ከክፍል ሃያ ስምንት የቀጠለ
የተከበራችሁ የዚች ጦማር ታዳሚዎች
ምእመናን!
እንደምን ሰነበታቸሁ? ጌታችንና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ የጾመውን ዐቢይ ጾም፤እኛም እንደ አቅማችን ጾመን እንድንፈጽመው የረዳን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ
የተመሰገነ ይሁን፡፡
ከዚህ በመቀጠል የጌታችንን የሕማሙን፣የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር በመጠኑ ለማዘከር እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!
ሰሙነ ሕማማት ወትንሣኤ
በዚህ “ሰሙነ ሕማማት ወትንሣኤ”በሚለው ርዕስ የዓለም መድኃኒት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች
የተቀበለውን መከራና የመስቀል ሞት እንዲሁም ሞትን ድል አድርጎ መነሣቱን በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
ሰሙነ ሕማማት ምን የተከናወነበት ነው?
ከሆሳዕና እሑድ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ስዑር /የትንሳኤ ዋዜማ/ ድረስ ያለው ሳምንት ማለትም ሰሙነ ሕማማት፤ በኃጢአት በሽታ
የሚሰቃየውን የሰው ልጅ ለመፈወስ የመጣውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገረ ሕማሙን የምናስብብበት ነው፡፡ይህ የጌታችን የኢየሱስ
ክርስቶስ የሕማሙና የሞቱ ነገር፤ አስቀድሞ በአምላካችን በእግዚአብሔር ለአባታችን አዳም በተሰጠው ተስፋ መሠረት ሲጠበቅ የኖረ፤
በነቢያት ትንቢት የተነገረለት ምሳሌም የተመሰለለት እንጂ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ በድንገት የተከሰተ አይደለም፡፡
ይልቁንም ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕማማችንንም ተሸከመ…. በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን…” በማለት
አስቀድሞ በግልጽ ቋንቋ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡ኢሳ.፶፫፥፬፡፡
ይህ ሳምንት የሰው ልጅ በሲዖል ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ ሲኖር የነበረበት ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ በልዩ ሁኔታ
የሚታሰብበት ነው፡፡በመሆኑም በዚህ ሳምንት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣፣ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፣ካህናት መስቀል
አያሳልሙም፣በዓላት አይከበሩም፣መሳሳም አይፈቀድም፣በአጠቃላይ ከማንኛውም ሥጋዊ ሥራ ተለይቶ የጌታችንን ሕማሙንና ሞቱን በማሰብ፤በጸሎትና
በስግደት ሥርየተ ኃጢአትን መለመን ብቻ ነው፡፡በቤተ ክርስቲያንም የሚነበቡት የብሉይና የአዲስ ምንባባት የጌታችንን ሕማሙንና ሞቱን
የሚያወሱ ሲሆኑ በየግላችንም የምንጸልየው ጸሎት ይህንኑ የተከተለ ነው፡፡በመሆኑም በሰሙነ ሕማማት በሚገኙ ዕለታት የተከናወኑትን
ዐበይት ተግባራት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡
ሆሳዕና፦ ሆሳዕና ማለት መድኃኒት ማለት ነው፡፡የመድኃኔዓለም ክርስቶስ ሌላው ስሙ
ነው፡፡“አሁን አድን” የሚል ትርጉም አለው፡፡በዚህን ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕፃናት ሳይቀር እየተመሰገነ በተናቀች
አህያ ላይ ሆኖ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ነው፡፡ማቴ.፳፩፥፩፡፡የእሳት ሠረገላ ገንዘቡ የሆነለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የተናቀች አህያን ለምን መረጠ?
