የተከበራቸሁ
አንባብያን!
በዚህ
የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "Bini
Zelideta" ከተባሉ
ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡
መልካም
ንባብ!
Bini Zelideta
“የተሃድሶ
መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ!”
ክፍል-1
(ስለ ነገረ ክርስቶስ) /መልዕክቱ የረዘመው ግጥሞች ስለበዙበት ነው/
መግቢያ
ቅድስት፤ኦርቶዶክሳዊት
ሃይማኖታችን ዕረፍት አልባ ዘመናትን ስታሳልፍ ዛሬ 2008 ዓመቷ ነው፡፡ ፈተናዎቿም እንደየ አዝማናቱና እንደፈታኞቿ የተለያዩ ነበሩ፡፡ ሠይፍ፣የዐላውያን መከራ፣የአናብሥት ትግል፣የክርስቲያኖች ስቃይ የሮም ኮሎሲየም አምፊ ቴአትር ትርዒት፣የቁም እሳት ቃጠሎ፣የካታኮምቡ ሕይወት፣የሠንሠለት ኑሮ እና የመንኩራኩር ስቃይ የመጀመሪያው እልህ አስጨራሽ ፈተናዋ ሲሆን እግር ተከትሎ፤ዓይነቱን ቀይሮ የመጣው የአርዮሳውያን ሃይማኖትን የመቀየር፣አስተምሕሮዋን የመበረዝ
እንቅስቃሴ ጣሯን፣ሰቀቀኗን፣መከራዋን አብዝቶባት ቆይቷል፡፡ ዮዲት ጉዲት፣የካቶሊክ ሚሲዮናውያን፣ጽንፈኛ አሕዛቦችና
የሉተር ርዝራዦች ዞረው ዞረው ሲሻቸው አንድ ላይ ሲሻቸው ደግሞ በፍርርቅ በመከረኛይቱ ሃይማኖት ላይ ቀንበር ሲጭኑ ኖረዋል ዛሬም ዕረፍት የላትም! የገሃነም ደጆች አይችሉአትም ተብሎ ስለተጻፈው አማናዊ ቃል ሁሉን አልፋ ዛሬ ብትደርስ ለሆዳቸው ያደሩ ሥጋውያን አስተምህሮዋን እናድሳለን ብለው ተነሡባት፡፡ ይህ ከቀደምት ዘመናት በዓይነትም በቅርጽም አካሄዱን ቀይሮ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ሥልት ይዞ የተነሣው ፕሮቴስታንታዊ ቡድን ስውር ተልዕኮውን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ በመሰንዘር ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል አሁንም በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ቅብ ይዘው፣ተቆርቋሪ መስለው መንገዷን ስታለች፣አስተምህሮዋ ልክ አይደለም፣አርጅታለች፣እናድሳታለን
ባዮች ሲሆኑ በትምርቶቻቸው እና ከዘፈን በተቃኙ መዝሙሮቻቸው ትውልድን መበረዝ የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል፡፡ በተለይም መዝሙሮቻቸው በአንድ ሌሊት ተደርሰው ንጋቱን ለጆሮ ስለሚበቁ ኑፋቄን ለማሰራጨት ደገኛ መሣሪያቸው ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
መዝሙር
በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ብዙዎችን ሊያድን የሚችል መሣሪያ ሲሆን ለክፋት ከዋለም ለብዙዎች መጥፊያ የሚሆን አደገኛ መሣሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ አትናቴዎስ አርዮስን በጉባዔ ፊት ከረታው በኋላ አርዮስ በንዴት አፈንግጦ በመውጣት እንደ ዛሬዎቹ የተሃድሶ መናፍቃን በየ ዓደባባዩና የተለያዩ አዳራሾች በመዘዋወር ግጥም እየገጠመና ዜማ እየደረሰ ብዙ ምእመናንን በክህደቱ መርዟቸዋል፡፡ አርዮስ ወደ መዝሙር የገባበት ዋና ዓላማ ትምህርቱን አልቀበል ስላሉት ነው፡፡ ከትምህርት ይልቅ መዝሙር ሰዎችን በቀላሉ ሊለውጣቸው እንደሚችል ካጠና በኋላ የክህደት ትምህርቱን ወደ መዝሙር በመቀየር ኑፋቄውን በቀላሉ ማስፋፋት ጀመረ፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስም የአርዮስን እኩይ ተግባር ቀድሞ በመረዳቱ የ325 ዓመተ ምህረቱን የሃይማኖት ድንጋጌ በግጥም መልክ በማዘጋጀትና ዜማ በመስጠት እንደ አርዮስ በየዓደባባዩ እና አዳራሹ ሳይሆን በየ አቢያተ ክርስቲያናቱ በመዘዋወር ለምዕመናን እየዘመረ ከአርዮስ ክህደት ታደጋቸው፡፡ አርዮስም አትናቴዎስም ትልቅ ሥራ የሠሩት በመዝሙር ነው! ለዚህ ይመስላል የዛሬዎቹ የተሃድሶ መናፍቃን ትምህርታቸውን አልቀበል ያሉ የዋሃንን በመዝሙሮቻቸው ለማታለል ቀን ከሌት የሚዳክሩት፡፡ በተለይ አሁን የምንፍቅና ጣቢያዎቻቸው ስለተዘጉባቸው ብቸኛ መተንፈሻ ሳንባቸው በየወሩ የሚያሳትሟቸው መዝሙራት ናቸው፡፡ አንዱ ዛሬ አዲስ የመዝሙር አልበም ካሳተመ በወሩ ሌላኛው ይለቃል እንዲህ እንዲህ እያሉ የለብ ለብ ዜማዎችን ከምንፍቅና ስንኞች ጋር እየቀየጡ በየሆቴሉና በየመናፈሻው መርቁልኝን ተያይዘውታል፡፡ በዛሬው መልዕክቴም እነዚህ ግለሰቦች በመዝሙሮቻቸው ትውልዱን ለማጣመምና ወደ ፈለጉት መንገድ ለመምራት እንዴት አድብተው እንደሚንቀሳቀሱ የሚያሰየውን ጥቂት መረጃ እነሆ እላለሁ፡፡ ይህን መረጃ ለማጠናቀር ከ30 የሚበልጡ የመዝሙር አልበሞቻቸውንና ከ300 በላይ መዝሙሮቻቸውን መዳሰስ ግድ ሆኖብኛል፡፡ ይህም ኑፋቄአቸውን በገሃድ በመዝሙሮቻቸው ማሰራጨት ከጀመሩበት ከ2000 ዓ/ም ወዲህ ያሉትን ሲሆን ይህ መልዕት እስከተዘጋጀበት ቀን ድረስ የወጡትን መዝሙሮቻቸውን ያካትታል፡፡ ሆኖም ይህን መረጃ በቀላሉ ለመረዳት እንዲያመች ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ለመጠቀም ተገድጃለሁ፡፡ የመዝሙሮቻቸው አዝማቾችና ስንኞች የተጠቀሱ ሲሆን የዘማርያኑ እና የገጣምያኑ ስም ግን አልተጠቀሰም፡፡ ስማቸው አለመጠቀሱ ምንም ዓይነት አንድምታ የማይኖረው ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ግን ሊጠቀስ ይችላል፡፡ በተጨማሪም መልዕቱ ዜማቸውን አይዳስስም ምክንያቱም የለየለትን ዘፈንኛ ዳንኪራና መንደርተኛ እንጉርጉሮ ጊዜ ሰጥቶ እንዲህ ነው እንዲህ አይደለም ለማለት አይመጥንምና! የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት፡-(ስለ ነገረ ክርስቶስ) የተሃድሶ መናፍቃን ዘማርያን በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ የሚዘምሯቸው ሁሉም መዝሙራት ማለት ይቻላል ፍጹም በአንድ ዓይነት ይዘት የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ የመዝሙሮቻቸው አቅጣቸውና ዓቢይ መልዕክት ‹‹ዕለተ አርብ›› እና ‹‹መስቀል ላይ ስለተፈጸመው ነገር ብቻ›› የሚተርኩ ከመሆናቸው ባለፈ ማዕከል አድርገው የሚዘምሩት በአንድ ነገር ዙርያ ብቻ መሆኑ ዕቅድ አውጥተው፣ቃለ ጉባዔ ይዘው፣ብዙ ተማከረው፣ከዚህ እንዳትወጣ፣ከዚህ እንዳታልፍ ተብለው የተገዘቱ ነው የሚመስለው፡፡ ከዚህ በታች በምሳሌ የተጠቀሱት መዝሙሮቻቸው አጠቃላይ የትኩረት አቅጣጫዎቻቸውን፣ ሃሳባቸውን፣ ኑፋቄአቸውንና
ሥውር ደባቸውን እንዴት ባለ መንገድ እንደሚገልጹ ያሳያል፡፡ እነዚህን በምሳሌ የቀረቡ የመዝሙር ስንኞች በቁሙ ስንመለከታቸው አወንታዊ አገላለጽን ያነገቡ ሲሆኑ ሃሳባቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ የስንኞቹ ይዘት ክርስቶስን አስታክኮ ድንግል ማርያምንና ቅዱሳንን መንቀፍ፣በቅጽበት የመዳንን ትምህርት፣ ክርስቶስን
አማላጃችን ማለት፣መመጻደቅ እና ዕለተ አርብ ስለተፈጸመው ነገር ብቻ ደጋግሞ መዘመር ላይ የሚያውጠነጥኑ ናቸው፡፡
(ምሳሌ-1)
‹‹እንድንበት
ዘንድ ተሰጥቶናል ስሙ
አማራጭ
የሌለው መዳኛ ነው ደሙ
ሞትን
መሞት እንጂ መግደል የተቻለው
ከኢየሱስ
በቀር ሌላ ጌታ ማነው››
ይህ
መዝሙር ከላይ እንደገለጽኩት ቁመናው ላይ ችግር የለውም ሃሳቡ ግን ሌላ ነው! ምክንያቱ ደግሞ ማዕከል ያደረገው ራንዮን፣ ዕለተ አርብን ብቻ
በመሆኑ ነው፡፡ ሥውር ዓላማው ሰዎችን ሁሉ አርብ ላይ ብቻ በማቆም ከዚያ በፊት ስለነበሩት(ስለተከናወኑት)የነገረ ድኅነት ትምህርቶች ማሰብ እንዳይቻል አቅደው የቀመሩት ነው፡፡ (አንኳር ሃሳቡ ‹‹መዳኛ ነው
ደሙ››
የሚለው ነው)፡፡
(ምሳሌ-2)
‹‹ይህ
ተረት አይደለም ይስማው ዓለም
አጥቦኝ
ነጽቻለሁ የበጉ ደም
ለኔስ
እንደ ኢየሱስ ማንም የለም
ለኔስ
እንደጌታ ማንም የለም››
ይህም
ከላይ በተመለከትነው መልኩ እለተ አርብን ብቻ ያማከለ ስንኝ ነው፡፡ (አንኳር ሃሳቡ ‹‹ነጽቻለሁ በበጉ ደም›› የሚለው ነው)፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክርስቶስ የግል አዳኝ ነው የሚለውን ስብከታቸውን ያመላክታል(ነጽቻለሁ፣እኔስ፣ለእኔ) የሚሉት ቃላት ግለኝነት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ያላንተ ጌታ… ፣ያላንተ ለኔ…. ብላ እንደዘመረችይቱ ማለት ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በዚህ ስንኝ ላይ ማስተላለፍ የፈለጉት ዋና ሃሳብ ጸድቄአለሁ፣ድኛለሁ፣ነጽቻለሁ፣በደል
የለብኝም የሚለውን ሃሳብ ነው፡፡ እንዲህ ማለታቸው ክርስቶስ ዕለተ ዓርብ ላይ በተከፈለው ዋጋ ብቻ ሰዎች ሁሉ ድነዋል፣ከዚያ ወዲህ ምንም ኃጢአት የለባቸውም ወደሚል አስተሳሰብ የሚመራ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሰዎች ክርስቶስ ሞልኛል በሚል ስለ በደላቸው ትሩፋት (ጾም፣ጸሎት፣ሥግደት፣ንሰሐ፣ሥጋወ
