Friday, April 29, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ ስምንት

ከክፍል አስራ ሰባት የቀጠለ

የተከበራቸሁ አንባብያን!
     በዚህ የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡እንዲሁም በክፍል አስራ ስድስትና አስራ ሰባት ደግሞ "Bini Zelideta" ከተባሉ ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ የእኛም ሃሳብ ስለሆነና ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አስነብበናችኋል፡፡አሁንም ከዚህ በመቀጠል "Blni Zelideta" መዝሙርን በተመለከተ የጻፉትን ክፍል ሦስትና ማጠቃለያውን እንድታነቡ እየጋበዝን፤ጉዳዩ ይመለከተናል የምንል ሁላችንም በዚህ ጽሁፍ ላይ በምናገኘው መልእክት መሠረት ችግሩን ከማስወገድ አኳያ የየድርሻችንን መልካም ስራ እንድናበረክት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
መልካም ንባብ!

Bini Zelideta
“የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ”
 ክፍል ሦስት እና የመጨረሻ (የማይዘምሯቸው/ ያልዘመሯቸው)
1ኛ) ነገረ ቅዱሳን
     ‹‹ዕለቱ የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነበር ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለሠርክ ጉባዔ አገልግሎት ወደ አንድ ደብር ያቀናል ጉባዔው በተለያዩ መዝሙራትና ዘማርያን ደምቋል፣ምእመኑም አብሮ ይዘምራል፡፡ ቢዘመር….  ቢዘመር….   ቢጠብቅ… ቢጠብቅ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያወሳ አንድ መዝሙር ግን ትንፍሽ አልተባለም! ኋላ ምነው ዕለቱ የሠማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ቀን አይደለምን? አንድ መዝሙር እንኳ ስለሰማዕቱ እንዴት አይዘመርም? አለ በዚያን ጊዜ በዕለቱ ከተጋበዙት ዘማርያን ውስጥ የሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን መዝሙር የሚችል አንድ ሰው እንኳ ጠፋ!››(ምንጭ የሲዖል ደጆች ከሚለው ስብከት የተወሰደ)፡፡
     እንግዲህ ስለደረስንበት አሳፋሪ ዘመን ዛሬውኑ  ተነቃቅፈን ወደ ቀደመው ዘመን መመለስ ካልቻልን መጪው ዘመን ወዴት ሊመራን እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ይህ ከላይ እንደ መግቢያ የተጠቀምኩበት ሃሳብ ብዙ አንድምታዎች አሉት፡፡ ዘማሪያኑ ወዴት እያመሩ እንደሆነ፣ምእመናንም የነማን መዝሙራት ላይ ተጠምደው እንደሚውሉ፣የደብር አስተዳዳሪዎችና የሥብከተ ወንጌል ኃላፊዎች የትኞቹን ዘማርያን እንደሚጋብዙ ፍንትው አደርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ይህን አነሣሁ እንጂ ዛሬ በየአድባራቱ ተመሳሳይ ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ዕለቱ ተክለ ሃይማኖት ነው ግን ስለ ተክለሃይማኖት አይዘመርም! እለቱ የገብረ መንፈስ ቅዱስ መታሰቢያ ቀን ነው ነገር ግን ስለ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አይዘመርም፣ዕለቱ የጻድቁ ዮሴፍ ነው ግን ቅዱስ ዮሴፍን አንሥቶ የሚዘምር የለም! ታዲያ ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ ብሎ መጠየቁ፣ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡
     እኛ እንደዋዛ አይተን የምናልፈውን ይህን ጉዳይ እነዚያ የተሃድሶ መናፍቃን በብዙ ድካም ያፈሩት ውጤት መሆኑን ማሰብ አለብን! ያንጊዜ ነው በቁጭት እኩይ ተግባራቸውን ማውገዝ እንደሚገባን የምናስበው፡፡ ያን ጊዜ ነው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓቷን፣አምልኮዋን፣ትውፊቷን፣አካሄዷን አውቀን ድንበሯን እና አጥሯን ልናስከብር የምንችለው፡፡ እንዲያ ካልሆነ ግን ተሸነጋግለን የትም አንደርስም! የተሃድሶ መናፍቃን ነገረ ቅዱሳንን የማስረሳት ስውር ተልዕኮ የጀመረው ዛሬ አይደለም ለረጅም ዓመታት ብዙ ሲደክሙበት የቆዩበት ጉዳይ እንጂ፡፡ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዎቹ እኛ እንጂ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡ ለዘመናት በየ ደጀ ሰላማችን እየተሽሎኮሎኩ ያሻቸውን ሲፎልሉ ዝም ያልን የገዛ ቤታችንንም ያስደፈርን እኛው ነን! በገዛ አውደ ምሕረታችን ሲያቅራሩና በቅዱሳን ሲዘባበቱ አይተን ዝም ያልንም እኛው ነን! ለገዛ ጥፋታቸው ሲፋጠኑ ታቦት ይመስል ስናጅባቸው የኖርን እኛው ነን! ዛሬ እነርሱ ሃሳባቸው ተሟልቶ፣ዕቅዳቸው ተሳክቶ ፍሬውን እየለቀሙ ሲሆን እኛ ግን ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እያልን በራሳችን እየተረትን እንገኛለን፡፡ እነርሱ ለጥፋታቸው የሚተጉትን ያህል እኛ ለደጀ ሰላማችን መደፈር አንቆረቆርም! እነርሱ ጥቂት ሆነው የጥፋት ሃሳባቸው ብዙ ሲሆን እኛ ደግሞ ብዙ ሆነን ቤተ ክርስቲያናችንን የማስከበር ሃሳባችን ጥቂት ነው፡፡ ብዙዎች ስንሆን እንዴት እኚህን ጥቂቶች ማቆም አቃተን? ዛሬ ለምን ስለ ቅዱሳን አይዘመርም? ለምን ተዘነጉ? ለማለት ያበቃን እኮ የራሳችን ስንፈፍና ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁንም ማንቃላፋቱ ካበቃ ደባቸውን መግታት የሚያስችል አቅሙ አለን፡፡ እውነት ለመናገር የተሃድሶ መናፍቃን ቅዱሳንን የምናይበትን የገዛ ዓይናችንን ለማወር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ማለት ይቻላል! መዝሙሮቻቸው ከነገረ ቅዱሳን አስተምሕሮ የጠፈርን ያህል የራቀ ነው፡፡
     በክፍል አንድ እና ሑለት መልዕቴ ላይ የተሃድሶ መናፍቃን በነገረ ክርስቶስ እና በነገረ ማርያም ዙርያ እንዲህ ብለው ዘምረው ነበር በሚል የተወሰኑ ምሳሌዎችን ለማቅረብ ሞክሬ ነበር በዚህ በክፍል ሦስት ግን ምንም ምሳሌ ማቅረብ አልቻልኩም ካልዘመሩት ምሳሌውስ ከየት ይምጣ? ለዚህ ነው የዚህ የክፍል ሦስት ርዕሴ የማይዘምሯቸው በሚል የቀረበው፡፡ ምድረ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ተክለ ሃይማኖትን፣ገብረ መንፈስ ቅዱስን፣አቡነ አረጋዊን፣አቡነ መልከፄዴቅን፣አቡነ አሮንን የማውቅ ዘማሪ ነኝ ባይ መኖሩ ያሳፍራል! ቅዱሳን መላእክትን፣ቅዱሳን ሐዋርያትን፣ቅዱሳን ነቢያትን ፣ቅዱሳን ሠማዕታትን የማይዘክር ዘማሪ ነኝ ባይ መፈጠሩ ያሳዝናል! ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህ ዘማሪ ነን ባዬች በኦርቶዶክስ ማሊያ መከሰታቸው የበግ ለምድ ለባሾች ለመሆናቸው ማሳያ ነው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ማለትም (ከ2003 ዓ/ም በፊት) በለቀቋቸው መዝሙራት ውስጥ ሚካኤል፣ገብርኤል፣ያሬድ የሚሉ መዝሙራንት ጥቂት ይሞካክሩ ነበር ሆኖም ፍላጎቱም ሆነ ዕውቀቱ ስለሌላቸው ነገረ ቅዱሳንን መዘመር በዳዴ የቀረ ነገር ሆኗል፡፡ ያቺንም የነካኳት መመሳሰል በሚለው ሥውር ስትራቴጂ ኦርቶዶክሳዊ ዘማሪ ሆኖ ለመገኘት ያደረጉት የማወናበድ ሥራ እንጂ ቅዱሳን ለነርሱ ምናቸውም ስለሆኑ አይደለም፡፡ እነዚህ ሰዎች የሞኝነት አካሔድ ስለሚከተሉ አንዳንድ ጊዜ ያሳዝኑኛ!(የምሬን ነው)ለምን መሰላችሁ ቅዱሳንን ማመሥገን ከጌታ ምሥጋና ላይ እንደመቀነስ አልያም የጌታን ምሥጋና እንደመሻማት ነው የሚቆጥሩት፡፡ ሆኖም በቅዱሳን አድሮ የሚመሰገን እርሱ አንድ አምላክ በመሆኑ ቅዱሳንን ማመሥገን የጌታን ምሥጋና ስለማይሻማ አትፍሩት፡፡ እንደውም በክፍል አንድ መልዕቴ ላይ ከነዚህ የተሃድሶ መናፍቃን ዘማርያን ውስጥ አንዱ ‹‹ቅዱሳንም እኮ እርሱን ብቻ ነው ያመሰገኑት እንጂ አመስግኑኝ አላሉም!›› የሚል ኮሜንት ሰጥቶኝ ነበር፡፡ ይህ አነጋገሩ በሁሉም የተሃድሶ መናፍቃን ዘማርያን ዘንድ ያለውን አቋም በቀጥታ የሚያመላክት ነው፡፡ በግልጽ ስለ ቅዱሳን አንዘምርም እያሉ መሆኑን ልብ በል! ወትሮውንስ ቅዱሳን አመስግኑኝ መች ይላሉ? እኛ ነን እንጂ በሠሩት ሥራና በፈጸሙት ተጋድሎ የምናመሰግናቸው! እነርሱም እንዲህ አይሉም ውዳሴ ከንቱ ነውና! ደግሞስ እነርሱን ለማመስገን የግድ አመስግኑኝ የሚል ቃል ስናስስ መዋል አለብን እንዴ? ያከበራቸውን ቅዱሳንን ማክበር ክብርን የሚያሰጥ እንጂ የሚያስኮንን አይደለም፡፡ አንዳንዴ መላእክት ሰዎችን ያድናሉ ብለው ሊያምኑም ሊዘምሩም ይችላሉ ያማልዳሉ፣ስግደትም ይገባቸዋል የሚለውን ግን አይደግሩትም! ከፍሎ ማመን ማለት እንዲህ ነው፡፡ ቅዱሳንን እግዚአብሔር ያከበራቸውና የመረጣቸው ናቸው ብለው ሊያምኑም ሊዘምሩም ይችላሉ ስግደት እንደሚገባቸው እና ስለ ሰዎች እንደሚማልዱ ግን አይዘምሩም! ከፍሎ ማመን ማለት እንዲህ ነው፡፡ ሲነሽጣቸው ቤተ ክርስቲያንን ቅድስት እያሉ ያቆላምጧታል ነገር ግን ገረገራዋን እና አውደ ምሕረቷን አይወዱትም ምክንያቱ ደግሞ ለነርሱ የሚመቻቸው በየአዳራሹ እና በየሆቴሉ የሚዘጋጁት ጉባዔያት ስለሆኑ፡፡ ያልኖሩባትንና የማያውቋትን ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ነች እንዲያ ነች በማለት ክርስትና ከተሰማችሁ እናፍራለን! ሃይማኖትን አስቤዛ ይመስል ግማሽ ከዚህ ግማሽ ከዚያ፣ ትንሽ ከዚህ ትንሽ ከዚያ እቆነጠሩ ማግበስበስ አይደለም በቆሙበት አለት ላይ ጸንቶ መኖር እንጂ!(ልቀጥል)
2ኛ)  ኢየሱስ ብቻ እንጂ እግዚአብሔር፣አማኑኤል፣መድኃኔዓለም፣ሥላሴ እያሉ አይዘምሩም፡፡
ኢየሱስ ማለት መድኃኒት
መድኃኔዓለም ማለት የዓለም መድኃኒት
እግዚአብሔር ማለት የሥላሴ የአንድነት መጠሪያ
አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ
ሥላሴ ማለት አንድ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
