Monday, June 27, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሦስት

"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሦስት)
ከክፍል ሃያ ሁለት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
     ‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሁለት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሁለተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡አሁን በገባነው ቃል መሠረት ሦስተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡በመግቢያችንና ቀደም ባሉት ክፍሎች እንደገለጽነው “የእምነት መግለጫ” ሰነዳቸው ብዙ የዋሃን ምዕመናንን ለማሳሳት  በተንኮል የተቀናበረ በመሆኑ ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ለእያንዳንዱ አንቀጽ መልስ ያስፈልገው ነበር፡፡ሆኖም የእነሱን አካሄድ ተከትለን ብንሄድ፤የእኛንም ሆነ የአንባብያንን ብዙ መልካም ሥራዎችን የምንሰራበትን ጊዜና አእምሮ በከንቱ ማባከን ስለሆነ በጣም ጎላ ብለው የሚታዩት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡

የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሁላችንም እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡


አንደኛ/ ከመግለጫቸው ገጽ 33 የተወሰደ፦ “ቤተ ክርስቲያን አንዲትና አለማቀፋዊት እንደመሆኗ መጠን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተለያየች ብትሆንም፤ እግዚአብሔር ወዳቀደላት አንድነትና ፍጹምነት እንድትመጣ የተቻለንን እናደርጋለን፡፡” ብለዋል፡፡

ከዚህ በላይ ባለው ሃሳባቸው ውስጥ የሚተኮርባቸው ሃሳቦች፤
1/ “ቤተ ክርስቲያን አንዲትና አለማቀፋዊት” መሆኗን ካመላከቱ በኋላ፤መልሰው በዚያው ዓረፍተ ነገር ላይ ቤ/ክ በየምክንያቱ የተለያየች መሆኗን በመግለጽ ያፈርሱታል፡፡ይህም የእነሱ እምነት ከተለያዩ የመናፍቃን የእምነት ድርጅቶች የተቃረመ ስለሆነ ያንን አሰባስበው ወደ አንድነት ለማምጣት አስበዋል ማለት ነው፡፡ከዚህ ሌላ “አንዲት፣ቅድስት፣ዓለማቀፋዊት…” የሆነችውን የተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በጭፍን ከመንቀፍ በስተቀር ማንነቷን የማያውቁ፤ለማወቅም የማይፈልጉ መሆኑን ያጠይቃል፡፡
2/ በእግዚአብሔር ወልድ ደም የተመሠረተችውን ቤተ ክርስቲያን ገና ፍጽምት እንዳልሆነች፤ ወደፊት በእነሱ ጥረት እግዚአብሔር ወዳቀደላት አንድነትና ፍጹምነት እንደምትመጣ እየተነበዩ ነውኮ! አይ ክርስትና! አይ ወንጌል ሰባኪነት! ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች ትታደስ የሚሉት አካላት እምነት እንግዲህ እስከዚህ ድረስ ነው፡፡በፈሊጣዊ አነጋገር "ለራሱ የማይበቃ ጠበቃ" እንደሚባለው፡፡