ደሙን እና ለድኅነት የሚሆን መንፈሳዊ ተግባራትን) እንዳይፈጽሙ የሚገፋፋ ሲሆን ነገረ ድኅነት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን የቅዱሳንን አማላጅነት ሰዎች እንዳይቀበሉ ታስቦ በሥውር የተደረሰ ምንፍቅናዊ አካሄድ ነው፡፡ (ከዚህ በታች እስከ ምሳሌ-6 ድረስ ያሉትም የመዝሙር ስንኞቻቸው ዕለተ አርብን ብቻ ያማከሉ ናቸው)
(ምሳሌ-3)
‹‹የውዴ
ቃል ነው ደጄን ይመታል
እኔ
ብተኛም ልቤ ግን ነቅቷል
ማንም
አይችልም ሊያስቀረኝ ከርሱ
ለኔው
መዳን ነው ደሙ መፍሰሱ››
ይህም
መዝሙር ዕለተ አርብን ብቻ የሚያወሳ ስንኝ ነው፡፡ (አንኳር ሃሳቡ ‹‹ለኔው መዳን ነው ደሙ መፍሰሱ›› የሚለው ነው)፡፡ በተጨማሪም ‹‹ውዴ›› የሚለውን ቃል በብዛት የሚጠቀሙበት ሲሆን ጌታን ያከበሩት ይመስል እንደ ሰፈር ጓደኛቸው ናፍቆቴ፣ ናርዶሴ፣የሳሮን ጽጌሬዳዬ፣መዓዛዬ…………… እያሉ ሲቀማጠሉ የሚያሳይ ነው፡፡ የኔ ናርዶስ…..፣የኔ ……ምናምን ብላ እንዘመረችዪቱ ዓይነት ማለት ነው፡፡
(ምሳሌ-4)
‹‹ያኔ
ያደክልኝን የማልረሳዉ
ለኔ
ብለህ ሞቴን የሞትከዉ
ለሕይወቴ
ቤዛ ባትሆን ኖሮ
ጠፍቼ
ነበረ ያኔ ድሮ››
ይህ
ስንኝ ሙሉ ሃሳቡ ‹‹ስለሞትክልኝ ድኛለሁ›› ነው፡፡
(የአርብ
ትምህርት)
(ምሳሌ-5)
‹‹ሁሌ
ይሄን ሳስብ የሚገርመኝ
በመስቀል
ላይ ለኔ የዋልክልኝ
ያኔ
በሰራኸዉ ታላቅ ሥራ
ሕይወትን
አገኘዉ እንደገና››
ይህም ሙሉ ሃሳቡ ‹‹በመስቀል ላይ የዋልክልኝ›› ነው፡፡
(የአርብ
ትምህርት)
(ምሳሌ-6)
‹‹ሞቴን
የሞተልኝ ለኔ እንደ አንተ የለም
ጭንቄን
የረገጠ ለኔ እንደ አንተ የለም
አርነት
ወጣሁኝ በአፈሰስክልኝ ደም
ነፃነት
ወጣሁኝ በአፈሰስክልኝ ደም
ፍቅር
ነህ ኢየሱስ ለዘላለም››
ይህም
ስንኝ እለተ አርብን ብቻ የሚሰብክ ነው፡፡ ፍሬ ሃሳቡ ‹‹ሞቴን የሞትክልኝ፣በአፈሰስክልኝ ደም›› የሚሉት ናቸው፡፡ መሠረታዊው ጥያቄ ከላይ የተጠቀሱት ተከታታይ የመዝሙር ስንኞች በሙሉ ‹‹ለምን የአርብ ሆኑ›. አይደለም ‹‹ለምን የአርብ ብቻ ሆኑ›› እንጂ፡፡ ‹‹ብቻ›› የምትለዋን ቃል አስምሩባት፡፡ አሁን ማስተዋል የሚኖርብን አንድ ነገር አለ ሰዎቹ ቀድመውናል! ሁላችንንም አርብ ላይ ብቻ እየሰበሰቡን ነው! አርብ ላይ መገኘቱ፣ቀራንዮ ላይ መዋሉ ችግር የለውም ግን ለምን አርብ ላይ ብቻ፣ለምን ቀራንዮ ብቻ የሚል ነገር በውስጣችን ማውጠንጠን አለበት፡፡
(ምሳሌ-7)
‹‹ከቶ
አያሻም ሌላ ቤዛ
አድኖናል
አንዴ ጌታ
በርሱ
ያመነ ሕይወት አለዉ
የእግዚአብሔር
ልጅ እግዚአብሔር ነው››
ይህ
ስንኝ አንጻራዊ ስድብ ያዘለ ነው፡፡ ዋና ሃሳቡ ‹‹ከቶ አያሻም ሌላ ቤዛ›› የሚለው ሲሆን ‹‹ቤዛዊት ዓለም›› የሚለውን የእመቤታችን ስያሜ ከምዕመናን ልብ ለመስደድ፣ለመቃወም በሥውር፣በአይታወቅብንም የሸረቡት ሴራ ነው፡፡አንዴ ድነናል ቤዛችን ኢየሱስ ብቻ ነው ሌላ ቤዛ አናውቅም ማለታቸው ልብ በል/በይ/፡፡ እኛም የጌታችንን ቤዛነት አንቃወምም ነገር ግን ታክኮ የመጣውን የቤዛዊት ዓለም ድንግል ማርያምን መነቀፍ ግን እንቃወማለን!
