ከክፍል አስራ አራት የቀጠለ
"እያወቁ ማለቅ"
"ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ፡፡"
በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ሁሉን ቻይ ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር እውቅና
እና ፈቃድ ውጪ የሚከናወን ምንም ነገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ይታመናልም፡፡ይሁን እንጂ ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን ከሌሎች ፍጡራን
ለይቶ በመልኩና በምሳሌው ሲፈጠረው የማሰብ፣የመናገርና ሕያው ሆኖ የመኖር ዕድል ሰጥቶታል፡፡የሰው ልጅ በዚህ በተሰጠው አእምሮ መመራት
አቅቶት በኃጢአት ቢወድቅ፤ይህንን አድርግ ይህንን አታድርግ የሚል የተጻፈ ህግ /ህገ ኦሪትን/ ሰጠው፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም፤እራሱ
እግዚአብሔር ወልድ ወደዚች ምድር መጥቶ ለሰው ልጅ የቤዛነቱንና የአርአያነት ሥራውን ፈጸሞለታል፡፡ ጌታችን መድሐኒታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ በጽንስ ጀምሮ በመሰቀል የፈጸመውን የቤዛነቱን ሥራ እፁብ! ድንቅ! ብሎ ከማመስገን በስተቀር በዚች አጭር ጽሁፍ የምንለው
ነገር አይኖረንም፡፡በአርአያነት/በምሳሌነት/ ሥራው ግን ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ህግ ሁሉ ፈጽሞ እኛም እንድንከተለው አዝዞናል፡፡በእኔ
ያመነ እኔ የምሰራውን ሁሉ ያደርጋል፤እንደውም የበለጠ ያደርጋል ብሎ፡፡ዮሐ.14፥12፡፡
ወደ ተነሳነበት ርዕስ ስንመለስ፤" እያወቁ ማለቅ"ብለን
የተነሳንበት ምክንያት፤ ከላይ ቀደም ባሉት ክፍሎች(ከክፍል አንድ እስከ አስራ አራት) በስፋት እንደገለጥነው፤
ከጥንት ጀምሮ ቀጥተኛይቱን ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ለመበረዝና ለመከለስ ብዙ የደከሙ የተለያዩ መናፍቃን እንደነበሩ ሁሉ፤በአሁኑም
ጊዜ እነዚህ የተለያዩ የጥፋት መልእክተኞች ከውጪ ሆኖ ከመዋጋት ይልቅ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ልጅ በመምሰል የግብር አባታቸው ዲያቢሎስ
በሚያሳያቸው የጥፋት መንገድ ስልታቸውን እየቀያየሩ ብዙ የዋሃን ምዕመናንን
የማደናገር ስራቸውን አጥብቀው ተያይዘውታል፡፡ቀደም ያለውን ታሪክ ትተን የዓይን ምስክር መሆን ከምንችልበት ከ1980
ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ ያለውንና በተለያየ መንገድ በመደራጀት የጥፋት አድማሱን እያሳደገ የመጣውን የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን
እንቅስቃሴ የማያውቅ የቤ/ክ ልጅ አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ታዲያ ከጊዜ
ወደ ጊዜ እየደገ መጥቶ ጥፋቱን በቀላሉ ለመግታት የማይቻለበት ደረጃ ላይ የደረሰበት ምክንያት ምንድነው ብለን ስናጠና፤ከብዙዎቹ
ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1/ "እግዚአብሔር ቤቱን ይጠብቅ!" የሚል ምክንያት፦
