Friday, April 29, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ ሰባት

ከክፍል አስራ ስድስት የቀጠለ

የተከበራቸሁ አንባብያን!
በዚህ የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡እንዲሁም በክፍል አስራ ስድስት ደግሞ "Bini Zelideta" ከተባሉ ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ ጥሩ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አስነብበናችኋል፡፡አሁንም ከዚህ በመቀጠል  ደግሞ የ"Blni Zelideta"ን ክፍል ሁለት መዝሙር ነክ ጽሁፍ አቅርበንላቸኋል!!!
መልካም ንባብ!

Bini Zelideta
“የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ!”
ክፍል-2 (በነገረ ማርያም)
 ስመ ማርያም የተሃድሶ መናፍቃን የንግድ ማስታወቂያ!
     የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ትውልድን በማጥፋት ተልዕኮ ውስጥ ሌላኛው አደገኛ አካሄድ ስመ ማርያምን መጠቀም! በአሁን ሰዓት ብዙ የዋሃንን ለማወናበድና ሥውር አጀንዳቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙበት ይህ ስመ ማርያም ለከፍተኛ ንግድ እየረዳቸው ይገኛል፡፡ኢየሱሴ፣ውዴ፣ፍቅሬ፣ናፍቆቴ በተሰኙ ዘጠኝ ቀረርቶዎች ላይ እንደ ውሃ ማንሻና ሚዛን ማስተካከያ አንድ ስመ ማርያም በመጫን የቀረርቶዎችን ቁጥር አሥር ማድረስ ላይ ያተኮረው እንቅስቃሴአቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀሙበት የንግድ ስልታቸው ነው፡፡ ‹‹የአገሬ ሰው ሞኝ ነው ማርያም የሚል ስም ካልሰማ መዝሙር ብጤ መስማት አይወድም፤አይገዛንም እንዳንከስር እስኪ አንድ ጣል አድርግበት!›› በሚል እሳቤ ብቻ ንግድን መሠረት ያደረገ ምንፍቅና ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለነገሩ አነርሱም ልክ ናቸው የአገሬም ሰው ሞኝ ነው! ስለ ምንም ይዘመር አይገደውም እንደው ማርያም የሚል ስም ይስማ ብቻ ሞንታርቦ በሰማበት መሰለፍ ይወዳል፡፡ ስለ የትኛዋ ማርያም እንደተዘመረ እንኳ አያጣራም! እነርሱም ይህን የምእመኑን ሁኔታ አጥንተው ነው ስሟን መነገጃ ያደደረጉት፡፡ እንዲያው ሰዎች እንዲከተሏቸውና ኦርቶዶክሳዊ ለመምሰል ብቻ ማርያም ከምላቸው ናት! እስኪ እናስበው እነዚህ ሰዎች አካሄዳቸው ልክ አይደለም ሲባል የብዙዎቻችን የዕለት ተዕለት ክርክር ‹‹ምን አጠፉ? ስለ ማርያም እየዘመሩ አይደል እንዴ?›› የሚል ከለላ እየሰጠን ዛሬ በገዛ ቤታችን አብረን የምናፌዝባት? ለመሆኑ ስለ ድንግል ማርያም ዘመርን ያሏቸውን መዝሙራት ከሲዲውና ሞንታርቦው ጋር አብረን ጮኽን ወይስ መረመርነው? እነርሱስ ንግዳቸው ነውና ይህን አደረጉት እንበል እኛ ምን ቤቶች ነን ያገኘነውን የምንቃርም? ያገኘነውን ከመሸመታችን በፊት እስኪ በተከፈተ ልብ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከምታስተምረው ትምህርት አንጻር ስለ ወላዲተ አምላክ፣ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ምን ዘመሩ? ወደሚል አስተሳሰብ እንምጣ፡፡ መዘሩንማ ይዘምሩታል ስሟንም ይጠቅሱታል ግን እንዴት ባለ መንገድ ዘመሩ? የሚለው ግን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡(ልቀጥል)
ጸጋሽ በዛ…ጸጋሽ በዛ የተሃድሶ መናፍቃን ቀረርቶ!
