ከክፍል ሃያ ሰባት የቀጠለ
የተከበራችሁ የዚች ጦማር ተከታታዮች ምእመናን! እንደምን
ሰነበታችሁ? ለዚች ዕለትና ለዚች ሰዓት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ከዓለም ዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ የተመሰገነ ይሁን፡፡በአገልግሎት
መብዛት ምክንያት ወቅታዊ መልእክቶችን ከማስተላለፍ ስለዘገየን አስቀድመን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.፲፪ ቁጥር ፱ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን
አንድ እስከሆነ ድረስ፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች
የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረው፤በዚች ክፍል የምናስነብባችሁ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ “ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው?”በሚል ርዕስ ያስተላለፉትን
እጅግ ተቃሚ ትምህርት በድረ ገጻቸው በጊዜው ማንበብ ላልቻላችሁ ምእመናን አቅርበንላችኋል፡፡ሙሉው መልእክት የዲያቆን ብርሃኑ አድማስ
ነው፤ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማድረግ በስተቀር የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡
መልካም ንባብ!
“ሠለስቱ ደቂቅን
ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው?” – ክፍል አንድ
በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ
ታኅሣሥ ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በአንድ ወቅት በተሐድሶ መናፍቃን በተሰራጨ አንድ የቪዲዮ ቁራጭ ላይ በሦስቱ ድርሳናት ማለትም በድርሳነ ገብርኤል ላይ
ገብርኤል፤ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት አዳናቸው ተብሎ ስለ ተገለጸ
‹‹ትክክለኛው ትምህርት የትኛው ነው? ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክስ ማን ነው?›› የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲነሣ ሰምተናል፡፡ከቅርብ
ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ በዋናነት የምንመለከተውን የመሰሉ ጥያቄዎችን እያነሡ ገድላትን፤ድርሳናትንና ሌሎች አዋልድ መጻሕፍትንም
የሚነቅፉና የሚያስነቅፉ ሰዎች ቍጥራቸው በርከት እያለ መጥቷል፡፡ከዚህም የተነሣ በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ጽሑፎችና የምስል ወድምፅ
ስብከቶች ይቀርባሉ፡፡ ይህም ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ወይም ምሥጢራት ግንዛቤአችን አነስተኛ የኾነብንን ሰዎች ሊረብሸን ይችላል፡፡
እኛም ነገሩን ከመሠረቱ ለመረዳት እንዲያመቸን ቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የሚነሡ ጥያቄዎችን ብቻ ሳይኾን የማንጠየቃቸውንም ጭምር በአግባቡ
ተረድተን እንድንጠቀም የሚረዳ መንገድ ለመጠቆም ይህንን ጽሑፍ አዘጋጅተናል፡፡
አስቀድመንም ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዴት ልንረዳ እንደምንችል ለማመላከት እንሞክራለን፤በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብ ሦስት
ዓይነት መልእክቶችን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው ታሪካዊ መልእክት ሲኾን ይህም ማለት ድርጊትን ሲዘግብልን ወይም የተጻፈው ደረቅ
ትንቢትና ቀጥተኛ ትምህርት ማን መቼ ለማን በምን ምክንያት እንደ ተናገረው ስናጠና የምናገኘው ታሪካዊና ተጨባጭ መልእክት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ምግባራዊ መልእክት ሊባል የሚችለውና ምን ማድረግ እንዳለብን ወይም እንደሌለብን፤ እንዴትና መቼ ትእዛዛትን መፈጸም
እንደሚገባን የሚያስተምረን ቀጥታ ልንተገብረው የሚገባንን ተግባር የሚያሳውቀን መልእክት ነው፡፡ሦስተኛውና የመጨረሻው ደግሞ ምሥጢራዊ
ወይም መንፈሳዊ መልእክት ነው፡፡ የዚህም ዋና ዓላማው ምሥጢሩን ከተረዳን በኋላ በገቢር (በተግባር) እንድንገልጸው ቢኾንም ዋናውን
መልእክት የምናገኘውም ምሳሌው ወይም ትንቢቱ ወይም ታሪኩ በውስጡ አምቆ የያዘው መለኮታዊ መልእክትን ስናውቅ ነው፡፡
ይህ ምሥጢራዊ ወይም መንፈሳዊ መልእክት ግን በግምት ወይም በመላምት የሚሰጥ ሳይኾን ከጥንት ከጌታችንና ከሐዋርያት ጀምሮ
እነዚህን መጻሕፍት ያስተማሩ ቅዱሳን አባቶች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ከተናገሩትና ካስተማሩት ትምህርት የሚገኝ ነው፡፡ለምሳሌ ጌታችን
ሉቃስንና ቀልዮጳን ወደ ኤማሁስ ከሚሔዱበት መንገድ የመለሳቸው እነርሱ እንደ ተናገሩት ‹‹ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተረጐመ›› ሲነግራቸውና
በምሥጢራቱም ‹‹ልቡናቸውን ካቃጠለው›› በኋላ ነው /ሉቃ.፳፬፥፲፫-፴፭/፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም መልእክቶቻቸውንና ወንጌሎቻቸውን
