Saturday, May 21, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ

የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
በክፍል አስራ ዘጠኝ ጽሁፋችን "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን! በሚል ርዕስ ጀምረን በይቀጥላል እንዳቆየነው ይታወሳል፡፡ ክፉውን ነገር እንድንጸየፍ ከበጎ ነገር ጋር እንድንተባበር ከቅዱሳት መጻሕፍት በተማርነው መሠረት ‹‹ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ››የተባለች እህታችን በface book ያስተላለፈችው ትምህርት የእኛም መልእክት ስለሆነ ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡

"ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ"
     ‹‹አምስቱ_አኃት_አብያተ ክርስቲያናት፤ አሁን ስድስት ሆነዋል፥የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣የግብፅ፣የሕንድ፣የሶርያ እና የአርመን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት በእምነት እና በሥርዓት አንድ መሆናቸው የታወቀ የተረዳ ነገር ነው።እንዲህም ሲባል በሌሎች ዘንድ የሌለ፥ እኛ ብቻ ያለን ብዙ ነገር መኖሩን ከማስተዋል ጋር መሆን አለበት።ምክንያቱም እግዚአብሔር፡-ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሰጣት ጸጋ ብዙ ነው ።የቅዱስ ያሬድ ዜማ የተሰጠው ለእኛ ነው፥ለሌሎቹ ስላልተሰጠ ወይም በእነርሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሌለ እንጣለው? በአጠቃላይ ሥርዓተ ማኅሌቱና ሰዓታቱ በእነርሱ ዘንድ ስለሌለ የእኛን እንተወው? ታቦትም የተሰጠው ለእኛ ብቻ ነው።ከእኛ የሚጠበቀው እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ መጽናት፥የተሰጠንን አደራ መጠበቅ ነው።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-ጢሞቴዎስን ፡-“ጢሞቴዎስ ሆይ! በውሸት እውቀት ከተባለ ለዓለም ከሚመች ከከንቱ መለፍለፍና መከራከር እየራቅህ የተሰጠህን አደራ ጠብቅ፤ ይህ እውቀት አለን ብለው፥አንዳንዶች ስለ እምነት ስተዋልና።” ያለው ለዚህ ነው።፩ኛ፡ጢሞ፡፮፥፳።ዳግመኛም፡-“መልካሙን አደራ በእኛ በሚኖረው በመንፈስ ቅዱስ ጠብቅ፤” ብሎታል።፪ኛ፡ጢሞ፡፩፥ ፲፬።እግዚአብሔር የሚጠይቀን በሰጠን እንጂ ባልሰጠን አይደለም።አንድ የተሰጠው፥ ሁለት የተሰጠው፥አምስት የተሰጠው አለ።ማቴ፡፳፭፥፲፭።
     ኢትዮጵያ፡-ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት፥ከሕገ ኦሪት ደግሞ ወደ ሕገ ወንጌል የተሸጋገረች ሀገር ናት።በመሆኑም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላታል።“እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀበልን፥ በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና፤ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ፤” ይላል።ዮሐ፡፩፥፲፮።ስለሆነም ንባቡን ይዛ ኑራ ከትርጓሜው የደረሰች ቤተ ክርስቲያን በሁሉ ባዕለ ጸጋ ናት ።የሐዋ፡፰፥፳፮።ከዚህም የተነሣ ከጥንት ጀምሮ የተከፈተባትን የመናፍቃንን እና የአሕዛብን ውጊያ ተቋቁማ ጸንታ ኖራለች ትኖራለችም።ጠላቶቿን ስትከላከል የኖረችው ደግሞ በትምህርተ ሃይማኖቷ እና በሥርዓቷ፥ በታሪኳ እና በትውፊቷ ነው።የራሷ የሆነ ጸጋ ስላላት፥ተመሳስለው መንጋዋን ለመቀላቀል ለሚፈልጉ ተኵላት አትመችም፥ ለዚህ ነው አገኝ አጣውን እየወረወሩ፥ዙሪያውን የሚንጫጩት።መናፍቃኑ ወደ ሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ተመሳስለው ለመግባት ብዙ አልተቸገሩም።ለምሳሌ፡-የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ብንመለከት፥ መናፍቃኑ በተሀድሶ ስም ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋት ስለ ነበር፥ሕዝቡ፡-በኦርቶዶክስና በፕሮቴስታንት መካከል ያለው የሃይማኖትና የሥርዓት ልዩነት ጠፍቶባቸው፥የጸኑትና ያልጸኑት ለሁለት ተከፍለው ነበር።በመጨረሻም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ፥ተሀድሶዎቹና ኦርቶዶክሶች፥የአንዲቷን ቤተ ክርስቲያን፡-ሕንፃና ንብረት ለሁለት ተካፍለዋል።