Sunday, January 25, 2015

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል ሦስት

ከቁጥር ሁለት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
     ቀደም ብለን ባስነበብናችሁ ሁለት ክፍሎች የቤተ ክርስቲያን ሳይሆኑ በተለያየ መንገድ የቤተ ክርስቲያን መስለው ስለሚያሳስቱ መናፍቃን የተወሰነ ግንዛቤ ለማሰጨበጥ ሞክረናል፡፡ሆኖም ዋና ዋናውን ጥፋታቸውን ለማመላከት ያህል ነው እንጂ የማሳሳቻ ስልታቸው ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም ፡፡ከሚናገሩትና ከሚጽፉት በተጨማሪ ዲያቆን ፣ካህን፣መነኩሴ፣ሰባኬ ወንጌል፣ወ...መስለው ለማሳሳት ካባውን፣ቆቡን፣መስቀሉንና ቀሚሱን ለብሰው ከበሮውን፣ ጸናጽሉን፣መቋሚያውንና የመሳሰለውን የቤ/ ንዋያተ ቅድሳት ይዘው በተለያዩ የሕዝብ መገናኛዎች ሳይቀር /የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጨምሮ/ የሐሰት ትምህርታቸውን በቤተ ክርስቲያናችን ስም ያስተላልፋሉ፡፡እኛ የተዋህዶ ልጆች የእኛና የእነሱ የሆነውን ለመለየት ነቅተንና ተግተን እራሳችንንም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችንን ከስህተቱ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላቸሁ

     ከላይ በመግቢያችን ላይ በጠቀስነው ወንጌል በጎችንና ተኩላዎችን መለየት የሚንችለው በሚሰሩት ሥራ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ከዚህ በመቀጠል ከእኩይ ሥራቸው አንዱ የሆነውንና በእነሱው ከሚዘጋጁት የተለያዩ መጽሐፎቻቸው አንዱ የሆነውንየአዲሰ ኪዳን መካከለኛየተባለውን መጽሐፋቸውን እኛ ደግሞ “‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን በሚል ርዕስ እናየዋለን፡፡


የመጽሐፉ የፊት ገጽታ
የመጽሐፉ ከፊል የውስጥ ገጽታ

የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ስለሆነ እሱን መፍራትን ያሳድርብን፡፡ማስተዋሉንና ጥበቡን ያድለን፡፡
     እንግዲህ ይህ ‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» የተባለው መጽሐፋቸው  በጥቅሉ ሲታይ የካህናትን አገልግሎትና የቅዱሳንን ምልጃ ክዶ ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ ዛሬም ስለኛ እየወደቀ እየተነሳ ወደ አባቱ ይማልዳል በማለት ላይ የተኮረ ነው፡፡ ይህ መጽሐፋቸው እንኳን ለሰው እውነትን ሊያስተምር ይቅርና አንዱ ምዕራፍ ከሌላው ምዕራፍ እየተጣረሰ ምን ለማለት እንደፈለጉ እንኳን ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ በአንዱ ርዕስ የካቡትን በሌላው ርዕስ ይንዱታል፡፡ ኦሮቶዶክሳዊ ለመምሰል ደግሞ ትርጉሙንና ዘይቤውን የማያውቁትን የግዕዝ ቋንቋ ከመጠቀም ጋር የቤተ ክርስቲያናችን ብቻ ከሆኑት ለምሳሌ እንደ መጽሐፈ ቅዳሴ፣መጽሐፈ ሰዓታት እና ከመሳሰሉት መጻሕፍትም ይጠቅሳሉ፡፡የሚጠቅሱትም ለማስተማር ሳይሆን ልክ የመጽሐፍ ቅዱሱን ቃል እያጣመሙ እንደሚተረጉሙት ከቃሉ ውጪ የሆነ ትርጉም እየሰጡ ለማሳሰት ነው፡፡በምን መንገድ እናሳስት ብለው ደክመው የሚያዘጋጇቸው መጽሐፎቻቸውም ሆኑ ጋዜጦቻቸው ግን ከስደብና ከአጓጉል ነቀፌታ ያለፈ ቁም ነገር ስለሌላቸው ዓይነ ልቡናው እንደነሱው በአዚማቸው የተያዘ ካልሆነ በስተቀር ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ይህንን መጽሐፍ  አንብቦ እውነት ነው ብሎ ሊቀበለው አይችልም፡፡ የምንናገረው እነሱ እንደሚሉት በከንቱ የጥላቻ ስሜት ተነስተን ሳይሆን እውንተኛነታችንን ለማረጋገጥ ከመጽሐፎቻቸው ቃል በቃል እያወጣን እንመለከታለን፡፡የሚዳኘንም  መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ያውም እነሱው ከያዙት 66 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳንወጣ፡፡