ብናይ በኦሪት የምናውቃቸውን ታሪኮችና ትእዛዛት መንፈሳዊና ምሥጢራዊ መልእክቶቻቸውን በሰፊው አስቀምጠውልናል፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ
እስራኤል ከግብጽ ሲወጡና ባሕረ ኤርትራን ሲሻገሩ የገጠማቸውን ነገር በሙሉ የጥምቀትና የመንፈሳዊ ወይም የጸጋ እግዚአብሔር ምግብና
እንደ ኾነ ተርጕሞልናል /፩ኛቆሮ.፲፥፩-፭/፡፡ አጋርንና ሣራንም የኦሪትና የወንጌል ምሳሌዎች አድርጎ ልጆቻቸው እስማኤልና ይስሐቅ
ለምን ዓይነት መንፈሳዊና ታላቅ ምሥጢራዊ መልእክት ምሳሌዎች እንደ ኾኑ ነግሮናል /ገላ.፬፥፳፪ እስከ ፍጻሜው/፡፡የኋላ ሊቃውንትም
በዚሁ በእነርሱ መንገድ ሔደው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተዝቆ የማያልቅ መለኮታዊ መልእክት ወይም ምሥጢር በስፋት አስተምረውናል፡፡አባታችን
ያዕቆብ በፍኖተ ሎዛ ሌሊት በሕልሙ ከላይ እግዚአብሔር ተቀምጦባት መላእክት ሲወጡባት ሲወርዱባት ያያትን መሰላል በሦስተኛው ክፍለ
ዘመን መጨረሻ ላይ የሚላኖ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ አምብሮዝ ሲተረጕም፡- ‹‹መላእክት የተባሉት ከሐዋርያት ጀምሮ ያሉ ቅዱሳን
ሊቃውንት ናቸው፡፡ የመሰላሉ ቋሚዎች የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍት ሲኾኑ በቋሚዎቹ ላይ ያሉ ርብራቦች ደግሞ ከእነርሱ የሚገኙት ምግባራት
ማለትም ጾም፣ ጸሎት፣ ቀዊም፣ ስግደትና የመሰሉት ናቸው፡፡ ሊቃውንት በእነዚህ በኩል ወደ ላይ በብቃት ይወጣሉ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስም
እስከ ሦስተኛው ሰማይ ይነጠቃሉ፡፡ ምሥጢራተ መጻሕፍትንም ይዘውልን ይወርዳሉ፤›› በማለት ያስረዳል፡፡ቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢራዊ
መልእክት አላቸው ሲባልም አንድ ሰው ከራሱ ዓለማዊ ዕውቀት ወይም ልምድ ብቻ ተነሥቶ ወይም ከአስተሳሰቡ አመንጭቶ የሚነግረን ሳይኾን
ቅዱሳን ሊቃውንት ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ጸጋ መሠረት ከእርሱ ተቀብለው የሚሰጡን ትምህርት ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት
በሰው ቋንቋ የተጻፉ የእግዚአብሔር መለኮታዊ መልእክቶች ናቸውና ከቃላቱ መደበኛ ትርጕም ያለፈውን መለኮታዊ ምሥጢር ወይም መልእክት
ልናገኘው የምንችለው ከእግዚአብሔር በሚሰጥ ጸጋ ብቻ ስለሚኾን ነው፡፡
በመጠኑም ቢኾን ስለ ትርጓሜ መጻሕፍት ምሥጢር ይህን ያህል ከጠቀስን አሁን ደግሞ ከላይ በርእሱ ስለ ተቀመጠው የኦሪት
ጥቅስ ምሥጢራዊ መልእክት እንመልከት፤በቅዱሳት መጻሕፍት ስለምንቀበለውና ስለማንቀበለው ትምህርት ከተነገረባቸው መንገዶች አንደኛው
ምሳሌያዊ መንገድ ነው፡፡ ይህም ማለት ለጊዜው ቀጥታ ለሚተገበር ምግባራዊ ሕግ የተሰጡ መስለው ምሳሌነታቸውና ምሥጢራዊ መልእክታቸው
ግን ሃይማኖታዊ ወይም ስለ ሃይማኖታችን ልንቀበላቸውና ላንቀበላቸው ስለሚገባን ትምህርቶች በምሳሌ የተገለጹ መኾናቸው ነው፡፡ ከእነዚህ
መልእክቶች አንደኛውን ለማስታወስ ያህል፡- ‹‹የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ዅሉ ብሉ፤ ነገር ግን ከማያመሰኩት፣
ሰኮናቸው ስንጥቅ ከኾነው ከእነዚህ አትበሉም፡፡ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። ጥንቸልም ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ
በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፤ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፤
በድናቸውንም አትነኩም፡፡ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤›› ተብሎ በኦሪት የተገለጸው ትእዛዝ ይገኝበታል /ዘሌ.፲፩፥፫-፰/፡፡በኦሪት
ሕግ እንድንመገባቸውና እንዳንመገባቸው ለማድረግ እግዚአብሔር ያዘዘን እያንዳንዳቸውን በሙሉ በመዘርዘር ሳይኾን በቡድን በመመደብና
ምሳሌ በመጥቀስ ነው፡፡ እንድንበላቸው የተፈቀዱት እንስሳት ሁለት ነገሮችን ሊያሟሉ ይገባቸዋል፤ ይኸውም በኦሪት ዘሌዋውያን እንደ
ተጻፈው የሚያመሰኩና ሰኮናቸው የተሰነጠቀ መኾን ይኖርባዋቸል፡፡ ሁለቱንም መሥፈርት የማያሟሉ ብቻ ሳይኾን ከሁለቱ አንዱንም የማያሟሉ
እንስሳት አይበሉም፡፡ ይህ ትእዛዝም ቀደም ብለን ባየነው ትምህርት መሠረት ሦስቱን መልእክታት ያስተላልፋል፤ታሪካዊ መልእክቱ ይህ
ነገር ሕግ ኾኖ መቼ? በማን? ለማን እንደ ተሰጠና የመሳሰሉትን ምሥጢራት ሲነግረን፣ ምግባራዊ መልእክቱ ደግሞ የፈጠራቸውን የሚያውቅ
አምላክ ሳስቶና ወይም ተመቅኝቶን ሳይኾን እንስሳቱ በሰውነታችን ላይ በሚያመጡት ጉዳትና በመሳሳለው ችግር ምክንያት እንዳይበሉ አዝዞናል፡፡
ዳግመኛም በዘመነ ኦሪት እነዚህን እንስሳት መብላትና አለመብላት የመርከስና የመቀደስ ዋና ምክንያትም ነበረ፡፡በሐዲስ
ግን የማይበሉትን እንኳ የማንበላው ጥንቱንም ስለማይጠቅሙን ነው (ምንም ሲበሉ የኖሩትን ክርስቲያን ማድረጉ ወይም ክርስትና የሚቀድሳቸው
መኾኑ የታወቀ ቢኾንም የማይበሉ የነበሩት ይብሉ ማለት አይደለምና) አይጠቅሙንምና አሁንም አንበላቸውም፡፡ ሐዋርያትም በዲድስቅልያ፡-
