ከክፍል አርባ ሦስት የቀጠለ፦
የተከበራችሁ የቅድስት
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት!
ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9 “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን
አንድ እስከሆነ ድረስ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች
የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረ፤ዛሬም ከ"ልጅ ረድኤት አባተ" ፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነውን እጅግ ጠቃሚ ትምህርት እንድታነቡት አቅርበነዋል፡፡በጽሑፉ ላይ
አልጨመርንም አልቀነስንም፡፡
<<♥ #ተነሺ_አብሪ ♥>>
☞ኢሳ.60፥1☜
#ይነበብ
#Share_ይደረግ
✔✔✔ ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ
ትንሣኤ እና ዕርገት በ6 መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ አመክንዮዎች (Bibilical & Historical logics) ወደመረዳቱ
እንለፍ፤ ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ እጀምራለሁ።
✞✞✞ ሞት በጥር ፤ ነሐሴ መቃብር! እንዴት ያለ ግሩም
ነው ። የእመቤታችን ትንሣኤ ልዩና ድንቅ ነው ። ሞት እኮ ለሚሞት ሰው የተገባ ነበር ፤ ድንግል ማርያም ከትንሣኤዋ በላይ እኮ
እንዲያውም መሞቷ ያስገርማል ። የሁሉን ቻይ አምላክ እናት ከዚህ ዓለም ድካም አረፈችና በሕይወተ ሥጋ ተለይታ ሞተች ። ሥጋዋ ግን
በመቃብር ፈርሶና በስብሶ አልቀረም ። እንደሌሎች ቅዱሳን እና ሰዎች ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ለእርሷ አያስፈልጋትም ። የልጇን
ሞቱንም በሚመስል ሞት በሥጋ ሞታ ፥ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከሞት ተነስታለች (ሮሜ.6፥5)። ለዚህ አንክሮ ይገባል።
ሉተራውያን የድንግል ማርያምን ትንሣኤ ለመቀበልና ለማመን ሲቸግራቸውና
ወገባቸውን ሲቆረጥማቸው እናያለን ። ከእነርሱም አለማመን የተነሣ ፥ እኛን ኦርቶዶክሳውያን የተዋህዶ ልጆችንም ለመውቀስና ለማስካድ
ሲደክሙም እንመለከታቸዋለን። በዚህም እናዝንላቸዋለን ። ይህም ወላዲተ አምላክ ላይ ያላቸው ስሑት (የተሳሳተ) ግንዛቤ መሆኑን እናውቅላቸዋለን
። ሆኖም ግን ድንግል ማርያም "ከሞት አልተነሳችም ፤ እንደእኛ ሥጋ ሞታ ፥ እንደእኛው ትንሣኤ ዘጉባኤን ትጠብቃለች"
/ላቲ ስብሐት/ የሚል አላዋቂነት ላይ ከመድረስ በፊት ፥ እስቲ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመክንዮችን እንመልከት
➊ ✞✔✞
#በመጀመርያም_ክብሯ_ነው! ስለድንግል ማርያም ከተነገሩ ግሩማን ቃላት ውስጥ ሁለት ዐበይት የክብር መገለጫዎቿን ለአብነት እንጥቀስ
፦ ልዩ እና አንዲት የሚለውን ።
☞ ♥ ♥ ♥ #ልዩ ፦
እመ
ብርሃን ልዩ ናት። ከአንስተ ዓለም የተለየች፣ የተባረከች፣ የተመሰገነች፣ የተቀደሰች ናት ። እርሷን የሚመስል፣ እርሷን የሚያህል
ከመላእክት ነገድ፣ ከሰውም ወገን፣ ከፍጥረተ ዓለምም ማንም የለም ። እርሷ ኪዳነ ምሕረት ፥ ኪሩቤልና ሱራፌልን ትበልጣለች ። አማላጃችን
ወላዲተ አምላክ ፥ ከቅዱሳን ሁሉ ትልቃለች ። እመቤታችን ድንግል ማርያም ከነብያት ከሐዋርያት ከሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ ከፍ ከፍ ያለች
ናት ። እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔርን በጸጋ ተቀበሉ ፤ እናታችን ግን በአካል ጸነሰችው፣ ወለደችው፣ አጠባችው፣ አቀፈችው፣ ሳመችው፣
አበላችው፣ አጠጣችው፣ ተሸከመችው፣ አሳደገችው ።
እነዚያ
ሁሉ ቅዱሳን፦ የእግዚአብሔር መልአክ፣ የእግዚአብሔር ነቢይ፣ የክርስቶስ ሐዋርያ፣ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ሲባሉ ፤ የተወደደችዋ ንግሥት
