Tuesday, May 22, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አርባ አንድ

ከክፍል አርባ የቀጠለ፦

ለዚች ዕለትና ለዚች ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

       የተከበራችሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ ልጆች!የመጨረሻው ዘመን የወለዳቸው የተለያዩ መናፍቃን ከውስጥም ከውጭም ሆነው  የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እምነት፣ ሥርዓትና እንዲሁም ትውፊት ሳይቀር የሚያፋለሱ የስህተት ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያናችን ስም እያሰራጩና ብዙዎችንም እያሳሳቱ መሆኑን ወቅታዊውን የቤ/ክ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተል ሁሉ ችግሩን በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡እኛም ይህችን "ወልድ ዋሕድ" የተሰኘች የጡመራ መድረክ የጀመርንበት ዋናው ምክንያት፤እነዚህን የጨለማ ሥራዎቻቸውን /የምንፍቅና ትምህርታቸውን/ ወደ ብርሃን በማምጣት ማለትም ስህተታቸውን በመግለጥና አቅማችንና እውቀታችን በሚፈቅድልን መጠን  መልስ በመስጠት፤ ትውልዱ እራሱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ከስህተቱ ትምህርት እንዲጠብቅ የሚያስችለውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡
       እነዚህ የስህተት ትምህርቶች በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በምሥጢረ ሥጋዌ (ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ሰውን ያዳነበት ምሥጢር) ትምህርት ላይ ነው፡፡ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ባስተማረው ትምህርት (ማቴ.24 በሙሉ ይመልከቱ)፤በመጨረሻው ዘመን ብዙ ሐሰተኞች አስተማሪዎች በስሙ እንደሚመጡና ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፤እኛም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሁሉ ከስህተት ትምህርታቸው እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡በመቀጠልም ይህንን የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ "ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ" ብሎ እሱ በመረጣቸው በሐዋርያትና በእነሱ እግር በተተኩ መምህራንም በየዘመኑ ለተነሳው ትውልድ ትምህርቱና ማስጠንቀቂያው ሲነገር የነበረ ወደፊትም እስከ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ይሁን እንጂ ስንቶቻችን ይህንን ችግር ተረድተናል? ምን ያህልስ እራሳችንንም ሆነ ሌላውን ከስህተት ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል? የሚለውን ጥያቄ እራሳችንን እየጠየቅን ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች መሆን ይገባናል፡፡
       ወደ ዋናው ነገር እንመለስና፤ እነዚህን የስህተት ትምህርቶች ከሚያስተላልፉት የእምነት ድርጅቶች አንዱ እራሱን "የእውነት ቃል አገልግሎት"ብሎ የሚጠራው የመናፍቃን ድርጅት ሲሆን፤ከመጽሐፍቻቸው አንዱ በሆነው ‹‹የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» በተባለው መጽሐፋቸው በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ የሚሰጡትን የክህደት ትምህርት በዚችው ጡመራ መድረክ ከክፍል ሦስት እስከ ክፍል አምስት ከብዙው በጥቂቱ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ይህ ድርጅት ቀድሞ ከእኛ ዘንድ በነበሩ ነገር ግን ከእኛ ወገን ስላልነበሩ በራሳቸው ፈቃድ በወጡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት አራማጆች የተመሠረተ ሲሆን ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘ ነው፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን፤

       “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” በማለት ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  በሰፊው አስተምሮናል፡፡በዚሁ መሠረት ዝግጅቱ የእኛ ባይሆንም፤ትክክለኛውን የተዋሕዶ ትምህርት የሚያስተምሩትን የሌሎች መምህራን ትምህርቶች ስናካፍላችሁ እንደነበር፤ዛሬም "ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልዳል" (ሎቱ ስብሐት) እያሉ ለሚዘባርቁ የተለያዩ የውስጥም ሆነ የውጭ መናፍቃን ተገቢውን ምላሽ የሰጡበትንና "ፀረ-በጋሻው ደሳለኝ ፀረ-ተሀድሶ!" በተባለው የፌስ ቡክ ገጽ ለንባብ የበቃውን የመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራውን ትምህርት እንዳለ አቅርበንላችሁዋል፡፡

መልካም ንባብ ከማስተዋል ጋር!


" መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው "ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልዳል" (ሎቱ ስብሐት) ላለው ቅብጥብጡ ሀራጥቃ ወልደ ትንሳኤ የሰጡት ድንቅ ወቅታዊ ኦርቶዳክሳዊ ምላሽ"
 “ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።” ሮሜ፡፰፥፴፬።(ክፍል-፩)
       የዚህን ኃይለ ቃለ ትርጉምና ዝርዝር ከመመልከታችን በፊት፡-በአማርኛ የተቀመጠው ንባብ ትክክል ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን እንመለከታለን። ምክንያቱም፡-መጽሐፍ ቅዱስ ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ ቋንቋ በሚተረጐምበት ጊዜ፥አንድም በስሕተት፥አንድም በድፍረት ብዙ የተበላሸ ንባብ ስላለው ነው። የንባቡ መበላሸት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ትርጓሜውን ያዛባዋል።ለምሳሌ፡-በግዕዙ፡-“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤” የሚለው ንባብ፡-“መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው ።”ተብሎ፥በሴት አንቀጽ መተርጐም ሲገባው፥“መሠረቶቹ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤” ተብሎ በወንድ አንቀጽ ተተርጉሞአል። መዝ፡፹፮፥ ፩። እንዲህ ዓይነቱ ስሕተት፡-መሠረታዊ ስሕተት ነው። ገጸ ንባቡ፡-በሴት አንቀጽ እንጂ በወንድ አንቀጽ ላለመናገሩ ምስክር የሚሆነን፥በዚያው ምዕራፍ በቍጥር ሦስት ላይ የተቀመጠው ንባብ ነው።“ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር፤የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ፥ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነው፤“ይላል። በብዙ ሰው እጅ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ ስትመለከቱ ደግሞ፡-“የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ፥በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል፤”ይላል።መዝ፡፹፮፥፫።
        ስለዚህ፡-ጥንተ ነገሩን ለማወቅ፥ለአማርኛ ቋንቋ ጥንት ከሆነው ከግዕዙ ንባብ ጋር ልናመሳክር ይገባል። ካመሳከርንም በኋላ ግዕዙ ዳኛ በመሆኑ የግዕዙን እንቀበላለን። በመግቢያው እንደተመለከትነው፡-“ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤” የሚለውን ንባብ በቅድሚያ የምናመሳክረው ከግዕዙ ጋር ነው። “ወሀሎ ይነብር በየማነ እግዚአብሔር፥ ወይትዋቀሥ በእንቲአነ፤” ይላል። ይኸንን ንባብ የአንድምታው ትርጓሜ፡-“በአብ ዕሪና(በአብ ቀኝ፥ከአብ ተካክሎ) ይኖራል፤ስለ እኛ ይከራከራል፥መከራከርስ የለም፤ስለ እኛ በዕለተ ዓርብ ባደረገው ተልእኮ ዋጋችንን የምናገኝ ስለሆነ ነው፤” ብሎ ይፈታዋል። በዚህም፡-“መከራከረስ የለም፥ፈርዶ ዋጋችንን ይሰጠናል እንጂ፤”በማለት አትሞታል። ግዕዙ፡-“ተዋቀሠ” የሚለውን፡- “ተሟገተ፥ተከራከረ፤” ብሎ በቁሙ ይተረጉመዋል።“መስተዋቅስ”ብሎ ደግሞ፡-“የሚያዋቅሥ፥የሚያከራክር፥ዳኛ፥የሚዋቀሥ፥ተዋቃሽ፥ተከራካሪ ፤”ብሎ ይፈታዋል። በዚህ አፈታት ውስጥ ፥“ይከራከራል፥ይሟገታል፤”ሲል፡-ፍጡር ከፍጡር ጋር እንደሚከራከረውና እንደሚሟገተው ዓይነት ክርክርና ሙግት ነው ወይስ አይደለም?” የሚል ጥያቄ ይወጣል። ለምሳሌ፡-“የመላእክት አለቃ ሚካኤል እንኳን ስለ ሙሴ ሥጋ ከሰይጣን ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብን ቃል ሊናገር አልደፈረም፥እግዚአብሔር ይገሥጽህ አለው እንጂ፤”ይላል። ይሁ፡፩፥፱። ምክንያቱም ፡-ፍጡር ከፍጡር ጋር ቢከራከር ዳኛው እግዚአብሔር ስለሆነ ነው።                                          
