"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ
ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሁለት)
ከክፍል ሃያ አንድ የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል
አስራ ዘጠኝ ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ
ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ መግቢያውን ተመልክተን በይደር አቆይተን፤ በክፍል ሃያ ደግሞ "ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ" የተባለች እህታችን ስለ ተሐድሶ መጠነ ሰፊ
ስህተቶች የጻፈችውን አስነብበናችሁ፤እንዲሁም በክፍል ሃያ አንድ "እምነ ጽዮን" ከተባለው ብሎግ ያገኘነውን ጠቃሚ
ዘገባ አስነብበናችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሁላችንም
የተዋህዶ ልጆች እንደምናውቀውና እኛም ይህንን የመወያያ መድረክ(ወልድ ዋሕድን)ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው፤
እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› ብለው የሚጠሩት መናፍቃን፤ኑፋቄያቸው ከተለያዩ የፕሮቴስታንት የእምነት ድርጅቶች የተውጣጣ መሆኑ እየታወቀ፤
ልክ ጠላታችን ሰይጣን ሰውን ለማሳሳት የብርሃን መልአክ መስሎ እንደሚታይ ሁሉ፤እነሱም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ለመምሰል
የማያምኑበትን የተለያየ ሥርዓት ሲፈጸሙ ይታያሉ፡፡(በእምነት ለሚቀበሉት የሚያድን እሳት፤ሳያምኑበት ለሚቀበሉት የሚባላ እሳት የሆነውን
ቅዱስ ቁርባንን በድፍረት እስከ መቀበል ድረስ!)
አሁን ወደ ጥንት ነገራችን ተመልሰን፤
ስለ "ተሐድሶ የእምነት መግለጫ" ቀጣዩን ክፍል እንዳስሳለን፡፡(ክፍል ሁለት)
ቀደም
ብለን በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፤ የዚህ መልእክታችን ዋና ዓላማ እነዚህ ተኩላዎች የለበሱትን የበግ ለምድ ገፎ ተኩላነታቸውን ለማሳየት
ያህል እንጂ እነርሱ ሥራ ፈትተው ሌላውን ሥራ ለማስፈታት ለጻፉት እርስ በርሱ ለሚጣረስ "መግለጫቸው"ለእያንዳንዱ
አንቀጽ መልስ ለመስጠት ባለመሆኑ አለፍ አለፍ እያልን የተወሰኑትን ብቻ እንመለታለን፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡
የ"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" አጠቃላይ ይዘት፤
ሀ/
የእምነት መግለጫቸውን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለማስመሰል የተጠቀሙባቸው የማጭበርበሪያ ስልቶች፤
1/ በአሁኑ ዘመን ለቋንቋ ጥናትና
ለምርምር ሥራ ካልሆነ በስተቀር ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውጪ የግዕዝ ቋንቋ የሚጠቀምበት እንደሌለ ማንም የማይክደው ሲሆን እነሱ ግን ይህንን የግዕዝን ቋንቋ መጠቀማቸው አንዱ የዋሃንን የማደናገሪያ ስልት ነው፡፡
2/ "መክሥተ አርእስት"
ብለው የጠቀሱት፦ጸሎተ ሃይማኖት፣አመክንዮ ዘሐዋርያት፣የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች የሃይማኖት ውሳኔዎች፣የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ
ጉባኤያት፣የቤ/ክ ታሪክ፣አዋልድ መጻሕፍት፣መጻሕፍተ ሊቃውንት፣ገድላት ድርሳናትና ተአምራት፣ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ነገረ ቅዱሳን፣ነገረ
ማርያም፣…በማለት በአርእስትነት የተጠቀሙባቸው ቃላትና ክፍለ ትምህርቶች በሙሉ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ በስተቀር ተሐድሶን
ጨምሮ በየትኛውም የእምነት ድርጅት የማይታመንባቸው መሆኑ እየታወቀ፤ እነሱ ግን ያው ዓላማቸው መስሎ ለማሳሳት ስለሆነ እነዚህን
ቃላት ተጠቅመው ጽፈዋል፡፡ሆኖም በእያንዳንዱ ርእስ ሥር የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ወደ ዝርዝሩ ስንገባ
የምናየው ይሆናል፡፡
3/ ተሐድሶዎች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን
እምነት፤ሥርዓትና ትውፊት እየተቃወሙ፤ነገር ግን "እናት ቤተ ክርስቲያናችን" እያሉ ስሟን ያለ አገባብ /ለማስመሰል/
እየጠቀሱ መጻፋቸው ነው፡፡
እዚህ ላይ አንባቢ እንዲፈርድ፤ እነሱ በዚሁ የእምነት መግለጫቸውም ሆነ
በየ ድረ-ገጾቻቸው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚሳደቡበትን አጸያፊ ቃላት መጥቀስ ይቻል ነበር፡፡እኛ ግን
ለቤተ ክርስቲያናችን ክብር ስንል መጻፍ አንፈልግም፡፡ስድብን በተመለከተ በመጨረሻው ዘመን የሚነሱ አሳቾች በአውሬ በተመሰለው በዲያቢሎስ
መንፈስ እየተመሩ እግዚአብሔርንና ማደሪያውን እንደሚሳደቡ በወንጌላዊው ዮሐንስ የተነገረውን ትንቢት በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 13
የተመዘገበውን ስንመለከት፤ተሐድሶዎቹ በገዛ እራሳቸው የዲያቢሎስ የግብር ልጆች መሆናቸውን መስክረዋል፡፡
ለ/
የእምነት መግለጫቸውን ያዘጋጁበት ምክንያት፦
ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 11 መግቢያ የተወሰደ፦"በልዩ ልዩ ምክንያቶች በማንነት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው የተሐድሶ
አገልግሎት አንዱ ጉድለትም ይህ ነው የሚባልና ወጥ የሆነ ኹሉም በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ የሚቀበሉት የእምነት መግለጫ የሌለው
መሆኑ ነው፡፡ይህንን ክፍተት ለመሙላት በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ይህንን የእምነት መግለጫና በዚያ ላይ የተመሰረተውን
አስተምህሮና ሌሎች ከእንቅስቃሴው ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የያዟቸውን አቋሞች ያካተተውን ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓቸዋል፡፡"
የተዋህዶ ልጆች እዚህ ላይ ልብ በሉልኝ!