ግን የእግዚአብሔር እናት፣ የክርስቶስ እናት፣ የኢየሱስ እናት፣ ወላዲተ
አምላክ፣ እመ አምላክ፣ እመ ብርሃን፣ የፍጹሙ የምሕረት ኪዳን ባለቤት፣ እመ አዶናይ፣ ኪዳነ ምሕረት ተብላ የምትጠራ ስትሆን በሰማይ
በምድር የሚተካከላት የሌለ ልዩ ናት ።
ልዩ
ስለመሆኗ ደግሞ 4 ምሥክሮችን ከመጽሐፍተ ብሉያትና ሐዲሳት መካከል እንጥራና በዚህ ትውልድ ላይ እንዲመሠክሩ እናቁም ፦
❖ ቅዱስ ዳዊት ✔
-
"ልዑል
ማደሪያውን ቀደሰ።" (መዝ.46፥4) እንዲል ፥ እግዚአብሔር አምላካችን ፦ የእግዚአብሔር ሀገር፣ የእግዚአብሔር ከተማ፣
የእግዚአብሔር ታቦት፣ የእግዚአብሔር መቅደስ የተባለች እናቱን ማደሪያውን ለየ ፤ አከበረ ፤ ቀደሰ ፤ መረጠ ፤ ወደደ ማለት ነው
። ዳዊትን በረከቱ እንዲያድርብን ተለማምነን ሌላኛውን ምሥክር እንፈልግ ።
❖ ንጉሥ ሰሎሞን ✔
-
"መልካም
ያደረጉ ብዙ ሴቶች አሉ ፥ አንቺ ግን ከዅሉ ትበልጫለሽ።" (ምሳ.31፥29) የሚለው የጠቢብ ቃል ብልጫ ያላት ልዩ እመቤት
መሆኗን ይመሠክራልና ንጉሥ ሆይ በጥበብህ አሳድገን ብለን እንለፍና 3ኛ ምሥክሩን እንስማው ።
❖ ቅዱስ ገብርኤል ✔
-
"መልአኩም
ወደ እርሷ ገብቶ፦ ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋራ ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።"
(ሉቃ.1፥28)። ወለም ዘለም የማንልበትን የሐዲስ ኪዳኑን ቃለ ብሥራት የነገረን መልአከ እግዚአብሔር በበረከቱ ይባርከን። እስቲ
ደግሞ ቅድስት ኤልሳቤጥን እንስማት ።
❖ ቅድስት ኤልሳቤጥ ✔-
"ኤልሳቤጥም
የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማሕፀኗ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፥ በታላቅ ድምፅም ጮኻ እንዲህ
አለች፦ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፥ የማሕፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው።" (ሉቃ.1፥41)። ሲጀመር እኮ ሰውና
መላእክት የተስማሙት ወይም የታረቁት በሥጋ ማርያም ክርስቶስ በመገለጡ ምክንያት ነው ። ከመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጋር የተባበረ
የቅድስት ኤልሳቤጥ ምሥጋና ምንኛ ድንቅ ነው።
ስለዚህም
ለአብነት ያህል እኝህን ጠቀስን እንጂ ስለእመቤታችን ከፍጥረተ ዓለም የተለየችና የከበረች መሆን በቅዱሳት መጻሕፍት የተመሠከረው
ሲበዛ ድንቅ ነው ። በመሆኑም ይህችን የአምላክ ማደሪያ እመ ብርሃንን "ሥጋዋ በመቃብር ፈርሶ በስብሶ ቀርቷል"
ብሎ ይህን ድፍረት ለመናገር ልዩ የሆነው ክብሯ ሲጀመር አይፈቅድልንም። እንደእኛ ተራ ማንነት የሌላትን ፥ እንደቅዱሳኑም የከበረ
ሰውነት የላቀ ክብር የተጎናጸፈችውን ልዩ የሆነችውን እናቱ ድንግል ማርያምን እንደኛው የሞተና የሚሞት ሥጋ "በመቃብር አለ"
ብሎ ለመናገር ድፍረቱ የማነው!? ጥንተ ጠላታችን ሰይጣንና የበኲር ልጆቹ ብቻ ካልሆኑ በቀር!!
እንጂማ፤
እመ ብርሃን ድንግል ማርያም ልዩ የመባሏም አንዱና ዋነኛ ምክንያትም ወላዲተ አምላክ ከመሆኗ ባሻገር ከዚህ ዓለም በሥጋ ከሞተች
በኋላ እንደ ልጇ ባለ ትንሣኤ ተነሥታ በወርቅ ልብስ አጊጣና ተጎናጽፋ ከነሙሉ ክብሯ በእግዚአብሔር ቀኝ መገኘቷ ነው።
"በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝኽ ትቆማለች።" (መዝ.44፥9) እንዲል በትንሣኤው ጌታ በሆነ
በንጉሡ ልጇ ዙፋን ቀኝ፥ በትንሣኤዋ ከምድር ተነጥቃ ለተወደዱ ልጆቿ በምልጃ የቆመች [ለማያምኑባት ለፍርድ የተቀመጠች] ንግሥታችን
ድንግል ማርያም ልዩ ነች።
ለመዳን
ከፈቀድን የተነገረው የሕይወት ቃል በቂ ነውና ቀጥሎ ደግሞ <አንዲት> የሚለውን እንመልከት ።
☞ ♥ ♥ ♥ #አንዲት ፦
ከላይ
በመጽሐፍት የተመሠከረላት ልዩ የሆነችው አንዲት ናት። ልዩ መሆኗ ሲገርመን ፥ በዚህ ክብር ደረጃ የምንጠራት እርሷ አንዲትና አንዲት
ብቻ ናት። እንደጌታ ትንሣኤ ሞት ሳያስቀራት በመንግሥተ ሰማያት በልጇ ክብር ያለችው አንዲት ናት። ሌሎቻችንና ቀደም ሲልም የሞቱ