     እውነት ለመናገር ከተሃድሶ መናፍቃን ዘማርያን ውስጥ ጸጋሽ በዛን ያልዘመረው የለም! በነገረ ማርያም ስብከታቸውና መዝሙራቸው ሁሉ ‹‹ጸጋሽ በዛ…ጸጋሽ በዛ…..›› ከሚል ቃል የማይዘለው ዲስኩር ከመሰልቸት አልፎ ማቃር ደረጃ ደርሷል፡፡ ዘምረው…ዘምረው፣ጮኸው….ጮኸው የሞቱለት ይህ ጸጋሽ በዛን አንድምታ አለው የሚለውን ከማየታችን በፊት ከራሳቸው ልሳን ማድመጡ ተገቢ ነው፡፡
ምሳሌ-1
‹‹እንዴት ይደንቃል ማርያም ሆይ ጸጋሽ በዛ
ወልደሽ ጡት ያጠባሺው የዓለሙን ቤዛ››
ምሳሌ-2
‹‹ጸጋን የተመላሽ ሆይ ጌታዬን የወለድሺው
ያንን የሚነድ እሳት እንደምን ቻልሺው››
ምሳሌ-3
‹‹የኢየሱስ እናቱ እጅግ ደስ ይበልሽ
ተወዳጅ አማኑኤል ፀጋን ስለሰጠሽ››
      ጌታዬን የወለድሽ…ጌታዬን የወለድሽ ሌላኛው እንጉርጉሮ የተሃድሶ መናፍቃን ከጸጋሽ በዛ መዝሙራቸው ቀጥሎ ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው ይህ ጌታዬን ወልደሽ፣ጡት አጥብተሽ….የሚለው ሲሆን ከድግግሞሽ አልፎ መፈክር ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ምሳሌ-1
‹‹አንሻም ማስረጃ ድንግል ለክብርሽ
ከበቂ በላይ ነዉ ጌታን መዉለድሽ››
ምሳሌ-2
‹‹ብወድሽ ምክንያት ኖሮኝ ነዉ
ጌታዬን በመዉለድሽ ነው››
ምሳሌ-3
‹‹ቀዳሽሽ ቅዱስ ነው ስሙ መሃሪ ቃሉን ለሰሙ
በፍቅር ባሪያው ነኝ ብለሽ ንጉሡን ለመውለድ ታደልሽ››
     ምነዋ! መዝሙሮቻቸው ሁሉ (ጸጋሽ በዛ እና ጌታዬን ወለድሽ) ብቻ ሆነ ካሉ ዓላማው ሰዎች ሁሉ ስለ ድንግል ማርያም የሚኖራቸው ዕውቀት ጌታን ስለመውለዷ እና ጸጋን እንደተመላች ብቻ ከማወቅ እንዳያልፉ የታሰበ ሴራ ነው፡፡ከሉቃስ ወንጌል በቀር ድንግል ማርያምን የሚያወሳ ጥቅስ የሌለ ይመስል ትውልዱን በአንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ አሥሮ የማቆም ሥውር ደባ ተፋፍሞ ቀጥሏል አስተዋይ ግን የለም፡፡ መናፍቃንን እስኪ ስለ ድንግል ማርያም ጥቀሱልን ብትሏቸው ከዚሁ ጸጋሽ በዛና ጌታን ከመውለዷ ውጭ አይጠቅሱም፡፡ የእኔ ተቃውሞ ለምን ‹‹ጸጋሽ በዛን›› እና ‹‹ጌታዬን ወለድሽ›› ብለው ዘመሩ አይደለም! ይልቁንም መዝሙሮቻቸው ሁሉ ለምን ‹‹ጸጋሽ በዛ›› እና ‹‹ጌታን ወለድሽ›› ብቻ ሆኑ እንጂ! እነዚህ አስመሳይ የመናፍቃን አጋፋሪዎች ቀደምት አበው በብዙ ኅብር የደረሷቸውንና ያስተማሯቸውን የነገረ ማርያም አስተምህሮዎች ለማስረሳት ታጥቀው የተነሡ የሠይጣን ሠራዊቶች በመሆናቸው እንጂ እውነተኞች ቢሆኑማ ድንግልን ማመሥገኛ ብዙ ምክንያት ነበራቸው፡፡ ጸጋን ስለማግኘቷ እና አምላክን ስለመውለዷ ብቻ በመጠቃቀስ መሠረታዊውን አስተምሕሮ የማይደፍሩ ተኩላዎች! አምላክን ስለመውለዷ እና ጸጋን ስለመሞላቷማ አሕዛቡም፣ካቶሊኩም፣መናፍቁም፣ሠይጣንም……ሌላው ሌላውም የማይክደው ሃቅ ነው! እውነተኛ ኦርቶዶክሳውያን ነን ካሉማ ለምን ክብሯን፣ቅድስናዋን፣አማላጅነቷን፣ዘለዓለማዊ ድንግልናዋን፣ከውርስ ኃጢአት ነጻ ሆና መፀነሷን አይዘምሩም? መሠረታዊ ከሆነው የነገረ ማርያም አስተምህሮ ውስጥ አንዷን ብቻ ዘግነው፣ቆንጥረው በመጮኽ ብቻ ኦርቶዶክሳዊነት የሚሰማቸው