Tuesday, August 8, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ አንድ

ከክፍል ሰላሳ የቀጠለ፦

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?

ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

      ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡
     ዛሬ በዚች ክፍል የምናስነብባችሁ "ማቴዎስ ናታኒም" የተባሉ ወንድማችን በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ "ነገረ ክርስቶስ በገድላት" በሚል ርዕስ ያስተላለፉትን ጠቃሚ ትምህርት ነው፡፡የመልእክቱ ይዘት  ለእኛ ለተዋሕዶ ልጆች ትምህርት፤ እንዲሁም ሳይገባቸውና ሳይገባቸው (" "ጠብቆ ይነበብ) ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለሚተቹ ደግሞ ምላሽ የሚሰጥ ስለሆነ ሁላችን አንብበን እንድንጠቀምበት ማስተዋሉን ያድለን፡፡
ጽሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማድረግና አንዳንድ የፊደላት እርማት ከማድረግ በስተቀር የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡

ነገረ ክርስቶስ በገድላት
======///=======
 የሚነበብ ጠቃሚ ትምህርት ነው!
 ዝክረ ቅዱሳን ዝክረ ቅዱሳን።
የተሃድሶ መናፍቃን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ከሚተቹባቸው መንገዶች አንዱ በቅዱሳን ገድላት ላይ ነው:: እስቲ ለመናፍቃኑ ምላሽ ይሆን ዘንድ ነገረ ክርስቶስን በገድላት ውስጥ እንመልከት።
ነገረ ክርስቶስ ምንድነው?
ነገረ ክርስቶስ ስለ ክርስቶስ የባህርይ አምላክነት የምንማርበት ምስጢር ነው:: አንድም ከድንግል ማርያም በነሳው ስጋ በምድር ላይ ተመላልሶ ከኃጢአት በስተቀር የሰው ልጅ የሚሰራውን ስራ ሁሉ ሰርቶ ለሰው ልጆች ፍቅር ሲል የከፈለውን ቤዛነት የምንረዳበት፣ የድህነት  ስራዎቹ የሚዘረዘርበት ትምህርት ነው:: ይህንንም የምናገኘው ከአምስቱ አዕማደ ምስጢር አንዱ በሆነው በምስጢረ ስጋዌ ነው።
ገድል ማለት ምን ማለት ነው?
ገድል፦ "በቁሙ ትግል፣ ፈተና፣ ውጊያ ሰልፍ ድልና አክሊል እስኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም፣ የሚሰሩት ስራ የሚቀበሉት መከራ ማለት ነው":: የገድል መጽሐፍት ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ ትዕዛዘ እግዚአብሔር እንዲከበር ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ከአላውያን ነገስታት፣ ከቢጽ ሐሳውያን፣ ከጠላት ዲያብሎስና ከፍቃደ ሥጋ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያወሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሃይማኖታቸው በኑሯቸው እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳዩ የሕይወታቸው መስታወቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ገድል ስንል የቅዱሳን ታሪክ፣ ተአምራት፣ ቃልኪዳንና መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህ እንዲህ ይሆናል፤ ይቻላል፤ ተብሎ የተነገረው ቃል በእውነት የሚኖር/ "" ጠብቆ ይነበብ/ በቃልና በሥጋም የሚገለጥ እንደሆነ የምናየው በቅዱሳን ገድል ነው።
ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው ራሱ የሐዋርያት ሥራ የምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያትን ግብር /ሥራ/ ገድልና ዜና የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ ከብሉይ ኪዳንም መጽሐፈ ጦቢት፣ መጽሐፈ አስቴር፣ መጽሐፈ ሶስናና የመሳሰሉትን በሰዎቹ ኑሮ የተገለጠውን የእምነታቸውን ፍሬ የሚያሳዩ የገድል መጽሐፍት ናቸው።