        እንግዲህ፡-“ይከራከርልናል፤” የሚለውን በዚህ መንገድ የሚያዩት ከሆነ፥በቅድሚያ፡-“ኢየሱስ የሚከራከረው በማን ዳኝነት ነው? ከእርሱ ጋርስ የሚከራከረው ማነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ፈጣሪ ነው፤“በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤ . . . ሁሉም በእርሱ ሆነ፥ከሆነውም ሁሉ ያለ እርሱ የሆነ ምንም የለም፤ . . . ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፥የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንደሆነ በእምነት እናውቃ ለን፤”ይላል። መዝ ፴፪፥፮፣ ዮሐ፡፩፥፫፣ዕብ፡፩፥፫። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፤“ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። . . . ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤(ነፍስንና ሥጋን ተዋህዶ ሰው ሆነ)፤ . . . እግዚአብሔር በገዛ ደሙ ዋጀን፤”ይላል። ዮሐ፡፩፥፫፤፲፬፣የሐዋ፡፳፥፳፰።ኢየሱስ የባሕርይ አምላክ ነው፤”ጌታዬ አምላኬም፤ . . . በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንኖራለን፥ እርሱም እውነተኛ አምላክና የዘለዓለም ሕይወት ነው፤” ይላል። ዮሐ፡፳፥፳፰፣፩ኛ፡ዮሐ ፡፭፥፳። ምናልባት ጌታን ክርክር የሚገጥሙት አጋንንት ናቸው፥ይባል ይሆናል፥ይህ ደግሞ ፈጽሞ የማይሞከር ነው። ምክንያቱም፡-አጋንንት ራሳቸው፡-“የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ከአንተ ጋር ምን አለን?(አንተን የምንቃ ወምበት፥ከአንተ ጋር የምንከራከርበት ምን ኃይል አለን)? ጊዜው ሳይደርስ ልታሠቃየን መጣህን? (ዕለተ ዓርብ አንድም ዕለተ ምጽአት ሳይደርስ ልትፈርድብን ነውን)? . . . ካወጣኸንስ በእሪያዎቹ መንጋ ላይ እንድናድር ወደዚያ ስደደን።” እያሉ ሲጮኹና ሲለምኑ ነው የተገኙት እንጂ ሲከራከሩ አልታዩም። ማቴ፡፰፥ ፳፱።ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆ ብም፡-“እንዲህስ አጋንንት ያምናሉ፥ይንቀጠቀጡማል፤”ብሎአል። ያዕ፡፪፥፲፬።=በሌላ በኵል ደግሞ፡-ኢየሱስ ክርስቶስ የሚከራከረው በአብ ዳኝነት ነው፥ይባል ይሆናል፤ይኸንን አባባል በሥጋዊ ፍርድ ቤት አሠራር ምሳሌነት ብንመለከተው፡-ዳኛ የበላይ፥ጠበቃ የበታች ነው፥በመሆኑም ጠበቃ ይከራከራል እንጂ መፍረድ አይችልም። በዚህ ምሳሌነት ምሥጢረ ሥላሴን ስንመለከት፡-በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት አሠራር የለም። ቅድስት ሥላሴ በሥልጣን መበላለጥ፥በዘመን መቀዳደም የለባቸውም፥በመሆኑም እንደ ፍጡር የበላይና የበታች የሚባል የሥልጣን ተዋረድ አለ ብሎ መናገር ክህደት ነው። እንዲህ እንዳይሆን ነው፥ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-“እኔና አብ አንድ ነን። . . . እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራ ችሁ ይህ ቃልም ከራሴ የተናገርሁት አይደለም፥በእኔ ያለ አብ እርሱ ይህን ሥራ ይሠራዋል እንጂ።እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑ፥ያለዚያም ስለ ሥራዬ እመኑኝ፤(ይኸንን ሥራ ፈጣሪ ቢሠራው እንጂ ፍጡር ሊሠራው አይችልም ብላችሁ በፈጣሪነቴ እመኑ)፤” በማለት አስቀድሞ የተናገረው። ዮሐ፡፲፥፴፤፲፬፥ ፲።                                                                                                     