ጥቅመኞች ናቸው እንጂ፡፡ እነዚህ አድር ባዮች አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ፣ቅዱስ ያሬድ፣ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፣አባ ሕርያቆስ እና መሰል ቅዱሳን አባቶች የደረሷቸውን ውዳሴ ማርያም፣መጽሐፈ አርጋኖን፣ተዓምረ ማርያም፣ቅዳሴ ማርያም እና አንቀጸ ብርሃንን መነሻ በማድረግ የዘመሯቸው መዝሙራትም የሉም! እንደው ይህስ ይቅር መጽሐፍ ቅዱሱ ያሰፈረውን ክብሯን እና ቅድስናዋን እንኳ ለምን አይዘምሩም? ቅዱስ ዳዊት፣ልጁ ሰሎሞን፣ነቢዩ ኢሳይያስ፣ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለ ድንግል ማርያም ምን ተናገሩ? ከሚለው በመነሣት ሲዘምሩ አይታዩም አይደፍሩምም! ከአዳም ጀምሮ እንዴት ባለ ምሳሌ እንደተነገረች፣የሙሴ ጽላት፣የጌዲዎን ፀምር፣የኖኅ መርከብ፣የያዕቆብ መሰላል ሆና መገለጧን እና በአበው ልብ እንዴት ስትታሰብ እንደኖረች ታላቁ መጽሐፍ በገሐድ የከተበው ሃቅ ሆኖ ሳለ የእነርሱ ዝማሬ ከሉቃስ ወንጌል (ጸጋሽ በዛና ጌታዬን ወለድሽ)የዘለለ አይደለም፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ ማስረሳት የሚለው ትልቁ ስትራቴጂ ነው፡፡ ነገሩ በዚህ ከቀጠለ ነገ ‹‹ድንግል ማርያም ከሉቃስ ወንጌል ውጭ አልተጠቀሰችም!›› የሚል ትውልድ መፈጠሩ አይቀርም፡፡ሲቀጥል ደግሞ አሁን የሚጠቃቅሷትንም ነገር ወደፊት አይገፉባትም መቅረቷ አይቀሬ ነውና፡፡ ቀስ በቀስ ድንግል ማርያምን ከልቦናችን የማሳደድ ነገር በሰፊው እየተስተዋለ ነው፡፡ ክብሯንና አማላጅነቷን ማስረሳት ታቅዶ እየተሠራበት ያለ ነገር ነው፡፡ (እንደኛው ሰው ነች፣ስግደት ለጌታ ብቻ፣አንድ መዝሙር ይበቃታል…..) የሚሉና መሰል ሃሰቦች በሰፊው ይስተጋባል፡፡ ሥውር ደባቸው ሳይነቃባቸው በፊት ሑለትና ሦስት መዝሙራት በስሟ ይለቁ ነበር አሁን ግን በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆል ቁጥር ማሟያ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በስሟ የሚወጡትም መዝሙር ተብዬዎች ፍጹም ክብሯን የማይገልጹና የማይመጥኑ ከንቱ ቀረርቶዎች ናቸው ለዚህም ጥቂት
ምሳሌዎችን ላንሣ፡-
‹‹በልጅሽ የምናምን እኛም ወዳጆችሽ
እንዳንቺ ከጸናን መንግሥቱን ነን ወራሽ››
     (በልጅሽ ብቻ እንጂ በአንቺ ብለው የመዘመር ፍላጎት የላቸውም ከዚህ ባለፈ እመቤታችን እንደማንኛውም ሰው በተጋድሎ ገነት እንደገባች አድርገው ዘምረውታል )
‹‹ከነሶምሶን ሁሉ በልዩ ናዝራዊ
ቃሉን በእምነት ልብ ያመንሽ ወንጌላዊ››
     (የድንግል ማርያምን ክብር በወረደ ሁኔታ ከሶምሶን ናዝራዊነት ጋር አነጻጽረውታል ልክ ሰውየው የጌታን ጨርቅ እና የድንግል ማርያምን ክብር እንዳነጻጸረው ማለት ነው! ከዚህ ባለፈም ወንጌላዊ ነሽ በማለት ምናምቴ ስም መስጠት ያዘወትራሉ እውን በቤተ ክርስቲያን ቋንቋ ድንግል ማርያም ወንጌላዊ ናትን?)፡፡
‹‹ተመሰጠ ልቤ ዐወደው ፀሎትሽ
የረዳሽን አምላክ አመሰንኩ ልጅሽ››