እርግጥ ነው ልዑል እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በውስጣቸውም የሚገኙትንም
ልዩ ልዩ ፍጥረታት ፈጥሮ በመግቦቱ ያስተዳድራል ይጠብቃል፡፡እንዲሁ ለከንቱ ነገር የተፈጠረ ፍጥረት ስለሌለ ለእያንዳንዱ ፍጥረት
የሥራ ድርሻ አለው፡፡ከሁሉም በላይ ደግሞ በቅድስት ሥላሴ አምሳል የተፈጠረ ሰው ከሌሎቹ ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡በተፈጥሮ
ሰው ከሆኑት መካከል ደግሞ በአንዲቷ ጥምቀት ከቅድስት ሥላሴ የጸጋ ልጅነት ያገኘና የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ
ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብሎ የዘላለም ሕይወትን ለመውረስ የተዘጋጀ ክርስቲያን ደግሞ ከሁሉም በላይ ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ ከነዚህ
ሥራዎች አንዱና ዋነኛው እራሱንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ከከሃድያንና
ከመናፍቃን የስህተት ትምህርት መጠበቅ ነው፡፡
ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ እዚህ እኛ
አለንበት ዘመን ድረስ የደረሰችበትን ታሪክ ስንመለከት፤ቅዱሳን አባቶቻችን ዓለምን ዞረው ከማስተማር ጋር በየጊዜው የሚነሱትን መናፍቃን
ተከራክረው እየረቱ፤አልመለስ ያሉትን እያወገዙ፤ቀጥተኛይቱን ሃይማኖት አያጸኑ፤ከከሃድያን ነገሥታት ፊት በድፍረት ስለ እግዚአብሔር እየመሰከሩ፤በአጠቃላይ እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው፤ንጽህትና
ቅድስት የሆነችውን ተዋህዶ ሃይማኖታችንን ለእኛ አስረከበውናል፡፡እኛም ይህንን የአባቶችችንን ፈለግ ተከትለን እውነተኛ መንፈሳዊ
ተጋድሎ በማድረግ ሃላፊነታችንን መወጣት ሲገባን፤ "እግዚአብሔር
ቤቱን ይጠብቅ!"፣ "እግዚአብሔር ዝም
ያላቸውን እኛ ምን ማደረግ እንችላለን?"ወ.ዘ.ተ. እያልን የራሳችንን ሥራ ለእግዚአብሔር በመስጠት ያለንበት የቸልተኛነት
ሁኔታ ከውጭም ሆነ ከውስጣችን ላሉት መናፍቃንና ሌቦች ያለ ጠያቂ እንደፈለጉ ለመመዝበር እንዲችሉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮላቸዋል፡፡
2/ "ትንቢቱ መፈጸም ስላለበት ነው" የሚል ዘበት፦
ስለ መጨረሻው
ዘመን አስከፊነት የተለያዩ ነቢያት ትንቢት መናገራቸው፣ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ሥጋዌው ተጠበቁ፣ተጠንቀቁ ብሎ ማስተማሩ፣እንዲሁም
ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ እስከ ዓለም
ዳርቻ ዞረው ወንጌልን ሲያስተምሩ፤ ከነሱም በኋላ የተነሱ ቅዱሳን
አባቶች ሁሉም በአንድ ቃል ስለዚሁ አስቸጋሪ ዘመን መናገራቸው አይካድም፡፡እዚህ ላይ አጥብቀን ልናስተውለው የሚገባን አንድ ትልቅ
ነገር አለ፡፡ይኸውም አንድን ነገር እንዲሆን ማድረግና ነገሩን እንደሚሆን አስቀድሞ አውቆ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር የተለያዩ መሆናቸውን ነው፡፡ልዑል እግዚአብሔር