       ቅዱሳት መጻሕፍት በጠቅላላ የሚመሰክሩት የኢየሱስ ክርስቶስን ፈራጅነት ነው። እርሱ ራሱ፡-በጐቹን(ጻድቃንን) በቀኙ፥ፍየሎቹን(ኃጥአንን) ግን በግራው አቁሞ እንደሚፈርድ ነገሮናል። “ የሰው ልጅ(በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) በጌትነቱ፡-ቅዱሳን መላእክትን ሁሉ አስከትሎ በሚመጣበት ጊዜ፥ያን ጊዜ በጌትነቱ ዙፋን (በፍርድ ወንበር) ይቀመጣል።አሕዛብ ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፥እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ እየራሳቸው ይለያቸዋል፤(ለጻ ድቃን ይፈርድላቸዋል ፥በኃጥአን ግን ይፈርዳባቸዋል)፤”ይላል።ማቴ፡፳፭፥፴፩።
        በተጨማሪም፡-“ የሰው ልጅ(በተዋህዶ ሰው የሆነ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ) መላእክቱን አስከትሎ በአባቱ ክብር (ከአብ ጋር አንድ በሆነ አምላካዊ ክብር) ይመጣ ዘንድ አለውና፥ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ይሰጠዋል፤(ይፈርዳል)፤” የሚል አለ። ማቴ፡፲፮፥፳፯።ጌታችን፡-ስለ ትንሣኤ ሙታን በተናገረበትም አንቀጽ ላይ፥“ፍርድን ለወልድ ሰጠው፤ በመቃብር ያሉት ሁሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚህ አታድንቁ። መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፥ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ። እኔ ከራሴ አንዳች አደርግ ዘንድ አልችልም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ፤ፍርዴም እውነት ነው፤”ብሎአል። ዮሐ፡፭፥፳፪፣፳፰ እርሱ ጠርቶ የመረጣቸው ቅዱሳን ሐዋርያትም ትምህርታቸው በዚህ እውነት ላይ የተመሠረተ እንደነበረ፥ሕያው ትምህርታቸው ምስክር ነው። ”መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥እያንዳንዱ በሥጋው ያደረገውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና፤” ይላል።፪ኛ፡ቆሮ፡፭፥፲።
        ቅዱስ ጴጥሮስም፡-“ከሙታን ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። በእግዚአብሔር ዘንድ በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ(ከእግዚአብሔር አብና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር በአንድነት የመፍረድ ሥልጣን ያለው) እርሱ እንደሆነ ለሕዝብ እናስተምር ዘንድ አዘዘን። ለሚያምንበትም ሁሉ ኃጢአታቸው በስሙ እንደሚሰረይላቸው ነቢያቱ ሁሉ ምስክሮቹ ናቸው።”ብሎአል። የሐዋ፡፲፥፵፩። በመሆኑም የኛ ጌታ፡-ኃጢአታችንን በስሙ አስተሥርዮ የሚፈርድልን አምላክ እንጂ የሚማልድ አምላክ አይደለም። ጌታ በአብ ቀኝ መቀመጡ፡-የሚያመለክተው፥ዕሩይ ምስለ አብ(ከአብ ጋር የተካከለ) መሆኑን ነው። ቅዱስ እስጢፋኖስ፡-ኢየሱስ ክርስቶስን በአብ ቀኝ ሆኖ ባየው ጊዜ፡-“ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ነፍሴን ተቀበል፤….