     (ሁል ጊዜ አምላክ በርሷ ስላደረገው ነገር ብቻ ከመዘመር በቀር በምልጃና ጸሎቷ ስላደረገችላቸው አልያም ስለምታደርግላቸው ነገር አይዘምሩም፡፡ ለመሆኑ የረዳሽን አምላክ ማለትስ ምን የሚሉት አገላለጽ ነው? አምላክን መውለዷ ከሆነ ትወልደው ዘንድ እርሱ ራሱ መረጣት እንጂ እርሷ እንድወልድህ እርዳኝ ብላው አይደለም!)፡፡
‹‹ደስ ይበልሽ ደስታን ጮኸሽ ተናገሪ
ስለመድኃኒትሽ በእልልታ ዘምሪ››
     (በርሷ ምክንያት መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ ማግኘታችንን ከመግለጽ ይልቅ ስለ መድኃኒትሽ ዘምሪ ሚል ቃል ተጠቅመዋል፡፡ እዚህ ጋር እንዲህ አድርጊ፣እንዲህ በዪ እያሉ ድንግል ማርያምን በተራ ስንኝ እያዘዟት መሆኑን አስተውል! ለመሆኑ ድንግል ማርያምን ዘምሪ….እልል በይ…..ለማለት ማን አዛዥ አደረጋችሁ? ለመሆኑስ እንዴት መሆን እንደሚገባን እርሷ ናት እኛን ማስተማር የነበረባት? ወይስ እኛ ነን እርሷን እንዲህ አድርጊ እያልን የምናስተምር??? ከዚህ ባለፈም እንደራሳቸው የተከፈተ ጉሮሮ ጩኸሽ ተናገሪ የሚል ስድ ቃል ተጠቅመዋል)፡፡
 አንጻራዊ አመስግኖ/አስታክኮ ማመስገን/ሌላኛው ስትራቴጂ!
     ይህ የሦስተኛ ወገን መስግኖ ወይም አንዱን ታክኮ፣ተንተርሶ ሌላን የማመስገን ስልት ዛሬ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ ‹‹ልጅሽ ፍቅር ነው፣ልጅሽ ቅዱስ ነው፣ልጅሽ እንዲህ ነው…›› እያሉ ይዘምራሉ እንጂ ‹‹አንቺ ቅድስት ነሽ፣አንቺ ብጽዕት ነሽ፣አንቺ ንጽኅት ነሽ፣አንቺ እንዲህ ነሽ…..›› ብለው በፍጹም አይዘምሩም፡፡ በርሷ ትከሻ ላይ ቆመው(እርሷን ረግጠው) ክርስቶስን ማየት ይፈልጋሉ እንጂ በርሷ ውስጥ ሆነው ክርስቶስን ማየት አይፈልጉም! እርሷን ተንተርሰው ክርስቶስን ብቻ ማመስገን ይፈልጋሉ እንጂ እርሷን በቀጥታ ማመስገን አይፈልጉም! ይህ አካሄድ በድንግል ማርያም አንጻር ጌታን ብቻ የማመስገን ልዩ ስልት ሲሆን ‹‹ኢየሱስ ብቻ/Only Jesus/›› ከሚለው የሉተራውያን አስተምህሮ በቀጥታ የተወሰደ ነው፡፡ ዓላማው ጌታ አይመስገን አይደለም እርሱ በሁሉ የተመሰገነና የሚመሰገን ልዑለ ባሕርይ አምላክ ነው ነገር ግን ክብርት ለሆነች እናቱም ቀጥተኛ ምሥጋና ይገባታል የሚለው መዘንጋት የለበትም! ዛሬ ዛሬ ስሟን መጠቀሚያ በማድረግ ብዙ ብዙ እየተሠራ ነው፡፡ እኛ የምናየው ስመ ማርያም መጠራቱን ብቻ ሲሆን አነርሱ ግን ኢላማቸው ሌላ ነው፡፡ በተለይ ይህ አንጻራዊ አመስግኖ በብዙዎች ያልተስተዋለና ቶሎ ሊነቃበት የሚገባ ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን አንጻራዊ አመስግኖ ለማስረዳት አንድምሳሌ ላንሣ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 11፥27 ላይ ‹‹ይህንንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው›› ይላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመስግኖ አንጻራዊ አመስግኖ ይባላል፡፡ በትርጓሜ ወንጌል እንደተቀመጠው ይህች ሴት አመጣጧ ውዳሴ ከንቱ ሽታ እንደነበር ተጽፏል፤እንዲህ ብዬ ባመሰግነው እርሱም ያመሰግነኛል ብላ ማለት