Thursday, April 5, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አርባ

ከክፍል ሰላሳ ዘጠኝ የቀጠለ፦
ዐቢይ ጾምን በሰላምና በጤና አስፈጽሞ ለዚች ቀንና ሰዓት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች!
ከዚህ በመቀጠል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ስለ ሰው ልጆች ሲል ለሞት ተላልፎ የተሰጠባትን   ምሴተ ሐሙስን  በማስመልከት በወንድማችን በ"አክሊሉ ደበላ" የተዘጋጀች ድንቅ ግጥም አቅርበንላችኋል፡፡

"Aklilu Debela"
~~ለምንት ትዘብጠኒ?? (ዮሐ 18፥ 23)~~
በቀያፋ ግቢ... በሊቀ ካህኑ
ያለ ሸንጎ ሥርዓት ...ሸንጎ ሊወስኑ
ቀን ሊሆን ያለውን... ማታ በጨለማ
ጌታዬ ሲፀፋ ...ለጆሮ ተሰማ!!

ለዓለሙ ህመም ...የዓለም መድኃኒት
ሰው ፊቱ ማይቆመው ...ቆመ ቀያፋ ፊት
'ማይመረመረው ...ታየ ሲመረመር
ሊቀ ካህናቱ ጋ ....ሎሌው ቆሞ ነበር።

ይህ ሎሌ:-ጌታዬን በበግ በር ...በቤተ ሳይዳ
አግኝቶት ነበረ... ሲከፍልለት እዳ
የእዳውም ዋጋ ...የዘመናት ክምር
ዘጵሩጳጥቄ ....ቅልንብትራ መንደር
ቤተ-ዛታ ይሁዳ ...በምህረቱ ሰፈር
ምህረትን ሳያገኝ ....በአልጋው ላይ ነበር።

ለአልጋ ያበቃውን ...የኃጢአቱን ግዝፈት
ደዌውን ንዶለት ...ወዲያው ከመቅፅበት
ከጓደኛ አልጋው... ወዲያው እንደተነሳ
በጥያቄ ጊዜ ....ያዳነውን ረሳ።

አሁንም ይኸው አይቷል... መድኅኑን በዓይኑ
ያ ባለ ውለታው... አለለት ከጎኑ
የከፋ እንዳይደርሰው .. ያኔ የነገረው
አሁንም በክፉ ቀን..ከጎኑ ነበረው።

የሠለሉ እጆች... ጠንክረዋል ዛሬ
ያዳነውን ረስቶ....ሆኗል ጋሻ ጃግሬ
በራራለት ላይ ..ልቦናው መረረ
በመድኃዔለም ላይ... ጥፊ ሰነዘረ።
መልካም ላረገለት...ከፋ በወዳጁ
ገፀ መለኮትን.. መታበት በእጁ።

የተኛኸው መፃጉዕ! ...መፃጉዕ ሥምኦን!!
የደነደነ ልብ...መጠኑ ምን ይሆን?
ንሳእ አራተከ... የተባልክ ጎልማሳ
ምነው ዛሬ አልጋህን ..አልተሸከምህሳ!
ዝምተኛ እረኛ.... የማይናገር በግ
ሊሞትልህ የመጣው...አንተኑን ሲፈልግ

በአስፈሪ ሰዓት እንኳ...በጭንቁ ደቂቃ
ስለ ህመሙ መጠን...በአርምሞ ሲያበቃ
ለአንተ ጥፊ ግን...አልቻለም ዝምታ
የዳነው ወዳጁ...ያዳነውን ሲመታ!

ይልሃል ጌታችን:-
ሰው ሆይ ስለፍቅሬ ...ህይወትን በሰጠሁህ
ተወልደህ በሞትከው... ሞቼ በዋጀሁህ
የውለታዬን ልክ.. በአረም ለውጠህ
ክህደት ቀንድ አብቅለህ ...ማመንህን ሽጠህ
ወልድ ዋህድ ማለት .. ጠፍቶት አንደበትህ
ከባህርይ አባቴ...ከባህርይ ህይወቴ ..እኔ መለየትህ
በምንፍቅና ቃል... ጥፊህን አንስተህ

ለምን ትመታኛለህ?
የሠላምህ መሪ...የሠላሙ ጌታ
የህይወትህ ታዳጊ.. የምድርህ አለኝታ
ሆኜ በሰበክሁህ... ባሳየሁህ እረፍት
ከምንጭ በተቀዳው...እኔው ሥቴ ህይወት
ህይወትን ልታገኝ...ተገብቶህ ሳለ
የህይወትህ መቅበዝበዝ... ተራራ እያከለ
ለፅድቁ ጠርቼህ..ለሞት የምትፈጥን
ልትከው'ን የምትሮጥ...የዓለሙን ውጥን
የኃጢአትን ስንዝር...በኔ ላይ አንስተህ

ግን ለምን ትመታኛለህ?
አህዛባዊ ህይወት...አረማዊ ኑሮ
ምድራዊ ዓላማ...ዓለማዊ ሮሮ
ሰው ሆይ በተግባርህ..በ'ሰው አልባው' ህይወት
በርኩሰት በክፋት...ርህራሄ አልባነት
በምድር ሁካታ...በዓለሙ ጫጫታ
ውለታዬን ትተህ ...የደሜን ጠብታ
ከመፃጉዕ ብሰህ.. በክፋት ተሽለህ
ልብህን በኔ ላይ... ልትወጋኝ ስለህ
'የከፋ እንዳይደርስህ'ን... እንብበኸው ሳለህ

ግን ለምን ትመታኛለህ?
ይልሃል መድኃዓለም
የባሰ እንዳይደርስህ...በደልህን አትድገም!
(አክሊሉ ደበላ 27/06/2010ዓ.ም)
ለወንድማችን ለአክሊሉ ደበላ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር ይህቺን ሳምንት በሰላም አስፈጽሞ የትንሣኤውን ብርሃን እንዲያሳየን ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
አሜን፡፡


No comments:

Post a Comment