ሁሉን አዋቂ በመሆኑ እንኳን የተደረገውን ይቅርና ሊታሰብ ያለውን ነገር ሳይቀር ያውቃል፡፡ስለሆነም ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ዓለም ፍጻሜ ሲጠይቁት ከነገራቸው ምልክቶች ውስጥ አንዱ፤ በተቀደሰው አደባባይ/በቤተ ክርስቲያን/ የረከሰ ሥራ እንደሚሰራ ነው፡፡ብዙዎቻችን
ይህንን ቃል በትክክል ካለመረዳታችን የተነሳ፤በቤ/ክ ውስጥ የተለያዩ የርኩሰት ሥራዎች ሲሰሩ እያየን ዝም የምንለው ጥፋቱን እግዚአብሔር
የፈቀደው እንደሆነ አድርገን ስለምናስብ ነው፡፡ሃሳቡን ግልጽ ለማድረግ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እንይ፤
ለምሳሌ፦
- አዳምና ሔዋን እፀ በለስን በመብላት ከፈጣሪያቸው ትእዛዝ እንደሚወጡ እግዚአብሔር አስቀድሞ አያውቅም ነበር ማለት አንችልም፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን እፀ በለስን የበሉት የራሳቸውን ነጻ ፈቃድ ተጠቅመው ነው እንጂ እግዚአብሔር ነገሩን አስቀድሞ ማወቁ በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮባቸው አለመሆኑን ማስተዋል አለብን፡፡ዘፍ3፥6.፡፡ እንዲሁም ስለ ሠሩት ኃጢአት ተጸጽተው ንሰሃ በመግባታቸው ከተወሰነ የቅጣት ዘመን በኋላ ፤ያውም በመልእክተኛ ሳይሆን እራሱ ልዑል እግዚአብሔር ወልድ ወደ ምድር ወርዶ በከፈለው የቤዛነት ሥራ ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል፡፡የቅ/ጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች 5፥10፡፡
- የነነዌ አገር ሰዎች ከኃጢአታቸው ካልተመለሱ በሶስት ቀን ውስጥ እንደሚጠፉ እግዚአብሔር በነቢዩ በዮናስ አማካይነት ከተናገረ በኋላ፤የነነዌ ሰዎች ተጸጽተው በጾምና በጸሎት ወደ ፈጣሪያቸው በመመለሳቸው፤እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከታዘዘው ጥፋት መዳናቸውን በትንቢተ ዮናስ 3፥1-10 እናነባለን፡፡
- እግዚአብሔር ንጉሥ ሕዝቅያስን "ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል" ብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል ከተናገረው በኋላ፤ንጉሡ በንስሃና በእንባ ወደ ፈጣሪው በመመለሱ፤ትሞታለህ የተባለው ሰው እንደገና አስራ አምስት አመት እድሜ ተጨምሮለት በሰላምና በጤና እንደኖረ /በ2ኛ ነገ.20፥1 /ተመዝግቦልናል.፡፡
የተነሳንበትንም ርዕስ በዚሁ መልክ ስናየው፤ ምንም
እንኳን በመጨረሻው ዘመን ረሃብ፣ቸነፈር፣የምድር መናወጥ፣የፍቅር መቀዝቀዝ፣ በተቀደሰው ሥፍራ በቤተ ክርስቲያን የርኩሰት ሥራ በዝቶ መሰራት፣…እና የመሳሰሉት የኃጢአትና የአመጻ ውጤቶች
እንደሚፈጸሙ ቢነገርም፤/ማቴ.24 በሙሉ ያንብቡ/ እኛ ከኃጢአታችን በንስሃ ከተመለስን፤ ለስሙ ክብር ምሥጋና ይግባውና በባሕርይው
ቸር የሆነ አምላካችን እግዚአብሔር ቁጣውን በትዕግስት መዓቱን በምሕረት እንደሚለውጥልን፤ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንም ወደ ቀደመ
ክብሯ እንደሚመልስልን የታመነ ነው፡፡ስለሆነም በራሳችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያለ አገባብ ያነገሥነውን
የርኩሰት ሥራ ለማስወገድ እግዚአብሔር በሚሰጠን ኃይል ቆርጠን መነሳት የሚገባን ሰዓቱ አሁን ነው፡፡
3/ አንዱ በሌላው ማመካኘት፦
