉ ለማጥናት የተመቸ በመሆኑ ያለ ምንም ድካምና ውጣ ውረድ ሁሉም ‹‹ዘማሪ››ይሆናል፡፡በጣም የሚያስገርመው ደግሞ እንደዚህ ዓይነቱ ስህተት ውስጥ የቤ/ክ ትምህርት ያላቸውና የዜማም ባለሙያ የሆኑ የቤ/ክ አገልጋዮች ጭምር ይህንን መዝሙር መሰል ዘፈን እተቀበሉ ማስተጋባታቸው ነው፡፡
ለ/ እያስከተለ ያለው ችግር
1/ ከያሬዳዊ ዜማ የራቁ መሆናቸው
ሁላችንም እንደምናውቀው አገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለማት ተለይታ ማለትም በሕገ ልበና፤በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል ልዑል እግዚአብሔርን ስታመልክ የኖረችና ወደፊትም እስከ ምጽአት ድረስ ወልድ ዋሕድ በሚለው የተዋሕዶ እምነት ጸንታ የምትኖር መሆኗን ቅዱሳት መጻሕፍት መሰክራሉ፡፡በምሥጋናም በኩል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ከሚመስሏት እህት አብያተ ክርስቲያናት እንኳን ሳይቀር ተለይታ በቅዱስ ያሬድ አማካይነት ሰማያዊውን ዜማ ከፈጣሪዋ ተቀብላ መላውን አልግሎቷን ትፈጽማለች፡፡ስለ ቅዱስ ያሬድና ስለ ተቀደሰው የዜማና የድርሰት አገልግሎቱ ለመተረክ የጀመርነው ርዕስ ስለማይፈቅድልን ወደ ተነሳነበት ርዕስ እንመለለሳን፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው በሁሉም አቅጣጫ የተሰለፉት አጥፊዎች፤ማለትም ሥራችን ብለው ለጥፋት የቆሙትም ሆኑ በግዴለሽነት ለገንዘብ ብቻ ብለው የሚሠሩት ክፍሎች ዋናው የጥፋት ተልእኳቸው የሚያነጣጥረው ያሬዳዊውን ዜማ በማጥፋት ላይ ነው፡፡በዚህ አካሄዳቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ከዚህ ልዩ ከሆነ መንፈሳዊ ጸጋ አውጥተው የዘፈንና የዳንኪራ ቤት ማድረግ ነው፡፡
2/ የመዝሙሮቹ ግጥሞች የሚያስተላልፉት መልእክት
እንግዲህ በዜማው በኩል ያለው ችግር ይህንን ሲመስል፤የሚያስተላልፉት መልእክትም እንደዚሁ የተዋሕዶውን እምነትና ሥርዓት እንዲሁም ትውፊት የሚያፋልሱ ናቸው፡፡ሆነ ብለው ለማጥፋት የተነሱት የመናፍቃን ክፍሎችም ሆኑ ከእውቀት ማነስ በዘፈቀደ የሚያዘጋጁት ክፍሎች ያንኑ የፕሮቴስታንቱን አመለካካት የሚያንጸባረቁ ከመሆናቸው ሌላ ምንም አይነት መንፈሳዊ ለዛ የሌላቸውና የልዑል እግዚአብሔርን፤የእመቤታችንንና የቅዱሳንን ሥም በፌዝ የተሞሉ ተራ ቃላት በመጠቀም በከንቱ መጥራታቸው እጅግ ያሳዝናል፡፡ያሳፍራልም፡፡ የማይሰራውን የማይናገር፤የተናገረውንም የማያስቀር አምላክ በመጨረሻው ዘመን ብዙ ሐሰተኞች በስሜ ይመጣሉ ያለው ቃሉ አይታበልም፡፡ምዕመናን እስኪ እናንተ ፍረዱ! የጌታችን የአምላካችንና የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የከበረ ስሙን፤በሰማይም በምድርም ከምድርም በታች ያሉ ፍጥረታት ሁሉ የሚግዱለትን፤የሚንቀጠቀጡለትን ከስምም በላይ የሆነ ስሙን! (ሎቱ ስብሐት) እንደ ግል ጓደኛቸው (በጣም አጸያፊ የሆኑትን ትተን) የኔ ወዳጅ ፣የኔ ናርዶስ፣ፍቅርህ ልቤን ነካው፣የጽድቅ ልብሳች፣የመልካሞች መልካም፣…ወ.ዘ.ተ እያሉ በድፍረትና በንቀት የሚናገሩት ምን ያህል ትዕቢት ቢይዛቸው ይሆን? ለመሆኑ ለወላዲተ አምላክ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምስ ‹‹ካለኝ ነገር ሁሉ አንቺን መርጫለሁ››ተብሎ ይነገራል? ያውም ዘማሪው ካለው ቁሳቁስ ጋር ተነጻጽራ?!እግዚኦ! ምን ዓይነት አለማስተዋል ነው? ጸጋ እግዚአብሔር ያደረባቸው ቅዱሳን አባቶቻችን ግን በማንና በምን እንመስልሻለን? በማለት ተጨነቁ!ተጠበቡ! እንጂ የድፍረት ቃላት አልተናገሩም፡፡
