Wednesday, September 14, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሰባት

 ከክፍል ሃያ ስድስት የቀጠለ

የተከበራችሁ  የዚች ጦማር ታዳሚዎች ምእመናን!

     ሁላችንም እንደምናውቀው ስለዚህ ስለ መጨረሻው ዘመን አስከፊነት አስቀድሞ በነቢያት፣ከዚያም በጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው፣እንዲሁም በጌታችን ደቀ መዛሙርትና ከነሱም በመቀጠል በየዘመኑ በተነሱ ቅዱሳን አባቶችና በሊቃውንት በሰፊው ሲነገር ኖርዋል፤አሁንም እየተናገሩ ነው፡፡በተለይም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁ.1-ፍጻሜ የተነገሩት የዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶች አሁን በእኛ እድሜ በስፋት እየተፈጸሙ እንመለከታለን፡፡የቀደሙት ቅዱሳን ከዚህ ዘመን እንዳይደርሱ፤ከእህል ውሃውም እንዳይቀምሱ፤ አጥብቀው በመጸለያቸው ምኞታቸው ተፈጸሞላቸው በሰላም ከዚህ ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ስለሆነም እኛም ክርስቲያኖች የዚህ የክፉ ትንቢት መፈጸሚያዎች እንዳንሆን ህገ እግዚአብሔርን ማወቅና ከክፉ ነገር መጠበቅ ብሎም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

ክቡራን አንባብያን!

     ስለ ዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶችና ጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ስለሚሆነው ንውጽውጽታ "አክሊሉ ደበላ" የተባሉ ወንድማችን በማህበራዊ ደረ-ገጽ በግጥም ያስተላለፉትን እጅግ በጣም አስተማሪ ጸሁፍ ለሁላችንም ጠቃሚ ስለሆነ እንድተመለከቱ እንጋብዛለን፡፡

መልካም ንባብ!

Aklilu Debela

***ና ልበል: አትምጣ??***

ተልከው ነፋሳት - ምድርን ሲያናውጡ
የክፋት ነቢያት - ካሉበት ሲወጡ
መንግስት መንግስት ላይ - ህዝብም በህዝብ ላይ
ድንጋይም በድንጋይ - ተደርምሶ ሲታይ
የደስታ ካብ ሁሉ - ሲናድ ከሰዎች ልብ
የጸጥታ ስፍራ - በክፋት ሲከበብ
ያላሰብኩት ሆኖ - ያልኩት ሲቀርብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መቃረቡ ሲሆን - የትንቢት ፍጻሜ
ሰማይና ምድር - የሚያልፉበት እድሜ
የጸሃይዋ መጥለቅ
የብርሃኗ መራቅ
ይሆናል ያልተባለው - መሆኑ ሲታወቅ
ሰማይ ሲጠቀለል - ከዋክብት ሲረግፉ
የዓለም ኩሬዎች ሁሉ - ሲዘጉ ሲነጥፉ
“ዓለም!” “ዓለም!” ያሉት - ሲሆኑ መና ዎና
የምናያት ምድር - እንዳልሆነች ሆና
ባዶነት ሲወረኝ - ተስፋ ሲጠፋብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
የቁጣ ነፋሳት - ከአዜብ ሲለቀቁ
መድረሻ ጠፍቶአቸው - የቆሙት ሲወድቁ
ዙሪያው ሲጨላልም - ሲዘጋጋ መንገድ
ከምስራቅ ሲሰማ - አስፈሪው ነጎድጓድ
ሲያይሉ መባርቅት - መለከት ሲነፋ
የነበረው ሲተን - የሞለው ሲጠፋ
ሰላሜ ሲታወክ - ጭንቁ ሲመጣብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ኀሳዊያን ደቂቃን - ኀሳዊ መምህር
ኀሳዊ ክርስቶስ - የሀሰት ደቀመዝሙር
ሲበዛ በዓለም - ሲበረክት በደጅ
በተዓምር ጨረቃን - የጨበጠው በእጅ
በቅዱሱ ስፍራ - ሲፈስ የንጹህ ደም
ሽሽት ክረምት ሲሆን - የኃላው ሲቀድም
በሰንበት መሰደድ - ሲሆን መጨረሻ
በሀዘን ሊከበብ - የህይወት መድረሻ
ያ ግርማህ ሊገለጥ - ያኔ ልትፈርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መዝገቡ ሲገለጥ ህይወቴ ሊነበብ
አንደበት ሲዘጋ አጽም ሲሰበሰብ
ዋይታ ዋጋ ሲያጣ ከንቱ ሲሆን ጩኸት
በጎቹ ከተድላ ፍየሎች ከእሳት
በሚጓዙበት ‘ ለት
በዚያ አስፈሪ ሰዓት
ኃጢአን በእንባ ብዛት - እጅግ ይጠቁራሉ
ጻድቃን ያለቅሳሉ - ክፉዎች ያነባሉ
ቅዱሳን መላእክት - ለሰው ልጆች ሲሉ
በዚያ ጭንቅ ሰዓት - ሁሉም ያለቅሳሉ፡፡
የሰማእታትን ደም - በከንቱ ያፈሰሱ
ጻድቃንን የገፉ - ንጹሃንን የከሰሱ
ስለነ አቤል ደም - መጥተህ ልትበቀል
ስለ ደሃ አደጎች - ሊሰማ የህይወት ቃል
ጉጉትና ፍርሃት - መንታ ሲሆንብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ይህንን እያወቅሁ - ዛሬን በማበሌ
ሳልሰንቅ ለጉዞ - ለሚሻለኝ ክፍሌ
“ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” - በሚል አንደበቴ
ሙሉ መስሎ ሲጓዝ - ባዶው እኔነቴ
“አይቴ ነበርከ?” ና “ምንተ ገበርከ” ስባል
ርዓዱን የሚያስተወኝ - ሳይኖረኝ አንድ ቃል
ሲታወሰኝ ዛሬ - ሲንቀጠቀጥ ጥርሴ - ልቤ እንዲርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
(አክሊሉ ደበላ በሰንበተ ክርስቲያን በእለተ ደብረ ዘይት 2007 ዓ.ም የተጫረ)


ለወንድማችን ለአክሊሉ ደበላ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

No comments:

Post a Comment