‹‹ወቦ እለ ይብሉ ሥጋ አኅርው ንጹሕ ባሕቱ ኢኮነ ንጹሐ አላ ርኩስ መፍትው ለነ ንርኀቅ እምዘ ከመዝ ግብር ወዘሰ ኮነ ንጹሐ በውስተ
ሕግ ይብልዑ እምኔሁ፤ የእሪያዎች ሥጋ ንጹሕ ነው የሚሉ አሉ፤ ነገር ግን ርኩስ ነው እንጂ ንጹሕ አይደለም፡፡ ከእንደዚህ ያለ ሥራ
እንርቅ ዘንድ ይገባናል፡፡ በመጽሐፍ ንጹሕ ከኾነ ግን ከእርሱ ይብሉ፤›› ሲሉ አዝዘውናል / አንቀጽ ፴፪፥፵፮-፵፯/፡፡በዚህ ኃይለ
ቃል ‹‹የሚያመሰኩና ሰኮናቸው የተሰነጠቀ ንጹሐን ናቸው›› የተባሉት በሃይማኖትና በምግባር የሚኖሩ መምህራንና ምእመናን ናቸው፡፡
የሚያመሰኳ (በአሁኑ አማርኛ የሚያመነዥክ ሲባል የምንሰማው ነው) ማለትም የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢራት በሕሊናው የሚያመላልስ ማለት
ነው፡፡ የሚያመነዥክ ወይም የሚያመሰኳ እንስሳ ሣሩንም ቅጠሉንም ከበላው በኋላ እንደ ገና ወደ ላይ ወደ አፉ እያመጣ ደጋግሞ እንደሚያላምጠው
ቅዱሳንና እውነተኛ መምህራንም አንዴ በትምህርት የተቀበሉትን ምሥጢር ወይም ቃለ መጽሐፍ በሚገባ ከተረዱትና በልቡናቸው ካሳደሩት
በኋላ ምሥጢሩን ወደ ሕሊናቸው እያመላለሱ፣ እያወጡና እያወረዱ የበለጠ እያራቀቁ ለራሳቸውም ለሌላውም ጤናና ሕይወትን የሚሰጥ ተስማሚ
ምግብ ያደርጉታል፡፡‹‹ብፁዕ ብእሲ … ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ፤ ሕጉን ወይም ቃሉን በሌሊትም በቀንም የሚያስብ (ምሥጢራቱን
የሚረዳ) ምስጉን፣ ንዑድ፣ ክቡር ነው፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ /መዝ.፩፥፫/፡፡ሰኮናው የተሰነጠቀ ማለት ደግሞ በተራመደ
ጊዜ መሬት በደንብ የሚቆነጥጥ፣ የሚጨብጥ ማለት ነው፡፡
ይህም ማለት የሚናገረውንና የሚያውቀውን በሕይወቱ ተግባራዊ አድርጎ የሚኖርበት ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ከላይ ከተጠቀሰው
መዝሙሩ በማከታተል፡- ‹‹ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ፤ እንት ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ ወቈጽላኒ ኢይትነገፍ፤
እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይኾናል፤ የሚሠራውም ዅሉ
ይከናወንለታል፤›› እንደ ጠቀሰው ማለት ነው /መዝ.፩፥፫/፡፡የማያመሰኳ እንስሳ የዋጠውን መልሶ እንደማያደቀው መልሶ መላልሶ እንደማያኝከው
ዅሉ መናፍቃንም አንድ ጥቅስን በኾነ መንገድ ጐርሰው ከዋጡት በኋላ ምሥጢር አያመላልሱም፤ ደጋግመውም አያኝኩትም፡፡ማለትም የሚመላለሱ
ምሥጢራትን አያገኙም፤ አይመረምሩም፡፡ ዳግመኛም ሰኮናቸው ስላልተሰነጠቀ መሬት አይቆነጥጡም፤ ሃይማኖቱንም በምግባር አይኖሩትም፤
እንዲሁ ሲያደናግሩ ይኖራሉ እንጂ፡፡ ይህም ማለት እንደ ግመል በአካል ገዝፈው ብናያቸውም ለሰኮናቸው የሚስማማ አሽዋ (ያልረጋ ልቡና)
ፈልገው በዚያ ይኖራሉ እንጂ እንደ ሌሎቹ እንስሳት መሬት ቆንጥጠው ረግጠው ገደልና ተራራ አይሻገሩም፤ሃይማኖት አቀበትን ሊወጡ ገደላ
ገድል ተጋድሎዎችንም አልፈው ለምሥጢር፣ ለክብር ሊበቁ አይችሉም፡፡በሃይማኖት ገና ያልረጋና እንደ አሸዋ የሚንሸራተት ልቡና ካለ
የመናፍቃን ድፍን ሰኮና ይረግጠዋል፤ የበለጠም ያንሸራትተዋልና ዅላችንም ልቡናችንን ለማጽናት መትጋት ይገባናል፡፡
ከዚሁ ከሚበሉና ከማይበሉ እንስሳት ምሥጢር ሳንወጣ በባሕር ውስጥ ካሉት እንስሳት መካከል እንድንበላቸው የተፈቀዱልን
ቅርፊትና ክንፍ ያላቸው ዓሦች ናቸው፡፡ቅርፊት ለባሕር ፍጥረታት ጋሻቸው መጠበቂያቸው እንደ ኾነ ዅሉ በክርስትናም ከመናፍቃን የኑፋቄ
ጦርና የክሕደት መርዝ ለመዳን የሃይማኖትና የምግባር ጋሻ መታጠቅ ያስፈልጋል፡፡ ዓሦች በክንፋችው ከላይኛው የባሕር ክፍል ድረስ
እንደሚንሳፈፉበትና ወደ ታች እንዳይዘቅጡ እንደሚጠበቁበት ዅሉ በመንፈሳዊ ሕይወትና በንጽሕና ክንፍ ወደ ከፍተኛው የእግዚአብሔር
ምሥጢርና መረዳት የማይወጡ እንደ ድንጋይ በከበደ በዚህ ዓለም ፍልስፍና እና ሥጋዊ ሙግት ወደ መሬታዊነትና ሥጋዊነት የሚዘቅጡት
መናፍቃን ‹‹ርኩሳን›› ከሚባሉት መመደባቸውን ማወቅ፣ አውቆም ከኑፋቄ ትምህርታቸው መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ ከላይ እንደ ገለጽነው
እነርሱ ከዘመን አመጣሽ ሐሳብና ክሕደት የሚጠበቁበት ቅርፊት (የሃይማኖት ጋሻ) የሌላቸው ናቸውና፡፡አንዳንዶቹ ‹‹አስኳሉን እንስጣችሁ
ስንላቸው ቅርፊቱን አትንኩብን አሉ›› ሲሉ እንደሚደመጡት፣ (በኤግዚቢሽን ማእከል በተደረገው የተሐድሶዎች ልፈፋ ላይ አንድ አባ
ተብየ የተናገረውን አስታውሱ) ቅርፊቱ የእንቁላሉን አስኳል የያዘውና ከጉዳት የሚጠብቀው አካል መኾኑን እንኳ ማሰብ ተስኗቸው መጠበቂያ
ቅርፊት የሌላቸው ብቻ ሳይኾኑ ካላቸውም ላይ መስበር የሚፈልጉ መኾናቸውን መንፈስ ቅዱስ ፊታቸውን ጸፍቶ፣ አፋቸውን ከፍቶ አናግሯቸዋል፤
በራሳቸውም ላይ አስመስክሯቸዋል፡፡
ስለዚህ ክርስቲያኖች ንጹሐን የሚበሉ (አምላካቸው የሚቀበላቸው) የሚኾኑት ጥርጥርንና ክሕደትን፣ ይህንም የመሰለ የመናፍቃንን
የመዘባበትና የክሕደት ጦር የሚከላከል በቅርፊት የተመሰለ የሃይማኖት ጋሻ ሲኖረን ነው፡፡ ከጋሻዎቻችን ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ የሃይማኖታችንን
