Monday, June 27, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ አራት

"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል አራት)
ከክፍል ሃያ ሦስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሦስት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሦስተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡በገባነው ቃል መሠረት አሁን አራተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡


ሦስተኛ-ከመግለጫቸው ገጽ 37-ነገረ ማርያም፦

5.1/ በተሐድሶ እምነት፤

1/ "በትውፊታዊ ታሪክ ትውልዷና ነገዷ የተገለጠው ቅድስት ድንግል ማርያም….. “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፤መንፈሴም በአምላኬ በመድሐኒቴ ሐሴት ታደርጋለች እንዳለችው በልጇ በወዳጇ ቤዛ መሆን ከዳኑት ቅዱሳን አንዷ እንደሆነች እናምናለን፡፡” ብለው ደግሞ ሌላ አስገራሚ ክህደት ጽፈዋል፡፡
እንደ እነ አስራት ገ/ማርያምና ሰይፈ ሥላሴ ዮሐንስን የመሳሰሉት ቀደም ያሉት አሳቾች፤ ክብር ምሥጋና ይግባትና እመቤታችን የውርስ ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ ነበረባት፤መልአኩ ትጸንሻለሽ ብሎ ባበሰራት ጊዜ ኃጢአቱ ተወግዶላት ጌታን ጸንሳለች እያሉ ለሚዘላብዱበት ልብ ወለድ ሃሳባቸው የቤ/ክ ሊቃውንት መልስ እየሰጡ አፋቸውን አዘግተዋቸው ኖረው ነበር፡፡ዛሬ ደግሞ ሁሉም ዝም ባለበት ሰዓት የነሱ ቡችሎች ክህደቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሳድገው፤ "በልጇ በወዳጇ ቤዛ መሆን ከዳኑት ቅዱሳን አንዷ ነች" ብለው አረፉት፡፡ይገርማል! በነሱ ቤት የወላዲተ አምላክን ክብር ዝቅ ያደረጉ መስሏቸው ነው፡፡ግን ከእሷም አልፈው ተርፈው ወልደ እግዚአብሔር የተዋሐደው ሥጋም ያው መርገም ነበረበት ማለታቸው ነው፡፡ታዲያ ለእነዚህ ምን ዓይነት መልስ ቢሰጣቸው አምነው ይቀበላሉ? ከመጸሐፍ ቅዱስም ሆነ በአጠቃላይ ከክርስትናው መንፈስ ጋር የሰማይና የመሬትን ያህል የተራራቁ ስለሆኑ፤ ለመወያየትም ለመከራከርም እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡

5.2/ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት
 
የእመ አምላክ፤ የወላዲተ አምላክ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አጠቃላይ ትምህርት በዚህ ርዕስ ሥር ለመግለጽ የሚሞከር ባለመሆኑ አሁንም ወደ ሊቃውንት ቀርበን እንድንማር እያሳሰብን፤ወደዚያ የሚያመራንን ጥቂት ጥቅሶችን ብቻ እንመለከታለን፡፡
1/ ተኩላዎቹ /ተሐድሶዎቹ/  "እመቤታችን ትውልዷና ነገዷ በትውፊት ብቻ የተገለጠ ነው" እንደሚሉት ሳይሆን፤በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ምሳሌና ትንቢት ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን፤ ተስፋ ፍጸሜ ሲያገኝ ደግሞ ፤በማቴ.1፥1 ከአብርሃም በመጀመር እስከ እጮኛዋ/ጠባቂዋ/ ዮሴፍ ድረስ፤በሉቃ.3፥23 ከጠባቂዋ ከዮሴፍ ጀምሮ ወደ ላይ አስከ አዳም ድረስ የተቆጠረው ዘር አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና የወለደችው የእመቤታችን ትውልድና ነገድ ዝርዝር ነው፡፡በቅዱስ ዮሴፍ በኩል የተቆጠረውም፤በእስራኤላውያን ህግ በሴት በኩል ዘር ስለማይቆጠር ነው፡፡እነሱ ይህንን የወንጌል ቃል ለማን ሊሰጡት ይሆን? ምናልባትም ቃሉ የሚለው  የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ ነው የሚሉ ከሆነ፤ እኛ ደግሞ ጌታ ከማን ተወለደ ብለን እንጠይቃቸዋለን?