በመጽሐፉ ገጽ 7 የተወሰደ ‹‹ መጽሐፍ ቅዱስ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ ‹‹አንድ» እርሱም ክርስቶስ መሆኑን በግልጽ ተናግሮ ሳለ ከዚህ ጋር በመቃረን በራሳቸውና በእግዚአብሔር መካከል ፍጡራንን መካከለኞች አድርገው ያቆሙ ወገኖች ምንኛ ስተዋል! » በማለት መልስ ለመስጠት እንኳን በማይመች መልኩ እንደ ልመና እህል አንዱን ከአንዱ አደበላልቀው  ከጻፉት ዐረፍተ ነገር ውስጥ
/‹‹ዛሬም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ /አማላጅ/ ክርስቶስ ነው›› የሚለውንና
/‹‹በራሳቸውና በእግዚአብሔር መካከል ፍጡራንን መካከለኞች አድርገው ያቆሙ ወገኖች ምንኛ ስተዋል! ›› የሚለውን በተናጠል እንመልከት፡፡

/‹‹ዛሬም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው መካከለኛ /አማላጅ/ ክርስቶስ ነው››

የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ
       የአዲስ ኪዳን ጉዳይ ሲነሳ ከሁሉ አስቀድመን ልናውቀውና ልንረዳው የሚገባ ነገር አለ፡፡ይኸውም ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ለምን እና እንዴት ሰው ሆነ ? የቀደመውን ዕዳ በደላችንንስ የደመሰሰልን በምን ሁኔታ ነው? ለሚለው ጥያቄ በቂ መልስ ማግኘት ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች ወደ ኑፋቄና ወደ ክህደት አዘቅት የሚወርዱት  የዚህን ትምህርት ትክክለኛ ምሥጢር ካለመረዳት ነው፡፡
       ሁላችንም እንደምናውቀው እግዚአብሔር ወልድ ሰው የሆነበት ዋናው ምክንያት በአዳምና በሄዋን ምክንያት ወደ ሰው ልጆች ሁሉ የመጣውን ኃጢአት ለመደመሰስ ሲሆን ከዚሁ ጋር አያይዞ እሱን ተከትለን ልንሰራው የሚገባንን እንድንሰራ ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ህግ ሁሉ ፈጽሞ አርአያ ሆኖ ለማሳየት ነው፡፡
       በብሉይ ኪዳን በነበረው ሥርዓት የሰውን ኃጢአት ለማስተስረይ ያገለግል የነበረው በብሉይ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት አማካይነት የሚቀርበው የእንስሳት መሥዋዕት ነበር፡፡ይህ የእንስሳት መሥዋዕት የሰዎችን ጊዜያዊ ኃጢአት ከማስተስረይና ለአማናዊው መሥዋዕት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ከመሆን አልፎ በዕፀ በለስ ምክንያት የመጣውን ኃጢአት አስተስርዮ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ሊያሰታርቅ አልቻለም ፡፡በዚያውም ላይ መሥዋዕት አቅራቢው ሊቀ ካህን ራሱም ኃጢአት ሰላለበት አስቀድሞ ስለ ራሱ ቀጥሎ ለሕዝቡ መሥዋዕት ለማቅረብ በየዓመቱ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ይገባ ነበር፡፡እንዲሁም ይኸው ካህን ሰው እንደመሆኑ መጠን ሲሞት ክህነቱም ይሻራል፤በምትኩ ሌላ ይሾማል፡፡ይህንንም የሚያረጋግጥልን ዕብራውያን መልእክት ምዕ.9 በሙሉ በይበልጥ ቁጥር 6-7 እንዲህ ይላል፡፡….