ነገር፣ የቅዱሳት መጻሕፍትንም ምሥጢር ለብሶ ማለትም አውቆ መገኘት ነውና ጊዜ ወስዶ ቁጭ ብሎ መማር እንኳ ባይቻል በተገኘው አጋጣሚ
ዅሉ ልቡናን ከፍቶ በወሬና በአሉባልታ ሳይጠመዱ መማር፣መጠየቅና እንደ ተገለጸው እያመላለሱ በማኘክ (በማጥናት) ቃሉን በሚገባ መያዝ
ተገቢ ነው፡፡ ከዚህም በላይ በሃይማኖት ልብን ማጽናት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ከኾነ ጠይቀን ያልገባንንና የማናውቀውን
ምሥጢር እስከምንረዳው ድረስ ጊዜ እናገኛለን፡፡ነገር ግን ብዙዎቻችን ትዕግሥት የለንም፤ ዛሬ ይህን ጽሑፍ ከምናነብበው እንኳ አንዳንዶቻችን
ቀጥታ ነገሩን በቅርቡ ማግኘት ባለመቻላችን ልንበሳጭም እንችላለን፡፡ነገር ግን አሁንም አስቀድመን አንዲት ጥያቄ ብቻ መልሰን እንሒድ፤
ይቆየን
ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት
ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሁለት
እንድንበላቸውና እንዳንበላቸው የታዘዝናቸው እንስሳት ከላይ
በተገለጸው መንገድ እኛን የሚወክሉ መኾንና አለመኾናቸውን የሚያረጋግጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ወይም የሐዋርያዊው ትምህርት
ትውፊት አለ ወይ? ከተባለ አዎን፤ በእርግጥ አለ፡፡ ሰፊውና ዋነኛው ምስክርም ቅዱስ ጴጥሮስ ያየው ራእይ ነው፡፡በሐዋርያት ሥራ
‹‹… ተርቦም ሊበላ ወደደ፤ ሲያዘጋጁለት ሳሉም ተመስጦ መጣበት፡፡ ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል
ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ዅሉ አራዊት፣ በምድርም የሚንቀሳቀሱ የሰማይ ወፎችም ነበሩበት፡፡
‹ጴጥሮስ ሆይ፣ ተነሣና አርደህ ብላ!› የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ጴጥሮስ ግን ‹ጌታ ሆይ አይሆንም፤ አንዳች ርኩስ የሚያስጸይፍም
ከቶ በልቼ አላውቅምና› አለ፡፡ ደግሞም ሁለተኛ ‹እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው› የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ፡፡ ይህም
ሦስት ጊዜ ኾነ፡፡ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፥፲-፲፮/፣ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ራእይ ደጋግሞ
ካየ በኋላ ራእዩ በቀጥታ ምግብ ሳይኾን ምሥጢራዊ መልእክት እንዳለው ተረድቶ ‹‹ትርጕሙ ምን ይኾን?›› እያለ ሲያስብ ነበር፡፡በኋላም
መንፈስ ቅዱስ ምሥጢሩን ገለጸለት፤ ‹‹…ጴጥሮስም ስለ ራእዩ ሲያወጣ ሲያወርድ ሳለ መንፈስ እነሆ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤ ተነሥተህ
ውረድ፡፡ እኔም ልኬአቸዋለሁና ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሒድ አለው፤››እንዲል /ቍ. ፲፱-፳/፡፡ ከታዘዘው ቦታ ከደረሰ በኋላም
‹‹አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም
ሰው ‹ርኩስና የሚያስጸይፍ ነው› እንዳልል አሳየኝ፤›› በማለት ምስክርነቱን አስቀደመ /ቍ. ፳፯/፡፡ በዚህ ራእይ ያያቸው የማይበሉ
እንስሳትም ምሳሌነታቸው ከእምነት ውጪ ላሉ ሰዎች እንደ ኾነ አረጋገጠ፡፡
ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው በሚያስተምርበት ጊዜ ‹‹…መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከዅሉም ዓይነት የሰበሰበች
መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጧት፡፡ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ
ውጪ ጣሉት፤›› በማለት /ማቴ.፲፫፥፵፯-፵፰/፣ መረብ የተባለችው ቤተ ክርሰቲያን ዅሉንም እንደምታጠምድ (ወደ እርሷ እንደምታቀርብ)፤
የዓሣዎቹ ሐዋርያትን ትምህርታቸውን ንቀው ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው የሚወድቁት ደግሞ መናፍቃንና ኀጥአንን እንደሚወክሉ በምሳሌ አስተምሮናል፡፡ለመሥዋዕት
የሚቀርቡት እንስሳትም የሰማዕታትና የቅዱሳን ምሳሌዎች መኾናቸውን ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት
‹‹አቤቱ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?›› በሚለው መዝሙሩ መምለክያነ እግዚአብሔር
እስራኤልን በጎች ብሎ ጠርቷቸዋል /መዝ.፸፬፥፩/፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፤ ወደ አሕዛብም በተንኸን፤›› ዳግመኛም
‹‹ስለ አንተ ዅልጊዜም ተገድለናል፡፡ እንደሚታረዱም በጎች ኾነናል›› በማለት ሰማዕትነታቸውና ተጋድሏቸው እንደ መሥዋዕት በጎች
እንደሚያስቈጥራቸው ተናግሯል /መዝ.፵፬፥፲፩-፳፪/፡፡ ይህ ቃል በእርግጥ ስለ ሰማዕታት የተነገረ መኾኑንም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ስለ
አንተ ቀኑን ዅሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን፤››በማለት አረጋግጦልናል /ሮሜ.፰፥፴፮/፡፡ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን
መከራና ሰማዕትነቱን ሲገልጽ ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፤የምሔድበትም ጊዜ ደርሷል፤›› በማለት ሕይወቱን
በመሥዋዕት መስሎ መናገሩም /፪ኛጢሞ.፬፥፮/፣ጥንቱንም እነዚህ የመሥዋዕት እንስሳት የቅዱሳን፣የንጹሐን ምእመናን፤ ርኩሳን የተባሉት
ደግሞ የማያምኑትና የመናፍቃን ምሳሌዎች መኾናቸውን አመላካች ነው፡፡
ጌታችንም በነቢዩ በሕዝቅኤል ላይ አድሮ‹‹‹እናንተም በጎቼ፣ የማሰማርያዬ በጎች ሰዎች ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ›
ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤››በማለት በተናገረው ቃል /ሕዝ.፴፬፥፴፩/ እስራኤልን ‹‹በጎቼ›› ብሏቸዋል፡፡ ነቢያትም ዅሉ ይህን ቃል
ደጋግመው ተናግረውታል፡፡ ጌታችንም በዘመነ ሥጋዌው ቃሉን አጽድቆታል፡፡ በመጨረሻው ዕለትም ‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ በዚች ሌሊት
ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፡፡ ‹እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ› የሚል ተጽፎአልና፤›› /ማቴ.፳፮፥፴፩/ ያላቸው
ቅዱሳኑ፣ ንጹሐኑ የመሥዋዕቱ እንስሳት የሚያመሰኩትና ቆንጥጦ ለመርገጥ የሚያስችል ስንጥቅ ሰኮና ያላቸው እነርሱ በመኾናቸው ነው፡፡ስለዚህ
በዘመነ ኦሪት ከሁለቱም ወገን የሚመደቡ እንስሳትን የሚያርዱና የሚበሉ ሰዎች የነበሩ ቢኾንም እግዚአብሔርና የእርሱ የኾኑት የሚቀበሉት
ግን ከንጹሐን ወገን የኾኑትን እንስሳት ብቻ ነበር፡፡ ይህም ምሳሌ ስለ ኾነ ዛሬም ከሁለቱም ወገን የሚመደብ አለ፤ እግዚአብሔርና
የእግዚአብሔር የኾኑት የሚቀበሉትም በንጹሐን እንስሳት ከተመሰሉት ከሐዋርያት፣ ከሰማዕታት፣ ከቅዱሳን ሊቃውንትና ከእውነተኞች መምህራን
የሚገኘውን ትምህርት ብቻ ነው፡፡
ቀደም ብለን እንደ ገለጽነው እነዚህ ቅዱሳን በበግና በመሳሰሉት የተመሰሉት ሰኮናቸው የተሰነጠቀ እንስሳት በትክክል መሬትን
ጨብጦ ወይም ቆንጥጦ መርገጥ እንደሚችሉት እንደዚሁ ሃይማኖታቸውን በሥራ ገልጠው ከእነርሱ የሚጠበቀውን መሥዋዕትነት ወይም ሰማዕትነት
በገቢር ገልጸው የሚኖሩ በመኾናቸው ነው፡፡ በባሕር ውስጥ በሚኖረው ቅርፊትና ክንፍ ባለው ዓሣ የተመሰሉትም በዚህ እንደ ባሕር በሚነዋወጥ
ዓለም ውስጥ እየኖሩ ወደ ከፍተኛው ጸጋና ክብር ብቻ ሳይኾን ወደ ላይኛው መለኮታዊ ምሥጢር ብቅ የሚሉበት ክንፈ ጸጋ፣ የዚህን ዓለም
አለማመን፣ ክሕደትና ኑፋቄ ድል የሚነሡበት በቅርፊት የተመሰለ የእምነት ጋሻና ጦር ስላላቸው ነው፡፡እኛንም ‹‹በዅሉም ላይ ጨምራችሁ
የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤›› ሲሉ አስተምረውናልና /ኤፌ.፮፥፲፮/፣
የእምነት ጋሻችንን እናነሣለን፡፡ ደግሞም ‹‹የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤››
/፪ኛቆሮ.፲፥፬/ ተብሎ እንደ ተጻፈው መሣሪያችንም ሥጋዊ የጦር ትጥቅ ሳይኾን የዲያብሎስን የተንኮልና የክሕደት ምሽጎች ለመስበር
የበረታው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ከተባሉት፤ ያለ መከላከያ ኾነው ራሳቸውን አስማርከው
እኛንም ወደ እነርሱ ጥርጥርና ክሕደት ሊስቡ ወደሚሮጡት፤ ዳግመኛም የእግዚአብሔርን ቃል ምሥጢራት ወደማያመላልሱትና ሰኮና በተባለ
ክሳደ ልቡናቸው መሬት ገቢርን ወደማይጨብጡት እንዳንጠጋ ‹‹እነርሱ ዅልጊዜም በነፍስ ርኩሳን ናቸው፤›› ተብሎ ተጽፎልናል፡፡
‹‹ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ማን ነው?››ለሚለውን
ጥያቄ ምላሽ የምንሰጠውም ‹‹ያመሰኳሉ›› የተባሉ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቃሉን እያመላለሱ መርምረው፣ ምሥጢሩን ከእግዚአብሔር
ዘንድ ተረድተው እንደ ጻፉልን በማመንና በዚሁ (በእነርሱ) መንፈስ ይኾናል ማለት ነው፡፡በእርግጥ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው
መልአክ ማን ነው? መጀመሪያውንም መጽሐፍ ቅዱሱ ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያወጣቸው ‹‹ገብርኤል ነው›› አይልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱ
የሚለው የሚከተለውን ነው፤ ‹‹የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፡-‹ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት
ውስጥ ጥለን አልነበረምን?› ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፡- ‹ንጉሥ ሆይ እውነት ነው› ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም፡- ‹እነሆ
እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል
ብሎ መለሰ፤›› /ዳን.፫፥፳፬-፳፭/፡፡ በዚህ አገላለጽ መሠረት አራተኛውን ሰው ያየው ንጉሡ ናቡከደነፆር ሲኾን የጨመረበት ቃል
ቢኖር ‹‹አራተኛው የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› የሚለው ነው፡፡ለመኾኑ አራተኛውን ሰው እርሱ ብቻ ለምን አየው? ሌሎቹ ለምን አላዩትም?