(ምሳሌ-8)
‹‹ስሙ
መለመኛችን ነው ማመስገኛችን
በረከትም
ነቀፋም ሁሉን መቀበያችን
የበጎች
በር የሆነው ወደ ክብር መፍሰሻ
ከፍጡር
ማንም የለም ቤዛም ሆነ መሸሻ››
ይህም
ስንኝ ከላይ ባየነው መልኩ ‹‹ከፍጡር ማንም የለም ቤዛም ሆነ መሸሻ›› የሚለውን ቃል በመድገም ‹‹ድንግል ማርያም ፍጡር ናት ቤዛ መሆን አትችልም›› ለማለት ፈልገው ነው፡፡ የሚገርመው ከላይ በምሳሌ-4 የተገለጸውና ይህ በምሳሌ-5 የዘመሩት መዝሙር በተለያዩ ጊዜአት የታተሙ ናቸው ግን መልዕክታቸውና ቋንቋቸው ፍጹም አንድ ነው፡፡ ክርስቶስ የዓለም ቤዛ ነው ብለው መዘመራቸው አያጣላንም ድንግል ማርያምን ‹‹ቤዛዊት ዓለም›› ከማለት እንድንታቀብ የሚሸርቡትን ሴራ ግን እንቃወማለን!
(ምሳሌ-9)
‹‹ከአቤል
ደም በተሻለ
ደሙ
ይጮሃል ማር እያለ
የኢየሱስ
ደም ለዘላለም
ያስታርቃል
ይህን ዓለም››
ይህ
ስንኝ ክርስቶስ አማላጅ ነው ብለው በግልጽ የሰበኩበት ነው፡፡ ‹‹ደሙ ይጮሃል ማር እያለ›› የሚለው ቃል አሻሚ የሌለው አማላጅነትን የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ‹‹ያስታርቃል ለዘላለም›› የሚለው ሐረግ ደግሞ አማላጅ ነው የሚለውን ሃሳባቸውን ይበልጥ ያጠናክረዋል፡፡ አንድ በቅርብ የወጣ መዝሙራቸው ላይ ደግሞ ይህንኑ ቃል በተመሳሳይ እንዲህ ብለው ተጠቅመውበታል፡-
(ማርልኝ
የሚል ደሙ ከአቤል የተሻለው
ዛሬም
ለታመኑበት ይቅርታን የሚያሰጠው
ከሳሹን
የሚያሳፍር ዋስትናችን ነው እርሱ
መማጸኛ
ግንባችን መዳን የለም ያለ እርሱ)፡፡
ማንን
ይሆን ማርልኝ የሚለው? ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ይህ እኮ በግልጽ ጌታችንን አማላጅ ነው እያሉ ምንፍቅናቸውን በገሃድ የሚዘሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ ስንኝ ነው፡፡ ስንቶቻችን ይህን መዝሙር አማላጅ ነው እያንል አብረናቸው ዘምረነው ይሆን?