“ይህም እንደዚህ ተዘጋጅቶ ሳለ ካህናት አገልግሎታቸውን እየፈጸሙ ዘወትር በፊተኛይቱ ድንኳን ይገቡባታል፤በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፤ እርሱም ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስህተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፡፡---” በተጨማሪ ዕብ. ምዕ.10 ቁጥር 11 “ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያሰወገዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚህን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሟል፤…”ይላል፡፡ፍሬ ሃሳቡን ጠቅለል አድርገን ስናየው በብሉይ ኪዳኑ የመሥዋዕት አቀራረብ ሥርዓት አቅራቢው ሊቀ ካህናቱ፤መሥዋዕቱ የእንስሳት ደም፤መሥዋዕት ተቀባዩ ልዑል እግዚአብሔር እንደነበር እናስተውላለን፡፡አትኩሮት!!! (እግዚአብሔር ስንል አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው፡፡)
        በዚህ ዓይነት ሂደት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ከተፈጸመ በኋላ እንደ ተስፋው ቃል ከሶስቱ አካላት አንዱ እግዚአብሔር ወልድ የአዳም የልጅ ልጅ ከሆነችው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በድንግልና ተፀንሶ በድንግልና ተወለደ፡፡እንደ ሰው ሥርዓት ቀስ በቅስ አደገ፡፡በሰላሳ ዓመቱ ተጠመቀ፡፡ለሶስት ዓመታት ወንጌልን አስተምሮ በፅንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በመስቀል ፈጸመ፡፡ ማለት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ፡፡ጥልቅና ረቂቅ ወደሆነው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰው የመሆን ምሥጢር(ምስጢረ ሥጋዌ) በስፋት ለማየት ጊዜውም ሁኔታውም ስለማይፈቅድልን ለጀመርነው ርዕስ የሚሆነንን ብቻ እንመለከታለን፡፡
       እንግዲህ  ሰውን ከፈጣሪው ጋር ለማስታረቅ አቅም ያልነበረውን የብሉይ ኪዳን መሥዋዕትና ድካም ያለበትን የብሉይ ኪዳኑን ሊቀ ካህናት ተክቶ ክህነቱ ለዘላለም የማይሻረው ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣበትን የቤዛነት ሥራ ለመፈጸም ወደ መስቀል ሲወጣ እራሱ መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት፤እርሱን እራሱን መሥዋዕት አድርጎ እንዲሁም ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መሥዋዕት ተቀባይ ሆኖ አንድን መሥዋዕት አንዴና ለዘላለም በማቅረብ የጥሉን ግድግዳ አፈረሰ፡፡እዳ በደላችንን ደመሰሰ፡፡ይህንንም በመስቀል ላይ ሆኖሁሉ ተፈጸመብሎ በተናገረው ቃሉ አትሞታል፡፡(ዮሐ.19 በሙሉ በተለይ .30)እንግዲህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ያሰኘው ይህ ሰውን ከራሱ፣ ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለማስታረቅ የፈጸመው የቤዛነት ሥራው ነው፡፡ እንግዲህ ጌታችን ስለእኛ ተወለደ፣ተጠመቀ፣ተሰቀለ፣ሞተ፣ተነሳ፣ዐረገ ብለን ስንናገር በየጊዜው ይወለዳል፣ ይሰቀላል ይሞታል ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ማለደ ሲባልም ያንኑ የቀደመውን በሥጋዌ ዘመኑ የፈጸመውን ማዘከር ነው እንጂ ዕለት ዕለት ይማልዳል ማለት አይደለም፡፡በፍጹም፡፡