2/ እመቤታችን የውርስ ኃጢአት /ጥንተ አብሶ/ አላገኛትም፡፡

ሀ/ "…እግዚአብሔር ዘርን ባያሰቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን እንደ ገሞራም በመሰልን ነበር…" ኢሳ.1፥9፡፡የዚህ ትንቢት ፍጻሜ "የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም..፡፡"ዕብ.2፥16 የሚለው ሲሆን፤ መርገም ያልወደቀባት ንጽህት ዘር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን ብሉይ ኪዳኑም አዲስ ኪዳኑም በመተባበር አረጋግጦልናል፡፡
ለ/ "መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፤ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤አንቺ ከሴቶች መካካል የተባረክሽ ነሽ አላት"  ሉቃ.1፥26 ይላል፡፡/ምዕራፉን በሙሉ ያንብቡ / ይህም ቅዱስ ገብርኤል ወደ እርሷ እንደገባ የመጀመሪያው ሰላምታ "ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ"…የሚለው ቃል እንከን የሌለባት፣ንጽህት፣ቅድስት መሆኗን ያረጋግጣል፡፡ይህንን የተሟላ ክብርና ቅድስና የሰጣት ለተዋህዶ የመረጣት እራሱ ልዑል እግዚአብሔር ነው እንጂ እኛ የተዋህዶ ልጆች ስለወደድናት ብቻ የሰጠናት ክብር አይደለም፡፡
እንግዲህ ከዚህ ከቅዱስ ገብርኤል ቃል በተቃራኒው የሚናገር ሁሉ ከእውነት የራቀ፤ሃሳቡም ቅዠት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያው ለነገሩ የጥርጥርና የክርክር ዘመን ላይ መሆናችን ነው እንጂ፤ያልተጻፈ እያነበቡ፣የተጻፈውንም ያልሆነ ትርጉም እየሰጡ፣ የማያስፈልግ ምርምር ውስጥ እየገቡ፣ ለራስ ግራ ተጋብቶ ሌላውን ግራ ከማጋባት ይልቅ  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እንዳለው "ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም" ብሎ በቀና ልቡና መቀበሉ የተሻለ ነበር፡፡እግረ መንገዳችንን  መልአኩ ድንግል ማርያምን ባበሠራት ጊዜ ከመርገም አነጻት የሚሉትን እነ አስራት ገ/ማርያምን፤ለመሆኑ በመላእክት ቃል ጥንተ አብሶ የሚሻር ከሆነ ለምን ጌታችን ሰው መሆን፤ለምንስ ደሙን ማፍሰስ አስፈለገው? ብለን እንጠይቃቸዋለን! ግን ከነሱ መልስ አንጠብቅም!