(ምሳሌ-10)
‹‹እኔ
አምናለሁ እንደዳንኩኝ
በክርስቶስ
ስላመንኩኝ
የለብኝም
ሞት ኩነኔ
ምትክ
ሆኗል ጌታ ለእኔ››
ይህ
ስንኝ ‹‹በቅጽበት መዳንን›› የሚሰብክ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በፕሮቴስታንቱ ዓለም በሰፊው የሚሰበከው ይህ በቅጽበት የመዳን ትምህርት ሲሆን ልክ አንድ ሰው በክርስቶስ አምኛለሁ ብሎ በተናገረበት ቅጽበት በቃ አሁን ድነሃል ብለው እንደሚያምኑት ማለት ነው፡፡ እነዚህ የተሃድሶ መናፍቃንም መዝሙራቸውና ስብከታቸው በቅጽበት የመዳን ነገር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህ ነው በስንኙ ላይ ‹‹እኔ አምናለሁ እንደዳንኩኝ በክርስቶስ ስላመንኩኝ›› በማለት ከዚህ በኋላ ኩነኔ የለብኝም፣ድኛለሁ በማለት የሚመጻደቁት፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ትውልዱን ከኃጢአተኝነት ስሜት ነጻ በማውጣት እንደነርሱ ድኛለሁ፣ጸድቄአለሁ፣በደል የለብኝም ወደ ወደሚል አስተሳሰብ እንዲገባና በጎ ምግባራትን እንዳይፈጽም የሚገፋፋ ነው፡፡ አሁንም እንኳ የመዝሙሮቻቸው ተጠቂዎች የሆኑ ብዙዎች ሰዎች በዚህ መንገድ እየተጓዙ ይገኛሉና አምላክ ይመልስልን!፡፡
(ምሳሌ-11)
‹‹እዩልኝ
የምለው ስሙልኝ የምለው
ምንም
የለኝ ሌላ ታሪኬ ኢየሱስ ነዉ
በራሴ
ያቆምኩት ሰራሁት የምለው
የኔ
ድርሻ ማለም መፈፀም የርሱነዉ
በአንደበቴ
ካለዉ ከስሙ ወለላ
መች
ይዋጥልኛል ከኢየሱስ ሌላ››
ይህ
ስንኝ ብዙ ውስብስብ ሃሳቦችን የያዘ ሲሆን ‹‹መች ይዋጥልኛል ከኢየሱስ ሌላ›› የምትለዋ ግን ብዙ እንቆቅልሽ የያዘች ናት፡፡ የማይዋጥላቸው ምን እንደሆነ ስለምናውቅ መልዕክቱ ግልጽ ነው፡፡
(ምሳሌ-12)
‹‹የአለም
ቤዛ ኢየሱስ ነው
የፈወሰኝ
ጌታ ነው
መዳን
በሌላ የለም
እኔ
አምናለሁ ዘላለም››
እዚህ
ጋር ‹‹መዳን በሌላ የለም›› የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ያለ አንድምታ፣በጥሬው፣እንደወረደ ተጠቅመውበታል፡፡ ነገር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንዲህ ዓይነት ፍቺ የሚሹ ቃላት በግርድፍ አይወርዱም፡፡ ይልቁንም በትርጓሜ ወንጌል እና በአንድምታ ተመሳጥረው ምእመናን ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ ይቀርባል እንጂ፡፡ ሆኖም እነዚህ ግለሰቦች የመተርጎምም ሆነ ምስጢራትን የመፍታት አቅሙ ስለሌላቸው የመጻሕፍት ቃል እንደወረደ መጠቀም ልማድ አድርገውታል፡፡
(ምሳሌ-13)
‹‹በማግኘት
በማጣት በደስታ በሀዘናችን
የለንም
ሌላ ቃል አንተው ነህ አዋጃችን
አድኖናል
ፀጋህ ጽድቃችን ሰማይ ነካ
ኢየሱስ
ውሀ ነው ትውልዱን የሚያረካ››
ይህ
‹‹በዘላለም ኪዳን›› ተሰኘው ዝማሬ ሲሆን ኃጢአት ምድሪቱን ከድኗት ሰው ሁሉ ወደ ገዛ መንገዱ በሚሄድበት በዚህ ክፉ ዘመን ‹‹ጽድቃችን ሰማይ ነካ›› በማለት ሲመጻደቁና ትውልዱን ሲያዘናጉ የሚያሳይ ስንኝ ነው፡፡ እውን ሰማይ የነካው ጽድቃችን ነው ወይስ በደላችን? ትውልዱን እንዲህ እያመጻደቁ ከፈጣሪ ከማራቅ የበለጠ ኑፋቄ ከየት ሊመጣ? እግዚኦ…. በሚያስፈልግበት በዚህ ጊዜ ጽድቃችን ሰማይ ከነካ መቼ ነው በደላችንን አውቀን የምንመለሰው? ይህ ስንኝ ጽድቃችን ሰማይ ደርሷልና ንሰሐው ይቅር፣መጸጸቱ ይቅር፣ሥጋወ ደሙን መቀበሉ ይቅር ………….እያለን ነውና እንንቃ!