ነው፡፡ ለዚህም አካሄዷ የተጠቀመችው ደግሞ ጌታችን አንጻር ድንግል ማርያምን ማመስገን ነው፡፡ አነጋገሯ ስህተት የለውም ነገር ግን ውዳሴ ከንቱ ሽታ ይህን በመናገሯ ግን ጌታ ገስጿቷል፡፡ በርሱ አንጻር እናቱን እንዲህ ብዬ ባመሰግን እርሱም አጸፋውን ይመልስልኛል በሚል እሳቤ ነው የተናገረችው፡፡ ይህን ምሳሌ ያነሣሁት አንጻራዊ አመስግኖ ወይም አንድን ነገር ተንተርሶ ሌላን ማመስገን ምን እንደሚመስል ለማሳየት ብቻ እንጂ ስለ ሴቲቱ ለማውራት ፈልጌ አይደለም፡፡ እነዚህ ግለሰቦችም ዛሬ የተያያዙት ስልት አካሄዱ እንዲህ ነው፡፡ ድንግል ማርያምን ታከው ጌታን ብቻ ያመሰግናሉ እንጂ እርሷን በቀጥታ አያመሰግኑም፡፡ እንደ ትክክለኛው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ግን ክብርና ምሥጋና ለሚገባው ሁሉ እንደየ ቅድስናው ደረጃ ቀጥተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ ምንም መጠማዘዝ ሳያስፈልገው፣በዚህ በዚያ ሳይባል፣መሽሎክሎክ ሳይኖር ማለት ነው!!! ድንግል ማርያምም ያለ ምንም ተዘዋዋሪ ቃል በቀጥታ ልትመሰገን ይገባል! ይህም ሲሆን መጽሐፉ የሚደግፈው እንጂ እኛ ስለፈለግን አልያም ደስ ስላለን አይደለም! ካሴት ለመቸብቸብም አይደለም! ቃሉ ስለሚያስገድደን እንጂ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት ኤልሳቤጥ ለአዲስ ኪዳን ምስክሮቻችን ሲሆኑ ከአዳም ጀምሮ እስከ ጌታ ልደት ድረስ በትውልድ ሁሉ ስትታሰብና ስትመሠገን መኖሯን ብሉይ ኪዳንም ልብ ይሏልና፡፡ አበው እና ውሉድ ስሟን፣ክብሯን በቀጥታ እየጠቀሱ አመሰገኗት እንጂ እንደ ዛሬዎቹ እናውቃለን ባዮች ስሟን መሸቀጫ አላደረጉትም! አመሰንም አላመሰገንም ክብራችን የሚጨምርና የሚቀንስ የእኛው አንጂ እርሷማ በቅዱሳን መላእክት የተመሰገነችና የምትመሰገን፣በልዑል ልጇም አንዴ የከበረች ናት፡፡ እኛ በየካፌው ተጎልተን በምንጽፈው ኮልኮሌ ግጥምና እና በየፓርኩ በምንለቀልቀው ምናምንቴ ስንኝ የድንግል ማርያምን ክብር እናጎድፋለን ማለት የቂልነት መጀመሪያ ነው! እስኪ በአንጻራዊ አመስግኖ ከተሰገሰጉ መዝሙር ተብዬ እንጉርጉሮዎች ጥቂት ላንሣ፡፡
ምሳሌ-1
‹‹ፍቅርሽ ኢየሱስ ነው ውድሽ
ታላቅ አድርጋዋለች ነፍስሽ
ዜማዬ ነው ድንግል ዜማሽ››
      ይህ ስንኝ ድንግል ማርያምን በቀጥታ የማመስገን ሃሳብም ፍላጎትም የለውም ቁመናው ግን ይመስላል! እንደምናወራላቸው ስመ ማርያምን ይዟል ነገር ግን ተጠማዞ….ተጠማዞ….ሌላ ሌላ ነገር የሚሰብክ ነው፡፡ ከአንጻራዊ አመስግኖ ባለፈም ስድ ግጥም ነው፡፡ ፍቅሬ፣ውዴ ከማለት አልፈው እርሷንም ውድሽ፣ፍቅርሽ ወደማለት የተሸጋገሩበትን አካሄድ ያሳያል፡፡
ምሳሌ-2
‹‹ዜማሽን ላድርገው ዜማዬ
ልዘምር ሽንፈትን ጥዬ
ትልቁን ታላቅ ላድርገው
መሻገር በምስጋና ነው››
     ይህም የመዝሙር ስንኝ ስሟን መታከኪያ አደረገ እንጂ እርሷን በቀጥታ የማመስገን አዝማሚያ የለውም፡፡ በድንግል ማርያም አንጻር ‹‹ትልቁን ታላቅ ላድርገው›› ማለት ፈለጉ እንጂ ‹‹ታላቁን አምላክ ለመውለድ ያበቃትን ታላቁን ንጽኅናዋን እና ቅድስናዋን›› መጥቀስም ማመስገንም አልፈለጉም!