       አባታችን /ጳውሎስ ከሌሎቹ መልእክታት ለየት ባለ ሁኔታ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የብሉይ ኪዳኑ ትንቢትና ተስፋ በአዲስ ኪዳን ያገኘውን ፍጻሜ እያነጻጸረና እያመሳጠረ ያስተማረበት ክፍል ስለሆነ ሙሉውን መልእከት በጥንቃቄ መመልከት ይጠቅማል፡፡
ለጊዜው ግን የጀመርነውን ርዕስ የበለጠ አጉልተው የሚያሳዩንን የተወሰኑ ጥቅሶችን እንመለከታለን፡፡
  1. ዮሐ.1626 “እኔም ስለ እናነተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም
    ዮሐ.14፥14 “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ”
    ዮሐ.14፥12 “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡” በማለት ጌታችን በተናገረው አምላካዊ ቃሉ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ያደርጋቸው የነበሩትን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ያስተላለፈ መሆኑን ያስረዳናል፡፡
  2. “…አንድ እግዚአብሔር አለና፤ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፡፡…” (1 ጢሞ.25) በማለት ራሱን በመስቀል ላይ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ የመካከለኛነቱን ሥራ እዚያ ላይ እንደተደመደመ ያስረዳናል፡፡
  3. እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፡፡ዕብ.56 ይህ ማለት የመካከለኛነቱ ሥራ የሆኑትን ሁሉ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ (በመዋዕለ ሥጋዌው) ያጠናቀቃቸው መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
  4. “…እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፤… ”ዕብ.1012፡፡ይህም  አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ባቀረበው መሥዋዕት ከአዳም ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚወለደውን የሰው ልጅ ሁሉ ሲያድንበት ይኖራል ማለት ነው፡፡የተቀመጠ ይፈርዳል እንጂ አይማልድም፡፡እንዲሁ በሰው ሰውኛው እንኳን ብንመለከተው በክብር ወንበር ተቀምጦ የሚፈርድ ዳኛ መፍረዱን ትቶ ለተበዳዩ ሰው ጥብቅና ሊቆም እንደማይገባው ማለት ነው፡፡
  5. “…ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፤አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም...” 1 ቆሮንቶስ ምዕ.516 ይህም ሲብራራ ጌታችን በዚህ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአምላክነትንም የሰውነትንም ሥራ ሲሰራ እንደነበረው ሳይሆን፤ የመካከለኛነቱን ሥራ ስለፈጸመ አንድ ወገን የአምላክነቱን ሥራ ብቻ ይሰራል ማለት ነው፡፡
