Sunday, May 1, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አስራ ዘጠኝ

   “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡ማቴ.716 ክፍል አስራ ዘጠኝ
 "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!
ከክፍል አስራ ስምንት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ከክፍል አንድ እስከ ዘጠኝ ባስነበብነው ጽሁፍ፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ፈተና የሆኑትን እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ››ብለው የሚጠሩትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን የጥፋት ተልእኮ ለማሳየት ሞክረናል፡፡የእኩይ ሥራቸው መራራ ፍሬዎች ከሆኑት መጻሕፍቶቻቸውም መካከል ‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» የተባለው መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ቀሎ የተገኘ /ከፍሬው ገለባ/ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስን ምስክር አድርገን አሳይተናል፡፡እንዲሁም

  1. በክፍል አስር፦ "ቢኒ ዘልደታ" የተባሉት ወንድማችን ያዘጋጁትን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ትምህርት አዘል በሆነ መንገድ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያስነበቡንን ጽሁፍ፤
  2. ከክፍል አስራ አንድ እስከ አስራ አራት፦  ስለዚሁ የኢ///ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ፈተና ስለሆነው የውስጥና የውጪ መናፍቃን /ተሐድሶ/ ጉዳይ ማህበረ ቅዱሳን በድረ ገጹ (www.eotcmk.org) በተከታታይ ያቀረበውን ዘገባ፤
  3. በክፍል አስራ አምስት፦ "እያወቁ ማለቅ" በሚል ርዕስ ከላይ የተጠቀሱት እነዚህ ችግሮች ከፍተኛ ደረጃ ለመድረሳቸው የእኛ /የተዋሕዶዎቹ/ ቸልተኝነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ፤
  4. በክፍል አስራ ስድስት እስከ አስራ ስምንት ፦በመዝሙር በኩል ያለውን አጠቃላይ ችግርና መፍትሄውንም ጭምር   "ቢኒ ዘልደታ" የተባሉት ወንድማችን በፌስ ቡክ ገጻቸው ያስነበቡንን አስተማሪ ጽሁፍ፤