ምሳሌ-3
‹‹በስደት በግብፅም ሆነሽ
በደስታ ቃና ታድመሽ
ለልጅሽ ፍቅርሽ አንድ ነው
ያንቺ ቃል እርሱን ስሙት ነው››
     ይህም ስንኝ አንጻራዊ አመስግኖ ሲሆን ‹‹ያንቺ ቃል እርሱን ስሙት ነው›› በሚለው ሐረግ በቀጥታ ምን ማስተላለፍ እንደፈለጉ ያሳያል፡፡ በቃና መገኘቷ ለማማለድ ሳይሆን እርሱን ብቻ ስሙት ለማለት እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ አንድም አታማልድም የሚል ቃል በቀጥታ እንዳይጠቀሙ ስለፈለጉ በእጅ አዙር አታማልድምን ለመስበክ ‹‹እርሷም እኮ እርሱን ስሙት ነው ያለችው ለምን እርሱን ብቻ አታዩም!›› ዓይነት ትምህርት እያስተማሩን ነው፡፡ በቃና የመገኘቷን ነገር ማቃለላቸውን አስተውል! እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች የተሃድሶ መናፍቃን ድንግል ማርያምን በቀጥታ ለማመስገን ምን ያህል እንደተቸገሩ የሚያሳይ ሲሆን በነገረ ማርያም ዙርያ ኦርቶካሳዊ መዝሙራትስ ምን ይመስላሉ ብሎ መመልከቱ የተሃድሶ መናፍቃን በነገረ ማርያም ዙርያ ከዘመሩአቸው መዝሙራት ጋር ያለውን ሠፊ ልዩነት ለማነጻጸር ስለሚረዳ የጥቂት ኦርቶዶክሳውያንን መዝሙራት በምሳሌ ላቅርብ፡፡
ምሳሌ-1(በኩረ መዘምራን ኪነ ጥበብ ወ/ቂርቆስ)
‹‹የሲና ሐመልማል የሙሴ ጽላት
የሲሎንዲስ ጥበብ እጸ መድኃኒት
አሁን በምን በምን እንመስልሻለን
እጹብ እጹብ ብለን እናወድስሻለን››
      ዝማሬ መላእክት ያሰማልንና እንዴት አድርጎ እንደዘመረ ልብ በሉ፡፡ ሙሴ በነደ እሳት በሲና ሳትቃጠል ያያት እጽ ድንግል ማርያም እንደሆነች ጠቅሶ ለሲሎንዲስ ጥበቡ እንደነበረች አነሣ (ውዳሴ ማርያምን ከመጽሐፍ ቅዱስ በማጣመር)፡፡ ኋላም ምሳሌ የሌላት እናት መሆኗን ገልጾ ክብሯን፣ቅድስናዋን መግለጽ የማይቻል ሲሆንበት ዕጹብ ብሎ ዘጋው፡፡
ምሳሌ-2(ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ)
‹‹በሔዋን ምክንያት በለሷን በልተን ገነት ቢዘጋ
በአንቺ እናትነት ዳግም ተዛመድን ከአምላካችን ጋ
የሲዖል ጽልመት በልጅሽ ጠፍቶ ብርሃን ሆነ
ዕረፍት አገኘን የምሕረት ዓመት ባንቺ ዘመነ››
     ዝማሬ መላእክት ያሰማልንና ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ ውዳሴ ማርያምን መነሻ በማድረግ ፍጹም ልዩ የሆነ ኦርቶዶክሳዊ አስተምሆን በመጠቀም ዘምሮልናል፡፡ መዝሙሩ ያለመጠማዘዝ በቀጥታ ድንግል ማርያምን የሚያመሰግን ሲሆን ነገረ ድኅነትን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ለዛ ያለው ዝማሬ ነው፡፡ ‹‹ስለሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን›› የሚለውን የውዳሴ ማርያም ክፍል በመተርጎም በልጇ ሞት እንደዳንን በርሷም ዕረፍት እንዳገኘን አስተምሮናል፡፡ እውነት ነው ድንግል ዕረፍታችን ናት! መዝሙር ትምህርት የሚሰጠው እንዲህ ባለ መንገድ ምሉዕ ተረድጎ ሲዘመር ነው!