ማጠቃለያ
ከላይ
የቀረቡት ምሳሌዎች በጌታ ሞት ብቻ ሰዎች እንደሚጸድቁ፣በጸጋው እንደዳኑ፣ከዚህ በኋላ በደል እንደሌለባቸው የሚሰብኩ መዝሙሮች ናቸው፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ነገሮች ሁሉ የተፈጸሙት ደግሞ ዕለተ አርብ ላይ ብቻ መሆኑ የነገረ ድኅነት ትምህርትን አርብ ላይ ብቻ አጥሮ እንደማስቀመጥ ይሆናል፡፡ ወደ እውነታው ስንመለስ ግን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ይህን ዓይነት ትምህርት አስተምራ አታውቅም! አታስተምርምም፡፡ ምክንያቱም ነገረ ድኅነት አርብ ተጀምሮ አርብ የተፈጸመ አይደለምና! ቤተ ክርስቲያን ነገረ ድኅነትን የምታስተምረው ከጌታ ስቅለት ተነሥታ አይደለም፣ከጌታ ጥምቀትም አይደለም፣ከጌታ ልደትም አይደለም፣ጌታ ይወለዳል ከሚለውም የነቢያት ትንቢት ተነሥታም አይደለም! ይልቁንም ገና አዳም ጌታውን ከበደለበት ጊዜ አንሥቶ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ከሚለው አማናዊ ቃል ተነሥታ እንጂ፡፡ ጌታ አዳምን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ አለው፡፡ ይህን መነሻ አድርገው ነቢያት ሁሉ ትንቢት ተናገሩ፤ይህ ትንቢታቸው ለነገረ ድኅነት መነሻ ምክንያት ነው! በዚህ ምክንያት (የመሲኹን መምጣት ስለነገሩን) ነቢያትን እንቀበላለን፡፡ እርሱም በነቢያት ትንቢት ቃሉን ሳያጥፍ ወደዚህ ምድር መጣ የመምጫው መሰላል ደግሞ ድንግል ማርያም ነበረች፡፡ እርሷ ደግሞ ቃል ሥጋ ስለሆነባት የነገረ ድኅነት ጅማሬ ሆነች! ስለዚህ ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ጉልህ ድርሻ አላት፡፡ አምላክ ከድንግል ከተወለደ በኋላ በርጉም ሄሮድስ አማካኝነት ተሰደደ ይህ ስደቱ ለነገረ ድኅነታችን ትርጉም ነበረው! ስለ አዳም ምክንያት ተሰዷልና፡፡ ኋላም በ30 ዘመኑ ተጠመቀ በዚህም ሠይጣን አዳምና ሔዋንን ያስፈረመበት የዕዳ ደብዳቤ ተደመሰሰ ይህም ለነገረ ድኅነታችን ትልቅ ድርሻ ነበው! ጾመ፣ጸለየ፣በቃና ተዓምራትን ፈጸመ፣3ዓመት ከ6ወር ምድርን በኪደተ እግሩ እየባረከ አስተማረ፣ቅዱሳን ሐዋርያትን መረጠ፣ምስጢረ ንሰሐንና ምስጢረ ቁርባንን
አስተማረ(ፈጸመ)ይህ ሁሉ ለነገረ ድኅነታችን ዋጋ ነበረው! ከዚህ ሁሉ በኋላ በዕለ አርብ በክቡር ደሙ መፍሰስ እና በቅዱስ ሥጋው መቆረስ የመርገም ኃጢአታችንን ደመሰሰው ያን ጊዜ የነገረ ድኅነታችን ፍጻሜ ሆነ፡፡ ነገረ ድኅነት ምሉዕ የሚሆነው እነዚህ ሁሉ በአንድ ሲነገሩ፣ሲሰበኩ፣ሲዘመሩ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሽረን፣ከድነን፣ሸፍነን አርብ ላይ በተፈጸመው ነገር ብቻ ድነናል፣ጸድቀናል