ከዚህ በላይ በተመለከትነው የእምነት መግለጫቸው እንደገለጹት፦
1/ እነሱ ለእራሳቸው የሚይዙትን
የሚጨብጡትን አጥተው አእምሯቸው /አስተሳሰባቸው/ የተቃወሰባቸው መሆኑን እየነገሩን ነው፡፡ ታዲያ "እራሷ ክርስትና ሳትነሳ
ልታቋቁም ሄደች" የሚለው ተረት አይስማማቸውም?
2/ እንደነሱ አባባል፤ በማንነት
ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከብዙ ጉድለቶቹና ክፍተቶቹ
አንዱ የእምነት መግለጫ ያልነበረው መሆኑ ሲሆን፤ይህም የተዋህዶን ሃይማኖት ከማጥፋት በስተቀር እውነተኛና ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርት ይዘውና አቅደው እንዳልተነሱ ያረጋግጣል፡፡ለመሆኑ
በራሱ ጉደለትና ክፍተት ያለበት "እምነት" ይዘው ነው ስንዱዋን እመቤት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚቹት? በእውነቱ እራስን አለማወቅ ትልቅ ድንቁርና
ነው!
3/ ከአሁን በፊት "ተሐድሶ
የሚባል የለም እነ እንትና የፈጠሩት ወሬ ነው" ሲሉ እንዳልነበር፤ዛሬ ማጣፊያው ሲያጥራቸው የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን
በራሳቸው አንደበት መናገራቸው፤ ከጥንቱም የድርጅታቸው መሠረቱ ሐሰት/ውሸት/ መሆኑንና ዓላማቸውም ከግብር አባታቸው ከሐሰት አባት
ከዲያቢሎስ የተወረሰ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡
4/ "ኹሉም
በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ …"የሚለው አባባል በመካከላቸው የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ነገር
ግን እንደ ወንጌሉ ቃል እርስ በእርሱ የተለያየ መንግስት አይጸናም፡፡
ሐ/
እነዚህ የውስጥ መናፍቃን /ተሐድሶዎች/ ከነባሮቹም ሆነ በየጊዜው ከሚፈበረኩት የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ጋር ተባባሪ ስለመሆናቸው፤
ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 5/የተወሰደ፦ "……ቤተ ክርስቲያን ራሷን በእግዚአብሔር ቃል እንድትመረምርና ከዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድትወጣ በየዘመናቱ ከውስጥም
ከውጭም ልዩ ልዩ ተሐድሷዊ ጥሪዎች ሲተላለፉ ኖረዋል፡፡አሁንም እየተላለፉ ይገኛሉ፡፡በታሪክ ከሚጠቀሱት መካከልም በዋናነት ከውስጥ
በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ፤ ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን ቀርቦ የነበረውን ትችት መጥቀስ ይቻላል፡፡…"
ማስገንዘቢያ፤አንባብያን እዚህ ላይ ልብ እንበል!