፩ኛ.ትንቢት፣ምሳሌ እና ምስጢር ስላለው ነው፤
ሀ/ ትንቢት፦ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ
ሆይ እልል በይ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፡፡ትሁትም ሆኖ በአህያም፤ በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል”ዘካ.፱፥፱
፡፡
ለ/ ምሳሌ፦ ቀደም ሲል ወዳጆቹ ነቢያት ዘመኑ የጦርነት ከሆነ በፈረስ ተቀምጠው ዘገር ነጥቀው ጦር ሰብቀው፤
ዘመኑ ሰላም ከሆነ ደግሞ በአህያ ላይ ተቀምጠው መነሳንሳቸውን ይዘው
ለሕዝቡ ይታዩ ነበር፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዘመኑ የሰላምና የምሕረት ነው፤ የመጣሁትም ለሰው ልጆች ሰላምን ለመስጠት
ነው ሲል በአህያ ተቀምጦ ተጉዟል፡፡
ሐ/ ምስጢር፦ በአህያ የተቀመጠ ሰው ሸሽቶ አያመልጥም ሌላውን አካልም እያሳደደ አይዝም፡፡መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም ከፈለጉኝ አልታጣም፤ካልፈለጉኝ ግን አልገኝም ሲል ነው፡፡
፪ኛ. ለትህትና፦ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብሱ እሳት መጎናጸፊያው እሳት ሠረገላዎቹ
እሳታውያን ሲሆኑ በአህያ መቀመጡ ትህትናውን ያሳያል፡፡
፫ኛ.አምላክነቱን ለማስመስከር፦ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ሕፃናቱና ሽማግሌዎቹ የዘንባባ
ዝንጣፊ ይዘው፤ ስንኳን አንተ የተሸከመችህ አህያም መሬት መንካት አይገባትም በማለት ልብሳቸውን እያነጠፉ ሆሳዕና በአርያም እያሉ
ከማመስገናቸው በተጨማሪ የቢታንያ ድንጋዮች ሳይቀሩ አናመሰግንም ባሉ በአይሁድ ተገብተው በማመስገናቸው አምላክነቱን አስመስክሯል፡፡
፬ኛ.ቤተ መቅደሱን ለማጽዳት ማቴ.፳፩፥፳፫
መመስገኛውን ቤተ መቅደስ ለጸሎት መሆኑ ቀርቶ ሻጮችና ለዋጮች የንግድ ማዕከል አድርገውት ነበር፡፡አምላካችንም “ቤቴ
የጸሎት ቤት ተባላለች እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችት” በማለት በጅራፍ እየገረፈ አስወጣቸው፡፡ለቤተ መቅደሱ ሊደረጉ የማይገባቸውን
አላስፈላጊ ነገሮችን ስላስወገደ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ይባላል፡፡
ሰኞ፦ የበለሷ መረገምና መድረቅ ማቴ.፳፩፥፲፰ በዚህ ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ ተራበ፡፡ፍሬ
ያገኝ ዘንድም ቅጠሏ ወደ ለመለመ በለስ ሄደ፡፡ፍሬ ግን አላገኘባትም፡፡ስለዚህም ረገማትና ወዲያው ደረቀች፡፡በለስ የተባለች ኃጢአት
ናት፡፡ኃጢአትን በንስሀ የምትደርቅና /የምትሰረይ/ በፍዳ የማታስይዝ አደረጋት፡፡
በዚህ ዘመን አምላካችን ወደ እኛ መጥቶ ቢጠይቀን ከእኛ የሚያገኘው ምን ይሆን? የሃይማኖት፣የፍቅርና የሥነ ምግባር ፍሬ
እንድናፈራ ይፈልጋል፡፡ስለሆነም ፍሬያማዎች ለመሆን ቅርንጫፎቹ እኛ ከግንዱ ከክርስቶስ ሳንለይ በእርሱ ሕግና ትእዛዝ ጸንተን በቤቱ
መኖር ይገባናል፡፡“በእኔ ኑሩ በእኔ የሚኖር ብዙ ፍሬ ያፈራል….”በማለት የነገረን ለዚህ ነው፡፡ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ዕለት ጸሐፍትና
ፈሪሳውያን ስለ ክርስቶስ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲመክሩ ውለው ሳይስማሙ ተበትነዋል፡፡
ማክሰኞ፦አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥያቄ የተጠየቀበት
ነው፤
መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በዚህ ዕለት፤ ልባቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች የቀረበለት፤ “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?”