አራተኛ- ከመግለጫቸው ገጽ 39 ያሰፈሩት አጽዋማትን በተመለከተ ሲሆን፦ጾመ ፍልሰታ ሙሉ በሙሉ እንደማይቀበሉ፣ባለፈ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ያሏቸውንም አጽዋማት መፈተሸ እንዳለባቸው፣ጾመ ነቢያትና ጾመ ሐዋርያት ደግሞ መታሰቢያው እንዳይጠፋ ብቻ በጾሙ መጨረሻ ያለው አንድ ሳምንት ብቻ ቢጾም፤የሚል ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ይህንን ያሉት ያው እንደተለመደው ለማስመሰል ያህል ነው እንጂ በአጠቃላይ ጾምን እንደማይቀበሉ በተለያዩ ጹሁፎቻቸው መረዳት ይቻላል፡፡የማያምኑበትን ጾም ከመተቸትና ማስተካካያ ከመስጠት ጥቅልል አድርገው ጾም አያስፈልግም ቢሉ የተሻለ ነበር፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤ/ክ እምነትና በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት ስንመለከት ግን ፤በአጭር አገላላጽ፤/ ወደ ዝርዝሩ ለመግባት ርዕሳችን ስለማይፈቅድልን / ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ጾሞ እንድንጾም፤ጸልዮ እንድንጸልይ በአጠቃላይ መልካም ሥራዎችን ሰርቶ እኛም እንድንሰራ አዝዞናል፡፡ወደፊት ለፍርድ ሲመጣም ዋጋችንን የሚከፍለን እንደየስራችን መሆኑን አስረግጦ ነግሮናል፡፡በመሆኑም ከጾም ጀምሮ ሌሎችም ምግባረ ሰናያት በአግባቡ ከተፈጸሙ ለሥጋችንም ለነፍሳችንም ጠቃሚዎች ናቸው፡፡
ከዚህም ሌላ ከመግለጫቸው በገጽ 25 ላይ "የቅዱሳት መጻሕፍት ቀኖና" ብለው ባስቀመጡት ዝርዝር ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ አንቀበልም ብለዋል፡፡/ይሄ መብታቸው ነው፤የሉተር ልጆች ስለሆኑ ከዚያም ማሳነስ ይችላሉ/ በዚህኛው ርዕስ ሥር   በገጽ 43 ደግሞ፤ ስሙን ብቻ እንጂ ትርጉሙን፣ ምሥጢሩንና ጥቅሙን የማያውቁትን ማሕሌቱን፣ ሰዓታቱን፣ ቅዳሴውን፣ ቅኔውን፣ ዜማውን፣ ምጽዋቱን፣ አስራቱን፣በኩራቱን፣በዓላቱን፣የአብነትና የነገረ መለኮት ትምህርቶችን፣ገድላቱን ድርሳናቱን /አዋልድ መጻሕፍቱን/ ሌሎችንም ሁሉ "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" በማለት በማይመለከታቸው ጉዳይ ገብተው ሲጨነቁና ሲጠበቡ ይታያሉ፡፡አቤት ድፍረት! አቤት ባዶ ጩኸት! አቤት ግራ ተጋብቶ ግራ ማጋባት! ለመሆኑ በየትኛው እውቀታቸው ነው ይህንን ሁሉ የቤ/ክ ዶግማውን፣ ቀኖናውን፣ትውፊቱን፣ ዜማውን፣ ቅኔውን፣ ድርሳናቱን፣ ገድላቱን፣…ወ.ዘ.ተ መርምረው! በመጽሐፍ ቅዱስ መዝነው! የሚቀበሉትንና የማይቀበሉትን የሚለዩት? በዚህ ከንቱ ውትወታቸውስ እነማን ይታለላሉ ብለው ይሆን እንዲህ የሚደክሙት?

በጣም የሚገርመው ደግሞ "አባ ሰላማ" በተባለው ድረ-ገጻቸው ላይ በፈረንጆቹ አቆጣጠር Thursday, June 23,2016 በለጠፉት ጹሁፍ፤ድርሳናትንና ገድላትን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡፡"…በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የሆኑና ቤተክርስቲያኒቱ ከወንጌል ጋር አንዳንዴም ከወንጌል በላይ ስፍራ የምትሰጣቸው ትውፊቶች፣ድርሳናት፣ገድላት ከዚያም ባለፈ ልዩ ልዩ አስማትና ተረቶች የእግግዚአብሔርን የክብር ሥፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን ያስተዋሉና ከውስጥ የተነሱ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ከነበሩበት ሁኔታ እየሰፉና እያደጉ መጥተዋል፡፡ " / በነገራችን ላይ "አባ ሰላማ" ተብየው ድረ-ገጻቸው ላይ የሚለጥፉት ጽሁፍ ከስድብ፣ ከአሉባልታና በሬ ወለደ ከማለት ያልተናነሰ የግለሰቦችን ስም ከማጥፋት በስተቀር ቁም ነገር የሌለው መሆኑን እግረ መንገዳችንን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡/