የተቀሩትም አኃት አብያተ ክርስቲያናት በተለያየ ጊዜ በተሀድሶ እንቅስቃሴ በጣም ተጐድተዋል። ለምሳሌ፡-በአስመራ ቅዳሴ የአረጋውያን ነው ተብሎ ወጣቶች አያስቀድሱም ነበር። ቅዳሴው ካለፈ በኋላ ግን ተሰብስበው የፕሮቴስታንቱን መዝሙር ያቀልጡት ነበር፥በመጨረሻም ጌታን የተቀበላችሁ እጅ አውጡ ይባል ነበር። በየክፍለ ሀገሩ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት፡-የመምህር ጥያቄ ሲያነሡ፥ቄስ እገሌ፣ዲያቆን እገሌ እየተባሉ የሚላኩላቸው፥የሙሉ ወንጌል ፓስተሮች ነበሩ። እነዚህ ነገረ ኦርጋን ያንገበገባቸው ሰዎች፡- ለነገረ ክርስቶስ፥ለነገረ ማር ያም እና ለነገረ ቅዱሳን ግድ የላቸውም።ኦርጋንን የምትጠቀመው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብትሆን ኖሮ፥ ዓይናቸውን አፍጥጠው፡-“መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለም፤”ብለው ከመከራከር ወደ ኋላ አይሉም ነበር።ለመሆኑ ተሀድሶዎቹ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን እንደ አብነት ለመጥቀስ ሞራሉን ከየት አመጡት፥አለማፈራቸው ይገርመኛል።ምክንያቱም፡-የኦርቶዶክስን መለያ ለብሰው ለፕሮቴስታንት የሚጫወቱ ናቸውና ነው።ከጥንት ጀምሮ “ኦርጋን፥ኦርጋን” ያሉ ሰዎች፡-አሁን ያሉት የፕሮቴስታን አዳራሽ እንደሆነ ባለፈው ጽሑፌ ላይ ጠቅሻለሁ።“የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ፤” እንደተባለው ሆኖ ነው እንጂ፥እነርሱም ያውቁታል።ልብ ካላቸው ዋናውን ክህደታቸውንም በየድረ ገጹ በብዕር ስም ከመጻፍ በትክክለኛው ስምና አድራሻ ይጻፉት።የፕሮቴስታንቱን መቀበላቸውን በግልጽ ያውጁ።ታቦታቸውን፡-ጊታርን ከሚያደክሙት እነርሱ ጓዛቸውን ጠቅልለው እርሱ ወደ አለበት ይሂዱ።ከእኛ የሚጠበቀው የአባቶቻችንን እምነት እና ሥርዓት ሳይከለስ እና ሳይበረዝ መረከብ ነው።ዛሬ እንደ አዲስ የምንጀምረው ምንም ነገር የለም።የተቀደሱት አባቶቻችን በረከታቸው ይደርብንና ሁሉን ነገር አስተካክለውልን ሄደዋል፥ያንን መከተል ነው። የቀደሙት አባቶቻችን እና እኛ፥እንዲሁም እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚነሡ አባቶታችን አንድ አይነት እምነት እና ሥርዓት እንጂ የተዘበራረቀ ነገር አይኖረንም።የተቀበልነው ሥርዓተ መላእክትን ስለሆነ፥ተጠርተን ወደ ሰማይ ስንሄድም ከቅዱሳን መላእክት ጋር አንድ ሆነን፥በአንድ አይነት ሥርዓት አናመሰግናለን።“በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ይሆናሉ፤”የሚለው ይኸንን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው።ማቴ፡፳፪፥፴።ስለ ነገረ ኦርጋን፡-የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንደ አብነት ለመጥቀስ የሚሞክሩ አሉ።አባቶቻችን እኮ ከቅዱሳን ነገሥታት ከአብርሃ ወአጽብሐ ጀምሮ፡-ለአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት ጳጳሳትን እንጂ ኦርጋንን አላስመጡም። ግብፃውያን ጳጳሳትም፡-ቅዱሳት መጻሕፍትን እና መስቀላቸውን ይዘው መጡ እንጂ ኦርጋን ተሸክመው አልመጡም።አንዳንዶች ደግሞ፡-“ጥንት ስላልነበረ ነው፥አሁን ግን ዘመኑ ኦርጋንን ስላመጣልን ከዘመኑ ጋር መዘመን አለብን፤” ይላሉ እንጂ ምክንያታቸው አሳማኝ አይደለም። ምክንያቱም፡-እግዚአብሔር፡-ዘመን በሚያመጣው ኦርጋን መመስገን ፈቃዱ ቢሆን ኖሮ አንዱን ነቢይ ትንቢት ማናገር ይችል ነበር።
      ቴክኖሎጂን በተመለከተ፡-ማኅበር ቅዱሳን የዛሬ ፳ ዓመት በ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ባሳተመው፡-“ቤተ ክርስቲያንህን እወቅ ፤” በሚለው መጽሐፍ መግቢያ ላይ፡-“የትውልድ ዕድገት አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ እስካልሆነ ድረስ ትውፊት(Tradition) ከቴክኖሎጂ ጋር አይጋጭም። ቴክኖሎጂ ባስገኘው ቴፕ ቅዳሴያችንን በድምፅ ቀርፀን ለተተኪው ትውልድ እናስቀምጥበታለን እንጂ፡-“የቴክኖሎጂ ውጤት ነው፥የሰው ኃይልና ጊዜ ይቆጥባል፤” ብለን በካህናቱ ምትክ የቅዳሴ ካሴት ቴፕ ውስጥ አስገብተን በሰንበት ጠዋት አናስቀድስም።ትክኖሎጂን ተጠቅመን በቀላሉ ጧፍ ለመሥራትና ለአብያተ ክርስቲያናትም በቶሎ ለማዳረስ የሚያስችለንን መንገድ እንቀይሳለን እንጂ ጧፍን በእጅ ባትሪ እንቀይርም።” ይላል።››
ለእህታችን! ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ! ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡
በቀጣይ ጽሁፍ እስከምንገናኝ ደህና ቆዩ፡፡


No comments:

Post a Comment