የሚል ጥያቄ ሲሆን፤ ጌታችንም “የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች ከሰማይን ወይስ ከሰው?” በማለት ጥያቄያቸውን በጥያቄ በመመለስ
ዝም አሰኝቷቸዋል፡፡በዚህ ዕለትም ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ጌታችንን እንዴት እንደሚያስወግዱት ሲመክሩ ውለው ቁርጥ ውሳኔ ላይ ሳይደርሱ
ተያይተዋል፡፡
ረቡዕ፦ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱ ውሳኔ የተወሰነበት ነው፤
ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታችንን ለመግደል ያልመከሩት ጊዜ ባይኖርም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በእሱ ላይ የነበራቸው ጥላቻ እያየለ
በመምጣቱ፤ ምን ብናደርገው ይሻለናል ዓለሙ ሁሉ ተከተለው” በማለት አጥብቀው ሲማከሩ ሰንብተዋል፡፡በዚህ ዕለት ግን “ሕዝብ ሁሉ
ከሚጠፋ አንድ ሰው ብንገድል ይሻለናል” /ዮሐ.፲፩፥፶/ በማለት በሊቀ ካህኑ በቀያፋ በቀረበው ሃሳብ ተስማምተው ይሙት በቃ ብለው
ፈረዱበት፡፡የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዕለተ ረቡዕን በየሳምንቱ እንድንጾም ያዘዘችበት ምስጢራዊ መሠረትም ይህ ነው፡፡
ሐሙስ፦ ዕለቱ ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፤ በዚህ ዕለት ጌታችን ያከናወናቸው ዓበይት ተግባራት የሚከተሉት
ናቸው፤
ሀ/ ትህትናው ያሳየበት ዕለት ነው ፤ የክብር ባለቤት ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ዝቅ ብሎ የተማሪዎቹን
እግር በማጠብ ፍጹም የሆነ ትህትናውን አሳይቷል፡፡ እሱ እንዳደረገው ያደርጉ ዘንድም አዘዟቸዋል፡፡“…ከእራትም ተነሳ ልብሱንም አኖረ
ማበሻ ጨርቅ ወሰደ.. የደቀ መዛሙርቱን እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ….፡፡እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር
ስሆን እግራችሁን ካጠብኩ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” በማለት አስተምሯል፡፡ ዮሐ፤፲፫፥፫-፲፮፡፡
ዛሬም በቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ሐሙስ አበው ካህናት የምእመናንን እግር የሚያጥቡበት ይህንን አብነት በማድረግ ነው፡
ለ/ የአዲስ ኪዳንን መሥዋዕት የመሠረተበት ዕለት ነው፡፡
እስራኤላውያን ከግብፅ ፈርኦን አገዛዝ ቀንበር በተላቀቁበት
ዕለት በጉን አርደው ፣ዳቦውን ጋግረው፣ ንፍሮውን ቀቅለው በፍጥነት ወጥተዋል፡፡ይህንን ዕለት ለማስታወስም በያመቱ የፋሲካ በዓል
ብለው ያከብሩት ነበር፡፡በዚህ ቀን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን በዓል ፍጻሜ በኋላ አንዱን ኅብስት አንስቶ አመስግኖ
/ቀድሶ/….“እንካችሁ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው፤ ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖ ሰጣቸው” እንዲህም አለ “ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ስለ ብዙዎች
ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” /ማቴ.፳፮፥፳፮ / በማለት አዲሱን ሥርዓተ መሥዋዕት አንድ ጊዜ ለሁልጊዜ