ሐ/ ለማስመሰል የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች
1/ የዜማ መሣሪያዎች
የቤተ ከርስቲያናችን የዜማ መሣሪያዎች ከበሮ፣ጸናጽል፣መቋሚያ፣በገና፣ዋሽንት፣ክራርና መሰንቆ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ስለሆነም እንደ ብዙዎቹ ምዕመናን አመለካከት አንድን መዝሙር የኦርቶደክስ ተዋሕዶ ነው የሚያሰኘው ከላይ በተጠቀሱት መሣሪያዎች መቀነባበሩ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ተኩላዎቹ ግን እንኳን የዜማ መሣሪያዎቹን ይቅርና የካህናትንና የመነኮሳትን ልብስ ለብሰው፤መስቀላቸውን ይዘው፤ዲያቀን፣ቄስ፣መነኩሴ፣…ወ.ዘ.ተ. መስለው እያሳሰተቱ መሆናቸውን ቀደም ባሉት ክፍሎች ለማሳየት ሞክረናል፡፡ስለሆነም የመዝሙሮቹን ትክክለኛነት የምንለየው በግጥሙና በዜማው እንጂ በመሣሪያው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ለዚህም ማረጋገጫው ከላይ ከተጠቀሱት የዜማ መሣሪያዎች ውስጥ የተወሰኑት ለዘፈንም ጭምር እያገለገሉ መሆናቸው ነው፡፡
2/ ከቅዳሴና ከመሳሰሉት በመጥቀስ
ከማስመሰያ ዘይቤያቸው አንዱ ከቅዳሴና ከመሳሰሉት እየቆነጸሉ በመጠቀም ሲሆን፤ለምሳሌ ብንጠቅስ፦ አንዲት ሴት ዘማሪ ‹‹ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ››ትርጉም ‹‹ልቡናዬ በጎ ነገርን አወጣ›› የሚለውን የእመቤታችንን ቅዳሴ እንደ መነሻ ተጠቅማ፤ከዚያ አሰከትላ ያንኑ የራሷን ደርሰት ትቀጥላለች፡፡ሌላው ይህንን የሚመስል ደግሞ አለ፡፡በዓመት አንድ ጊዜ፤ በዕለተ ስቅለት፤ ዓርብ ከቀኑ በስድስት ሰዓት፤ በስግደትና በልዩ ሥርዓት በዲያቆናት የሚሰበከው ‹‹ቀነዉኒ እደውየ ወእገርየ--››ትርጉም ‹‹እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ--›› የሚለው ምስባክም በአሳዛኝ ሁኔታ ከላይ እንደተጠቀሰው ለአጓጉል ዓላማ ሲጠቀሙበት ማየትና መስማት አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ይህንን የመሳሰሉ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ይህ አድራጎታቸው ሁለት ትልልቅ ስህተቶችን ያሳየናል፡፡አንዱ በቤተ ክርስቲያን ያውም በካህናት ብቻ የሚከናወኑትን እነዚህን የጸሎት ክፍሎች በማይገባው ሰውና ቦታ መዋሉ ሲሆን፤ሁለተኛው ደግሞ የራሳቸውን ልብ ወለድ ድርሰት የተዋሕዶ ለማስመሰል የተጠቀሙበት የማጭበርበሪያ ዘዴ መሆኑ ነው፡፡በውኑ ታዲያ ይህ አካሄድ እግዚአብሔርን ማገልገል ነው ወይስ በስሙ መዘባበት? መልሱን ለአንባቢያን፡፡
መ/የመፍትሔ ሃሳቦች
1/ በየደረጃው ከሚገኙ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች/ልዩ ልዩ አገልጋዮች/