  6. ሐዋርያው /ጳውሎስ እንኳንመልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ ፤ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ ወደፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡” (2 ጢሞ.47-8) አለ እንጂ ከሞት በኋላ ሌላ ተጋድሎ ይጠብቀኛል አላለምኮ፡፡የሌሎቹም ቅዱሳን እንደዚሁ ነው፡፡ቃል ኪዳኑ ለዘላለም የማይሻረው ልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን በዚህ ምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለ ሰሩት የቅድስና ሥራቸው የሰጣቸውን ቃል ኪዳን ወደ ፈጣሪያቸው እያሳሰቡ፤ልክ እንደ መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ እግዚአብሔርን ከማመስገን በስተቀር ድካምና ውጣ ውረድ የለባቸውም፡፡ እንግዲህ በፍጥረቶቹ በቅዱሳን እንኳን ያለው ሁኔታ ይህን ከመሰለ ሁሉን ቻይ አምላክ  ለኛ ለሰዎች ሲል በዚህ ምድር ላይ የተንገላታው አንሶት እንደገና ዛሬም በሰማይ ላይ ሆኖ ይማልዳል ብሎ ማሰብና ይህንንም ትምህርት ነው ብሎ ማስተማር አሳፋሪ ነው ! በእውነት ! ፡፡
            ነገሩማ እነሱኢየሱስየሚሉትኮ የዓለም ቤዛ ለመሆን ወደዚህ ዓለም የመጣውን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን በማቴ.241-28  በመጨሻው ዘመን በስሜ ይመጣል (ይመጣሉ) ተብሎ የተነገረለት፤ /ዮሐንስም በራዕዩ ምዕ.13 በአውሬ መልክ ያየውና እግዚአብሔርንና ማደሪያዎቹን ለመሳደብ አፉን የሚከፍተውን፤ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ በአዋጅ የሚነግሰውን ሐሰተኛውን ክርስቶስ ነው፡፡ እንግዲህ አሁን የሚነግሥበት ጊዜ ስለተቃረበ ብዙዎቹ የእሱ መንገድ ጠራጊዎች በመሆን እውነተኛይቱን ሃይማኖት እነሱ ክደው ሌላውንም ለማሰካድ ተግተውና እንቅልፋቸውን አጥተው እየሰሩ ነው፡፡ይህም ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት ከሚሉት ጀምሮ ክርስቶስን አማላጅ፣ነቢይ፣ሁለት ባህርይ .. የሚሉትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ አይደለም ካሉ ያስረዱን!
        ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ መጽሐፋቸው ገጽ 8 ቁጥር .1 ላይ ደግሞ እንዲህ ብለው መስክረውልናል፡፡(የጠላት ምስክርነት እንዴት ያስደስታል! በነሱ ቤት ስህተት ያገኙ መስሏቸው ነው!) “ቀሳውስት ጸሎታቸውን በሚቋጩበት ወቅት ሁልጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ካህንና ሊቀካህናት መሆኑን ያወሳሉ፤እንዲህ በማለት ‹‹ይኅድግ ይፍታሕ ያንጽሕ ወይቀድስ እግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ሊቀካህናት ሠራዬ ኃጢአት ወደምሳሴ አበሳ » ይላሉ፡፡ትርጉሙም‹‹ኃጢአትን የሚያስተሠርይ በደልን የሚደመስስ ካህን ሊቀካህናት የሆነው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር ይበል ፤ይፍታ፤ያነጻ፤ይቀድስም»የሚል ነው፡፡በማለት የቤተ ክርስቲያን አምላክ ሳያስተውሉት እንዲመሰክሩ አድርጓቸዋል፡፡በዚህ የቡራኬ ቃል ውስጥ የሌለውን ያማልዳል የሚለውን ቃል ታዲያ ከየት አመጡት? ይቅር ይበል አለ እንጂ ይቅር ያስብል /ያማልድ/ አላለማ፡፡