ምሳሌ-3(ቀሲስ ምንዬ ብርሃኑ)
‹‹የአምላክን ይመስላል ድንግል ውበትሽ
ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽ
ድንግል የዳዊት ልጅ የአባትሽን ቤት እርሽ
በዓለሙ ንጉሥ ታይቷል ውበትሽ››
     በድጋሚ ዝማሬ መላእክት ያሰማልንና እንዴት አድርጎ እንዳመሳጠረው ተመልከቱ፡፡ የአምላክን ይመስላል ድንግል ውበትሽ የሚለውን የጠቀሰው ‹‹የእመቤታችን መልኳ እንደ ልጇ ነው›› ከሚለው የተዓምረ ማርያም መቅድም ላይ ሲሆን እንደገና ወደ ብሉይ ኪዳን በመሄድ ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽ››(ማኅ ዘሰ4፡7)የሚለውን በመጥቀስ ከውርስ ኃጢአት ነጻ ስለመሆኗ ከገለጸ በኋላ በድጋሚ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ልጄ ሆይ ስሚ አድምጪ፣ጆሮሽንም አዘንብዪ የአባትሽንም ቤት ርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዷልና››(መዝ 45፡10)የሚለውን በመጥቀስ እጹብ በሆነ መንገድ ቅድስናዋን፣ክብሯን ከመጽሐፍ ቅዱስ፣ከተዓምራት መጽሕፍት፣ከውዳሴ ማርያም እና መሰል መጻሕፍት እያጣቀሰ አሳይቶናል፡፡
ምሳሌ-4(ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ)
‹‹ስደተኛው ያዕቆብ በመንገድ ተኝቶ
እጅጉን ተጽናና ድንግል አንቺን አይቶ
ለእኔም ለኃጢአተኛው መድኃኒቴ ነሽ
ከለላ ሁኚልኝ ጠላቴ እንዲሸሽ››
      አሁንም ዝማሬ መላእክት ያሰማልንና መጀመርያ ያዕቆብ በሎዛ ተንተርሶ ድንግል ማርያምን እንደተመለከታት አነሣ ከዚያም በርሷ መጽናናቱን ጠቀሰ በመቀጠል ወደ ተዓምረ ማርያም መቅድም በመመለስ ‹‹ውዳሴዋን አታስታጉሉ ለእናንተ መድሃኒታችሁ ናትና……›› ከሚለው በመውሰድ ለኔ ለኃጢአተኛው መድኃኒቴ ነሽ አላት በስተመጨረሻ ደግሞ በደሉን አምኖ ጠላቴ እንዲርቅ ከለላ ሁኚልኝ ይላታል ወይ ግሩም! (እነርሱ ግን ጽድቃችን ሰማይ ነካ ይሉናል)፡፡
ምሳሌ-5 (ሊቀ መዘምራን ይልማ ኃይሉ)
‹‹ድሆችን እንጀራ ያጠግባል በእርሷ
ምድርም ታበራለች በጸጋ ታድሳ
የካሕናት ሞገስ የደኅንነት ልብስ
በእመቤታችን ሁሉ ሚታደስ››
     ይህ ዝማሬ ቤተ ክርስቲያንን በመዝሙራችን እናድሳለን ብለው ለተነሡ ሠዎች ከዘማሪ ይልማ ኃይሉ የተሰነዘረ ቀጥተኛ የአጸፋ ምላሽ ነው፡፡ እናድሳለን ባዮችን የሚያድስ ድንቅ ዝማሬ! ይህ ስንኝ ድንግል ማርያምን ለማመስገን በጓሮ መግባት አላስፈለገውም፣መጠማዘዝም አላስፈለገውም በቀጥታ ፍጥረት ሁሉ በድንግል ማርያም እንደሚታደስ ተናገረ እንጂ፡፡ እውነት ነው በድንግል ታድሰናል!