ሌላውና ሁላችንም ልንገነዘበው ያልቻልነው ሁኔታ "የፉክክር ቤት
ሳይዘጋ ያድራል" እንደሚባለው ዘይቤያዊ አነጋገር ሁሉም የየራሱን ድርሻ መወጣት ሲገባው ምዕመኑ በካህኑ፤ካህኑ በደብር አስተዳዳሪው፤የአስተዳዳሪው
በጳጳሱ፤ጳጳሱ በፓትርያርኩ፤ፓትርያርኩ በመንግሥት፤እያመካኙ ዝም በማለታቸው ምክንያት፤ቤ/ክ የከሃድያን፣የመናፍቃንና የሌቦች ዋሻ
ሆናለች፡፡ሆኖም ምክንያት ከፍርድ እደማያድን አዳም በሔዋን፤ሔዋን
በእባብ፤አመካኝተው ከቅጣት አለማምለጣቸውን ስናስብ የእኛም እንዲሁ መሆኑን ልብ ማለት አለብን፡፡
4/ ከእውቀት ማነስ፦
ከጥንት ጀምሮ እንደሚታወቀው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ምዕመናን ፍጹም በሆነ
ፈሪሃ እግዚአብሔርና ቅንነት በተሞላው የተሰበረ ልቦና ሆነው አምልኮታቸውን
ከሚፈጽሙ በቀር እንደ ካህናቱ መጻሕፍትን ተምረውና ተመራምረው አልነበረም ፡፡ እንደዛሬው የመጨረሻው ዘመን የወለዳቸው በክርስትና
ሥም የተመሰረቱ የተለያዩ ድርጅቶች ስላልነበሩ ከአንዲቷ የተዋሕዶ ቤ/ክ አውደ ምህረት የሚነገረውን ቃል ብቻ ሰምተው ያንኑ በመልካም
ተግባር እየተረጎሙ መላ እድሜያቸውን በእውነተኛ ክርስቲያናዊ ሕይወት አሳልፈዋል፡፡ይህ ዓይነቱ አካሄድ እስከ እኛ አያቶች ድረስ
ያለ ምንም ችግር ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ቅድስት ቤ/ክ ዘመኑ ያመጣውን የሐሰተኞች መምህራንን መብዛትና የስህተቱንም
ስፋት በመመልከት፤ከዚህ የጥፋት ጎዳና ልጆቿን ለመጠበቅ፤እምነቷን ሥርዓቷንና ትውፊቷን በተለያየ መንገድ በማስተማር ላይ ትገኛለች፡፡ይሁን እንጂ ሁሉም ምዕመን የራሱን
ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት ከሌላው የሚለይበትን ነገር አውቆና ተረድቶ ቢያንስ እራሱንና ቤተሰቡን እንኳን ከስህተቱ ትምህርት ለመጠበቅ ዝግጁ እንዳልሆነ የሚያመለክቱ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ለምሳሌ፦
ፕሮቴስታንታዊ ተሀድሶዎቹ ዛሬ እራሳቸውን "ተሀድሶ
ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ "የተሀድሶ ህብረት ንቅናቄ" …ብለው ከመሰየማቸውና፤ለድርጅታቸውም የእምነት መገለጫ ከመውጣታቸው
በፊት ስራቸውን ሲጀምሩ በጽዋ ማህበር እያስመሰሉ ነበር፡፡ነገር ግን ወጣቶቹ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከወር እስከ ወር በሚከናወነው
"የጽዋ ማህበር" ፕሮግራም መሶበ ወርቅና ጽዋው ጸዲቅና ጸበል ሳይጨመርበት ለማስመሰያ ብቻ ባዶውን ሲቀመጥ፤ ወላጆቻቸው
ሌላው የፕሮገራሙ ይዘት ለጊዜው ባይገባቸው እንኳን እስኪ ከጸዲቁና
ከጸበሉ እኛም እንቅመስ ብለው አለመፈተሻቸው ከየዋህነትም ያለፈ ጅልነት አይደለም? እንግዲህ ወጣቶቹ በዚህ ዓይነት ተራ የማጭበርበር
ስራቸው ከወላጆቻቸው ምንም ዓይነት ተቃውሞ ስላልገጠማቸው፤ይህንኑ የሥራ ልምድ በመያዝ ቀስ በቀስ እያደጉ መጥተው ዛሬ በማናለብኝነት
የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት እየተቃወሙ አልፈው ተርፈውም ቤተ ክርስቲያንን እኛው እናስተዳድራት እስከ ማለት የደረሱት የምዕመኑን
የእውቀት አናሳነትና ቸልተኝነት በማየት ነው፡፡ስለሆነም ነው ዛሬ በታላላቅ ገዳማት ዓውደ ምህረት ሳይቀር የተዋህዶ ያልሆኑ ትምህርቶችና