ሙታን የሚጠብቁትን ትንሣኤ የማትጠብቀው እርሷ አንዲት ናት። ድንግልም እናትም የተባለች አንዲት ናት። የአምላክ እናት ለመሆን የበቃች
እርሷ አንዲት ናት። ከመንፈስ ቅዱስ የተገኘው [የተሰጠው] ጸጋ አንዳችም ያልጎደለባት ወይም ተከፍሎ ያልተሰጣት ፥ ምልዕተ ጸጋ
(ጸጋን የተመላች) አንድ እርሷ ድንግል ማርያም ብቻ ናት። አንዲት ስለመሆኗ መጽሐፍ እንዲህ ይመሠክራል ፦
❖ መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ✔
-
"ርግቤ
መደምደሚያዬም አዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት፤ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቆነጃጅትም አይተው አሞገሷት ፤ ንግሥታትና ቁባቶችም
አመሰገኗት።" (መኃ.6፥9) ሲል ከመዝሙራት ሁሉ በሚበልጥ መዝሙሩ ንጉሡ የተቀኘላት ድንግል ማርያም፥ ድኅነታችን የተጀመረባት፣
ደግሞም የተፈጸመባት የሠላማችን ርግብ አንዲት ናት። ለእናቷ ለቅድስት ሃና ለአባቷም ቅዱስ ኢያቄም አንዲት ናት፤ ለልጇም ለክርስቶስ
አንዲት ናት፤ ለእግዚአብሔርነቱም ለሥላሴነቱም አንዲት ናት፤ ለእኛም ለክርስቲያን ልጆቿም አንዲት ናት።
❖ ቅዱስ ገብርኤል ✔
-
እግዚአብሔር
አምላክ ንጽሕናዋን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የተባለን ብርሃናዊ መልአክ ሲልክ ፥ ለዚህ ክብር የተለየችና የተመረጠች "ወደ
አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፥ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።" ተብሎ መሥክሮ አስመሥክሮ ነው (ሉቃ1፥27)።
ደግሞም እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ላዳነበት ጥበቡ ልቃ ተገኝታ የሥላሴ ዙፋኑ የሆነች እና ይህን ሰማያዊ
ቃለ ብሥራተ ሐዲስ የሰማች ፥ ለመስማትም ብቁ ሆና የተገኘች እርሷ አንዲት ድንግል ማርያም ብቻ ናት ።
ስለዚህም፤
ስለእርሷ ግሩም ድንቅ እመቤታችን የተነገረውና የተደረገው ነገር ሁሉ ድንቅ ነው (መዝ.86፥3)። ሞት የማይገባት መሆኗ ሊደንቀን
ሲገባ ፥ ትንሣኤዋ ይበልጡን ደነቀን። ወደ መቃብር መውረድ የማይገባት መሆኗ ሊደንቀን ሲገባ ፥ ሙስና መቃብርን አሸንፋ መነሳቷ
ይልቁን ደነቀን ። ፍልሰቷ ሊያስገርመን ሲገባ እጅጉን ዕርገቷ አስገረመን ። ከሰው ወገን ይህ ሁሉ የሆነላት ለእርሷ ለአንዲቷ ለእመ
ብርሃን ድንግል ማርያም ብቻ ነው ። ምክንያቱም ይህን የጸጋ ክብር እንዳትጎናጸፍ የሚያደርጋት አንዳችም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታ አልጎደለባትምና!
ምልዕተ ጸጋ ምልዕተ ክብር ናትና (ሉቃ.1፥30)!!
ስለሆነም
የድንግል ማርያምን ትንሣኤና ዕርገትን ለማመንም ሆነ ለመቀበል መቸገር፤
#_ልዩ እና #_አንዲት መሆኗን ለማመንና ለመቀበል መቸገር ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን ልዩ እና አንዲት አድርጎ የወደዳትን
ያከበራትን የመረጣትን ልጇን ወዳጇን አምላኳን አምላካችንን አለማወቅና አለማክበርም ጭምር ነው። ኧረ ተው ዓይንህን ግለጥና አስተውል
እንጂ ፦ #_ትንሣኤና_ሕይወት_እኔ_ነኝ_ላለው_ጌታ_እኮ_እናቱ_ናት ። እውነት እልሃለሁ ትንሣኤዋና ዕርገቷ ተፈጽሟል።
➋ ✞✔✞
#ሁለተኛውን_አመክንዮ_እናስረዳ ፤
ከዚህ
ባሻገር ግን አንድ "ክርስቲያን ነኝ" ለሚል አማኝ ስለ ትንሣኤ ምንነት እና ስለ ድንግል ማርያም ክብር መንፈሱ
ከሚጨነቅበት ይልቅ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ትንሣኤን በእነ አልዓዛር፣ በእነ ጣቢታ፣ በእነ የሰራፕታዋ መበለት ልጅ እና በመሳሰሉት
#ትንሣኤ_ሙታንን_ቢለማመደው መልካም ነው እላለሁ።
ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ ለከበረች መልእክቱ ክብር ይግባውና የእነዚህን ትንሣኤ እንዲህ አስረድቶናል፦ "#ሴቶች_ሙታናቸውን_በትንሣኤ_ተቀበሉ፤
ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ #የሚበልጠውን_ትንሣኤ_እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤" (ዕብ.11፥35) እንዲል።
☞ #አልዓዛር ✔
-
የጌታ
ወዳጅ ብቻ ተብሎ ከሞተ በኋላ ከተነሳና ለሚበልጠው ትንሣኤ ከተጠበቀ (ዮሐ.11፥44) ፤
☞ #ጣቢታ ✔
-
መልካም
አድራጊ ሴትና ደቀ መዝሙር ብቻ ተብላ ከሞተች በኋላ ተነስታና ለሚበልጠው ትንሣኤ ከተጠበቀች (ሐዋ.9፥40) ፤
☞ #የሰራፕታዋ_መበለት ✔
-
የእግዚአብሔር
ነቢይ ኤልያስን በቤቷ በመቀበሏ ብቻ ልጇ ከሞተ በኋላ ከተነሳና ለሚበልጠው ትንሣኤ ከተጠበቀ (1ኛነገ.17፥22) ፤
ዛሬ
ላይ ድንግል ማርያም በሚበልጠው ትንሣኤ ከሞት መነሣቷና ማረጓ ለምን ጥያቄ እንደሚሆንባቸው አይገባኝም። ልብን በክፉ ሐሳብ ከመደለልና
ጠላትነት ከመሆን በቀር!? እነዚያ ሁላ "የእግዚአብሔር ወዳጅ" ተብለው ብቻ ለጊዜው ከሞቱ በኋላ ትንሣኤያቸው ከተሰበከና
ለኋለኛውም ትንሣኤ ዕድል ከተሰጣቸው ፤ ከእነዚህ ሁሉ የተለየችውና የከበረችው ደግሞም ለእግዚአብሔር እናቱ የሆነችው ልዩ እና አንዲቱ
እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደ ልጇ ያለ ትንሣኤ ምንኛ ድንቅ ይሆን?!! ፍሬንድ ቢያንስ ደረጃ የሚባል ነገር እኮ አለ!? የአልዓዛርን
ትንሣኤ የሰበከ አንደበት የድንግል ማርያምን ትንሣኤ መግለጥ ለምን ያፍራል!? የጣቢታን ከሞት መነሳት የመሰከረ ሕሊና የእመቤታችንን
ማረግ ለመመስከር ምን ይገደዋል!? ምንም እንኳ የድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ ከእነኚህ በክብሩም በትርጉሙም የተለየ ቢሆንም ቅሉ
(እነሱ እንደገና ትንሣኤ ዘጉባኤን መጠበቅ ቢኖርባቸውም) ቢያንስ ግን ለእነዚህ "የጌታ ወዳጆች" እንኳ ትንሳኤያቸው
ተሰብኳል።
ታዲያ
እነዚያ ከአሁን በኋላ ሌላ ትንሣኤ የሚጠብቁ ሆነው እንኳ ከሞት መነሳታቸው ከተመሠከረ ፤ ልዩ እና አንዲት የሆነችው ድንግል ማርያም
በሥላሴ ዘንድ ባላት ሥልጣንና ሞገስ የሚመጣውን ትንሣኤ መጠበቅ አሁን ላይ ሳይኖርባትና ሳያሥፈልጋት ያኔ በክብር ተነሥታ ዐርጋለች
ብለን ዛሬን ማክበራችን እንዴት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያጣል!? ከጌታ ወዳጆች የምትበልጠው የጌታ እናት ከሞት ተነሥታ በክብሯ
አጊጣ በንጉሡ ቀኝ ትገኛለች። ማስተዋሉን ያድለን።
➌ ✞✔✞
#ሦስተኛውን_አመክንዮ ደግሞ ከነሄኖክና ከነኤልያስ ዕርገት ጋር አነጻጽረን የምንመለከተው ይሆናል።
መናፍቃን
የእመቤታችንን ዕርገት ለመቃወም ከሚጠቅሱት ጥቅስ አንዱ "#ከሰማይም_ከወረደ_በቀር_ወደ_ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም
በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" (ዮሐ.3፥13) የሚለውን ለኒቆዲሞስ የተሰጠውን የጌታ ትምህርት ነው። ኒቆዲሞስ የአይሁድ
መምህርና አለቃ ሲሆን የክርስቶስን ሰው የመሆን፣ የመወለድ፣ የማደግ፣ የመጠመቅ፣ የመሰቀል፣ የመሞት፣ የማረግ እና ዳግም የመምጣት
ትንቢቶች፣ ምሳሌዎችና ትምህርቶችን በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀቱ መመርመርና ማወቅ የሚጠበቅበት ከመሆኑም በላይ፤ ስለ ዳግም ልደት
ወይም ስለ ጥምቀት የተሰበከውን የሕይወት ቃል አላስተዋለም።
በመሆኑም
የጌታን ንግግርና ትምህርት ባለመረዳቱ "የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?" ተብሎ አስወቅሶቷል። ቢያንስ
አጠገቡ ባለ የዮሐንስ ጥምቀት ምሳሌነት አነጻጽሮ ማየትና፥ የዳግመኛ መወለድን ትምህርት መረዳት ያልቻለ ኒቆዲሞስ "ከሰማይ
ስለወረደው ቃል፣ በሥጋ ማርያም ስለተገለጠውና ደግሞም የመጣበትን የቤዛነት ሥራ ፈጽሞ ወደሰማይ ስለሚያርገው ያ ቃል የተባለ ክርስቶስ"
መረዳት በመቸገሩም ምክንያት "ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ?"