አንባቢዎች እዚህ ላይ ልብ በሉ እንግዲህ! በዚያው በአንድ እራሳቸው ስንት ምላስ እንዳለቸው! "መጽሐፍ ቅዱስን በማይቃረን መልኩ እንጠቀምባቸዋለን" ያሏቸውን መጻሕፍት "የእግግዚአብሔርን የክብር ሥፍራ ወስደውና ጋርደው መገኘታቸውን…" በማለት መልሰው እንደ እንቧይ ካብ ይንዱታል፡፡ይህንን ሁሉ ለማሳየት የፈለግነው እንኳን ወንጌል አስተምረው ሌላውንም ወደ እውነት ሊመሩ ይቅርና ለራሳቸውም የሚመሩበት ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ አቋም የሌላቸው መሆኑን ሁሉም ሰው እንዲረዳው ለማደረግ ብቻ ነው፡፡
እንዴ! አይገርማችሁም? አሁን ያሉት የተሐድሶ ድርጅቶኮ እኛ እያየናቸው የተመሰረቱ ናቸው፡፡ገና 30 አመት እንኳን አልሞላቸውም፡፡እባካችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በጭፍን ከመንቀፋቸሁ በፊት በቀና ልቡና ሆናችሁ ተማሩ፤ያልገባችሁን ጠይቁ፤አትቸኩሉ፤ሃይማኖቱ ካልተመቻችሁ ደግሞ በመሰላችሁ መንገድ መሄድ እንጂ በግድ የተያዛችሁ ይመስል የማታምኑበት ቤ/ክ ውስጥ ሆናችሁ አታውኩን እያልናቸው ነበር፡፡ግን አልሰሙንም፡፡ምክንያቱም እነሱ የተሰማሩት ለመንፈሳዊ ሥራ ሳይሆን፤በመንፈሳዊ ካባ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ሌላ ደባ ለመፈጸም ስለሆነ፡፡ እነዚህ ናቸው እንግዲህ ከአዲስ ኪዳን ጀምረን እንኳን ብንቆጥር 2000 ዘመናት ያሳለፈችውን ቀጥተኛይቱን የተዋህዶ ሃይማኖት የሚተቹት፣የሚነቅፉትና የሚሳደቡት!

የማጠቃለያ መልእክት

እንግዲህ "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን! በሚል ርዕስ በአራት ተከታታይ ክፍሎች ከብዙው በጣም በጥቂቱ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሞክረናል፡፡ባለ 44 ገጹ የእምነት መግለጫቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ለመመዘንም እንኳን የማይበቃ ባዶ የቃላት ጋጋታ፣ ፉከራና ስድብ ብቻ መሆኑን ቁልጭ አድርገን አሳይተናል፡፡ተገቢውን ምላሽ ግን ከኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሊቃውንት እንጠብቃለን፡፡በእኛ በኩል ለጥፋት መልእክተኞቹ ለተሐድሶዎች አጭር መልእክት አስቀምጠን ርዕሳችንን እንቋጫለን፡፡

ለተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች በያላቸሁበት፤
እባካችሁ !
በብእር ስምና በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች ጀርባ ተደብቃችሁ፤
በተለያዩ የቤ/ክ አገልግሎት ክፍሎችና በየአጥቢያ ቤ/ክ ተሰግስጋቸሁ፤
በማታመኑበት እምነት ውስጥ አዩኝ አላዩኝ በማለት እየተጨነቃችሁ ፤
የእመቤታችንና የቅዱሳን ስም ሲጠራና መስቀል ስታዩ እየበረገጋችሁ፤
ማህሌቱን ቅዳሴውን ስትሰሙ እየተቃጠላችሁ፤ የምትኖሩት እስከ መቼ ነው?
ከተደበቃችሁበት ውጡና ፊት ለፊት እንነጋገር፡፡ሃሳባችሁን በመናገራችሁ ተፈለጡ ተቆረጡ የሚላችሁ የለም፡፡ብዛ ቢል ስህተታችሁን ካመናችሁ ንስሃ ግቡ፤ ካላመናችሁ ደግሞ የማታምኑባትን ቤ/ክ ለቃችሁ ውጡ ብትባሉ ነው ፡፡በእውነት በወንጌል የምታምኑ ከሆነ  አስመሳይነት በሃይማኖት ውስጥ ቦታ ስለሌለው ኮራ ብላችሁ እራሳቸሁን ችላችሁ እምነታችሁን በአደባባይ ስበኩ፡፡ለአዳራሽ ኪራይና ለአጠቃላይ እንቅስቃሴያችሁ ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑ ፈረንጆች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ገንዘቡን ለቤ/ክ ማጥፊያ ከምትበትኑት ለራሳችሁ የሚጠቅም ነገር ብትሰሩበት ይሻላል፡፡ እኛ ግን ያለችን አንድ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ሃይማኖታችንም መተኪያ የሌላት አንዲት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ብቻ ስለሆነች ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጃችሁን አንሱ! እያልን በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን፡፡

ለቀጣዩ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡

አነሳስቶ ላሰጀመረን ፤አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ምሥጋና ይድረሰው፡፡




No comments:

Post a Comment