     ከላይ ከተጠቀሱት የአምላክ ስሞች ውስጥ ነጠላ ትርጉም ያለው ኢየሱስ የሚለው ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ እና መድኃኔዓለም የሚሉትን ሁለት ሥሞች ያላቸውን ትርጉም ስንመለከት፡- ‹‹ኢየሱስ›› ማለት ‹‹መድኃኒት››፣‹‹መድኃኔዓለም›› ማለት ‹‹የዓለም መድኃኒት›› የሚል ትርጉም አላቸው፡፡ መድኃኒት ከሚለው ትርጉም ይልቅ የዓለም መድኃኒት የሚለው ትርጉም ሚዛን ይደፋል ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ሁሉ ሲል ቤዛ መሆኑን ያስረዳል የተሃድሶ መናፍቃን ኢየሱስ ብቻ እንጂ መድኃኔዓለም፣እግዚአብሔር፣አማኑኤል፣ሥላሴ የሚሉትን ሥሞች አይጠቀሙም ይህም ግለኝነት ላይ ብቻ በማጠንጠን የግል አዳኝ ነው ወደ ሚል የመናፍቃን ትምህርት ለመምራት ነው፡፡እርሱ ግን የግል ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ሁሉ መድኃኒት እና አዳኝ ነው፡፡ አሁን እነዚህን ስችን ሚዛን ላይ አስቀምጦ የማወዳደር እሳቤ ውስጥ እንዳንገባ በትርጉም ረገድ ያላቸውን ይዘት እንረዳ እንጂ፡፡ አንድም እነዚህ ስሞች ለተለያዩ አካላት የተሰጡ አይደሉም ለአንድ አምላክ እንጂ፡፡ የተሃድሶ መናፍቃን ሌሎቹን የክብር ስሞች የማይጠቀሙበት ምክንያት አዳኝነቱን በብዝሃነት ስለሚመሰክሩ ሲሆን እነርሱ ደግሞ ከግል አዳኝነቱ በቀር መመስከርም መዘመርም አይፈልጉም፡፡ ይህም አምላክነቱን፣ፈጣሪነቱን፣እግዚአብሔርነቱን ከመጠራጠር የመነጨ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ለነገሩ ሰውዬውም ኢየሱስ እና እግዚአብሔር የሚለውን ሥም አትቀላቅሉ፣ሥላሴ ምናምን እያላችሁ ነገር አታራዝሙ፣ኢየሱስ ብቻ በሉ ብሎ አስተምሮን የለ! መዝሙሮቻቸው እኮ የትምህርቶቻቸው ግልባጮች ናቸው፡፡አማኑኤል ብለው ከዘመሩ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው ብለው መናገራቸው ስለሆነ በፍጹም ይህን አይደፍሩትም፣እግዚአብሔር ብለው ለመዘመር ደግሞ የባሰ ወደሚጠሉት ሥም መጡ ማለት ነው፣ሥላሴ ብለው ዘመሩ ማለት ደግሞ ጭራሽ አለቀላቸው ማለት ነው፣መድኃኔዓለም ብለው እንዳይዘምሩ ደግሞ የዓለም መድኃኒት ማለታቸው ስለሆነ የግል አዳኝ ነው የሚለውን ስብከታቸውን ያመክንባቸዋል ስለዚህ ብቸኛና ተስማሚ ሆኖ ሃሳባቸውን የሚያሳካላቸው ስም ኢየሱስ የሚለው ስም ብቻ ይሆናል፡፡ እነዚህ ሰዎች እኮ ያለማወቅ ጣሪያ ላይ በመድረሳቸው ብሉይ ኪዳንን እየዘመሩ ኢየሱስ የሚሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ጌታችን በብሉይ በተለያዩ ምሳሌዎች ቢገለጥ ብሉይን እግዚአብሔር፣ሐዲስ ኪዳንን ደግሞ ኢየሱስ/ እግዚአብሔር እየተባለ መዘመር አለበት እንጂ ብሉይ ሐዲስም ኢየሱስ…ኢየሱስ ብቻ እየተባለ መዘመር የለበትም፡፡አሁንም ለምን ኢየሱስ ብለው ይዘምራሉ ማለቴ አይደለም ለምን ኢየሱስ የሚለውን ስም ብቻ ይዘምራሉ እንጂ! ምነው ለራሳቸው ያልተገባ ስም ሲደራርቡ የጌታችንን ስም ማራቆት ፈለጉ? ምነው እነርሱ በተለያየ ስም እየተሞጋገሱ እና እየተሸላለሙ የጌታችንን ክብር በእንድ ስም ብቻ ለመገደብ አሰቡ? እነርሱ መጋቢ…ዲያቆን….ቀሲስ እያሉ ከፌስ ቡክ ያልዘለለ ስመ ክሕነት ይዘው ሳለ የክቡር አምላካችንን ስም ማቃለል አስፈለጋቸው? ሁሉንም ስሞች መጠቀም ይገባል እንጂ አንዱን ብቻ አንጠልጥሎ ሲጮኹ መዋል ኦርቶዶክሳዊ አያሰኝም፡፡
 ከዚህ በተጨማሪ
 ስነ ነገረ ተዋሕዶ
 ስለ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን
 ስለ ንሰሐ እና ቁርባን
ስለ ኃጢአታቸው እና ኃጢአታችን
 በፍጹም አይዘምሩም፡፡ ወትሮውንስ ጸድቀናል፣ድነናል፣ጽድቃችን ሰማይ ነክቷል የሚል ትውልድ ንሰሐ ምኑ ነው? ቁርባኑስ ምን ሊፈይድለት? አዳራሽና መናፈሻ የለመደ ትውልድ እንዴት ስለ ቤተክርስቲያንና ምስጢራቷ ሊዘምር ይችላል?በተዋሕዶ መሠረት ላይ ያልታነጸ ትውልድ እንዴት ስለ ነገረ ተዋሕዶ ሊዘምር ይችላል?