(ዮሐ.3፥12) ለመባልም በቅቷል።
ይህን
በመሰለው ምክንያት መነሻነትና እንዲሁም ክርስቶስን ሆኖ የተገለጠ፣ ደግሞም ሊገለጥ የሚችል ሌላ መሲሕ የለምና "ከሰማይም
ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" በማለት ለድኅነተ ዓለም መምጣቱን፤
ደግሞም ለሕልፍተ ዓለም ለፍርድ ዳግም የሚመጣው እርሱ ራሱ መሆኑን ያስገነዘበበት ትምህርት እንጂ ወደሰማይ ስለመውጣትና ስለመውረድ
ዋና ጭብጡ አድርጎ የተነገረ አይደለም። ይህ አለመሆኑን የምንገነዘበው ደግሞ በብሉይ ኪዳን የእነ ሄኖክ እና ኤልያስን ወደሰማይ
መወሰድን፣ በሐዲስ ኪዳን እስከ ሦስተኛው ሰማይ የተነጠቀው ቅዱስ ጳውሎስን መመልከት እንችላለን።
☞ #አባታችን_ሄኖክ ✔
-
"ሄኖክም
አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም፤ እግዚአብሔር ወስዶታልና።" (ዘፍ.5፥24)
"ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው
አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤" (ዕብ.11፥5)
☞ #ነቢዩ_ኤልያስ ✔
-
"ሲሄዱም ፥ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት
ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።" (2ኛነገ.2፥11)
ይህ
ኤልያስ ወደሰማይ እንደወጣ እንዲሁ ይመጣል። በትንቢተ ሚልክያስ "እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ
ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።" (ሚል.4፥5) ተብሎ እንደተገለጠው ሄኖክንም ጨምሮ ኤልያስ ይመጣል። ጌታችንና መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን አረጋግጦልናል ፦ "ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።" (ማቴ.11፥14)፤
"ኢየሱስም መልሶ ፥ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤" (ማቴ.17፥11) እንዲል። ጸሐፍት ፈሪሳውያንም
በእሳት ሠረገላ ወደሰማይ የተነጠቀው ኤልያስ እንደሚመጣ ግንዛቤ ስለነበራቸው ጌታችንን ፦ "እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ
ነህን?" (ዮሐ.1፥21)፤ "ሌሎችም ፥ ኤልያስ ነው አሉ" (ማር.6፥15) እያሉ ይከራከሩበት [ይሰናከሉበት]
ነበር።
☞ #ቅዱስ_ጳውሎስ ✔
-
"...
እንዲህ ያለው ሰው ከአሥራ አራት ዓመት በፊት እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ተነጠቀ።" (2ኛቆሮ.12፥2) እንዲል ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መመካት እንዳይሆንበት ራሱን ሳይጠቅስ በሌላ ሰው አንቀጽ እያደረገ የነገረን ትሕትናው ምንኛ ግሩም ነው!?
ስለዚህ
ወደተነሳንበት ነጥብ ስንመለስ ... ከሰማይ የወረደው አስቀድሞ ቃል የነበረው (ዮሐ.1) ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ቢሆንም፤ ወደሰማይ የተወሰዱ [ሄኖክ]፣ የወጡ [ኤልያስ]፣
የተነጠቁ [ጳውሎስ] አሉ ማለት ነው።
በመሆኑም
"ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።" (ዮሐ.3፥13)
ሲል ጌታ ስለራሱ የተናገረው ከላይ እንዳብራራነው እንጂ የቅዱሳኑን ወደሰማይ ማረግ የሚቃወም ትምህርት አለመሆኑን በዚህ እናረጋግጣለን።
ታዲያ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሙታን ተለይታ ወደሰማይ እንዳታርግ ፥ አካሄዱን ከአምላኩ ጋር ካደረገው ከሄኖክ ምን ያሳንሳታል?
ጻድቁ አባት ሄኖክ ፥ አካሄዱን [የጽድቅ ሕይወት ኑሮውን] ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር አድርጎ ያውም ሞትን ሳያይ ወደሰማይ ከተወሰደ፤
እመቤታችን ፦ አካሄዷን ብቻ ሳይሆን "እነሆኝ የጌታ ባሪያ" ስትል ራሷን በፍጹም ትኅትና ገልጣ ከቤተልሔም እስከ
ቀራንዮ ከልጇ ያልተለየች፤ ለዘላለሙ የሐዲስ ኪዳን ኪሩብ ሆና ለሥላሴ ዙፋን ፤ ለአምላክ ማደሪያነት የተመረጠች ሳለች፤ ሲሆን ሲሆን
እንደ ሄኖክ ሞትን ሳታይ ወደሰማይ ልትወሰድ ሲገባ፤ እርሷ ግን በልጇ ፈቃድ ሞትን አይታ፥ ከሞትም ተነሳች፤ ዐረገችም ብለን እውነቱን
መግለጣችን ምን ይበዛባት ይሆን?!
የእግዚአብሔር
ነቢይ የሆነው ኤልያስ ሞትን ሳያይ ያውም በእሳት ሠረገላ ሰማያትን አልፎ ከወጣ፤ የእግዚአብሔር እናቱ የሆነች ወላዲተ አምላክ በሐዋርያት
ምሥጋናና በመላእክት ዝማሬ ታጅባ ከሞት ተነሥታ ወደሰማይ ወደገነት
ወደልጇ ወደአምላኳ ዐረገች ብለን የተደረገላትን እውነተኛ ክብር
ማመናችንና ማክበራችን ምን ይሆን ስህተቱ? ነቢዩ ኤልያስ ስለክብሩ ይህ ከተደረገለት ፥ የእመ ብርሃን ክብር ምን ያህል
ይደንቅ? የቱን ያህል ይልቅ ይሆን?!