የጥያቄው ቍልፍ ምሥጢር ያለው ከዚህ ላይ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ ሰው ጥንቱንም ሠለስቱ ደቂቅን ወደ እሳት የጣላቸው ሕዝቡን
ለራሱ ምስል በማሰገድ ራሱን አምላክ አድርጎ ሊያስመልክ አስቦ ነበር፡፡ ታዲያ ራሱንና እርሱን የመሰሉትን አማልክት አድርጎ የሚቈጥር
ከኾነ የሚያየውን አራተኛውን ሰው ‹‹የእኛን ልጅ ይመስላል›› ወይም ‹‹እኛን ይመስላል›› ለምን አላለም? ከዚያ ይልቅ አርቆ ሌሎች
አማልክትን የሚያመልክ አስመስሎ ‹‹የአማልክትን ልጅ ይመስላል›› ያለበት ምሥጢር ምንድን ነው? ንጉሡ ይህን ያለበት ምክንያት እነርሱ
ሳያዩት ከሠለስቱ ደቂቅ ጋር አራተኛ ሰው ወደ እሳቱ ገብቶ ሳይኾን ነገሩ የወልደ እግዚአብሔርን በሥጋ መገለጥ የሚያመላክት ምሥጢር
ስለለው ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ከተገለጹት ታላላቅ ሦስት የእግዚአብሔር መገለጦች ውስጥ ሦስተኛው ይህ የሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ
ነው፡፡ አንደኛው መገለጥ በመምሬ የአድባር ዛፍ ሥር እግዚአብሔር ለአብርሃም በሦስት ሰዎች አምሳል የተገለጠው መገለጥ ሲኾን /ዘፍ.፲፰/፣
ሁለተኛውም እግዚአብሔር ለአባታችን ለያዕቆብ በጐልማሳ አምሳል ተገልጾ ሲታገለው ያደረበት ታሪክና ያዕቆብም መጀመሪያ ‹‹ካልባረከኝ
አልለቅህም›› ብሎ ከተባረከ በኋላ ‹‹‹እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ድና ቀረች› ሲል የዚያን ቦታ ስም ‹ጵንኤል›
ብሎ ጠራው፤›› ያሰኘው መገለጥ ነው /ዘፍ.፴፪፥፳፭-፴፪/፡፡ ሦስተኛው መገለጥ ደግሞ አላዊው የባቢሎን ንጉሥ ሠለስቱ ደቂቅን ወደ
እቶነ እሳት በጣለበት ወቅት ያደረገው መገለጥ ነው፡፡ሦስቱም መገለጦች የሚያመሳስሏቸው ሁለት ጠባይዓት አሏቸው፡፡ የመጀመሪያው በሦስቱም
መንገድ እግዚአብሔር በሰው መልክና አምሳል መገለጡ ሲኾን ሁለተኛውና ዋነኛው ቃለ እግዚአብሔር በሥጋዌ (ሰው በመኾን) ተገልጦ ለሰው
ፍጹም ድኅነት የሚሰጥ መኾኑን አስቀድሞ በምሳሌ መግለጥ ነው፡፡ መሠረታዊ መልእክቱ ደግሞ አምላክ ሰው ከኾነ በኋላ የሚያድነው የተስፋውን
ዘር እስራኤልን ብቻ ሳይኾን አሕዛብንም ጭምር መኾኑን ለማሳየትና አሕዛብም የሥጋዌው ነገር ቀድሞ የተገለጠው ለእስራኤል ብቻ ስለ
ኾነ እኛ ልናምንበት አይገባም እንዳይሉ ለዚህ ደንዳናና ጨካኝ ናቡከደነፆርም ጭምር ተገለጠለት፡፡
የነነዌ ሰዎች ታሪክም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ኾኖ የተቀመጠውና እግዚአብሔር ለአሕዛብም ድኅነት ይፈጽም እንደ ነበር የተመዘገበው
እግዚአብሔር የእስራኤል ብቻ ሳይኾን የዅሉም አምላክ መኾኑን ራሱ ብሉይ ኪዳንም ምስክር እንዲኾን ነው፡፡ እነዚህን የመሰሉ ሌሎች
ታሪኮችና ምሳሌዎችም በብዛት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ በሠለስቱ ደቂቅ ድኅነት ውስጥ የታየው መገለጠጥ ዋነኛው ምሥጢርና
መልእክትም የእግዚአብሔርን ሰው መኾንና አዳኝነት፤ እንደዚሁም እንደ ሠለስቱ ደቂቅ እሳትና ስለት፣ ሰይፍና ጐራዴ፤ እስራትና ግርፋት
የሚቀበሉ ሰማዕታትን ዅሉ የሚያድናቸው እርሱ መኾኑን መግለጽ ነው፡፡ ታዲያ ዋነኛው መልእክቱና ምሥጢሩ ይህ ከኾነ ገብርኤልም ኾነ
ሌሎቹ መላእክት ለምን ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት አወጡ (አዳኑ) ይባላሉ? በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት መሠረት ለሰዎች ከጊዜያዊና
ምድራዊ አደጋና ሰዎች ከሚያመጡባቸው መከራ ድኅነት ሲደረግላቸው ድኅነታቸውን የሚፈጽሙላቸው ቅዱሳን መላእክት ማለትም ጠባቂ መላእክቶቻቸው
ናቸው፡፡ይህም ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ በግልጽ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በምሥጢር ቢገለጽም የእግዚአብሔር መላእክት ከሚጠብቋቸው
ሰዎች ተለይተው አያውቁም፡፡ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ ላይ ቅዱስ ያዕቆብን ያስገደለው ሄሮድስ ቅዱስ ጴጥሮስንም ለመግደል ባሰረው ጊዜ
በዚያ ወቅት እንዲሞት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ መልአኩ እንዲያድነው አድርጓል፡፡ ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ቀረበ፤ በቤትም ውስጥ
ብርሃን በራ፡፡ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና ‹ፈጥነህ ተነሣ› አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም፡-‹ታጠቅና ጫማህን
አግባ› አለው፤ እንዲሁም አደረገ። ‹ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ› አለው። ወጥቶም ተከተለው፡፡ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር
እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ኾነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው
ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፡፡ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ፡፡ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም
ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ‹ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ዅሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ›
አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሐዋ.፲፪፥፯፲፩/፡፡
ይቆየን!
ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት
ያዳናቸው መልአክ ማን ነው? – ክፍል ሦስት (የመጨረሻ ክፍል)
ሙት ላነሣውና ብዙ ተአምራትን ላደረገው ቅዱስ ጴጥሮስ አሁን ግን ይህን ዅሉ ጥበቃ የሚያደርግለት መልአኩ ነው፡፡ ይህ
መልአክ የቅዱስ ጴጥሮስ ጠባቂ መልአክ እንደ ኾነ ብዙ ሊቃውንት በትርጓሜአቸው አስተምረዋል፡፡ በዚሁ ታሪክ ላይም፡- ‹‹ጴጥሮስም
የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መኾኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ
የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ ‹አብደሻል› አሏት።
እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ኾነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ ‹መልአኩ ነው› አሉ፤›› ተብሎ ተጠቅሷል /ቍ.፲፫-፲፭/፡፡ ከቤት
ውስጥ የነበሩትም ‹‹ጴጥሮስ አይኾንም፤ መልአኩ ነው›› ያሏት ‹‹እርሱን ሊመስልሽ የሚችለው ጠባቂ መልአኩ ነው›› ማለታቸው ነበር፡፡
ይህም የኾነው በጥንት ክርስቲያኖች ዘንድ የጠባቂ መላእክት ጥበቃና መገለጥ በሰፊው ይታወቅ ስለ ነበረ ነው፡፡ በመጽሐፈ ጦቢት ላይም
ቅዱስ ሩፋኤል ሰው መስሎ ለጦብያና ለቤተሰቡ እንደዚሁም ለራጉኤልና ለቤተሰቡ ቀድሞ ጸሎታቸውን በማሳረግ፣ በኋላም ከፈተናቸው በማዳንና
ሕይወታቸውን በመባረክ ተገልጦ አይተነዋል፡፡
እነዚህ ሁለት ታሪኮች የሚያስረዱን ጠባቂ መላእክት በድኅነታችን ውስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጣቸውና በእርግጥም እነርሱ የሌሉበት
ድኅነት የሌለ መኾኑን ነው፤ ልዩነቱ በአንዳንዶቹ ታሪኮች ላይ መገለጣቸው፣ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተገልጠው ለሰው አለመታየታቸው
ብቻ ነው፡፡ ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን
ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፤›› በማለት የተናገረው ስለ ጠባቂ መላእክቶቻችን ነው /ማቴ.፲፰፥፲/፡፡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችንና
ፈተናችን ላይ ወደ እግዚአብሔር እያመለከቱ የሚጠብቁን፣ የሚያድኑን፣ የሚያስፈርዱልን ወይም የሚያስፈርዱብንም እነርሱ (ቅዱሳን መላእክት)
ናቸውና፡፡ እንደ ናቡከደነፆር ያለውን አስፈርደውበት አውሬ አድርገው ሣር ያስግጡታል፡፡ እርሱ ራሱም ‹‹አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ
ሲወርድ አየሁ፤›› ብሎ አሁንም እውነቱን አረጋግጧል /ዳን.፬፥፲፫/፡፡ እንደ ሄሮድስ ያለውን ደግሞ ‹‹ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ
ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፪፥፳፫/፣ በእግዚአብሔር አስፈርደው ይቀሥፉታል፡፡እንደ
ዳንኤል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ጻድቁ ዮሴፍ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉትን ደግሞ በጠባቂነታቸው ያድኗቸዋል፡፡ ‹‹… እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፣
ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፡፡ እውነት እንደ ጋሻ ይከብሃል። ከሌሊት
ግርማ፣ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፣ በጨለማ ከሚሔድ ክፉ ነገር፣ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺሕ በቀኝህም ዐሥር
ሺሕ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የኀጥአንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ አንተ ተስፋዬ ነህና
ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፤ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ዅሉ ይጠብቁህ ዘንድ
መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል … ›› ተብሎ ተጽፏልና /መዝ.፺፥፩-፲፪/፡፡ሠለስቱ
ደቂቅንም ጠባቂ መላእክቶቻቸው የሚያድኗቸው ቢኾንም ‹‹ለናቡከደነፆር የታየው አንድ መልአክ ኾኖ ሳለ ሦስቱ መላእክት እንዳዳኗቸው
ተደርጎ ለምን ይገለጻል?›› የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን፡፡
እንዲህ ያሉትን ምሥጢራት መረዳት የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን ተመሳሳይ ታሪኮችና ይህ የሚኾንበትን ምክንያት
ስናውቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የጌታችንን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውልናል፤ አራቱም የመዘገቡበት መንገድ ተቃርኖ ባይኖረውም
ልዩነት ግን አለው፡፡ ዐበይት ልዩነቶቹም ሦስት ነገሮች ላይ ይስተዋላሉ፤ ይኸውም የተገለጹት መላእክት፣ ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች
ማንነት እና ሴቶቹ የመጡበት ሰዓት በአዘጋገብ ይለያያል፡፡ለርእሰ ጉዳያችን ቅርበት ባለው ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን ጥቂት
ምሳሌዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤ቅዱስ ማቴዎስ፡- ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤
ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ
ተናወጡ እንደ ሞቱም ኾኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ ‹እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡
እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፡፡› የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሒዱና ከሙታን ተነሣ፤ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፡፡
በዚያም ታዩታላችሁ፤› ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው፤›› ሲል የገለጸውን /ማቴ.፳፰፥፪-፯/፣ ቅዱስ ማርቆስ፡- ‹‹ወደ መቃብሩም
ገብተው ነጭ ልብስ የተጐናጸፈ ጐልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ …›› በማለት መዝግቦታል /ማር.፲፮፥፭/፡፡ ቅዱስ ሉቃስ
ደግሞ ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤›› ብሎ ጽፎታል /ሉቃ.፳፬፥፬/፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ትንሣኤው ብዙ ነገር ካተተ በኋላ ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ
መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ
ተቀምጠው አየች፤›› ሲል መዝግቦልናል /ዮሐ.፳፥፲፩-፲፪/፡፡
እነዚህን አገላለጾች ስናያቸው የአዘጋገብ ልዩነት ቢታይባቸውም ተቃርኖና የእውነታ ልዩነት ግን የላቸውም፡፡ቅዱስ ማቴዎስና
ቅዱስ ማርቆስ ስለ አንድ መልአክ ሴቶችን ማነጋገር ቢገልጹም ሌላ መልአክ እንዳልነበረ ግን አላመለከቱም፡፡ ወንጌላውያኑ ስለ አንድ
መልአክ መታየት ይመዝግቡልን እንጂ የተናገሩት ግን ስለ ተለያዩ መላእክት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ከመቃብሩ ወጭ ድንጋዩን
አንከባሎ ስለ ተቀመጠው መልአክ ዘግቦ ከመቃብሩ ውስጥ በቀኝ በኩል (በራስጌ ወይም በግርጌ) ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ቅዱስ
ማርቆስ ደግሞ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስላለው መልአክ መዝግቦ ከውጭ በኩል ስላለው ወይም የመቃብሩ ድንጋይ ላይ ስላለው መልአክ