ስለዚህ ይበቃናል ብሎ መስበክም፣ማስተማርም፣መዘመርም ልክ አይሆንም! የተሃድሶ መናፍቃን እነዚህን የነገረ ድኅነት መንገዶች መሸፈን የፈለጉትበት እና አርብን ብቻ የማወጃቸው ምክንያት ነቢያትን፣ድንግል ማርያምን፣ሐዋርያትን፣ንሰሐንና ቁርባንን ለመቃወም ነው ምክንያቱም እነዚህን አካላት አርብ ላይ ብቻ ማግኘት ስለማንችል፡፡ ሌላው ደግሞ አርብን እንኳ ሲዘምሩ፣ሞተልን
እያሉ
ሲያወሩ መስቀሉ ሥር ስለዋሉት(ስለነበሩት) ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ትንፍሽ ብለው አያውቁም፡፡ ለነገሩ
‹‹አስኳሉ
ኢየሱስ ነው ቅዱሳን ቅርፊት ናቸው! አስኳሉን እንጂ ቅርፊቱን አንሰብክም!›› የሚለው ቃል መመሪያቸው ስለሆነ በነርሱ መፍረድ አንችልም! በተጨማሪም ጌታ ስለሞተልን ድነናል፣ጸድቀናል፣ከዚህ በኋላ ኃጢአት የለብንም የሚለው ስብከታቸው ፍጹም ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ከሰው ልጅ የተወገደው ከአዳም ጀምሮ በሰው ልጅ ሁሉ ላይ የነገሠው የውርስ ኃጢአት እንጂ ከጌታ ሞት በኋላ የበደለ ሁሉ ጻድቅ ነው የሚል አስተምህሮ የለም! እንዲህማ ከሆነ ባለቤቱ ራሱ ጹሙ፣ጸልዩ፣ንሰሐ
ግቡ፣ቁረቡ
ለምን አለ? ጌታ አንዴ ሞቶልናል እና ጸድቀናል፣ድነናል ከተባለ ሰማዕታት ለምን መከራን ተቀበሉ? ቅዱሳን በዱር በገደሉ ለምን ተጋደሉ? ሁሉም ጻድቅ ከሆነ ጌታስ ዳግም ለፍርድ መምጣት ምን ያስፈልገዋል?፡፡ እውነት ነው በጌታ ሞት ገነት ተከፍቷል፡፡ እንደቀድሞው(በዘመነ ብሉይ)እንደነበረው ሰው መልካም እንኳ ቢሠራ ገነትን መግባት ተከልክሎ ነበር ይህም በውርስ ኃጢአት ምክንያት ነው፡፡ አሁን ግን ሰው መልካም እስከሠራ፣እስከ ጾመ፣እስከ ጸለየ፣ንሰሐ እስገባና ምስጢረ ቁርባንን እስከፈጸመ ድረስ ገነት መግባትን የሚከለክለው የለም! ምክንያቱም ጌታችን በሞቱ መርገምን ከእኛ ስላጠፋል፡፡ ነገር ግን! ያለ ምንም በጎ ምግባርና ትሩፋት ጌታ ሞቶልኛልና ድኛለሁ፣ጸድቄአለሁ ብሎ መኮፈስ የትም አያስገባም! አነርሱም ስለነዚህ ምክንያቶች የተሃድሶ መናፍቃን ተባሉ! እኛም ስለነዚህ ምክንያቶች የተሃድሶ መናፍቃንን መዝሙራት አንሰማም!
ከላይ በ13-ምሳሌዎች ብቻ የቀረበው የመዝሙር ስንኝ ከለቀቋቸው መዝሙራት አንጻር ከመቶው አንድ እጁን እንኳ አያህሉም፡፡ መልዕክቱ እንዳይበዛ እንጂ አንድ መጽሐፍ የሚወጣው ነበር፡፡ ሆኖም መዝሙሮቻቸው ይብዙ እንጂ የትኩረታቸው አቅጣጫ ግን ከላይ በገለጽኩት መልኩ ፍጹም አንድ ነው፡፡
ክፍል
ሑለት “የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ! -‹‹በነገረ ማርያም ማርያም›› በሚል ርዕስ ይቀጥላል፡፡
(ይቆየን)
(ቢኒ
ዘልደታ)
No comments:
Post a Comment