ሁለተኛ ከመግለጫቸው ከገጽ 29-36 ባለ እምነት መግለጫዎቹ ተሐድሶዎች፤ አእማደ ምሥጢራትን በራሳቸው አገላለጽ "መሠረተ እምነት" ብለው ከአምስቱ ምሥጢራት መካከል ሁለቱን ብቻ ገልጸዋል፡፡ይህም ምሥጢረ ሥላሴን “ትምህርተ ሥላሴ፣”ምሥጢረ ሥጋዌን “ትምህርተ ሥጋዌ”…..እያሉ እያድበሰበሱ ካለፉ በኋላ ወጉ እንዳይቀርባቸው ምሥጢራተ ቤ/ክ ብለው ከላይ በተጠቀሱት ገጾች ላይ አስፍረዋል፡፡ በእነርሱ እምነት ምሥጢራተ ቤ/ክ ያሏቸው 3ቱ ማለትም ምስጢረ ጥምቀት ፣ምሥጢረ ቁርባን፣ ምስጢረ ተክሊል  ብቻ ሲሆኑ “ሌሎች ምሥጢራት” ብለው የሰየሟቸውን፤ ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ እና ምስጢረ ቀንዲልን ግን “መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን” ብለዋል፡፡
ወደ ትንታኔው ሳንገባ እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስተዋል አለብን፡፡ ሁልጊዜ በመደጋገም እንደምንገልጸው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት አራማጆች ከሌሎቹ የእምነት ድርጅቶች የሚለዩበት ልዩ ጠባያቸው ኦርቶዶክሳዊ ሳይሆኑ መስለው ለመታየትና ሰዎችን ለማሳሳት ብቻ የሚጥሩ መሆናቸው ነው፡፡ዓላማቸው ይህ ባይሆን ኖሮ የራሳቸው የሆነውን እምነት ብቻ ከመግለጽ አልፈው፤ የማያምኑባቸውን አእማደ ምሥጢራትና ምሥጢራተ ቤ/ክ ስማቸውን እየጠቀሱ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" በማለት ባልዘባረቁ ነበር፡፡በዚህ አባባላቸው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ የምትመራበት ትምህርተ ሃይማኖትና ለምዕመናን ጸጋን የምታድልባቸው ምሥጢራተ ቤ/ክ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያልተገኙ ናቸው ማለታቸው ነው፡፡
ከዚህ በመቀጠል በእነርሱ እምነት ምሥጢራተ ቤ/ክ ያሏቸው 3ቱ ምስጢረ ጥምቀት ፣ምሥጢረ ቁርባን፣ ምስጢረ ተክሊልን  እና ቀሪዎቹን 4ቱን ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ እና ምስጢረ ቀንዲልን በተመለከተ እነሱ የሚከተሉትን የተሳሳተ አተረጓጎምና ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ የምትሰጠውን ትርጉም እያስተያየን በማቅረብ በቅደም ተከተል እንስቀምጣለን፡፡
1/ ምስጢረ ጥምቀት
      1.1/ በተሐድሶ እምነት፤ “የጥምቀት ዓላማ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባባር ነው፡፡” አለቀ፡፡በቃ፡፡
እንግዲህ አንባብያን እናስተውል! ያለ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ እንደማይቻል ወንጌሉ እየተናገረ፤እነሱ ይህን የጌታችንን ቃል ወደ ጎን ትተው የተብብር ማሳያ /ድራማ/ ብቻ አድርገውታል፡፡

       1.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
ሀ/ ጥምቀት የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ፡፡ዮሐ.3፥ 1-15 ፤ማር፤16፥16
ለ/ ጥምቀት የኃጢአት ሥርየት ለማግኘትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ለመቀበል፡፡የሐ.ሥራ 2፥38
ሐ/ ጥምቀት አሮጌውን ሰውነት አስወግደን በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፡፡ሮሜ.6፥1-11 እና ሌሎችም፡፡

2/ ምሥጢረ ቁርባን
   2.1/ በተሐድሶ እምነት፤
“ምስጢረ ቁርባን የሚያስፈልገው ጌታ እስኪመጣ ድረስ የክርስቶስን ሞትና መከራ ለማሰብ፤ትንሣኤውንም ለመመስከር፤የዳግም ምጽአቱን ተስፋ ለማስታወስ፤ከክርስቶስ ጋርና እርስ በርሳችን ህብረት ለማድረግ ነው፡፡በጌታ እራት መሳተፋችን እስከ ዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ሲሆን፤በዚያን ጊዜ በበጉ ሠርግ እራት፤ማለት በጌታ ጋር በሚደረግ የእራት ግብዣ ይጠናቀቃል፡፡”