ገድላት በሶስት ይከፈላሉ። እነርሱም፦
ገድለ ሰማዕታት፦ ለምሳሌ ገድለ ጊዮርጊስ፣ ገድለ ፋሲለደስ፣ ገድለ ኢየሉጣ፤
ገድለ ሐዋርያት፦ በአንድነት የተሰበሰቡ የሐዋርያት አገልግሎት ተአምራት መከራ የያዙ መጽሐፍት፤
ገድለ ጻድቃን፦ ገድለ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስና የመሳሱሉትን ነው።
ስለሆነም የእያንዳንዱ ቅዱስ ስራ ተጽዕኖ ከትውልድ ወደ ትውልድ ቢተላለፍ ከዚህ ቅዱስ በረከት ከማሰጠቱም ጋር ለሕይወት አስተማሪ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የእያንዳንዱን ቅዱስ ስራ የሚገልፀው መጽሐፍ "ገድል" ይባላል ይኸውም ከፍትወታት እኩያትና ከአጋንንት ጋር ያደረጉትን ተጋድሎና ያሸነፉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው ፡፡ጠላት ሰይጣን እያንዳንዱን ሰው የሚፈትነው ሊያሸንፈው በሚችልበት መልኩ ስለሆነ የእያንዳንዱን ቅዱስ ገድል ማንበብ የሰይጣንን ልዩ ልዩ አመጣጥ ያስተምራል፡፡ ታሪክ መጻፍ ካለፈው ለመማር ነውና ከቅዱሳንም ህይወት ጠቃሚ ትምህርት ይገኛል።
አንድ ሀገርና ህዝብ በታሪኩ ውስጥ የነበሩትን ባለውለታዎቹን ስማቸው እንዳይረሳና ለተተኪ ትውልድም አርአያ እንዲሆኑ ሥራቸውንም በመጻፍና በማስተማር ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፋል፡፡ ለስማቸው መታሰቢያ እንዲሆን መንገዶችን፣ ጎዳናዎችን፣ አዳራሾችን፣ ህንጻዎችንና የመሳሰሉትን በስማቸው ይሰየማል፡፡ ሐዋርያዊትና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ቅዱሳን ልጆችዋ በሃይማኖት ያፈሩትን ፍሬ ለመታሰቢያቸው እንዲሁም ለትውልድ ትምህርት እንዲሆንና በረከትም እንዲያስገኝ ጽፋ ታስቀምጣለች፡፡ ገድል ከሰዎች ጋር ብቻ የሚገናኝ ነው ለምሳሌ፦ ለመላእክት ድርሳን እንጂ ገድል አንልም ገድል ስጋችንን ለማሸነፍ የምናደርገው ተጋድሎና ከአላውያን ነገስታት፣ ከመናፍቃን፣ ከኢ-አማንያን ጋር የምናደርገው ተጋድሎ ነው።
ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውን? አዎ።።። ይህም፦
ይሁዳ 1፥3 "ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።"
ዕብ 11፥32 "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና።"
1ኛ ቆሮ 9፥24 "በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ፤ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።... የመሳሰሉትን ጥቅሶች ማንሳት ይቻላል።"
ገድል መጽሐፍ ቅዱስ ተተርጉሞ ያየንበት ነው፡፡ ለምሳሌ ማር 16፥17 ላይ ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ ይላል፡፡ ነገር ግን እነ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ አንበሳውን ባይጋልቡ፣ እነ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንበሳና ነብርን ባያስገዙ፣ እነ አቡነ አረጋዊ ዘንዶውን ባይጨብጡ ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስን ማን ኖሮት ያውቃል? በማለት ምንፍቅና ውስጥ እንገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ገድላት መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎማቸው ምንፍቅና ውስጥ እንዳንገባ ታድገውናል።
