በስመ
አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ከቁጥር አንድ የቀጠለ
ተከበራችሁ
አንባብያን!
“ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡”በሚለው ርዕስ እንደ መግቢያ የሆነውን ክፍል አንድን ተመልክተን በይቀጥላል አቆይተነው እንደነበር የታወሳል፡፡ ስለሆነም በገባነው ቃል መሰረት ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ከመግባታችን በፊት ነገር ከሥሩ ውሃ ከጥሩ ነውና በአሁኑ ጊዜ እራሳቸውን “ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ
ተዋህዶ” ብለው ስለሚጠሩት ክፍሎች ወቅታዊ ግንዛቤ
መጨበጥ ይኖሮብናል፡፡
እነዚህ ክፍሎች ቀደም ባሉት በ1980ዎቹ ዓመታት እንዲህ እንደ አሁኑ ሳይደራጁ ማለትም ገና በጽዋ ማህበር ደረጃ ይሰባሰቡ በነበረ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የማፍረስ ዓላማቸውን እንዲህ በለው ገልጸውት ነበር፡፡“ አስቀድሞ የተመሠረተው መሠረት (የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት) በአንድ ጊዜና በቀላሉ ተገርስሶ ሊወድቅ አይችልም፡፡እኛ ሥርዓቱን ለይምሰል እየፈጸምን ውስጥ ውስጡን የእኛን እውነት ስናስተምር ያ የቀድሞው መሰረት ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ሲወድቅ ያን ጊዜ የኛ መሰረት በዚያ ላይ ይመሰረታል፡፡”በማለት ነበር ገና ከጅምሩ ከሐዋርያው ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ጋር የተጣሉት፡፡ እንጠቅሳለን ፦“በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ኤፌ.2፤20-21 እንዲሁም“ ከተመሰረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሰርት አይችልምና ፤እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” 2ኛ ቆሮ.3፤11
ቅ/ጳውሎስም ይህንን መልእክት የጻፈው ከራሱ ልብ አመንጭቶ ሳይሆን የዓለም መድኃኒት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውንና ወንጌላዊው ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕ.16 ቁ.16-20 እንዲህ ብሎ የመዘገበውን መሠረት አድርጎ ነው፡፡ “ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ ” አለ፡፡ጌታችንም መልሶ…“.በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሰራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም፡፡…” በማለት
እምነቱን አጽድቆለታል፡፡ይህም ማለት ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ወይም አምላክ ወልደ አምላክ /ወልድ ዋሕድ/ ብላ የምታምን ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ፍጻሜ ሳትናወጥ ትኖራለች ማለት ነው፡፡ውድ አንባብያን! እንግዲህ ጌታችን “የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም ”/አያሸንፏትም/ አለ እንጂ አይፈትኗትም አላለምና ይኸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ወልዳ ባሳደገቻቸው ከዳተኛ ልጆቿ እየተፈተነች ትገኛለች፡፡