የተወደዳችሁ አንባብያን! ጥምቀቱም፣ቁርባኑም፣ሌላውም መታሰቢያ ነው እንጂ ለድህነታችን ምንም አስተዋጽኦ የለውም” የሚለውን ቀልድ በፕሮቴስታነቱ ዓለም ስንሰማው የነበረ፤እነሱም/ተሐድሶዎቹ/ የእነሱው ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመሆናቸው ከዚያው የተቀበሉት በመሆኑ አይደንቀንም፡፡ከዚህ በተጨማሪ ግን እንደምንም ከሌላው የተለዩ ለመምሰል ብለው አዲስ የፈለሰፏት "በጌታ እራት መሳተፋችን እስከ ዳግም ምጽአተ ክርስቶስ ሲሆን፤በዚያን ጊዜ በበጉ ሠርግ እራት፤ማለት ከጌታ ጋር በሚደረግ የእራት ግብዣ ይጠናቀቃል፡፡” የምትለዋ የእራት ግብዣዋ ነገር ነች፡፡ በዚህ አባባላቸው የሐሰተኛው ክርስቶስ መንገድ ጠራጊዎች ለመሆናቸው  ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡እንግዲህ እነሱ ጌታ የሚሉት በብዙ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የክፋቱና የጥፋቱ ሁኔታ ትንቢት የተነገረበት፤በይበልጥም በዮሐ.ራዕይ ምዕ.13 በአውሬው ምሳሌነት የተገለጠው ሐሰተኛው ክርስቶስ መሆኑ ነው፡፡ይህ ዓለሙን ሁሉ በክህደት ትምህርቱ የሚቆጣጠረው ሐሰተኛው ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ42 ወራት  ለመንገሥ ሲመጣ፤እነሱ ቀደም ብለው ቤተ ክርስቲያንን በማጥፋት ሥራ መንገድ ጠራጊዎች ሆነው ስለተገኙለት ምናልባት ምሳም እራትም ሊጋብዛቸው ይችል ይሆናል እንጂ፤እውነተኛው  ጌታ ሰማይንና ምድርን ሊያሳልፍ ሲመጣ  እራት ያበላኛል ብሎ የሚቋምጥ ሃይማኖተኛ ሰው በምንም ሁኔታ ሊኖር አይችልም፡፡ እንዴ! “አይወልድም፤አይወለድም፤ነቢይ ነው፤” የሚሉት እንኳን እምነታቸው ትክክል ባይሆንም የሚመጣው ለፍርድ መሆኑን ይናገራሉኮ፡፡ጭራሽ ከእነሱም አንሶ መገኘት? ኧረ ተሐድሶ ነን የምትሉ ወደ አእምሯችሁ ተመለሱ! እባካቸሁ ትንሽ እፍረት ይኑራችሁ! በእግዚአብሔር ቃል በደሙ የተመሠረተችዋን ፤የማትፈርሰዋን ቤ/ክ ለማፍረስ ቀን ከሌሊት ከምትደክሙ እስቲ መጀመሪያ እናምንበታለን በምትሉት በ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንኳን የራሳቸሁን እምነት መርምሩት፡፡"በሃይማኖት ብትኖሩ እራሳችሁን መርምሩ" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡2ኛ ቆሮ.13፥5
እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን የምናምነው፤ መጽሐፍ ቅዱስም የሚነግረን እውነት፤ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም የሚመጣው ለሁሉም እንደየሥራው ሊከፍል ነው፡፡    "እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከኔ ጋር አለ፡፡አልፋና ዖሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው፤መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡ ዮሐ.ራዕይ  22፥12-13፡፡

 2.2/ ምሥጢረ ቁርባን በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
እኛ የተዋህዶ ልጆች ምስጢረ ቁርባን ከሌሎቹ ምሥጢራት ሁሉ በተለየ ሁኔታ ነው የምናከብረው፡፡ምክንያቱም ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሥጋ ተዋህዶ የእኛን ሞት በሞቱ ለመደምሰስ፤በጽንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በሞቱ ለመፈጸም ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ እስከ ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ብዙው አንድ እየተባለ 13ቱን ህማማት በፈቃዱ ተቀብሎ የሰጠን ስለሆነ ነው፡፡ይኸውም በአይሁድ እጅ በመደብደብ፣በጥፊ በመመታት፣በመገረፍ፣የሾክ አክሊል በመቀዳጀት፣መስቀል ተሸክሞ በመውደቅና በመነሳት፣ በችንካሮች በመቸንከርና በመስቀል በመሰቀል፤በመጨረሻም ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በፈቃዱ በመለየት፤ሥጋውን ቆርሶ፤ደሙንም አፍሰሶ፤እኛ በበደልን እሱ ክሶ የሰጠን ነው ቅዱስ ቁርባን፡፡

ስለሆነም ከቅዱስ ቁርባን የምናገኘው ጥቅም፤
ሀ/  የዘለዓለም ሕይወት ለመውረስ ዮሐ.6፥54
ለ/ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ዮሐ.6፥56
ሐ/ የኃጢአት ሥርየት ለማግኘት፤ማቴ.26፥28
መ/ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፍርድ እስኪመጣ ድረስ ሞቱንና ትንሣኤውን እንድንመሰክር፤--1ኛ ቆሮ. 11፥26