ኤልያስ
እና ሄኖክ ስለጽድቃቸውና ክብራቸው ሞትን ሳያዩ እስከ ዳግም ምጽአት በሕይወት እንዲኖሩ ወደሰማይ ከተነጠቁ፤ የኤልያስ እና የሄኖክን
አምላክ እናቱ የሆነች ድንግል ማርያም በተወደደው ልጇ መልካም ፈቃድ ሞታ፤ ቅዱስ ያሬድ እንዳለው "ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፤
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ - ሞትማ ለሚሞት ሰው ይገባል፤ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል" ሲል እንደገለጸው ከገናናው
ክብሯ የተነሳ፥ ኤልያስ እና ሄኖክ ለጊዜውም ቢሆን እንኳ ሳይሞቱ፥ እርስዋ ግን በመሞቷ ልንደነቅ ሲገባ ፥ ስለቅድስናዋ፣ ስለንጽሕናዋ፣
ስለፍጹም ክብሯ የበለጠው ተደርጎላት ከሞት ተነስታ ማረጓ ተገቢ እንጂ ስህተት አይሆንም። እኛም ኦርቶዶክሳውያን ይህን አምነን ማክበራችን
በትክክለኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ላይ ለመቆማችን ማሳያ ነው። እንኳንም የተዋሕዶ ልጆች ሆንን!
ይህ
ለሄኖክ እና ለኤልያስ የተደረገው ክብር በሐዲስ ኪዳን ለወንጌላዊው #ቅዱስ_ዮሐንስም ተፈቅዶለታል። ዮሐንስ ወንጌላዊ አልሞተም።
ጌታችን ፥ ቅዱስ ጴጥሮስን "በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ" ካመላከተው በኋላ፥ ቅዱስ ጴጥሮስ
ግን ዮሐንስ ጌታን ሲከተለው አይቶ "ይህስ እንዴት ይሆናል?" ብሎ በጠየቀው ጊዜ ጌታችን "እስክመጣ ድረስ
ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ?" ሲል ለቅዱስ ጴጥሮስ ይመልስለታል። "ስለዚህ ፥ ያ ደቀ መዝሙር አይሞትም
የሚለው ይህ ነገር ወደ ወንድሞች ወጣ፤ ነገር ግን ኢየሱስ ፥ እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ ምን አግዶህ? አለው እንጂ አይሞትም
አላለውም።" ተብሎ ተጽፏል (ዮሐ.21፥18-24)። ይህ ምስክርነቱም እውነት እንደ ሆነ እናውቃለን።
ታዲያ
የጌታ ወዳጅ - ፍቁረ እግዚእ የተባለ ዮሐንስ፣ ድንግል ማርያምን በአደራ ከመስቀሉ ሥር የተቀበለ ዮሐንስ፣ የጌታን ወንጌል የጻፈ
ዮሐንስ ፥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሳይሞት በሕይወት እንዲኖር የተገባው ክብር ከሆነ ... ለወንጌል መጻፍ ፊደል የሆነች፣ የጌታ ወዳጅ
ከመባል በላይ ራሱ ወንጌላዊው #የኢየሱስ_እናት_ማርያም የሚላት፣ ዮሐንስ ከደረቱ ቢጠጋ እንጂ ድንግል ማርያም ግን ጸንሳው፣ ወልዳው፣
ታቅፋው፣ አጥብታው፣ ስማው፣ አዝላው፣ ደግፋው ... ግን የዚህን ዓለም ሞት እንድትሞት የልጇ ፈቃድ ሆነና ለክብሯ ግን ሥጋዋ ሞቶ
በስብሶ ከመቃብር ይኖር ዘንድ ልጇ አልወደደምና ከሞት መነሳት የተገባት ሆነ። ደግሞስ የነሳው ሥጋ ይህን የማርያምን ክቡርና ቅዱስ
ሥጋ መሆኑስ እንዴት ይረሳን ዘንድ ይቻለናል?! ድንግል ማርያም ከሞት ተነሳች ስንል ካልተቀበላችሁ ፥ እንደ ጌታ ቃል
"ድንግል ማርያም ከሞት ተነሳች ካልን ምን አግዷችሁ ትቃወሙናላችሁ?" እንላችኋለን።
➍ ✞✔✞
#በአራተኛነት ከላይ ያነሳናቸውን አመክንዮች በቀጥታና በግልጽ ወደሚያስረዱን #የመጽሐፍ_ቅዱስ ጥቅሶች እንለፍ።
✞♥ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ✔
-
"
#አቤቱ_ወደ_ዕረፍትህ_ተነሥ፥ #አንተና_የመቅደስህ_ታቦት።" ሲል በመዝሙር 132 ቁ.8 ላይ ተናግሯል። የመቅደሱን ታቦት
ከላይ በከፊል ገልጸናል። ከሦስቱ ቅዱስ ለአንዱ ቅዱስ ማደሪያ መቅደስ የሆነችው አማናዊት ታቦት ድንግል ማርያም ናት። ፍጹም እረፍት
ያለባትም ሥፍራ መንግሥተ ሰማያት ናትና ቅዱስ ዳዊት ወደፍጹሙ የዕረፍትህ ቦታ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከንጉሡ ቀኝ ከምትቆመው [ከምትቀመጠው]
ከመቅደስህ ታቦት ከማደሪያ ዙፋንህ ይህችውም ድንግል ማርያም ናትና ተነሥ በማለት በምሥጢር ቅኔ ትንሣኤዋን ገልጿል።
✞♥ ጠቢቡ ሰሎሞንም ✔ -
"ውዴ
እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ #ወዳጄ_ሆይ_ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ
ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ ፤ መዓዛቸውንም ሰጡ፤ ወዳጄ ሆይ፥
ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ። "(መኃ.2፥10-13) ሲል ክረምት ሞት ማለፉንና የነበረውንም የደስታ መዓዛ "ተነሺ
፥ ነዪ" እያለ በግልጽ በመዘመር የትንሣኤዋን ነገር ቀድሞ
ተናግሯል።
✞♥ ነቢዩ ኢሳይያስ ✔
-
ለዚህ
ጽሑፍ ርዕሳችን የሆነውን የሕይወት ቃል በማውሳት ነገራችንን እናጠናክር። ቃሉን ነቢየ ልዑል ኢሳይያስ ተናግሮታል ፤ "ተነሺ