ጌታ ሆይ፥ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው፤”እያለ ለኃጢአተኞች ማለደ እንጂ፥“አብ ነፍሴን እንዲቀበላት አማልደኝ፥የእነርሱንም (የገዳዮቼንም) ኃጢአት አንዳይቆጥርባቸው አማልዳቸው፤” አላለም።ዮሐ፡፯፥፶፱። አንድ ቃል የሚተረጐመው እንደ ባለቤቱ ማንነት ነው፥ለፍጡር የተቀጸለ ቃል ከሆነ ከዚያ አንጻር ይተረጐማል፤ ለፈጣሪ ከተቀጸለ ደግሞ ከፈጣሪ ማንነት አንጻር ምሥጢሩ ተብራርቶ ይተረጐማል እንጂ እንደወረደ ወይም በቁሙ አይተረጐምም።ምክንያቱም፡-ለፈጣሪም ለፍጡርም የምንጠቀምበት ቋንቋ አንድ ዓይነት በመሆኑ ከእምነት አንጻር ችግር ውስጥ እንዳንወድቅ ነው።
       ለምሳሌ፡- እግዚአብሔር ሙሴን፡-“እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፥ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል፤” ብሎታል። ዘጸ፡፯፥፩። እርሱ ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን በጠቅላላ “አማልክት፤” ተብለዋል ።መዝ፡፹፩፥፮። ቅዱሳን “አማልክት” ስለ መባላቸው ኢየሱስ ክርስቶስም በአዲስ ኪዳን ትምህርቱ አጽንቶታል። ዮሐ፡ ፲፥፴፬።ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፥እግዚአብሔር፡-“የአማልክት አምላክ፤”ተብሎአል።መዝ፡ ፵፱፥፩።እንግዲህ፡-ቋንቋው፡-ለፈጣሪም ለፍጡርም የተጠቀመው በተመሳሳይ ቃል “አምላክ፤” የሚለውን በመሆኑ እንደ ማንነታቸው ተተርጉሞ መነገር አለበት።በዚህም መሠረት፡-ለፈጣሪ ሲሆን፥ “የባሕርይ አምላክ(ገዥ)”፥ለፍጡር ሲሆን ደግሞ “የጸጋ አምላክ(ገዥ)” ተብሎ ይነገራል። ጥንቱንም ቢሆን የሰው ልጅ፥ አላውቅበት ብሎ እንጂ፡-በእግዚአብሔር አርአያና መልክ መፈጠሩ፥ከሰማይ በታች ያለውን ሁሉ እንዲገዛ ነበር። ዘፍ፡፩፥፳፮።                                
        ቅዱሳን አባቶቻችን፡-“ይትዋቀሥ፥ይከራከራል፤” የሚለውን ለፈጣሪም ለፍጡርም እኵል ተርጉመው አላለፉም።ለፍጡር ሲሆን፡-“ይትዋቀሥ፥ይከራከራል፤” ብለው ሲተረጉሙ፥ለፈጣሪ ሲሆን ግን “ይትዋቀሥ፥ይፈርዳል፤” ብለው ተርጉመዋል። በ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት መልካም ፈቃድ፥በናሽናል ባይብል ፕሬስ አማካኝነት፥አሜሪካን ሀገር ፊላዳልፊያ በታተመው የአማርኛ አዲስ ኪዳን ላይ፡-“ክርስቶስ ኢየሱስ ከሙታንም ተነሣ፥ በአብ ቀኝ ተቀምጦአል ስለኛ ይፈርዳል፤” በማለት በትክክል ተርጉሞታል።ሮሜ፡ ፰፥፴፬። -(Manifactured in the united states of America by national Bible press, philadalfia) የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በ፪ሺ  ዓ.ም. ባሳተመው መጽሐፍ ቅዱስ ላይም “የሚፈርድስ ማነው? የሞተው፥ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ደግሞ ስለእኛ የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፤”ይላል።  
       በመጨረሻም ልናስተውለው የሚገባን ነገር ቢኖር ሐዋርያው፡-የተጠቀመበትን የአጻጻፍ ስልት ነው። የጽሑፉ አቀማመጥ በጥያቄና በመልስ በመሆኑ፥ጥያቄውና መልሱ ተገናዝቧል ወይስ አልተገናዘበም? ማለት ያስፈልጋል። “እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ(በተዋህዶ ሰው ከሆነ) ማን ይቃወመል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን (ቅዱሳንን) ማን ይከሳቸዋል? (በአጸደ ሥጋ ሲያማልዱ እንደነበረው በአጸደ ነፍስ አያማልዱም፥የሚላቸው ማነው)? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥የሚኰንንስ(የሚፈርደው) ማነው? የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤”ይላል። ለመሆኑ እንዲህ ተብሎ የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ሊቀበሉ ቻሉ? ምክንያቱም፡-ጥያቄውና መልሱ ፈጽሞ አልተገናኘም። ጥያቄው የሚለው፡