ጌታችን አምላካችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ከመሠረተ በኋላ፤ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፤ አስቀድሞ የመረጣቸውን ቅዱሳን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሁሉ እየዞሩ፤ ወንገልን እያስተማሩ፤እያጠመቁና እያቆረቡ የሰውን ልጆች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ወደ እግዚአብሔር ያቀረቧቸው ምዕመናን በልዩ ልዩ ፈተና እንደይሰነካከሉ መጠበቅ ስላለባቸው በሐዋርያው በቅ/ጴጥሮስ አማካይነት ግልገሎቼን አሰማሩ፤ጠቦቶቼን ጠብቁ፤በጎቼን አሰማሩ በማለት አዟቸዋል፡፡ /ዮሐ.21፤15-17/ ይህንንም የጌታችንን ትእዛዝ መሰረት በማድረግ ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሐ.ሥራ 20፤28-30 ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤ/ክ ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡ከሄድኩ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባቸሁ ደቀ መዛሙርቱንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሱ እኔ አውቃለሁ››በማለት አስጠንቅቋል፡፡በእነርሱም እግር የተተኩት ካህናትም ይህንኑ አገልግሎት እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
ሆኖም አሁን በዘመናችን የምናየው ግን ከላይ ከጳጳሳት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያሉ የቤ/ክ አስተዳዳሪዎችና ልዩ ልዩ አገልጋዮች ላይ የሚታየው ቸልተኝነትና አንዳንዶቹም ተባባሪ መሆናቸው ከችግሩ ስፋት ጋር ተደምሮ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እንመለከታለን፡፡ከላይ በጥቂቱ ለመግለጽ እንደሞከርነው በሐሰተኛ ትምህርቶችም ሆነ በመዝሙሮች በኩል የገለጽናቸው ችግሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳይገቡ ገና ከጅምሩ መታረም የሚገባቸውን በማረም፤ ሊታረሙ የማይችሉትን ደግሞ እንዲወገዱ ማድረግ ሲገባቸው በጊዜው ችላ ብለው በማለፋቸው ምክንያት ስህተቱ በእያንዳንዱ ምዕመን ልብ ውስጥ ሰርጾ ስለገባ በቀላሉ ለማስተካከል የማቻልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡አሁንም ቢሆን ግን ቢያንስ በቤተ ክርስቲያኒቱ አውደ ምህረት፤በሰንበት ት/ቤትና በተለያዩ የቤ/ክ ጉባዓዎች መዝሙሮቹ እንዳይዘመሩና እንዳይሸጡ በማድረግና ስለ ስህተቱ ምዕመናኑን በማስተማር ከገቡበት አዘቅት እንዲወጡ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በምዕመናንም በኩል ቢሆን ምንም እንኳን ያሬዳዊውን ዜማ ከሌላው ዜማ መለየት ከባድ ቢሆንም ቢያንስ የመዝሙርና የዘፈን ዜማና ይዘቱን መለየት አያዳግትምና፤ይህንን ቤተ ክርስቲያናችንንና የእያንዳንዳችንን መንፈሳዊ ሕይወት የሚጎዳ ነገር በገንዘባችን እየገዛን በመጠቀም ጥፋተኞችን ማበረታታት አልነበረብንም፡፡የለብንምም፡፡ለመሆኑ የዋሆች ናቸው እየተባልንስ የመናፍቃንና የነጋዴዎች ሸቀጥ ማራገፊያ የምንሆነው፤ያለንበትን ዘመን እየዋጀን ማዘንና ማልቀስ ሲገባን መዝሙር በመሰለ ዘፈን እራሳችንን እየደለልን የምንኖረው፤ትክክል ያልሆነውን ትምህርትና መዝሙር እየሰማን በ‹‹ምናለበት›› አባዜ ተይዘን ዝም መለታችን አንሶ ፤ለሚያሳዝነውም ሆነ ለሚያስደስተው ትምህርትና መዝሙር እልል እያልንና እያጨበጨብን የምንኖረው፤እስከ መቼ ነው ? ልንነቃና ልናስተውል ይገባናል፡፡