3/ ምስጢረ ተክሊል
3.1/ በተሐድሶ እምነት፤
ስለ ምስጢረ ተክሊል ዓላማውንም ሆነ ጥቅሙን ሳይገልጹ “ወንድ ለወንድ ወይም ሴት ለሴት የሚፈጸም ጋብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ የተከለከለና አጸያፊ ርኩሰት ስለሆነ በእግዚአብሔር ቃል እንቃወማለን፡፡”ብለዋል፡፡እዚህ ላይ ስለ ምስጢረ ተክሊል ጀምረው ወደ ግብረ ሰዶም ተቃውሞ የሄዱበትን ጉዳይ ማንሳቱ አሰፈላጊ ነው፡፡እነዚህ ቤ/ክ እናድሳለን ባዮች በተለያዩ ግለሰቦችና ማህበራት ስም የተመሰረቱ ናቸው፡፡የሁሉም  ዋነኛ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖትን ማጥፋት ሲሆን በየራሳቸው ደግሞ ልዩነት አላቸው፡፡ከነዚህ ድርጅቶች መካከል አንዱ የግለሰብ ድርጅት በዚህ የግብረ ሰዶም ልክፍት መያዙንና በጓደኝቹ ተመክሮ ተመክሮ አልመለስ ማለቱን የራሰቸው ድረ-ገጽ “አባ ሰላማ” አስነብቦናል፡፡/ያልሰማን መስሏቸው ነው?/
አንባብያን እንግዲህ ልብ በሉ፤ይህንን በኖህ ዘመን የሰው ልጅ በንፍር ውሃ ከምድረ ገጽ እንዲጠፋ ያደረገውን፤በሎጥ ዘመን ደግሞ ሰዶምና ገሞራ የተባሉትን ከተሞች በእሳት እንዲጠፉ፤ደረገውን አጸያፊ የዝሙት ኃጢአት እየሰሩ ነው ወንጌል እንሰበካለን የሚሉት፡የተዋህዶ ልጆች እባካችሁ እንንቃ! እኩይ ዓላማቸውንም እንቃወም!

3.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
ምሥጢረ ተክሊል፦አንድ በንጽህና በድንግልና የኖረ ወንድና አንዲት በንጽህና በድንግልና የኖረች ሴት በጸሎተ ተክሊልና በቅዱስ ቁርባን ጋብቻ አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር ሲሆን መነሻዎቹ አዳምና ሔዋን ናቸው፡፡ ዘፍጥ.2፥22-24፡፡
ዓላማውና ጥቅሙም፦ ለመባዛትና ምድርን ለመሙላት፤/ ዘር ለመተካት/ ዘፍጥ.1፥28፣ ከዝሙት ለመጠበቅ 1ኛ ቆሮ.7፥2፣ለመረዳዳት ዘፍጥ.2፥18 ሲሆን፤ የቅዱስ ጋብቻ ክቡርነት ለክርስቶስና ለቤ/ክ ምሳሌ እስከ መሆን ድረስ ከፍ ያለ ነው፡፡ኤፌ.5፥22-33

4/ “ሌሎች ምሥጢራት” ብለው የጠቀሷቸው፦ምስጢረ ሜሮን፣ምስጢረ ክህነት፣ምስጢረ ንስሃ፣ምስጢረ ቀንዲል፤ 
4.1/ በተሐድሶ እምነት፤
ከላይ የተጠቀሱትን 4ቱን ምሥጢራት " መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረኑበት መንገድ እንጠቀምባቸዋለን" ከማለት በስተቀር የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡

4.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነት
የሁላችንም ዳኛ መጽሐፍ ቅዱስ ስለነዚህ ምሥጢራት የሚለውን ቀጥለን እንመልከት፤
1/ ምስጢረ ሜሮን፦ "እናንተም ከቅዱሱ ቅባት ተቀብላችኋል፡፡…..1ኛ ዮሐ.2፥20፡፡
2/ ምስጢረ ክህነት፦ …"ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፡፡/ሥልጣነ ክህነትን/፡፡ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው፡፡"ዮሐ.20፥21-23፡፡በተጨማሪ ማቴ.16፥18-19፣ ዮሐ.21፥15-17፣የሐ.ሥራ.20፥28 ማንበብ ይቻላል፡፡
3/ ምስጢረ ንስሃ፦ ከምሥጢረ ክህነት ጋር የተያያዘ ሲሆን "ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል" በሚለው ቃል መሰረት ኃጢአተኛው ጥፋቱን አምኖ ሲጸጸት ለካህኑ ይናዘዛል፤ካህኑ አስፈላጊውን ሥርዓት አስፈጽሞ እግዚአብሔር ይፍታህ ሲለው ሥርየት ያገኛል፡፡ኑዛዜን በተመለከተ ያዕ.5፥16፣…፡፡
4/ ምስጢረ ቀንዲል፦ "ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤ/ክ ቀሳውስትን ወደ እርሱ ይጥራ፤በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት፡፡"የያዕ.መል. 5፥14

ማሳሰቢያ ለአንባብያን፤ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረኑበት መንገድ" በማለት ላቀረቡት ጭፍን አስተሳሰባቸው መልስ ለመስጠት ያህል እንጂ እንደ ውቅያኖስ የሰፋውን የቤ/ክ ትምህርት ለማስተማር ስላልሆነ ተገቢውን ትምህርት ወደ ሊቃውንት በመቅረብ እንድንማር እግረ መንገዳችንን እንመክራለን፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡
ይቀጥላል፡፡




No comments:

Post a Comment