 ማስረሳት የተሃድሶ መናፍቃን የመጨረሻ ግብ!
     ከክፍል አንድ ጀምሮ ባቀረብኩት የተወሰነ የዳሰሳ ጥናት ላይ ለመታዘብ እንደሞከራችሁት ዋነኛ የተሃድሶ መናፍቃን ግብ ማስረሳት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በነገረ ክርስቶስ ዙሪያ ዕለተ አርብ ከተፈጸመው የነገረ ድኅነት ውጪ የተቀረውን የነገረ ድኅነት ትምህርቶች ማስረሳት፣በነገረ ማርያም ዙርያ ጸጋሽ በዛ እና ጌታን ወለደች ከሚለው ውጪ ክብሯን አማላጅነቷን ንጽኅናዋንማስረሳት፣በነገረ ቅዱሳን ዙርያ ምንም ባለመዘመር ቅዱሳንን ፈጽሞ ማስረሳት ዋነኛ ዒላማቸው ሆኗል፡፡ ቅዳሴውን ማስረሳት፣ኪዳኑን ማስረሳት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው፡፡ሌላው ከስውር ሴራዎቻቸው ውስጥ ወጣቱን በምን አለበት ሰበብ ስርዓተ ቤተክርስቲያንን መጣስ ማለማመድ፣ እየጨፈረ "የዘመረ" እንዲመስለው ማኮላሸት፣በመናፍቃኑ የክህደት ትምህርት እና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት፣ቀኖና እና ዶግማ መካከል ያለውን ልዩነት እንዳያስተውል እና እንዳይረዳ ማደናገር ዋነኛ ስልቶቻቸው ሲሆኑ የወጣቱ ክፍል በሱስ መጠመድ ለአላማቸው ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸዋል።
     ሌላው በዚህ መልዕክት አልተካተተም እንጂ በሸጧቸው አልበሞች እና ባጋበሱት ገንዘብ ቤትና መኪና ገዝተው ከችግር ሕይወት መላቀቃቸውን የገለጹባቸውን ‹‹ኑሮዬ ተደላደለ፣ጓዳዬ ሞላ፣ችግር ደህና ሰንብት………ዓይነት መዝሙራትም ነበሯቸው፡፡በተጨማሪም ምድርን ከደናት….አጥለቀለቅናት…..ሸፈናት……በዛን…..በረከትን ብለው ያቅራሩትንም አላቀረብኩም፡፡ የታዘብኳቸው ግን አንድ አዳራሽ ውስጥ ባዩት ግብስብስ ሕዝብ እንዴት ምድርን ሊከድኗት እንደቻሉ ማሰባቸው ነው፡፡ መቼም አደንዛዥ ዕጽ የወሰደ ሰዉ ካልሆነ በቀር የአንድን መናፈሻ ወይም አዳራሽ ሕዝብ አይቶ ምድርን እንዴት ሊከድናት እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ነው ወይስ? የአዳራሹ ሰዎች መናፍስት ናቸው ሲወጡ ምድርን የሚከድኗት? ሆሆ…ለነገሩ ማን ያውቃል ሆነውም ይሆናል! መቼም ምድር እራሱ ግዑዝ ሆና እንጂ ትከሳቸው ነበር ስብዕናዋን ነክተዋታል እኮ ከደናት…ሸፈናት እያሉ!