3/ ከሰንበት ት/ቤት ወጣቶች
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እምነቷንና ሥርዓቷን ከአባቶች ወደ ልጆች ለማስተላለፍ እንደ ቀድሞው እንዲሁ በልማድ ብቻ መቀጠሉ በቂ ስላልሆነ በእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት አቋቁማ ህጻናትና ወጣቶች በዕለተ ሰንበት እየተሰበሰቡ በመንፈሳዊው ትምህርትና ሕይወት ተኮትከተው እንዲያድጉ አድርጋለች፡፡እያደረገችም ነው፡፡ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ቀደም ብለን የጠቀስናቸው የቤ/ክ ጠላቶች ዋናው የዓለማቸው ማስፈጸሚያ ለማደረግ የሚፈልጉት ወጣቱን ትውልድ ነው፡፡የወጣትነት ዕድሜ ክልል ደግሞ አዲስ ነገርን ለመቀበል ፈጣን ስለሆነ፤ተኩላዎቹ ከአዋቂዎች ይልቅ ወጣቶቹን መስለው ለማሳሳት ይመቻቸዋል፡፡ስለዚህ እኛ ወጣቶች ወላጆቻችን ከቀደሙት አባቶቻችን የተረከቧትን ቅድስትና ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ሳትበረዝና ሳትከለስ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ መንፈሳዊ ግዴታ ሰላለብን ወደ እውነተኞቹ መምህራን እየቀረብን ትክክለኛውን ትምህርትና መዝሙር በመማር ከሐሰተኞቹ ወጥመድ እራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡መዝሙሩ ዜማውም ሆነ ግጥሙ ለማጥናት ቀላል ስለሆነ ብቻ በየዋህነት መቀበል የለብንም፡፡
ማጠቃለያ
‹‹ለሰይጣን የተሰናዳ መንገድ አትሁኑ!›› ድርሳነ ሰንበት ገጽ 53
እንግዲህ የብሉይ ኪዳኑን ዘመን ትተን ከአዲሱ ኪዳን ዘመን እንኳን ብንነሳ፤የቀደሙት ቅዱሳን አባቶቻችን ለሁለት ሺህ ዘመናት ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለው፤እምነታችንን፣ሥርዓትችንንና ትውፊታችንን በሥርዓቷ አጥርነት ጠብቀው በቅብብል እኛ ዘመን ላይ አድርሰዋታል፡፡እኛም ይህችኑ ቀጥተኛ ሃይማኖት ሳትበረዝና ሳትከለስ ለልጆቻችን ማሰረከብ ሲገባን ምዕመናን በካህናት፤ካህናት በአስተዳዳሪዎች፤አስተዳዳሪዎች በበላይ ሃላፊዎች እያመካኘን ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለቤት አጥታ፤ የሰይጣን መልእክተኞች በሆኑ በመናፍቃንና በሥርዓተ አልበኞች ስትወረር ዝም ብለን የምናየው እስከ መቼ ነው? ሁላችንም እንደየድርሻችንና እንደየአቅማችን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን ካልተወጣን በፍርድ ቀንኮ እያንዳንዳችን የምንጠየቀው በተሰጣችሁ ጸጋ ምን ሰራቸሁ ተብለን ነው፡፡ታዲያ በዚያን እናት እንኳን የሴት ልጇን ጩኸት በማትሰማበት የፍርድ እለት ምን እንመልሳለን? ሁላችንም በዚህ ምድር ከታሪክ ወቀሳና ተጠያቂነት፤በሰማያዊው ቤት ደግሞ ከዘላለም ፍርድ ለመዳን፤ምን እናድርግ ? ብለን በቅን ልቡና በመነሳት ለቤተ ክርስቲያናችን ህልውና አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ነገ ዛሬ ሳንል አሁኑኑ መነሳት አለብን፡፡
ለዚህም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡
ምን ይሰማህ ይሆን?