እምነቱን አጽድቆለታል፡፡ይህም ማለት ጌታችንና መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ወይም አምላክ ወልደ አምላክ /ወልድ ዋሕድ/ ብላ የምታምን ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ፍጻሜ ሳትናወጥ ትኖራለች ማለት ነው፡፡ውድ አንባብያን! እንግዲህ ጌታችን “የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም ”/አያሸንፏትም/ አለ እንጂ አይፈትኗትም አላለምና ይኸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ወልዳ ባሳደገቻቸው ከዳተኛ ልጆቿ እየተፈተነች ትገኛለች፡፡
በዚሁ እቅዳቸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ላይ ከሚገኙት ሃላፊዎች የተወሰኑ ደጋፊዎቻቸውን ይዘው በራሱ በቤተ ክህነት ውስጥ፣ በየሰንበት ት/ቤቱ ፣በየሰበካ ጉባኤዎች ፣በየመንፈሳዊ ኮሌጆችና እንደ ዋልድባ በመሳሰሉት በትላልቅ ገዳማት ሳይቀር ተሰገስገው አቅማቸውና ሁኔታው የፈቀደላቸውን ያህል የጥፋት ተልእኳቸውን በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ምንም እንኳን በዚህ የስህተት ትምህርታቸው/በኋላ በዝርዝር የምናየው/ ብዙ ምዕመናን በተለይም ወጣቶች እነሱን ተከትለው ከእውነተኛይቱ የተዋሕዶ እምነታቸው በመውጣታቸው የተጎዱ ቢሆንም/እናዝናለን!/ በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን የቅድስት ኦርቶዶከሳዊት ተዋህዶ መሰረተ እምነት ማፍረስ ቀርቶ መነቅነቅ አልቻሉም አይችሉምም፡፡ የሆነው ሆኖ እራሳችንንም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችንን ከስህተት ለመጠበቅ የምንችለው እነሱ እንደ ጽድቅ የሚቆጥሩትን የማጭበርበሪያ ስልታቸውን ስናውቅ ስለሆነ ከቤ/ክ ተገንጥለው የወጡትንም ሆነ በቤ/ክ ውስጥ ሆነው የሚሰሩትን ጥፋት ከብዙው በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
ሀ/
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ
1. ኑፋቄያቸውን
በቤተ ክርስቲያን ሰም ማስተላለፍ
የሐሰት
ትምህርታቸውን እንደፈለጉ ለመስበክ የሚችሉት መድረክ ሲያገኙ ስለሆነ ብዙዎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱን መሪዎች ቸልተኝነት ተጠቅመው በቤተ ክርስቲያኒቱ የአብነት ት/ቤቶች፣ መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ገብተው ይማራሉ፡፡