፥ አብሪ" እያለ የምሥራቹን ያውጃል ። ሙሉውን ኃይለ ቃል እንመልከተው ፦
"#ብርሃንሽ_መጥቷልና፥
የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻልና፥ ተነሺ፥ አብሪ። እንሆ፥ ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን፥ ባንቺ
ላይ እግዚአብሔር ይወጣል፡፡ ክብሩም ባንቺ ላይ ይታያል፤ አሕዛብም ወደ ብርሃንሽ ፥ ነገሥታትም ወደ መውጫሽ ጸዳል ይመጣሉ።"
(ኢሳ.60፥1) ይላል ።
✔✔✔♥ #_ተነሺ_አብሪ ♥✔✔✔
ትንሣኤ
ብርሃን አለው። ትንሣኤ ክብር አለው። እንደዚሁ ሁሉ የእመቤታችን ትንሣኤ ብርሃን አለውና ተነሺ ፥ አብሪ ተብሎላታል ። ድቅድቅ
ጨለማ ሞት ፥ ድቅድቅ ጨለማ መቃብር እርሷን አላሸነፋትምና የብርሃን እናቱ ተነስታለች ። ለትንሣኤው ጌታ እናቱ የሆነች እርሷ ዐርጋለች።
በእርሷም የአምላካችን የእግዚአብሔር ክብር ተገልጧል። በእርሷም አምላካችን እግዚአብሔር እራሱ ተገልጧል። እርሱ ብርሃን የሆነ ጌታ
፥ የብርሃን እናቱ ወደሆነች ወደ እመ ብርሃን አሕዛብና ነገሥታት ሁሉ ሳይቀሩ ወደምሥራቋ በር መጥተው "ተነሺ ፥ አብሪ"
እያሉ ከነብዩ ጋር አመሥግነዋል። ይሄን ማመንና መቀበል ለተሳናቸው ግን
ጨለማ ከድኗቸዋል ይላል። አቤት የተዋሕዶ ልጅ መሆን!? አቤት ኦርቶዶክሳዊ ብልጫ!?
በሐዲስ
ኪዳኑ የትንቢት መጽሐፍ ላይ ፥ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ እንደተመለከተው ፦ "ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት
በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።" (ራእይ.21፥27) ተብሎ ተጽፏልና
፤ ወደ ዳግሚት ሰማይ ወደ መንግሥተ ሰማያት ወደ ብርሃኗ መውጫ ጸዳል ወደ እመቤታችንም ለመቅረብ በብርሃኗ መመላለስና በትንሣኤዋም
ማመን ይገባል። ያለ ድንግል ማርያም ክርስቶስ ፤ ያለክርስቶስም ክርስትና የለም እንዳለ ዘማሪው!!
➎ ✞✔✞ ሌላው በአምስተኛነት የምናየው አመክንዮ #የእመቤታችን_መቃብር_ባዶ_መሆኑን ነው።
በእርግጥ
መናፍቃኑ ይህንንም አያምኑንም። እንኳን በጌቴሰማኒ የእመቤታችንን መቃብር ባዶ ሆኖ ሊያምኑና ሊቀበሉ ቀርተው፤ የልጇን የአምላካችንን
የጌታን መቃብር ባዶ ሆኖ እያዩት ዘመዶቻቸው ጸሐፍት ፈሪሳውያን ፦ "እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው
#ሰረቁት በሉ።" (ማቴ.28፥13) ሲሉ ለጠባቂዎቹ ገንዘብ ከፍለው የጌታን ትንሣኤ ለመደበቅ ብሎም ለመካድ ጥረዋል። አልተሳካም
እንጂ። የዛሬዎቹ ተረፈ አይሁዳውያንና ውሉደ ፈሪሳውያንም የእመቤታችንን መቃብር ባዶ ሆኖ እያዩት "#ሰርቃችሁ_ወስዳችኋት_ነው"
ማለታቸው አይቀርም። እነሱ ያፍራሉ እንጂ የድንግል ማርያም መቃብር ባዶ ነው።
➏ ✞✔✞
#በመጨረሻም ድንግል ማርያም "አልተነሳችም" ለሚሉን ፥ እንዲያውም "ሞታለች ካላችሁን ቃል በቃል
<ማርያም ሞተች> ተብሎ የተጻፈ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ አቅርቡ" እንላቸዋለን።
ክብር
ይግባውና ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቅደስ ገብቶ ሕዝቡን ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች
ወደ እርሱ ቀረቡና "በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?" ባሉት ጊዜ ለልባቸው ክፋት
ጥያቄያቸውን በጥያቄ ሲመልስ "እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን
በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው?" አላቸው። መናፍቃንና
ተቃዋሚዎች መጠየቅና መቃወም እንጂ መመለስና መረዳት አይፈልጉምና "አናውቅም" አሉት። ጌታ እርሱም ደግሞ
"እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም" አላቸው። (ማቴ.21፥23-27) ይላል።
ዛሬም
በእመቤታችን ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች እንዲሁ ተመሳሳይ ናቸው። እኛ የእመቤታችንን ትንሣኤና ዕርገት እንናገራለን፤ እነሱ ደግሞ
"ሞታ ቀርታለች" ይላሉ። እኛ ከሞት ለመነሳቷ ከላይ ያቀረብናቸውን አመክንዮ ሁሉ እናስረዳለን፤ እነሱ ደግሞ ማመንም
መቀበልም ባለመፈለጋቸው "በግልጽ ቃል በቃል ከሞት ተነሳች" የሚል ጥቅስ አሳዩን" ይላሉ። ለእንዲህ ዓይነቱ
የፈሪሳውያን "በምን ሥልጣንህ ይህን ታደርጋለህ?" ጥያቄ እኛም በተመሳሳዩ "እንኪያስ እናንተስ በምን ሥልጣናችሁና
በየትኛው ጥቅስ ሞተች" ትላላችሁ ስንል እንጠይቃቸዋለን። እስቲ "ማርያም ሞተች" የሚል ጥቅስ ቃል በቃል
አሳዩን? በሏቸው። በእርግጠኝነት እንደአባቶቻቸው አይሁድ "አናውቅም" ይሏችኋል። ካላወቁ እንግዲህ ምን ይደረጋል?