“የሚኰንን(የሚፈርድ)ማነው?”ሲሆን
መልሱ ደግሞ፡- “የሚማልደው፤”ይላል።
 ከጥያቄው አንጻር ግን፡-“የሚፈርደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤”ተብሎ መቀመጥ እንደነበረበት በጐ ኅሊና ላለው ሰው ሁሉ ግልጥ ነው። በሮሜ ፰ ላይ ያለው ችግር ከላይ የተገለጠው ብቻ አይደለም፥መንፈስ ቅዱስን በተመለከተም የሚለው አለ።“ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና፤”ይላል። ሮሜ፡፰፥ ፳፯። በመሠረቱ፡-ለመንፈስ ቅዱስ “ይቃትታል፤” አይባልም፥ምክንያቱም፡-መቃተት (መድከም፥መዛል፥መቸገር) ለሰው እንጂ ለፈጣሪ አይደለም። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ፡-አንድ እግዚአብሔር፥አንድ አምላክ፥አንድ ፈጣሪ ብሎ ለሚያምን ክርስቲያን፡-ይኸንን ንባብ ለመቀበል እጅግ አስቸጋሪ ነው። በ፲፱፻፴፰ ዓ.ም. እና በ፪ሺ ዓ.ም. የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ግን የቃሉን ምሥጢር ጠብቆ ፡-“ወባሕቱ መንፈስ ለሊሁ ይትዋቀስ ለነ በእንተ ሕማምነ ወምንዳቤነ፤ወውእቱ የሐትቶ ለልብነ፥ወየአምር ዘይሔሊ መንፈስ፥ወይትዋቀስ በኀበ እግዚአብሔር በእንተ ቅዱሳን። ነገር ግን ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፥ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ (ከእግዚአብሔር አብ እና ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ በሆነ ሥልጣን) ይፈርዳል፤”ይላል። መጽሐፍ ቅዱስ፡-እግዚአብሔር አብንም “ይከራከራል፤” በሚል ቃል የገለጸበት ክፍል አለ። ተናጋሪው እግዚአብሔር ነው።“ንዑ ንትዋቀሥ ይቤ እግዚአብሔር፤እመኒ ኮነ ኃጢአትክሙ ከመኳኳ ፥አፀዓድዎ ከመበረድ፤ ወእመኒ ቄሐ ከመለይ አነጽሖ ከመ ጸምር፤ኑና እንዋቀሥ ይላል እግዚአብሔር ፤ኃጢአታችሁ እንደ አላላ ቢሆን፥እንደ በረዶ አነጻዋለሁ፤እንደ ደምም ቢቀላ እንደ ባዘቶ አጠራዋለሁ፤” ይላል ። ኢሳ፡፩፥፲፰።
       ይህም፡-እግዚአብሔር አብ፡-ኃጢአትን የሚያስተሠርይ፥በደልን የሚደመስስ፥የሚፈርድም አምላክ መሆኑን ያመለክታል እንጂ፥አብንም ጠበቃ፣አማላጅ አያሰኘውም። ወገኖቼ፡-በንባብ ብቻ ከተሄደ እኮ አብም፥ወልድም ፥መንፈስ ቅዱስም “አማላጆች” መሆናቸው ነው። ታዲያ የሚማለደው ማነው? =“አባ” ቢቸግራቸው እንደ ወላጆቻቸው እንደ መናፍቃን “በአምላክነቱ ይፈርዳል፥በሰውነቱ ደግሞ ያማልዳል፤”ብለው እርፍ አሉ። ለመሆኑ ነገረ ድኅነትን ምን ብለው ሊያስተምሩ ነው? ምክንያቱም አምላካችን ያዳነን በመስቀል ላይ ሥጋውን ቆርሶ፥ደሙንም አፍስሶ ስለ እኛ ሞቶ ነው። ሞቶም አልቀረም፥በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቶአል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡-ያንን በመስቀል ላይ የፈሰሰ የክርስቶስን ደም፡-“የእግዚአብሔር ደም” ብሎታል።የሐዋ፡፳፥ ፳፰።እንደ እርስዎ አባባል ክርስቶስ ለሁለት የሚከፈል ከሆነ፥ሐዋርያው ማለት የነበረበት “የእግዚአብሔር ደም” ሳይሆን “የሥጋ ደም” ነው። የሥጋ ብቻ ደም ከሆነ ደግሞ በፍጡር ደም ዓለም እንዴት ሊድን ይችላል? በፍጡር ደም ዓለም የሚድን ከሆነስ የአምላክ መውረድ፥መወለድ ለምን አስፈለገ? በአንድ ቅዱስ ሰው ደም ዓለምን አያድነውም ነበር?