ስለሆነም ከቤ/ክ አውደ ምህረት በተጨማሪ እንደ ጽዋ ማህበራት፣የጉዞ ማህበራትና በመሳሰሉት በማንኛውም ምዕመናንን በሚያገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ ባያምኑበትም የቤ/ክንን አስተምሮ ስለሚያውቁት እየመረራቸውም ቢሆን ትክክለኛውን ትምህርት ያስተምራሉ፡፡አመቺ ሆኖ ሲያገኑት ደግሞ በልባቸው ከቋጠሩት የጥርጥር መንፈስ እያደባለቁ እንክርዳዳቸውን ይዘራሉ፡፡በቃል ከማስተማር አልፈው በጋዜጣ፣በመጽሔት ፣በመጽሐፍ ፣በድረ ገጽ ፣ በካሴት ፣ በሲዲ፤ በቪሲዲና እንደ ይህንንም በመሳሰሉት ሁሉ በሚያዘጋጇቸው ትምህርቶች ፣መዝሙሮችና የመሳሰሉት ላይ ሰም ለበስ በሆነ አቀራረብ ያንኑ የተለመደ የኑፋቄ መርዛቸውን ጨምረው ካዘጋጁ በኋላ ከላይ ሽፋኑ“ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ህግና ሥርዓት የተዘጋጀ ” ተብሎ ይለጠፍበታል፡፡በዚህም ብዙ የዋሃን ምእመናን ሳያውቁ ከቀናችው ሃይማኖታቸው እንዲወጡ አድርገዋቸዋል፡፡
2. የስም
ማጥፋት
ይህንን
ስህተታቸውን የሚይዝባቸውንና ይህ የተዋህዶ ትምህርት አይደለም የሚላቸውን ክፍል ደግሞ አሳዳጅ፣ወንጌል ያልገባው፣ፈሪሳዊና የመሳስለውን ስም በመስጠት ያልተደረገውን ተደረገ ያልሆነውን ሆነ እያሉ ሰው እንዲጠላውና አገልግሎቱ እንዲስተጓጎል ያደርጋሉ ፡፡
3. ምዕመኑን
የኑፋቄ አካሄዳቸውን ማለማመድ
ሌላው
ምዕመናንን ለማጥመድና የራሱ የሆነውን እየረሳ የነሱን የስህተት ትምህርታቸውን፤ መዝሙራቸውንና የአነጋገር ዘይቤያቸውን
ለማለማመድና በየሰዉ ልብ ውስጥ ለማስረጽ የሚጠቀሙበት ዘዴ ደግሞ ምዕመኑ ተገቢ በሆነውም ባልሆነውም ጊዜ እልል ፣አሜን እያለ በስሜታዊነት እንዲያጨበጭብላቸው ማድረግ ነው፡፡ይህም አንዱና ዋነኛው
ዓላማቸው ሲሆን የመጨረሻው ግባቸው ደግሞ ምእመኑን ወደ ሌላ አዳራሽ መውሰድ ሳያስፈልግ እዚሁ ባለበት የነሱ ተከታይ መናፍቅ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
4. ምዕመኑን
እርስ በርሱ እንዲከፋፈል ማድረግ
ይህ
ሁሉ ተሞክሮ አላዋጣ ሲል ምዕመኑን እርስ በርሱ እንዲከፋፈል በተቀደሰው በቤ/ክ አውደ ምህረት ረብሻ እንዲፈጠር እስከ ማደረግ ይደርሳሉ፡፡ለምሳሌ በአዋሳ ቅ/ገብርኤል ቤ/ክ የፈጠሩት ውዝግብ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ከሁሉም በላይ አሳፋሪው ስራቸው ደግሞ ያገር ቆሻሻ ሰብስበው በዚሁ ቤ/ክ ውስጥ ማቃጠላቸው ነው፡፡ ውይ! ውይ !ውይ ! ይህንንና የመሳሰለውን ኢክርስቲያናዊና ኢሰብዊ ድርጊት እየፈጸሙ ደግሞ “ቤ/ክ እንወዳታለን ”የሚሉት ? በዚህም እራሳቸውን ካልሆነ በስተቀር ማንንም አያታልሉም ፡፡ይልቁንም ለእግዚአብሔርና ለቤቱ እንዲሁም ለምዕመናን ያላቸውን ንቀት ይህንንና ይህን በመሳሰለው የውንብድና ሥራቸው አሳይተዋል፡፡እንኳን በወንጌል አምናለሁ እሰብካለሁ የሚል ይቅርና ከአረመኔውም አይጠበቅም፡፡
5. ተገፋን
ተሰደድን እያሉ እሮሮ
ጅራፍ
እሱው መትቶ እሱው ይጮሃል እንደሚባለው ተረት ይህንንና የመሳሰለውን የውንብድና ስራ እየስሩ እንደገና ተገፋን ተሰደድን እያሉ እሮሮ ያሰማሉ፡፡ ነገሩማ ቃየል ምስክር በሌለበት ያፈሰሰው የወንድሙ የአቤል የደሙ ድምጽ እየጮኸበት እድሜውን በሙሉ የሚያገኘው ሁሉ የሚያሳድደው የሚገድለው እየመሰለው ሌላው ቀርቶ የራሱ ጥላ ሳይቀር እያስበረገገው እድሜውን በሙሉ እንደተቅበዘበዘ ነው ያሳለፈው፡፡የእነሱም እንዲሁ ነው፡፡