መዝሙሮች ሲተላለፉ ሁሉም አጃቢና ተባባሪ ሆኖ እልል ሲልና ሲያጨበጭብ የሚስተዋለው፡፡
5/የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዝምታና አልፎ ተርፎም ለጥፋተኞቹ ተባባሪ
መሆን፤
ሁላችንም እንደምናየውና ከተሉያዩ
የዜና ምንጮች እንደምንሰማው፤ በአሁኑ ጊዜ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን እምነት፤ሥርዐትና
ትውፊት ለመለወጥና ብሎም የፕሮቴስታንት ለማድረግ የተነሱት መናፍቃንም ሆኑ የተለያየ የአሰራረቅ ዘዴ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት እየዘረፉ
ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉት ዘራፊዎች ቁጥራቸው ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ይታያል፡፡ይህም የሆነበት ዋናው ምክንያት የጥፋቱ ሰንሰለት
ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ የተዘረጋ በመሆኑ ነው፡፡በዚህም ምክንያት ምንም ዓይነት የተጨበጠ
ማስረጃ ቢቀርብ እንኳን በጥፋተኞቹ ላይ ውሳኔ አይሰጥም፡፡የዚህ ጥፋት ተባባሪ ያልሆኑት ክፍሎች ደግሞ በሥራችንና በግል ሕይወታችን
ላይ ችግር ይደርስብናል ብለው በመፍራት ሁሉንም ነገር እያዩና እየሰሙ፤እንደ ባዕድ ለቅሶ፤እራሳቸውን ከጉዳዩ አርቀው በቸልተኝነት
ሲመለከቱት ይስተዋላል፡፡ ይህም ሁኔታ መናፍቃኑም ሆኑ ሌቦቹ እግዚአብሔርን አናውቅም፤ቤተ ክርስቲያንንም አንለቅም ብለው እንደፈለጉ
እንዲያጠፉ እድሉን አመቻችቶላቸዋል፡፡
እንግዲህ ርዕሳችንን "እያወቁ
ማለቅ" ብለን የጀመርነው በነዚህ ከላይ በዘረዘርናቸውና በሌሎችም ምክንያቶች ነው፡፡
ከእኛ ከተዋሕዶ ልጆች ምን ይጠበቃል?
1. ትክክለኛውን የተዋህዶ ትምህርትና የስህተቱን ትምህርት ለመለየት እንድንችል ከእውነተኞቹ መምህራን እየተማርን የራሳችንን
እምነት አጥርተን ማወቅ ፡፡
2. በተለያዩ ማህበራዊ ኑሮ ገጠመኞቻችን ( ሠርግና ለቅሶ የመሳሰሉት) ላይ የምንሰማውን ትምህርትም ሆነ መዝሙር በጥንቃቄ
መለየትና እራስንም ሆነ ሌላውን ከስህተት መጠበቅ፡፡
3. በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በየግላችን ከተዋሕዶ ትምህርት ውጪ የሆነ የተሳሳተ ትምህርትም ሆነ መዝሙር( በቃልም ይሁን በመጽሐፍ)
ሲያጋጥመን፤ ስህተት ፈጻሚውን አካል በመጠየቅና ስህተቱንም በመቃወም የተዋሕዶ ሃይማኖታችን እምነት፤ሥርዐትና ትውፊት እንዳይበረዝና
እንዳይከለስ ስለ እውነት ልንቆም ይገባናል፡፡
4. የቤተ ክርስቲያናችንን ሀብትና ንብረትም ከውስጥ ሌቦች መጠበቅና መንከብከብም መንፈሳዊ ግዴታችን መሆኑን አውቀን፤ እኔን
ምን አገባኝ ሳንል ከእኛ ከልጆቿ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን፡፡
5. ጦር መሣሪያችን ሥጋዊ ስላልሆነ፤ ልዑል እግዚአብሔር ኃይሉንና ጥበቡን እንዲያሳድርብን በጾምና በጸሎት መትጋት አማራጭ
የሌለው መፍትሔ ነው፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
አሜን፡፡
ይቆየን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣይ በሌላ ርዕስ እንመለሳለን፡፡
No comments:
Post a Comment