እስቲ ተናገረኝ ለአንድ አፍታ አጫውተኝ
ቅዱስ ያሬድ ሆይ ቃሎችህ ናፈቁኝ
የዛሬው ልጆችህ ላይነቁ ቢተኙ
ያንተ ያልሆነውን ቅኝቱን ቢቃኙ
ፒያኖ ኦርጋኑን ሊያስገቡ ቢመኙ
ዜማውና ግጥሙን ባሻቸው ቢወስዱት
ለአንተ የቆመውን በነገር ቢወጉት
''ምን ችግር አለው'' የሚል ፈሊጥን ቢያመጡ
ነፍሳቸውን ትተው ለስጋ ቢሮጡ
ይሄ ክፉ ዘመን ይሄንን ቢያሳየኝ
ሰምቼ እንዳልሰማ አይቼ እንዳላየ መሆኑ ቢያቅተኝ
ከአባቴ ከአንተ ጋር ማውራቴ ናፈቀኝ
እኔም እንዳልወድቅ ያሬድ ሆይ አበርታኝ
እስቲ ልጠይቅህ ከልብህ አጫውተኝ
ያንተ ደቀ መዝሙር መሆኑ አማረኝ
ሶስቱ አዕዋፍ ወደ ላይ ሲወስዱህ
ከመላዕክቱ ዘንድ ዜማ ሲያስተምሩህ
ምን ብለውህ ነበር እንዴትስ አስረዱህ
ሰማያዊን ዜማ እንዴት ገለጡልህ
ደግሞስ ምድር መጥተህ ዜማውን ስታዜም
የአርያሙን ዜማ በምድር ስትደግም
በየትኛው ቋንቋ ለሰዎች አስረዳህ
በየቱስ አዕምሮ ምሥጢሩን ተረዱህ
ይሄኛው ትውልድስ እንደምን አቃተው
ያንተን ዜማ ማወቅ ለምንስ ከበደው?
እውነት ግን ያሬድ ሆይ እስቲ ተናገረኝ
ያንተ ደቀ መዝሙር መሆኑ አማረኝ
ያንተ ልጅ ያልሆነው እንዲህ ብሎ ያማሀል
ባንተ ሀሳብ ሳይሆን በአህዛብ ተወስዷል
ኦርጋኑ ፒያኖ ቢኖር በዚያ ዘመን
ያኔ ቢገኝ ኖሮ ሌላኛው ሳክስፎን
እንደ ምትጠቀም በብዙ ያማሀል
ከየት እንደተማርክ ፍፁም ረስተውታል
በገና መለከት መሰንቆ ዋሽንቱ
እንቢልታው ከበሮ ሁሉን በየአይነቱ
ደግሞም ሌላኛው ጽናጽል መቋሚያ
አርገህ ስታስቀምጥ የዜማ መሳሪያ
ጠፍቶህ ይሆን እንዴ ኦርጋኑ ፒያኖው
ወይስ ስለሌለ ሳክስፎን በጊዜው
ጠማማውን ትውልድ እሰስቲ ተናገረው
ቃልህን ወርውረህ አፉን ዝም አሰኘው
አሁንስ ያሬድ ሆይ ምን ይሰማህ ይሆን?
ብልሽትሽት ሲያደርጉት ቅዱሱን ዜማህን
የያሬድ ነው ብለው በሚያዜሙት ዜማ
ዜማው ካንተ ዜማ ፍጹም ማይስማማ
ባንተ ስም ነግደው ባንተ ስም አትርፈው
በየካሴቱ ላይ ስምህን ለጥፈው
ሲሸጡ ሲያሸጡ ለብራቸው ብለው
ለነፍሳቸው ሳይሆን ለስጋቸው ሮጠው
ዛሬ ብታያቸው ምን ይሰማህ ይሆን?
ብልሽትሽት ሲያደርጉት ቅዱሱ ዜማህን
ደግሞም በሌላኛው ያንተን መሳሪያዎች
ሲጠቀሙ ስታይ በየአዳራሾች
አንተ የጨበጥከውን ጽናጽል ጨብጠው
አንተ የያዝከውን መቋሚያውን ይዘው
መናፍቅ ተብዬው ትርጉሙን ባያውቀው
እንደ አውሎ ንፋስ ዥው ዥው ቢያረገው
ድንገት ብታገኘው ባልኖረበት ቦታ
ዛሬ ላይ ብታየው ከበሮው ሲመታ
ምን ይሰማህ ይሆን?
በየትኛው ቃልስ ትገስፀን ይሆን?
(ምንጭ: ከማህበራዊ ድረ ገጽ)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ርዕስ እንቀጥላለን፡፡
ምን ይሰማህ ይሆን?