6. የማስመሰል
ይቅርታ መጠየቅ
እነዚህንና የመሳሰሉትን ስህተቶች
መፈጸማቸው ሲረጋገጥና እንደበፊቱ መስሎ ለመቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲደርሱ ደግሞ ተንኮላቸውን በልባቸው ይዘው ተሳስተናል ይቅርታ ይደረግልን ወደ ማለት ይመጣሉ፡፡ይህ አባባላቸው ከእውነት የመነጨ ቢሆን መልካም በሆነ ነበር ፡፡ የቤ/ክንም ተልእኮዋ የጠፉትን መፈለግ ተጸጽተው የተመለሱትን በንስሃ መቀበል ስለሆነ፡፡እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በትክክል መመለሳቸው የሚረጋገጠው ስህተታቸውን በግልጽ
ተናግረው ፤ በነሱ ምክንያት ከእውነት የሳቱትን ሰዎች ጭምር ይቅርታ ጠይቀው ፤ ተገቢውን የቤ/ክ
ቀኖና ተቀብለውና ፈጽመው ከተገኙ ብቻ ነው ፡፡
ለ/
ከቤተ ክርስቲያን ከወጡ በኋላ
ከላይ በጥቂቱ ለመግለጽ እንደተሞከረው መስሎ የማሳሳቱን ስራ መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ የደርሱት ክፍሎች ያልተነቃባቸውን ወኪሎቻቸውን ቤ/ክ ውስጥ ትተው የራሳቸውን ድርጅት መስርተው በግልጽ እየሰሩ ቢሆንም ያጸድቀናል ብለው ያመኑበትን የራሳቸውን እምነት ብቻ ማስተማር ሲገባቸው ከነባሮቹ መናፍቃን በባሰ ሁኔታ ቅድስት ቤ/ክንን በአፍም በመጽሐፍም እየሰደቧት ይገኛሉ፡፡ቀደም ሲል እኛ ስርዓቱን ለይስሙላ የምንፈጽመው የኛን ትምህርት ውስጥ ውስጡን በዘዴ ለማስተማር እንዲመቸን ነው ብለው ባቀዱት መሰረት በመጀመሪያ በተለያዩ ቅዱሳን ሥም የጀመሩትን ጽዋ ማህበር ቆየት ብለው ደግሞ የ”እንትን” ሕብረት (ካስፈለገ ስማቸውን መጥቀስ ይቻላል) እያሉ ስማቸውን በመለዋወጥና የጥፋት ተልእኳቸውን
በማጠናከር ብዙ ሊያጭበረብሩ ሞክረዋል፡፡
ይህንን ስውር ደባቸውን አውቀው ሲቃወሟቸው የነበሩትን የተዋህዶ ልጆች ወንጌል ያልገባቸው፤ሰውን በከንቱ የሚያሳድዱና ለሰው መዳን ግድ የሌላቸው ስለሆኑ ነው እንጂ ተሐድሶ የሚባል ነገር የለም እያሉ ሲክዱና ሲያስተባበሉ እንዳልነበር ይኸው ዛሬ
በራሳቸው አንደበት ስማቸውን “ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብለው በመሰየም በግልጽ መስራት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ሰውን ወደ ስህተት ጎዳና የሚመሩበትን ስውር ዓላማቸውን የቅድስና ስራ ለማስመሰል በዚሁ ጦማራቸው
ላይ “በመሠረቱ ጌታ “እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ”ሲል ያስተማረውን መሰረት በማድረግ ስልትን በየጊዜው መቀያየር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ነው፡፡”ብለው አረፉት፡፡እኛ ግን ቅ/ጳውሎስ ያስተማረን ሰውን መስሎ ለማሳሳት ስልቱን የሚቀያይረው ጠላታችን ሰይጣን መሆኑን ነው፡፡ እንጠቅሳለን “---እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡ይህም ድንቅ አይደለም ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡እንግዲህ አገልጋዮቹ ደግሞ የጽድቅን አገልጋዮች እንዲመስሉ ራሳቸውን ቢለውጡ ታላቅ ነገር አይደለም፤ፍጻሜአቸውም እንደ ሥራቸው ይሆናል፡፡”2ኛ ቆሮ.11፤13-15 ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስም “በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ”(ማቴ.10፤22)በማለት አስተማረን እንጂ እንደ እነሱ በጨለማና በየጓዳና ጎድጓዳው ስበኩ አላለም፡፡ “እንደ እባብ ብልሆች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ”የሚለውም ጥቅስ ያለአገባብና ያለቦታው የተጠቀሰ ነው፡፡
ለመሆኑ ይህንን ስም “ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ” ብለው ለራሳቸው ሲሰይሙ አውቀው ካልካዱት በስተቀር የቃሉ ትርጉም ምን እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ይኸውም ኦርቶዶክስ ማለት ቀጥተኛ ሃይማኖት ፣ ተዋህዶ ማለት ደግሞ በምሥጢረ ሥጋዌ ትምህርት ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን የሰውን ሥጋ መልበሱን አምነን የምንመሰክርበት የሃይማኖት መግለጫችን ነው፡፡እና ታዲያ ከዚህ ሃይማኖት ውስጥ ምኑ ነው የሚታደሰው ? ደግሞ ካልጠፋ ስም ? ምነው እነሱነታቸውን የሚገልጽ ሌላ ስም ቢያወጡና እንደልባቸው ቢፈነጩ አይሻልም ነበር ? ወይስ አሁንም በዚህ ስም የሚሳሳት ሰው አለ ብለው እያሰቡ ነው ይሆን ? እነሱው ያውቃሉ፡፡
ለዛሬው
ይቆየን ፡፡
ይቀጥላል፡፡
ዉድ ወልድ ዋህዶች እንደምን አላችሁ? እኔ መናፍቃኑ ለሚያወጧቸው ቤተክርስቲያንንና የቤተክርስቲን ልጆችን በሐሰት ለሚወነጂሉበትና በፀያፍ ቃላቶቻቸው ለሚዘልፉበት፤ እንዲሁም ሐሰተኛ ትምህርታቸው በሚያስተላልፍባቸው ጽሑፎቻቸው እሾህን በሾህ እንደሚባለው ባይሆንም በአዳራሾቻቸው የማውቀውን የክህደት ሰይጣናዊ የሆነውን ተውኔት እየጠቀስኩ አስተያየት እሰጣለሁ። ብዙ ጊዜ የኮሜን ስሜን እየቀያየርሁ ነው አስተያየት የምሰጠው። ያንም የማደርገው ካወጡት ክህደት አንፃር ይሄን ልጠቀም በማለት ነው። በቅርብ ግን ዳሞት በሚል ብዙ አስተያት ሰጥቻለሁ። በእናንተ እይታ አስተያየት መስጠቴ ስህተት አድርጌ ይሆን? በአስተያየቴስ ቤተክርስቲያንን አስነቅፊያት ይሆን? ሌላው መናፍቃኑ የተጠቀሙበት የመጠሪያ ስም ተሐድሶ ከሚለው ውጪ የቤተክርስቲያኗ ስም ነውና ስሟን በህግ ለምን አታስከብርም? ሰይጣን ይሄን ስም የመረጠው ለማወናበድና ለማሳሳት መሆኑ ግልጽ ነው። በተረፈ በእኔ አይታ የያዛችሁት ተሐድሶ ተብየዎቹ ምን እየሰሩና ምን እያሉ በሐሰት መንገድ እንደሚጏዙ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየጠቀሳች የምታደርጉት ማጋለጥና የምትሰጡት ትምህርት መልካም ሆኖ አግኝቸዋለሁና በዚሁ በርትታችሁ ቀጥሉ። ለእናንተም እግዚአብሔር ከፈታኙ ፈተና ድል የምታደርጉበትን ሐይል ይስጣችሁ።
ReplyDeleteአሜን ፡፡ውድ አስተያየት ሰጪ በጣም እናመሰግናለን፡፡የእኛም አላማ ሁሉም የተዋህዶ ልጅ እንደዚህ ነቅቶ እራሱንም ሆነ ሌላውን ከስህተት እንዲጠብቅ ስለሆነ አስተያየት ከመስጠትም በላይ ጉዳዩ የሁላችንም ስለሆነ አብረንም ብንሰራ ደስ ይለናልና አልተሳሳቱም፡፡ ከሁሉም ትህትናዎን እናደንቃለን፡፡
ReplyDelete