አንብባችሁ ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እንናምናለን፡፡
 የተከበራችሁ የቅድስቲቱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች!
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››
በሚል ርዕስ ጥቂት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!
     "ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ" እንዲሉ ከሃያ ሁለቱ ስነ ፍጥረት መካከል ቅዱሳን መላእክትና የስው ልጆች የተፈጠሩበት ዋነኛው ምክንያት ልዑል እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ለዘላለምም ሕያዋን ሆነው እንዲኖሩ ነው፡፡በስነ ፍጥረት የመጀመሪያው ቀን ከተፈጠሩት ከመቶው ነገደ መላእክት መካከል በዚያን ጊዜ አለቃቸው የነበረው ሳጥናኤል ፈጣሪያቸሁ እኔ ነኝ ብሎ በድፍረት ተናገረ፡፡በዚያን ቅጽበት አንዱ ነገድ  አዎ! ፈጣሪያችን አንተ ነህ ብለው ሲቀበሉት ቀሪዎቹ ዘጠና ዘጠኙ ነገድ ለተወሰነ ጊዜ ቢታወኩም በመላእክት አለቃ በቅዱስ ገብርኤል አረጋጊነት የፈጠራቸው አምላክ በብርሃን እስኪገለጥላቸው ድረስ ጸንተው ተገኝተዋል፡፡በመሆኑም ልዑል እግዚአብሔርን ያለ ማቋረጥ /ለዘለዓለም/ ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ! እያሉ የሚያመሰግኑበት ጸጋ የተላበሱ ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ ሳጥናኤል ከነጭፍሮቹ በማስካድና በማሳሳት ሥራቸው እንደጸኑ ናቸው፡፡ የሰው ልጅንም ሁኔታ ስንመለከት ይህ ቀረሽ የማትባል ገነትን ያህል ቦታ እንዲያጣና ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያህል ጌታ እንዲለይ /በባሕርይው እንዲጎሰቁል/ ያደረገው ይኸው ጠላት ሳጥናኤል የጠነሰሰው ክፉ ምክር ነው፡፡
     ስለማይነገረው ስጦታው ስሙ ይመስገንና፤ይህንን የጠላታችንን ክፉ ምክር ለማፍረስ ሰውን ወዳጅ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር እራሱ ሰው ሆኖ የኃጢአታችንን ዕዳ ባይከፍልልን ኖሮ ለዘላለም በገሃነመ እሳት በሳጥናኤል እጅ ስንቀጠቀጥና ስንቃጠል በኖርን ነበር! አሁንም በፍጥረታት ሁሉ አንደበት ስሙ ይክበር ከፍ ከፍም ይበልና! ጌታችን አምላካችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ጠላታችንን ሳጥናኤልን (ሰይጣንን፣ዲያብሎስን) በመስቀል ቀጥቅጦ ድል ካደረገው በኋላ፤ እኛም ክርስቲያኖች ፈጣሪያችን በሰጠን መሳሪያ፤ ማለትም በሃይማኖትና በመስቀሉ ኃይል ተጋድሏችንን እንድንፈጽም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሰጥቶናል፡፡ይህ ስጦታው ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን አምነው፤ሰይጣንን ክደው የሚኖሩት ግን በጣም ጥቂቶች ናቸው፡ስለሆነም እግዚአብሔርን ለማወቅ ህጉንም ለመጠበቅ ያልወደዱት ሁሉ በክህደትና በጥርጥር ማዕበል እየዋኙ፤ሌሎችንም ሲያስክዱና ሲያጠራጥሩ ይኖራሉ፡፡
     እንግዲህ የሐሰተኞችን የእውነተኞች ልዩነት ከዚያን ጊዜ /ከዓለመ መላእክት/ ጀምሮ እስከ ዛሬ አለ፤ ወደፊትም እስከ ምጽአት ድረስ ይኖራል፡፡የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች በሆኑትና የሳጥናኤል የግብር ልጆች በሆኑ ሰዎችም መካከልም ፈጽሞ ሊታረቅ የማይችል፤ የብርሃንና የጨለማ ያህል የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ጠላት ዲያቢሎስም በዘመነ ብሉይ የአዳምን ልጆች በግድ ሲገዛቸው የኖረ ሲሆን፤ በዘመነ አዲስ ደግሞ ሰውን የሚገዛው እንደየ ሰው ዝንባሌ የተለያየ የማስመሰያ /የማታለያ/ ዘዴ በመጠቀም ነው፡፡ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስኪመስል ድረስ እራሱን ይለውጣል እንደተባለው፡፡
     የክርስትና መገለጫዎች ከሆኑት ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው፤ ማንኛውም ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በልቡ ያመነውን እውነተኛ እምነት በአማንያንም ሆነ በኢአማንያን ፊት ሳያፍርና ሳይፈራ መመሰከር እንዳለበት ጌታችን እራሱ  ‹‹ሰው በልቡ አምኖ በአፉ መስክሮ ይድናል፡፡›› ሲል ተናገሯል፡፡በፍጻሜ ዘመን የተነሱት ሐሰተኞች መምህራን "የወንጌል" ሳይሆን "የወንጀል" ትምህርት ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡
     ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔርም "ሕጌንና ትእዛዜን ብትጠብቁ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤በመጨረሻም የዘላለምን ሕይወት ትወርሳላችሁ፤ ህጌን ባትጠብቁ ሰይፍ ይበላቸኋል፡፡" አለ አንጂ ማንንም ፍጡር አሰገድዶ እንዲያመልከው አላደረግም፡፡የጸጋው ግምጃ ቤት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከፈጣሪዋ በተቀበለችው ትእዛዝ መሰረት እምነቷንና ሥርዓቷን አምነው ለተቀበሉት ብቻ አስፈላጊውን አገልግሎት ትሰጣለች፡፡
     አንዳንዶቹ ዘባቾች ግን የኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን እየተቃወሙ፤ነገር ግን የዋሁን ምዕመን በለመደውና በሚወደው ነገር መስለው ለማሳሰትና ወደ ራሳቸው የጥፋት ዓላማ ለማስገባት ሲሉ የማያመኑበትን ሥርዓት ለይሰሙላ ብቻ ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሆኖም ያዋጣናል ብለው የሄዱበት የማሳሳቻ መንገድ ሁሉ እንደፈለጉት ስላልሆነላቸውና ተስፋ ስለቆረጡ፤"እንግዲህ ምን ታመጣላችሁ"? ያሉ ይመስላል፤አንድ እርምጃ ወደፊት ተራምደው እምነታችን ይህ ነው ብለው የእምነት መገለጫቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ይሁን እንጂ እንደማንኛውም የእምነት ድርጅት የራሳቸውን ቢሮና የአምልኮ ስፍራ ለይተው የወደዱትን ማድረግ ሲችሉ፤ዋናው አላማቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው እንክርዳድ ትምህርታቸውን በየዋሃኑ ምዕመናን ላይ መዝራት ስለሆነ ከላይ እስከ ታች ባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአገልግሎት ክፍሎች ውስጥ ተሰግስገው ይገኛሉ፡፡እነዚህም ክፍሎች እራሳቸውን "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ" ብለው የሰየሙ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች ናቸው፡፡ 
     ሰለ እኩይ ሥራቸው ለማስታወስ ያህል ይህንን ካልን፤ከዚህ በመቀጠል"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ" እና "አባ ሰላማ" በተባሉት ድረ-ገጾቻቸው ላይ "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" ብለው ያወጡትን ባለ 43 ገጽ መገለጫቸውን፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ተገቢውን ምላሽ እስከሚሰጡ ድረስ፤ ለይሰሙም ቢሆን እናምንበታለን ብለው የሚፎክሩበትን 66ቱን መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ምስክር በማድረግ የእምነት መገለጫቸው ይዘቱ ምን እንደሚመስል ከብዙው በጥቂቱ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
ለሁላችንም ጥበቡንና ማስተዋሉን ይስጠን፡፡
ለዛሬው እዚህ ላይ ይቆየን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንቀጥላለን፡፡






No comments:

Post a Comment