እስቲ ተናገረኝ ለአንድ አፍታ አጫውተኝ
ቅዱስ ያሬድ ሆይ ቃሎችህ ናፈቁኝ
የዛሬው ልጆችህ ላይነቁ ቢተኙ
ያንተ ያልሆነውን ቅኝቱን ቢቃኙ
ፒያኖ ኦርጋኑን ሊያስገቡ ቢመኙ
ዜማውና ግጥሙን ባሻቸው ቢወስዱት
ለአንተ የቆመውን በነገር ቢወጉት
''ምን ችግር አለው'' የሚል ፈሊጥን ቢያመጡ
ነፍሳቸውን ትተው ለስጋ ቢሮጡ
ይሄ ክፉ ዘመን ይሄንን ቢያሳየኝ
ሰምቼ እንዳልሰማ አይቼ እንዳላየ መሆኑ ቢያቅተኝ
ከአባቴ ከአንተ ጋር ማውራቴ ናፈቀኝ
እኔም እንዳልወድቅ ያሬድ ሆይ አበርታኝ
እስቲ ልጠይቅህ ከልብህ አጫውተኝ
ያንተ ደቀ መዝሙር መሆኑ አማረኝ
ሶስቱ አዕዋፍ ወደ ላይ ሲወስዱህ
ከመላዕክቱ ዘንድ ዜማ ሲያስተምሩህ
ምን ብለውህ ነበር እንዴትስ አስረዱህ
ሰማያዊን ዜማ እንዴት ገለጡልህ
ደግሞስ ምድር መጥተህ ዜማውን ስታዜም
የአርያሙን ዜማ በምድር ስትደግም
በየትኛው ቋንቋ ለሰዎች አስረዳህ
በየቱስ አዕምሮ ምሥጢሩን ተረዱህ
ይሄኛው ትውልድስ እንደምን አቃተው
ያንተን ዜማ ማወቅ ለምንስ ከበደው?
እውነት ግን ያሬድ ሆይ እስቲ ተናገረኝ
ያንተ ደቀ መዝሙር መሆኑ አማረኝ
ያንተ ልጅ ያልሆነው እንዲህ ብሎ ያማሀል
ባንተ ሀሳብ ሳይሆን በአህዛብ ተወስዷል
ኦርጋኑ ፒያኖ ቢኖር በዚያ ዘመን
ያኔ ቢገኝ ኖሮ ሌላኛው ሳክስፎን
እንደ ምትጠቀም በብዙ ያማሀል
ከየት እንደተማርክ ፍፁም ረስተውታል
በገና መለከት መሰንቆ ዋሽንቱ
እንቢልታው ከበሮ ሁሉን በየአይነቱ
ደግሞም ሌላኛው ጽናጽል መቋሚያ
አርገህ ስታስቀምጥ የዜማ መሳሪያ
ጠፍቶህ ይሆን እንዴ ኦርጋኑ ፒያኖው
ወይስ ስለሌለ ሳክስፎን በጊዜው
ጠማማውን ትውልድ እሰስቲ ተናገረው
ቃልህን ወርውረህ አፉን ዝም አሰኘው
አሁንስ ያሬድ ሆይ ምን ይሰማህ ይሆን?
ብልሽትሽት ሲያደርጉት ቅዱሱን ዜማህን
የያሬድ ነው ብለው በሚያዜሙት ዜማ
ዜማው ካንተ ዜማ ፍጹም ማይስማማ
ባንተ ስም ነግደው ባንተ ስም አትርፈው
በየካሴቱ ላይ ስምህን ለጥፈው
ሲሸጡ ሲያሸጡ ለብራቸው ብለው
ለነፍሳቸው ሳይሆን ለስጋቸው ሮጠው
ዛሬ ብታያቸው ምን ይሰማህ ይሆን?
ብልሽትሽት ሲያደርጉት ቅዱሱ ዜማህን
ደግሞም በሌላኛው ያንተን መሳሪያዎች
ሲጠቀሙ ስታይ በየአዳራሾች
አንተ የጨበጥከውን ጽናጽል ጨብጠው
አንተ የያዝከውን መቋሚያውን ይዘው
መናፍቅ ተብዬው ትርጉሙን ባያውቀው
እንደ አውሎ ንፋስ ዥው ዥው ቢያረገው
ድንገት ብታገኘው ባልኖረበት ቦታ
ዛሬ ላይ ብታየው ከበሮው ሲመታ
ምን ይሰማህ ይሆን?
በየትኛው ቃልስ ትገስፀን ይሆን?
(ምንጭ: ከማህበራዊ ድረ ገጽ)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ርዕስ እንቀጥላለን፡፡
ይቆየን፡፡
ቃለ ህይወት ያሰማልን መልእክቱን በፌስ ቡክ እያስተላለፍኩ ነው ፍቃደኛ መሆናችሁን ብትገልጡልኝ
ReplyDelete