       እንዲህስ ከሆነ በየት በኵል አልፈን ነው አምላካችን ተራበልን፥ተጠማልን፥ተገረፈልን፥ተሰቀለልን፥ሞተልን የምንለው? ምክንያቱም እንደ እርስዎ አባባል የተራበልን፥የተጠማልን፥የተገረፈልን፥የተሰቀለልን፥የሞተልን ሥጋ ነውና።ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ፥በሰውነቱ እየተባለ ለሁለት የሚከፈል ከሆነ፡- በተዘጋ ቤት በገባ ጊዜ፥በአምላክነቱ በሩ እንደተዘጋ ከገባ በኋላ በሰውነቱ ደግሞ ለምን በሩን አስከፍቶ አልገባም? “ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ በመካከ ላቸውም ቆሞ፡-ሰላም ለእናንተ ይሁን፤”አላቸው፤”ይላል።ዮሐ፡፳፥፲፱፣፳፮።ደቀ መዛሙርቱ በሮቹ ባለመከፈታቸው መንፈስ የሚያዩ መስሎአቸው በደነገጡ ጊዜ፡-“ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደሆንሁ እጆቼን እና እግሮቼን እዩ፤በእኔ እንደምታዩት መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና፥እኔን ዳስሳችሁ እዩ፤”ብሎአቸ ዋል።ሉቃ፡፳፬፥፴፮
       ስለሆነም በዕደ ሃይማኖት ዳስሶ፥ከተዋህዶ በኋላ ሁለትነት የሌለበት አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ማመን ይገባል።“አባ” እንደሚሉት ከሆነ፥ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ ጊዜ፡- በአምላክነቱ መቃብሩ እንደታተመ ከተነሣ በኋላ በሰውነቱ ለምን መቃብር አስከፍቶ አልወጣም? ወይም ሥጋ ለምን በመቃብር  አልቀረም? የመናፍቃን መስሚያቸው ተደፍኖ እንጂ፡-ቅዱስ ቄርሎስ “እንቲአሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ፥ወእንቲአሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል፤ በተዋህዶ፡-የቃል ገንዘብ ሁሉ ለሥጋ፥የሥጋም ገንዘብ ለቃል ሆነ፤”ብሎአል። በመሆኑም አምላካችን፡-መራብ፥መጠማት፥መድከም፥መሞት የሚስማማውን የሥጋን ባህርይ በመዋሀዱ፡-ተራበለን፥ ተጠማልን፥ በጸዊረ መስቀል ደከመልን፥ ሞተልን እንላለን። በቅዱስ ዲዮስቆሮስ ቅዳሴ ቍጥር ፴፭ ላይ፡-“ሞተ ዘኢይመውት፥ሞተ ከመ ይሥዓሮ ለሞት፥ሞተ ከመ ያሕይዎሙ ለሞት፤የማይሞት እርሱ ሞተ፥(ሞት የሚስማማውን የሥጋን ባህርይ በመዋሀዱ ሞተ)፥ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞተ፥ሙታንን ያድናቸው ዘንድ ሞተ፤ ”የሚል አለ።ምናልባት፡-“በሥጋ ሞተ፥ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፤”የሚለው ይጠቀስ ይሆናል። ፩ኛ፡ጴጥ፡ ፫፥፲፰። ነገር ግን ትርጉሙም ምሥጢሩም የተለያየ በመሆኑ ይኸንን ከዚያ ጋር ማገናኘት አይገባም። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፡-“በሥጋ ሞተ፤” ያለው የነፍሱን እና የሥጋውን መለያየት እንጂ የመለኮትን ከሥጋ መለየት አይደለም። ምክንያቱም፡-“ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ፤”ይላልና።ዮሐ፡፲፱፥ ፴። ነፍስና ሥጋ በሞተ መስቀል በተለያዩ ጊዜ፥መለኮት ከሥጋም ከነፍስም ጋር በተዋህዶ ነበረ። ቅዱስ ጴጥሮስ መንፈስ ያለው ረቂቅ መለኮትን ነው። ዋናው መልእክቱ ሥጋን፡-ነፍስ ተለይታው ሙት ብታሰኘውም ሕያው መለኮት አልተለየውም ለማለት ነው። ከሥጋ የተለየች ነፍስንም መለኮት አልተለያትም። ይህም ይታወቅ ዘንድ፡-”በእርሱም ደግሞ(ነፍስን እንደ ተዋሀደ) ሄዶ በወኅኒ(በሲኦል) ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤”ይላል።መለኮት ወደ መቃብር ከወረደ ሥጋ ጋርና ወደ ሲኦል ከወረደች ነፍስ ጋር በተዋህዶ ነበረ።
        ለመምህራችን ለአባታችን ለመካሪያችን በየጊዜው መናፍቃን በጠየቁን ሰዓት በድንቅ ኦርቶዶክሳዊ ምላሽ አንገታቸውን እያስደፉ የኛን አንገት ቀና ለሚያደርጉ ለመላእከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በእውነት የሚያሳርፈውን የህይወትን ቃል አሰምተውናልና ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን መጨረሻቸውን ያሳምርልን በረከታቸው ይድረሰን እንዲሁ በየጊዜው እንዲመልሱልን እድሜ ከጤና ጋር አብዝቶ አብዝቶ ይስጥልን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን-ይቆየን።

©ፀረ-በጋሻው ደሳለኝ ፀረ-ተሀድሶ!