       እንግዲህ ወንጌሉ የሚያሰተምረን እውነት ይህ ሆኖ ሳለ  “ጌታ ዛሬም የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ሆኖ ስለኛ ወደ አባቱ ይማልዳልእያሉ በፈጣሪያቸው ላይ መዘበታቸው ሊያሳፍራቸውና ሊጸጽታቸው ሲገባ፤ እውነተኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከእርሱ ከባለቤቱ በወንጌል በተማረችው መሠረት  ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ወልደ አምላክ ነው፤ምልጃ ተቀባይ ዋጋ ከፋይ ነው፤ ብላ የምታምነውን እምነት የሚተቹት የተለያዩ የፕሮቴስታንት ክፍሎችና ተሐድሶ ነን ባዮቹ ይህንን የስህተት ትምህርት ከየትኛው መጽሐፍ ቅዱስ አግኝተውት ይሆን? ደግሞስ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ያለውን እናምናለን እያሉ የሚያወሩትስ እንዴት ነው? ምናልባት እነዚህንና የመሳሰሉትን ክፍለ ትምህርቶች እንዳያነቡ የሚከለክል ህግ ይኖር ይሆን እነሱጋ ? ወይስ በእምነትና በትህትና ሆኖ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ብቻ ሊተረጎም የሚገባውን መጽሐፍ ቅዱስ በራሳቸው ሥጋዊና ደማዊ አስተሳሰብ ያውም ለጥፋታቸው እያጣመሙ እየተረጎሙት ይሆን ? እንግዲህ ለነዚህና ሌላም ተጨማሪ ምክንያት ካላቸው በስተጀርባ ሆኖ ከመተቸት፤የተለያየ ድረ ገጽ (ዌብ ሳይት) እየከፈቱ የመንደር አሉባልታ ሰብስቦ ከማውራት ያለፈ ቁም ነገር ካላቸው  እስቲ ከያሉበት ወደ አደባባይ ይምጡና መልስ ይስጡና !!!
       መቼም አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃ እንደሚባለው ነውና እንደዚህ ዓይነቱንስ ቅንነት ከነሱ አንጠብቅም ምክንያቱም /ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ .ምዕ. 6 ቁጥር 4-6 “አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን ሰማያዊውንም ስጦታ የቀመሱትን ከመንፈስ ቅዱስም ተካፋዮች ሆነው  የነበሩትን መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃልና ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል የቀመሱትን በኋላም የካዱትን እንደ ገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና፡፡በማለት መስክሮባቸዋል፡፡ ምናልባት ቢመጡም ልብ ከማድከም በስተቀር ጥቅም ስለሌለው እዚያው ባሉበት ወደ ልባቸው ተመልሰው እራሳቸውን እንዲመረምሩበትክርስቶስ ዛሬም ስለእኛ ይማልዳልሲሉ  ምን ማለታቸው እንደሆነ እንጠቁማቸዋለን፡፡ ምንስ ቢሆን የኛው አልነበሩም!?
  1. ዕለት ዕለት ስለእኛ ይማልዳል ማለት ዕለት ዕለት ይሰቀላል ማለታቸው ነው፡፡
  2. አንዴና ለዘለዓለም በመስቀል የፈጸመውን  ቤዛነቱን ከንቱ ማድረጋቸው ነው፡፡
  3. የክርስቶስን አምላክነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡታል፡፡በአምላክነቱ የሰውን ልመና ሰምቶ እንደ ፈቃዱ መስጠት እየቻለ ከማንና ለምን ይማልዳል ተብለው ቢጠየቁስ መልሳቸው ምን ይሆን ?
  4. ከባህርይ አባቱ ከአብና ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን የባህርይ አንድነትና እኩልነት መካዳቸው ነው፡፡
  5. ጌታ ዕለት ዕለት ስለእኛ ይማልዳል እያሉ የፈለጉትን እንዲሰሩ ለኃጢአት ሥራ እሳራቸውን እያበረታቱ ነው፡፡ ...
/“በራሳቸውና በእግዚአብሔር መካከል ፍጡራንን መካከለኞች አድርገው ያቆሙ ወገኖች ምንኛ ስተዋል! ”