አፉ በሏቸው! አለማወቅ ግን ኃጢአት አይደለም፤ እውነቱን አለመቀበልና አለማመን ግን በደልም አመጽም ነው።
ስለ
አማሟቷም ሆነ ስለመሞቷ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል በቃል የተጻፈ ጥቅስ እንኳ የማያውቁ ፥ ስለትንሣኤዋ ስለዕርገቷ እንዴታ ሊያውቁና
ሊያምኑ ይችላሉ?!
"#ስለምድራዊ_ነገር_ብንነግራችሁ_ያላመናችሁ
፥ ስለ ሰማያዊው ነገር ብንነግራችሁማ እንዴት ታምኑናላችሁ?" (ዮሐ.3፥12) ተብሎ እንደተጻፈ ፥ የድንግል ማርያምን ምድራዊ
ሞት የማታውቁ ፥ ስለትንሣኤዋ ስለዕርገቷ ለመከራከር ምንስ ብቃት አላችሁ? ይህን ለመነጋገር እኮ ቅድሚያ ስለመሞቷ እንኳ የተጻፈ
ማስረጃ ሊኖራችሁ ይገባል። የለማ! እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ <መሞቷ> የተጻፈ ጥቅስ ያሳዩንና እኛ ደግሞ ስለ [ዕርገቷ]
ማረጓ እንነግራቸዋለን። ታዲያ እነሱ ገና የሞት ጥቅስ ሲፈልጉ ፥ እኛ ኦርቶዶክሳዊያን ግን ሞት ያፈረበትን ሰማያዊውን ዕርገት እንናገራለን።
እናምናለን። እንሰብካለንም። #እንዲያውም_እኮ_መሞቷንም_የነገርናቸው_እኛው_በመሆናችን_ሊያመሠግኑን_ይገባል። ከፍቅራችን የተነሳ
ሞቷን ያልደበቅን ፥ ትንሣኤዋን ከመመስከር አናፍርም።
ከእመቤታችን
በዓለ ትንሣኤና ዕርገት ረድኤት በረከትን ልጇ ወዳጇ ቅዱስ ዐማኑኤል ያሳትፈን ። ከትንሣኤዋ ብርሃን ይደምረን። ታቦት ዘዶር ወዳለችበት
ይኽችውም ሕይወትን የምታሰጥ ድንግል ማርያም ናትና ወደ መንግሥቱ ያግባን። እኔን ባሪያውን ሀብተ ወልድንም በጸሎታችሁ ኃይል አስቡኝ።
(N.B:
ይህ ጽሑፍ ካቻአምና ነሐሴ 16 ቀን 2009 ዓ.ም በፌስቡኬ የለጠፍኩት ሆኖ፥ ጥቂት ማስተካከያና ተጨማሪ ሐሳቦችን በማካተት በድጋሚ
ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም የተለጠፈ ሲሆን፤ በዚሁ ቀን በሰሜን ሸዋ ሰላሌ ፍቼ (ግራሪያ) ደብረ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት
ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ደግሞ በጉባኤ ተሰብኳል። እነሆ ዛሬም እንድንማርበትና የእመቤታችን በረከት እንዲያድርብን ይኼው ተለጥፏል)
ልጅ
ረድኤት አባተ
ዲያቆን፣
የነገረ መለኮት የማስተርስ ድግሪ ምሩቅ፣ የኮንስትራክሽን መሀንዲስ፣ የዩኒቨርስቲ መምህር
rdtabate@gmail.com
©Re-post
(ዓርብ
ለእሁድ አጥቢያ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም)
ለመምህር ልጅ ረድኤት አባተ
አጥንትን የሚያለመልመውን የመላእክትን ምስጋና
ያሰማልን፡፡
እኛንም አብሮ ያሰማን፡፡
በሌላ ርዕስ እስከምንገናን በደህና ቆዩን፡፡
ከወልድ ዋሕድ ዝግጅት ክፍል፡፡
No comments:
Post a Comment