1/ ከውስጥ
በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ መቀበል ነበረባት፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ
ገጽ 49 እንዲህ ይነበባል፦
"የቤተ ክርስቲያናችን ስነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብን ያስፋፉት፣አምልኮ ጣኦትን
ከምድረ ኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት የታገሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው፡፡ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሡት በ1444-1468 ዓ.ም ነው፡፡ከዚህም
ሌላ በዘመናቸው ዜና መዋዕላቸው እንደሚለው ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ስግደት አይገባም የሚሉ መናፍቃን
እንደ ተነሱ ይጽፋል፡፡ይኸው ዜና መዋዕል እንደሚለው እነዚህን መናፍቃን ንጉሡ ባሉበት ሊቃውንቱ ተከራክረው ረቷቸው፡፡……"
2/ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን የቀረበውን ትችት መቀበል ነበረባት፤ ፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ
ገጽ 57-59 እንዲህ ይነበባል፦
"ኢየሱሳውያን የሚባሉት ካቶሊኮች ተንኮል ውስጥ ውስጡን ሲሔድ
ቆይቶ በይፋ የተከሰተው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡/1607-1632/ ጴጥሮስ ፓኤዝ እንደ አንድርያ ኦቢያዶ ግትር ሳይሆን
በጣም ፈሊጠኛ ነበር፡፡የሀገሪቱን የአምልኮት ማቅረቢያ ቋንቋ ግዕዝ ተምሮ ይሰብክ፤ ይቀድስ ነበር፡፡ወደ ንጉሡ እየቀረበ የሮማ ካቶሊክን
እምነት ቢቀበሉ የፖርቱጋል መንግሥት የጦር መሣሪያ ያስታጥቅዎታል እያለ ይሰብካቸው ነበር፡፡…ዐፄ ሱስንዮስ በ1622 ዓ.ም በጴጥሮስ
ፓኤዝ እጅ ከነቤተሰቦቻቸው በሮማ ካቶሊክ ሥርዓት ተጠምቀው ካቶሊክነታቸውን አስታወቁ፡፡ (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 57)…ዐፄ ሱስንዮስ
በነገሡ በ27ኛው ዓመት ታመው አንደበታቸው ተዘጋ፤…የገዳማቸው መነኮሳት….ሦስት ሱባኤ በጸሎት በምህላ ቆይተው ጸበል አጠመቋቸው
በዚህ ጊዜ የተዘጋ አንደበታቸው ተፈታ…፡፡" (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 59)
እንግዲህ
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መቀበል ነበረባት እያሉ እንደ አብነት የጠቀሷቸው ከላይ የተመለከትናቸውን "ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል
ስግደት አይገባም" ይሉ የነበሩትን የውስጥ መናፍቃን ደቂቀ እስጢፋን/እስጢፋኖስን/፤ ከውጭ ደግሞ ኢየሱሳውያን የተባሉትን
የካቶሊክ መልክተኞችን ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር ለማጥፋት የተሰለፉ ነበሩ፡፡እንግዲህ የዛሬዎቹ
"ወንጌላውያን" ነን ባዮች /ተሐድሶዎች/ በጥቂቱ 500 አመታትን ያስቆጠረውን፤ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ኩራት፤ለመናፍቃን
እፍረት፤የሆነውንና በዚያን ጊዜ ቅዱሳን አባቶች በቂ መልስ ሰጥተውና በእግዚአብሔር ቃል እረትተዋቸው የዘጉትን ታሪክ እያስታወሱ፤
አሁንም በድፍረት ይህንኑ የጥፋት መልእክት ተቀበሉ እያሉ የሚወተውቱት፤ እውነትም በማንነት ቀውስ ውስጥ ቢሆኑ አይደል እንዴ?
ሌላው ቢቀር!
1/ ዐፄ ሱስንዮስ በካቶሊክ ሥርዓት
ሲጠመቁና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ሲያውጁ አንደበታቸውን የዘጋውን፤
2/ ተጸጽተው ንስሃ ሲገቡ ደግሞ
በአባቶች ጸሎትና በጸበል ተጠምቀው ወደ ቀደመ ጤንነታቸው የመለሳቸውን፤
3/ በዚህም የተዋህዶ ቤ/ክ በእግዚአብሔር
ወልድ ደም የተመሰረተች በመሆኗ ያረጋገጠበትን፤
4/ በአጠቃላይ ከዚችው ከአንዲቱ
ተዋህዶ በስተቀር ሌላው ሁሉ ከንቱ መሆኑ፤/በክርስትናው ዓለም ውጭ ያሉትን አይጨምርም/
አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በድንቅ
ተአምራት የመሰከረውን እውነት መቀበል አለመቻላቸው፤ አይነ ህሊናቸው
የታወረና "እምነት" ብለው የያዙትም መንገድ/ተሐድሶ/ ከእውነት የራቀ ለመሆኑ ሌላ ምስክር አያሰፈልገውም፡፡
ውድ አንባብያን!
የተሐድሶ ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም ገና ብዙ አስቂኝ ነገር አለ፡፡!
እንደ እግዚአብሔር
ፈቃድ በሌላ ጊዜ እንቀጥላለን፡፡
እናንተም
ከጾምና ከጸሎት ጋር በትዕግስት ጠብቁን፡፡
"ንቁ
! በሃይማኖት ቁሙ!"
የዘወትር
መልእክታችን ነው፡፡!
No comments:
Post a Comment