 ማጠቃለያ
     ዓሳውን ለመግደል ምንጩን ማድረቅ ትልቁ መፍትሔ ነው! የተሃድሶ መናፍቃንን መዝሙራት ማዳፈን የክሕደት ደባቸው ላይ አፈር ማልበስ ስለሚሆን ዛሬውኑኑ ከነዚህ ኅብረት በመውጣት ኦርቶክሳዊ መዝሙራትን ማድመጥ እንጀምር፡፡ ዛሬ ዛሬ የሚታየው ለውጥ ይበል የሚያሰኝ ነው ከንቱ ቀረርቶአቸውን የሚገዛቸው አጥተውና ገበያ ቀንሶባቸው ኪሳራ እያስተናገዱ ነው፡፡ የሞንታርቦው አልበቃ ብሎአቸው በፌስ ቡክ ገጾቻቸው ጭምር ‹‹ኧረ ግዙን?›› እያሉ በማለቃቀስ ላይ ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ ብቻ በቂ ነው አንልም አሁንም ባለማወቅ እነዚህን ግለሰቦች የሚከተሉ የዋሐንን መታደግ የግድ ነውና፡፡ ሙሉ በሙሉ አቅማቸውን በማዛል እውነተኞች ዘማርያንን ማብዛት ይኖርብናል፡፡ በተለይም በነዚህ የተሃድሶ መናፍቃን ብዙ የተሸፈኑ ኦርቶክሳውያን ዘማርያን በመኖራቸው እነዚያን ዳግም ወደ መድረኩ እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ያን ጊዜ የኃይል ሚዛኑ ወደ እውነተኞቹ ስለሚያጋድል እነዚያን መናፍቃን በቀላሉ ከመድረኩ ለማውረድ ጊዜ አይፈጅም፡፡ እዚህ ጋር ምንም ይሉኝታ አያስፈልግም! ማሽሞንሞንም አይገባም! ምንፍቅናቸውንከነ ቀረርቶአቸው ይዘው ውልቅ ይበሉልን!
     በስተመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት በክፍል አንድ እና ሁለት መልዕክቴ ላይ በኮሜንት እገሌ እኮ እንዲህ ብላ ዘምራለች እገሌም እኮ እንዲህ ብሎ ዘምሯል እያላችሁ ስትጠቅሱ የነበራችሁ ግለሰቦች ከአስተያየታችሁ በፊት መልዕክቱን በሚገባ ተረዱ፡፡ ለምሳሌ የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት አርብ ላይ ብቻ ያተኩራሉ ባልኩት ሃሳብ ላይ ቴዲ እኮ እንዲህ ብሎ ዘምሯል፣ይልማም እኮ እንዲህ ብሎ ዘምሯል ያላችሁ ሰዎች ነበራችሁ እውነት ነው ኦርቶክሳውያን ዘማርያን እለተ አርብ ስለተፈጸመው ነገረ ድኅነት አይዘምሩም አላልኩም በደንብ ይዘምራሉ! ነገር ግን እንደ ተሃድሶ መናፍቃን ሁሌ ዕለተ አርብን ብቻ አይዘምሩም አትዘላብዱ፡፡ እንደገናም የተሃድሶ መናፍቃን ስለ ድንግል ማርያም አይዘምሩም አላልኩም ከዩቱብና ከተለያዩ ምንጮች መዝሙሮቻቸውን እያመጣችሁ በኮሜንት ስትለጥፉት ተመልክቻለው ይህም መልዕክቱን በአግባቡ ካለመረዳት የመነጨ ስለሆነ ይስተካካል! ስሟንማ ያነሡታል ነገር ግን በስሟ የሚለቀቁት መዝሙራት ፍጹም ክብሯን ማይመጥኑ መሆናቸውን ይልቁንም አማላጅነቷን እና ንጽኅናዋን የሚጻረሩ እንደሆኑ በምሳሌ አስደግፌ አቅርቤዋለሁ በድጋሚ ተመልከቱት፡፡
አምላከ ቅዱሳን ቤተክርስቲያናችንን ከእነዚህ ነጣቂ ተኩላዎች እና ዓላውያን መሪዎች ይታደግልን። (ይቆየን)
(ቢኒ ዘልደታ መጋቢት 28/2008 ዓ/ም)


No comments:

Post a Comment