ምሳሌ-6(ዘማሪ ዲያቆን ቴዎድሮስ ዮሴፍ)
‹‹አንቺ የምሥራቅ ደጃፍ ሕዝቅኤል በራዕይ ያየሽ
የመዳናችን ምዕራፍ የጽድቃችን ምክንያት ነሽ
ሕይወት ፈሰሰ መቅደስሽ እየቀዳን ጠጣነው
ልጅሽ ሲባርከን ነው በልምላሜ ያደግነው››
      ሕዝቅኤል 44፡1 ላይ ያለውን የዘለዓለማዊ ድንግልናዋን ምስጢር ይጠቅስና የመዳናችን ምክንያት መሆኗን ያነሣል፤ቤተ ክርስቲያን በልጇ ምክንያት የተጎናጸፈችውን ሕይወት እና ያገኘነውን በረከት ይዳስሳል፡፡ ተሃድሶዎች ዛሬ ነገ ሳትሉ ከነዚህ ብርቅዬ ዘማርያን እግር ሥር ተቀምጣችሁ ተማሩ፡፡
 ማጠቃለያ
     ኦርቶክሳዊ መዝሙራት መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ በማድረግ፣ገድላትን፣ድርሳናትን፣የተዓምራት መጻሕፍትን፣ኪዳንን፣ቅዳሴን ሁሉ ያካተቱ ሆነው መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከዚያ ባለፈ መዝሙራት የማንም ሥውር አጀናዳ ማስፈጸሚያና የግለሰቦች ግጥም መለማመጃ አይደሉም! ድንበር አበጅቶ ከዚህ ውጭ አልዘምርም፣ከዚህ ፈቀቅ አልልም በማለት የሚዘጋጁ ከሆነ ግን ምንፍቅና ነው፡፡ በተለይ በዚህ በነገረ ማርያም ዙርያ የተሃድሶ መናፍቃን የሚለቋቸው መዝሙር ተብዬ አንጉርጉሮዎች ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ለዛ የሌላቸው ናቸው፡፡ስለምን መጻሕፍትን አጣቅሰው በትክክል መዘመር ተሳናቸው ቢሉ የመጀመሪያው ምክንያት ዕውቀቱ ስለሌላቸው ነው፡፡ እውነት ለመናገር የተሃድሶ መናፍቃን ስለ ድንግል ማርያም አንደው ለደቂቃ ስበኩ አልያም አስተምሩ ቢባሉ የሉቃስ ወንጌልን መቶ ጊዜ ቢደጋግሙት እንጂ ከዚያ የዘለለ ቃል እንደማይናገሩ ግልጽ ነው፡፡ ስለ ድንግል ማርያም መናገር የተሣናቸው ደግሞ ስለእርሷ ማወቅ ስለማይፈሉጉ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ቅድስት ኦርቶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ ደግሞ ከፈጣሪ በታች ሁሉንም ቅዱሳን እንደየ ቅድስናቸው ማዕረግ ማክበርና ማመሥገን ተገቢ በመሆኑ ላለፉት 2ሺህ ዘመናት ይህን ስትተገብር ኖራለች እስከ ምጽዓተ ክርስቶስም በዚሁ መንገድ ትጓዛለች፡፡ ከቅዱሳን በተለየ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የምታመሰግንበት መንገድ ደግሞ ልዩ ነው ምክንያቱም እርሷ ቅድስተ ቅዱሳን ናትና! ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ‹‹አንቺ ከሊቃነ ጳጳሳት ትበልጪያለሽ፣ከነቢያትም ከመምሕራንም ትበልጪያለሽ፣ከሃሳቦችም ሁሉ ትበልጫለሽ፣ከሡራፌልና ከኪሩቤልም ይልቅ የመወደድ ግርማ አለሽ ……›› በማለት መሥክሯልና፡፡ ይህንንም ቅድስናዋን አበው፣ነቢያት፣ቅዱሳን፣ሐዋርያት እና ሠማዕታት ሁሉ መሰከሩት እንጂ እርሱ ብቻ የመሰከረው አይደለም! ስለዚህም ምሥጋና ይገባታል፡፡ ቅድስናዋን፣ልዕልናዋን፣ክብሯን፣ንጽኅናዋን፣አማላጅነቷን ከሠፊው የምሥጋና ባሕር አየጨለፉ ማመሥገን ይገባል እንጂ አንድ ምዕራፍ ላይ ብቻ ቆሞ መጮኽ ዘመርን አያሰኝም! የተሃድሶ መናፍቃንም ከዚህ ተማሩ፡፡ እንዲያው በሜዳ ክብራችን ተነካ፣ገበያችን ቀነሰ ብሎ መጮኽ ትርጉም አይኖረውምኦርቶዶክሳዊ ዘማሪ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው መፍትሔው!
“የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ-(የማይዘምሯቸው)” በሚል ክፍል ሦስትና የመጨረሻ ክፍል ይቀጥላል፡፡
(ይቆየን)፡፡

(ቢኒ ዘልደታ መጋቢት-20/2008ዓ/ም)

No comments:

Post a Comment