አልመዘገበም፡፡ ሁለቱም ግን ‹‹ሌላ መልአክ አልነበረም›› በሚያሰኝ መንገድም አልገለጹልንም፡፡ ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ
ሁለቱም መላእክት መኖራቸውንና በግርጌና በራስጌ መኾናቸውን ገልጸውልናል፡፡ ስለዚህ ዅሉም ትክክል ናቸው ማለት ነው፡፡ የተለያዩና
የማይቃረኑ የተባለውም ስለዚህ ነው፡፡የተለያዩትስ ለምንድን ነው ስንል ደግሞ አንድ መሠረታዊ መልእክት እናገኛለን፤ ይኸውም ስለ
መላእክቱ የተለያየ ዓይነት መገለጥ የገለጹት ለተለያዩ ሰዎች በትንንሽ የጊዜ ልዩነት የታየውን መገለጥና ለአንዳንዶችም በተቀራራቢ፣ነገር
ግን በተለያየ ጊዜ የተገለጠውን ስለ መዘገቡ ነው፡፡ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ ለመግደላዊት ማርያም የተደረገውን የአንድ ጊዜ መገለጥ
ብቻ ሲነግረን፣ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች የተደረገውን (ምክንያቱም ተመላልሰው ያዩም አንድ ጊዜም ያዩ አሉ፤ እንደዚሁም
ብዙ ታሪኮች በውስጡ አሉና) እያሉ ከነሰዓቱ ስለ መዘገቡ እንጂ አንዱን ነጠላ ድርጊት ለያይተውና አሳሰተው መዝግበውት አይደለም፡፡
በዚህ መሠረት በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ክፍል ላይ እንዳየነው ከመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ተሰጥቷቸውና በጊዜው የነበረውን እውነተኛውን
ትውፊት ከሐዋርያትና ከነበሩት ቅዱሳን ተምረው ከተረጐሙት መምህራን ሳይረዳ ልክ እንደነዚያ ርኩሳን እንደ ተባሉት እንስሳት ሳያመሰኳ
ወይም እውነታውን ሳይቆነጥጥ ወይም እንደ ዓሣዎቹ ሐዋርያት የእምነት መከላከያ ቅርፊት (ጋሻ) እና ምሥጢራትን የሚረዳበት ክንፈ
ጸጋ ሳይኖረው በአመክንዮ (ሎጂክ) ብቻ እረዳለሁም፣ አስረዳለሁም ቢል ይሳሳታል፡፡ ስለዚህ የሠለስቱ ደቂቅ ድኅነትን በተመለከተ
በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል፤ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ መገለጹ
ከላይ በወንጌል እንዳየነው ትውፊቱን ለያይቶ መዘገብ እንጂ ተቃራኒ ነገር አይደለም፡፡ በዚሁ መሠረት ሦስቱን ሕፃናት አናንያ፣ አዛርያና
ሚሳኤልንም ያዳኗቸው ጠባቂ መላእክቶቻቸው፤ እነዚህም ቅዱስ ሚካኤል፣ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ልክ ሥላሴ ለአብርሃም
በተገለጹለት መንገድ ሦስት ኾነው ከሦስቱ በስተጀርባ ቆመው መታየት ነበረባቸው ካላልን በስተቀር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተላለፈው ትውፊት
ሦስቱ መላእክት የሦስቱ ሕፃናት ጠባቂ መላእክት ነበሩ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ሦስት ኾነው ይቅርና አንድም ሰው ቢኾን ሦስትና ከዚያ በላይ
መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና፤›› እንዳለው /፩ኛሳሙ.፲፬፥፮/፣
በአንድም በብዙም መንገድ ማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሥጢር እንጂ የመላእክቱ የማነስና የመብዛት ጉዳይ የሚከራክር አይደለም፡፡እንዲህ
ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ዘንድ ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱ፣ በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ
መኾኑን ከተለያዩ ገድላት ለመረዳት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ አንድ ዓሣ አስጋሪ ሰው ‹‹መርምሕናም እርዳኝ?›› እያለ ቅዱስ መርምሕናምን ሲማጸን ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ
መርምሕናም በአንድነት መጥተው ዓሣ አስጋሪውን እንደረዱት ‹‹ወበጊዜሃ መጽኡ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተጽዒኖሙ
ዲበ አፍራሲሆሙ ….›› ተብሎ በተአምረ ጊዮርጊስ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደ
ኾነ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡
ልዩነት ያለ የሚመስለን መገለጦችን የምንረዳበት ሒደት አነስተኛ ሲኾን ብቻ ነው፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠቃለያም፡- ‹‹ይህ ከኾነ ታዲያ በሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ ለምን ይወጣል?
ዕለቱ (ታኅሣሥ ፲፱ ቀን) በዓል ኾኖ የሚከበረው ለቅዱስ ገብርኤል፤በሥዕልም ላይ ‹አራተኛው ሰው› ተብሎ በናቡከደነፆር የተገለጸው
የቅዱስ ገብርኤል ሥዕል የሚሣለው ለምንድንነው?›› ለሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ይኾናል፡፡ይህ የኾነበት ምክንያት ዝም
ብሎ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋዌውን አስቀድሞ የገለጸው መላእክትንም በሰው አምሳል እንዲገለጹ በማድረግም ጭምር
ነው፡፡ ለምሳሌ ለሙሴ መጀመሪያ የተገለጠለት በዚሁ መንገድ ነበረ፡፡ ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾኽ ቍጥቋጦ
መካከል ታየው፤እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ፣ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዘፀ.፫፥፪/፡፡ ይህም ነገረ ተዋሕዶን
ወይም ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያስረዳ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመላእክት አምሳል ሲገልጥ ደግሞ ቅድሚያውን ስፍራ የሚይዘው
ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ምክንያቱም ገብርኤል ማለት ‹‹ቃለ እግዚአብሔር›› እንደዚሁም ‹‹ሰውና አምላክ›› ማለት ስለ ኾነ ነው፡፡
እመቤታችንን ሊያበሥር የተላከውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹አራተኛ ሰው አያለሁ›› እስኪል ድረስ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር
ሥጋዌውን (ሰው መኾኑን) ገልጦ ያሳየው ከሦስቱ ሊቃነ መላእክት መካከል ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር በስሙም በተልእኮውም ቅዱስ ገብርኤል
የተሸከመው በመኾኑ ነው፡፡
ስለዚህም ሦስቱም ሊቃነ መላእክት በጠባቂ መላእክትነታቸውና ረቂቃን ኃይላት በመኾናቸው በአዳኝነት ቢጠቀሱም እግዚአብሔር
ሊገልጠው ለፈለገው ታላቅ ምሥጢር ተስማሚ የኾነውን መልአክ (ራሱ ገብርኤል መኾኑ ትርጕምና መልእክት ያለው ነውና) የነገሥታትን
ልጅ በሚመስል ጐልማሳ አምሳል የንጉሠ ሰማይ ወምድር የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ምሳሌ ኾኖ እንዲገለጽለት አድርጓል፡፡ በዓሉ ለገብርኤል
የተሰጠውና ሥዕሉ የእርሱ የኾነበት ምክንያትም ይኸው ምሥጢር ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር መሠረት
አድርጋ በዓሉ በቅዱስ ገብርኤል ስም በታላቅ ሥርዓት እንዲከበር፣ በሥዕሉም ቅዱስ ገብርኤል ጐልቶ እንዲታይ በማድረግ ነገረ ሥጋዌውንም፣
የሕፃናቱን ተጋድሎም፣ የመላእክቱን ጠባቂነትም ስትገልጽበትና ስታስረዳበት ትኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምልዓት መረዳት ያለውም
በእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ጸንታ በምትኖረው በዚህች ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ነው፡፡የእግዚአብሔር
ቸርነት፤ የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጅነት፣ የሊቃነ መላእክቱ ጥበቃና የቅዱሳን ዅሉ ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ለዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡
No comments:
Post a Comment