የተከበራቸሁ
አንባብያን!
በዚህ
የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "Bini
Zelideta" ከተባሉ
ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡
መልካም
ንባብ!
Bini Zelideta
“የተሃድሶ
መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ!”
ክፍል-1
(ስለ ነገረ ክርስቶስ) /መልዕክቱ የረዘመው ግጥሞች ስለበዙበት ነው/
መግቢያ
ቅድስት፤ኦርቶዶክሳዊት
ሃይማኖታችን ዕረፍት አልባ ዘመናትን ስታሳልፍ ዛሬ 2008 ዓመቷ ነው፡፡ ፈተናዎቿም እንደየ አዝማናቱና እንደፈታኞቿ የተለያዩ ነበሩ፡፡ ሠይፍ፣የዐላውያን መከራ፣የአናብሥት ትግል፣የክርስቲያኖች ስቃይ የሮም ኮሎሲየም አምፊ ቴአትር ትርዒት፣የቁም እሳት ቃጠሎ፣የካታኮምቡ ሕይወት፣የሠንሠለት ኑሮ እና የመንኩራኩር ስቃይ የመጀመሪያው እልህ አስጨራሽ ፈተናዋ ሲሆን እግር ተከትሎ፤ዓይነቱን ቀይሮ የመጣው የአርዮሳውያን ሃይማኖትን የመቀየር፣አስተምሕሮዋን የመበረዝ
እንቅስቃሴ ጣሯን፣ሰቀቀኗን፣መከራዋን አብዝቶባት ቆይቷል፡፡ ዮዲት ጉዲት፣የካቶሊክ ሚሲዮናውያን፣ጽንፈኛ አሕዛቦችና
የሉተር ርዝራዦች ዞረው ዞረው ሲሻቸው አንድ ላይ ሲሻቸው ደግሞ በፍርርቅ በመከረኛይቱ ሃይማኖት ላይ ቀንበር ሲጭኑ ኖረዋል ዛሬም ዕረፍት የላትም! የገሃነም ደጆች አይችሉአትም ተብሎ ስለተጻፈው አማናዊ ቃል ሁሉን አልፋ ዛሬ ብትደርስ ለሆዳቸው ያደሩ ሥጋውያን አስተምህሮዋን እናድሳለን ብለው ተነሡባት፡፡ ይህ ከቀደምት ዘመናት በዓይነትም በቅርጽም አካሄዱን ቀይሮ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ሥልት ይዞ የተነሣው ፕሮቴስታንታዊ ቡድን ስውር ተልዕኮውን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ በመሰንዘር ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል አሁንም በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ቅብ ይዘው፣ተቆርቋሪ መስለው መንገዷን ስታለች፣አስተምህሮዋ ልክ አይደለም፣አርጅታለች፣እናድሳታለን
ባዮች ሲሆኑ በትምርቶቻቸው እና ከዘፈን በተቃኙ መዝሙሮቻቸው ትውልድን መበረዝ የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል፡፡ በተለይም መዝሙሮቻቸው በአንድ ሌሊት ተደርሰው ንጋቱን ለጆሮ ስለሚበቁ ኑፋቄን ለማሰራጨት ደገኛ መሣሪያቸው ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