በራሳቸውና በእግዚአብሔር መካከል ፍጡራንን መካከለኞች አድርገው ያቆሙ ወገኖች ምንኛ ስተዋል! ” ብለው የጻፉትም ከግብር አባታቸው ከዲያቢሎስ የተማሩት እጥፍ ድርብ ሐሰት እንጂ የእኛ / ትምህርት ስላልሆነ በመጣበት እግሩ ወደራሳቸው መልሰነዋል፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን በእርሷና በፈጣሪዋ መካከል ያቆመችው ነገር የለም ስለዚህም አልተሳሳተችም፡፡ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ ! ብለን እንድናመሰግነው የፈቀደልን አምላካችንና እኛ መካከል ማን ይገባል? አባትና ልጅ መካከል ? አይደረግም፡፡
ለማንኛውም የእነሱን የፈጠራ ሃሳብ ለነሱው እንተወውና በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማለት ምን እንደሆነ ጥቂት ግንዛቤ እንድናገኝ የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት፦
  1. በዚያን ጊዜ ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሳል፡፡ትን.ዳን.121
  2.  “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፡፡ሉቃ.118
  3.  “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፡፡ማቴ. 1810
  4. የተመረጠው ሙሴ በመቅሰፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ ፡፡መዝ.105/106/23
  5. በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ፡፡እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማለድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን፡፡” 2 ቆሮ.519-20
       እነዚህንና ሌሎቹንም ክፍለ ትምህርቶች ስንመለከት  ቅዱሳን ሰዎችም ሆኑ ቅዱሳን መላእክት ለኃጢአተኞች ይቅርታ ለማሰጠት በእግዚአብሔር ፊት ልመና ወይንም ምልጃ እንደሚያቀርቡ የሚገልጹ ናቸው፡፡የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች አንዱ በሽታቸው እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳን ማቃለል ስለሆነ ምናልባትም ‹‹መካከለኛ›› ሲሉ የቅዱሳንን ምልጃ ለማለትም ፈልገው ከሆነም የሚቃወሙት እኛን ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሱን መሆኑን ማወቅ አለባቸው፡፡
       እንግዲህ ጌታችን እንዲህ አድርጎ የጥሉን ግድግዳ ስላፈረሰልን እኛ ክርስቲያኖች ከፈጣሪያችን በተሰጠን የልጅነት ጸጋ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከጽንስ ጀምሮ በመስቀል የፈጸመውን የቤዛነት ሥራውን እያሰብን ማለትም ስለእኛ ብሎ መወለዱን ፣መጠመቁን፣መሞቱን፣ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱንና በክብር ወደ ሰማይ ማረጉን እያሰብንና እየመሰከርን፤ዳግም ለፍርድ መምጣቱን ተስፋ እያደረግን ልዑል እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፡፡እንለምናለን፡፡እንደ ፈቃዱም ይደረግልናል፡፡የምንጸልየውም ለራሳችን ብቻ አይደለም ፡፡ አንዱ ስለሌላው ይጸልይ ስለተባለ፡፡ከሥጋችን ደካማነት የተነሳ ዕለት ዕለት በምንሰራው ኃጢአት ከእግዚአብሔር እንዳንርቅ በኃጢአታችን እየተጸጸትንና ንስሃ እየገባን ጌታችን እራሱ በመረጣቸውና በሾማቸው ሐዋርያትና በእነርሱ እግር የተተኩት ካህናትም በተሰጣቸው ሥልጣን በእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቁናል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጡልንን  የሚከተሉትን ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንመልከት፡፡ ዮሐ.2115-17 2 ቆሮ.520-21 ያዕ.513-18 ... (መቼም መናፍቃኑ ይህም አይጥማቸውም አይደል? ካስፈለገ በዚህ ርዕስ ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡)

የተከበራችሁ አንባቢያን ለቀጣዩ ከዚሁ መጽሐፍ ‹‹እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ...›› በሚለው ርዕስ እንመለሳለን:: ለዛሬው ይቆየን::

2 comments:

  1. ዉድ ወልድ ዋህዶች በእግዚአብሔር ስም እንደምን አላችሁ?
    የሐሰቱንና እንግዳ የሆነውን ወደ ሞትም የሚወስደውን የመናፍቃኑን አዲስ ትምህርታቸውን ሐዋሪያት በሰኩት እውነተኛ ወንጌል እእየሱስ እያጋለጣችሁ ለምትሰጡት ትምህርት እጂግ መልካም ነውና በርትታችሁ ቀጥሉበት። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ያበርታችሁ።

    ReplyDelete