ማጠቃለያ ከዝግጅት ክፍሉ
       ይህ ከላይ የተመለከትነው ትምህርት ለመናፍቃኑ ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጀ ይሁን እንጂ ከዋናው ትምህርት በተጨማሪ ሁላችንም ልንገነዘበው የሚገባን እጅግ በጣም ጠቃሚ መልእክቶችንም እናገኝበታለን፡፡እነዚህም
  • የቅዱሳት መጸሕፍትን ጥሬ ንባብ ብቻ እየተከተሉ መሄድ ወደ ትልቅ ስህተት የሚወስድ መሆኑን፤
  • መጽሐፍ ቅዱስ በተለያየ ጊዜና በተለያየ ቋንቋ የተተረጎመ በመሆኑ በትርጓሜው ሥራ ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ስህተቶች እንደተፈጠሩና እንደሚፈጠሩ፤
  • በእኛ ቤ/ክ የሚያሻማ (የሚያከራክር) ንባብ ሲያጋጥም የሚዳኙት ጥንታውያኑ የግዕዝ መጻሕፍት መሆናቸውን፤
  • አንድን ቃል ወይንም ሐረግን ብቻ ይዞ የራስን ትርጉም ከመስጠት ይልቅ የጽሁፉን አጠቃላይ ይዘትና፤ ማን? ለማን? ለምን? የት? መቼ?እንዴት? ወዘተ፡፡ተጻፈ ብሎ መጠየቅና ከእውነተኞቹ መምህራን መማር እንደሚገባ፤
  • ይህንን መልስ ለመስጠት መነሻ የሆኑት "አባ"መሆናቸው፤(መልስ የተሰጠው ለተሳሳቱት "አባ" እንደውም "ጳጳስ" መሆኑ) ቅድስት ተዋሕዶ ቤ/ክ ያለችበትን አስቸጋሪ ፈተና ፍንትው አድርጎ ማሳየቱ ነው፡፡

የተከበራችሁ የተዋሕዶ ልጆች!

       ዛሬ ሃይማኖት ለዋጮች እታች ካለው ምእመን ጀምሮ እስከ ላይኛው የቤ/ክ አካል ድረስ ተስግስገውና ሰንሰለት አበጅተው (በዘመኑ ቋንቋ ኔትወርክ) ወሳኝ ወሳኝ የሆኑትን ሥፍራዎች በመያዝ የምንፍቅናውን ትምህርት እውነተኛ ትምህርት አስመስለው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንዲሰፋፋ ቀን ከሌሊት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ስለዚህ እንደ ቤ/ክ ልጅነታችን እራሳችንንም ሆነ ሌላውን ከስህተቱ መጠበቅ የምንችለው ትክክለኛውን ትምህርት ስንረዳ ስለሆነ፤ ወደ እውነተኞቹ መምህራን እየቀረብን በመማርና የእውነት ምስክር በመሆን ከአባቶቻችን የተረከብናትን ርትዕት ሃይማኖት ሳትበረዝና ሳትከለስ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ መንፈሳዊ ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በፍርድ ቀንም "ኑ እናንተ የአባቴ ቡሩካን" የምንባለው በስም ብቻ ክርስቲያን ተብለን ስለኖርን ሳይሆን፤ በተሰጠን ጸጋና እውቀት መጠን ዕለት ዕለት በምናፈራው መልካም ስራ መሆኑን አውቀን ከፊት ይልቅ ልንተጋ ይገባናል፡፡

ለዛሬው ይቆየን፡፡


ለቀጣዩ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ርዕስ እንመለሳለን፡፡ 

No comments:

Post a Comment