መሥርቶልናል፡፡ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም የአዲስ ኪዳን መሥዋዕት የተመሰረተበትን ይህን ዕለት ከሌሎቹ የሕማማት
ቀናት በተለየ ሁኔታ በቅዳሴ የምታከብረው ለዚህ ነው፡፡
ሐ/ የጸሎት ዕለት ነው፤ ይህ ዕለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ተለይቶ በጌቴሴማኒ
የአትክልት ስፍራ የጸለየበት ነው፡፡የፍጥረቱን ጸሎት የሚቀበል አምላክ
ሲሆን በዚህን ዕለት የጸለየውም እኛን ዕዳ ለመክፈልና፤ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ በማለት የጸሎትን ሕይወት በተግባር
ለማሳየት/ለአርአያነት/ ነው፡፡
ዓርብ ፤ዕለተ ስቅለት፤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሐሙስ ማታ አራት ሰዓት ሰዓት ጀምሮ እስከ
ዓርብ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ለአስራ ስምንት ሰዓታት ስለ እኛ
ብዙ መከራ ተቀብሏል፡፡ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
፩/ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኔ አትክልት ስፍራ፤ ወዙ እንደ ደም ነጠብጣብ እስኪወርድ ድረስ ስለ ሁላችን ያቀረበውን እጅግ
አድካሚ ጸሎት ከጨረሰ በኋላ፤ ሌባና ወንበዴ የሚይዙ ይመስል ሰይፍና ጐመድ፣ጦርና ጋሻ ይዘው በይሁዳ መሪነት በመጡ አይሁድና ጭፍሮቻቸው
እጅ በፈቃዱ ተያዘ፡፡ከዚያች ሌሊት ጀምሮ እስኪነጋ ድረስ ፤ሲዘብቱበት፣ሲሰድቡት፣ፊቱን በጨርቅ ሸፍነው በጥፊ ሲመቱት፣ከሊቀ ካህናቱ
ከቀያፋ ቤት ወደ ሐና ቤት ሲመላልሱትና ሲያንገላቱት አድረዋል፡፡
፪/ ሲነጋ /ማለዳ/፤ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች አስረው ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስ
አሳልፈው ሰጡት፡፡ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ጲላጦስ ጌታችንን የተለያየ ነገር ሲጠይቀውና ሲመረምረው አረፈደ፡፡ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፡፡ጲላጦስም
ጌታችን ምንም በደል እንደሌለበት ቢያረጋግጥም፤የከሳሾቹን ፈቃድ ለመፈጸም እንዲገርፉት አሳልፎ ሰጣቸው፡፡
፫/ በሦስት ሰዓት፤ አይሁድ ጌታችንን ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ ከገረፉት በኋላ፤የሚሰቀልበትን
ከባዱን መስቀል አሸክመው ሊሰቅሉት ሲወስዱት፤ ይህንን ሁሉ መከራ የምታጸኑብኝ በምን ዕዳዬ ነው ሳይል፤እኛን ከወደቅንበት ለማንሳት
እሱ እየወደቀና እየተነሳ በፍቅር ተከተላቸው፡፡
፬/ በስድስት ሰዓት፤ በፍጡር ህሊና ፈጽሞ ሊታሰብና ሊነገር የማይችለውን፣በቆሰለ ሰውነቱ መስቀል
ተሸክሞ የጀመረውን አሰቃቂ ጉዞ ጨርሶ ቀራንዮ ደረሰ፡፡ከዚያም “እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ”/መዝ.፳፩፥፲፮/ በማለት አስቀድሞ
ያናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ በአምስት ችንካሮች እጆንቹንና እግሮቹን ተቸንክሮ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ተሰቀለ፡፡
“መለኪያ ለሌለው ፍቅሩ ምስጋና ይገባዋል!!!”
፭/ በዘጠኝ ሰዓት፤ “ሁሉ ተፈፀመ!!!” ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በሥልጣኑ፣በፈቃዱ
ለየ፡፡
፮/ በአስራ አንድ ሰዓት፤ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡እስከ ትንሣኤው ድረስ ስለእኛ
ዝም አለ፡፡
በዚህ እለት የጌታችንን የቤዛነት ሥራ ለማስታወስ በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይፈጸማሉ፡፡ምእመናን
በወይራ ቅጠል ይጠበጠባሉ፤ለእኛ ስትል እንዲህ ተገረፍክ፤እኛም ስለ አንተ መከራ እንቀበላለን ስንል ነው፡፡
በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊትም
ሦስት መስቀሎች በተራ ይቆማሉ፡፡የመካከለኛው ቁመቱ ከፍ ያለ ሲሆን በግራና በቀኝ የሚቆሙት መስቀሎች ግን አነስ አነስ ያሉ ሆነው
የሁለቱ ወንበዴዎች መስቀል ምሳሌዎች ናቸው፡፡ የመካከለኛው ደግሞ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ምሳሌ ነው፡፡በዚህ እለት
አስከሬን ያለበት የሚመስል አጎበር ይዘጋጃል፡፡ክርስቶስ ሆይ ለሰው ልጅ ሕይወትን ለማዳን ስትል ሞትህ ተገነዝህም ለማለት ነው፡፡ካህናትም
አጎበሩን ይዘው እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያሉ መንበሩን ይዞራሉ፡፡በመጨረሻም
ሥርዓተ ኑዛዜ ተከናውኖ እግዚአብሔር ይፍታ ተብሎ ሕዝቡ ይሰናበታል፡፡
ቅዳሜ ስዑር፦ ይህች ዕለት የዓለም ቤዛ ክርስቶስ በመቃብር የዋለባት ናት፡፡ቅዳሜ ስዑር
መባሏም የማትጾመዋ ቀዳሚት ሰንበት ለአንድ ቀን በጾም ስለተሻረች ነው፡፡የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምና የክርስቶስ ደቀ
መዛሙርት ትንሣኤውን ሳናይ አንበላም ብለው ከዐርብ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ድረስ በጾም ሰንብተዋል፡፡ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መሠረት
በማድረግ ልጆቿ ምእመናን እንዲጾሙ ታስተምራለች፡፡ በተጨማሪ በዚህ
ዕለት ለምለም ቄጤማ በካህናት ተባርኮ ይሰጣል፡፡ይህም ምሳሌ አለው በዘመነ ኖህ ዓለምን የንፍር ውሃ አጥለቅልቆት በነበረ ጊዜ፤ለኖህ
የውሃውን መጉደል ለማብሰር ርግብ ለምለም ቄጤማ ይዛ ተመልሳለች፡፡ቤተ ክርስቲያንም በማይጠፋ እሳት በሲኦል መቀጣት ቀረ፤ እግዚአብሔር
ይቅር አለን፤ የሰላምና የምህረት ዘመንን መጣልን፤ ለማለት ለምእመናን ለምለም ቄጤማ ታድላለች፡፡
ትንሣኤ
ትንሣኤ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳውን የክርስቶስን መነሣት ለመግለጽ ብቻ የምንጠቀምበት ቃል ነው፡፡ትንሣኤ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ” ብሎ በተናገረው መሠረት ዐርብ ተቀብሮ እሑድ በሦስተኛው
ቀኑ ሞትን ድል አድርጎ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ተነስቷል፡፡ማቴ. ፳፰፥፮፡፡ይህ ዕለት እጅግ ታላቅ የሆነ የደሥታ ቀን ነው፡፡
ምክንያቱም፤
፩/ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት የክርስቲያኖችም
ትንሣኤ ስለሆነ ነው፡፡
“አሁን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኲር ሆኖ ከሙታን ተነስቷል፡፡ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሣኤ ሙታን በክርስቶስ ሆነ፡፡ሁሉ በአዳም
እንደሚሞቱ ሁሉ ደግሞ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ በማለት ሐዋርያው አስረግጦ ጽፎልናል፡፡፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፳
፪/ ሞት /ዲያቢሎስ/ ድል ስለተነሣ፦ ከክርስቶስ ትንሣኤ በፊት ዲያብሎስ የሰው
ልጆችን ነፍሳቸውን በሲኦል ሥጋቸውን በመቃብር ተቆራኝቶ ይገዛቸው ነበር፡፡መድኃኒታችን ከተነሳ በኋላ ግን ሞት /ዲያብሎስ/ ይህንን የማድረግ አቅሙ ደከመ፡፡የሰው
ልጅም “ ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል/መቃብር/ ሆይ ድል መንሣትህ የት አለ?”...በማለት ለመናገር በቃ፡፡ስለዚህ የትንሣኤን
በዓል ይህንንና የመሳሰሉትን ጥልቅ ምስጢራትን እያስታወስን በመንፈሳዊ
ሐሴት ልናከብረው ይገባናል፡፡
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር
No comments:
Post a Comment