አንድ ገድል በትንሹ ስድስት ነገሮችን ይይዛል ለምሳሌ፦
1ኛ፦ ታሪክ፦ ይህም የቅዱሳንን ከትውልድ እስከ እረፍት ወይም እስከ እርገት  ድረስ ያለውን ታሪክ ይይዛል፡፡
2ኛ፦ ተጋድሎ፦ የቅዱሳንን የተጋድሎ ብዛት፣ አይነት፣ ስቃይ፣ የገዳዮችን ጭካኔ ያሳያል፡፡
3ኛ፦ ትምህርት፦ ስለፀሎት፣ ስለ ቤተክርስቲያን፣ ስለ አለባበስ፣ ቅዱሱ ስለተማረውና ስላስተማረው ትምህርት የያዘ ነው፡፡
4ኛ፦ ተአምር፦ ለቅዱሳን የተደረጉትንና ቅዱሳን ያደረጉትን ተአምራት ይይዛል፡፡
5ኛ፦ ፀሎት፦ ፀሎትን ያስተምራል፡፡
6ኛ፦ ቃልኪዳን፦ ለቅዱሳን ከፈጣሪያችን የተገቡ ቃል ኪዳኖችን ይይዛል... ስለዚህ ከአንድ ገድል በትንሹ እነዚህን ነገሮችና ከዚህ የበለጡትን  እናገኝበታለን ማለት ነው።
እስቲ ከላይ የተጠቀሱትን ስድስቱን ነገሮች  በአባቻችን በፃዲቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል ላይ እንመልከት፦
1ኛ፦ ታሪክ ፦ ገድለ ተክለሃይማኖት አባታችን እንዴት እንደተወለዱ፣ በነበሩበት ዘመን የአካባቢው መልክዓ ምድር ምን እንደሚመስል፣ በዚያን ጊዜ የነበረውን የአስተዳደር ሁኔታ ወይም የፖለቲካ ሁኔታ ምን አይነት እንደነበረ ለታሪክ አስቀምጦልናል።
2ኛ፦ ተጋድሎ፦ ይህም አባታችን ያደረጉትን ተጋድሎ ያሳያል ለምሳሌ፦ አባታችን በ16 አመታቸው ከግብፃዊው አባ ቄርሎስ ዲቁናን ተቀብለዋል፣ በወጣትነታቸውም ጊዜ ወላጆቻቸው ሊድሯቸው አስበው ነበር ነገር ግን አባታችን ራሳቸውን ለክርስቶስ እንደአጩ በመናገር በምንኩስና ኖረዋል፡፡ ይህንን እራስን ለክርስቶስ ማጨት ከየት ተማሩ ስንል  በ 2ኛ ቆሮ 11፥2 ላይ በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና ይላል፡፡ አባታችንም ራሳቸውን ለክርስቶስ ማጨትን የተማሩት ከቅዱስ ጳውሎስ ነው፡፡ ለዛም ነው ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ክርስቲያናችን ገድላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው ብላ የምታስተምረን፡፡ ገድለ ተክለሃይማኖት መጽሐፍም የአባታችንን ገድል ሲያጠቃልለው "ከዚህ በኋላ አባታችን ተክለ ሃይማኖት ተነስቶ የሐዋርያነትን ስራ ይከታተል ጀመረ ይኸውም ወንጌልን ለማስተማር፣ እንደጌታ ለመቸንከር፣ ወደመስቀል ለመውጣት፣ በክርስቶስ ስም ሁልጊዜ በሰማዕትነት ለመሞት ቆረጠ... የወላጅና የዘመድ ፍቅርን፣ የገንዘብ ፍቅርን ይህን ሁሉ ተወ አላሳዘነውም፡፡ አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ እያለ ቤቱ እንደተከፈተ ትቶ ወንጌልን ለማስተማር ፈጥኖ ወጣ... ፡፡የሀገሩም ሰዎች የክርስቶስን ስም ሲያስተምር ሰምተው በጠላትነት ተነሱበት" ይላል፡፡ ታዲያ ከአቡነ ተክለሃይማኖት ውጪ አርአያ ሊሆነን የሚችል ማነው?? ገድላቱም እንዲህ ነገረ ክርስቶስን እየሰበኩ ይቺን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሃድሶ መናፍቃን ክርስቶስን አታውቅም ለምን ይሏታል?? እኛ ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖትን ያከበርነው የክርስቶስን ስም ስላስተማሩ፣ ስለ ክርስቶስ እራሳቸውን ጃንደረባ ስላደረጉ፣ ስለ ክርስቶስ ስለተሰደዱ፣ ስለክርስቶስ ስለተነቀፉና ስለተጠሉ ነው ለዚህም ነው በ ማቴ 24፥9 ላይ በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ የተባለው ይህም ቃል በአቡነ ተክለሃይማኖት ላይ ተፈጽሟል።
3ኛ፦ ትምህርት፦ አባታችን ሲያስተምሩ ከስነ ፍጥረት ጀምሮ ነው፡፡ ለምሳሌ በገድላቸው ላይ እንደምናነበው አባታችን ሰዎችን ከአጠመቁና መንፈስ ቅዱስ ከአደረባቸው በኃላ ስለመንፈስ ቅዱስ ሊያስተምሩ ፈልገው ከላይ ከስነ ፍጥረት ጀምረው ካስተማሩ በኋላ "...ከዚህ ሁሉ በኋላ የአዳም ልጆች ኃጢአት አብዝተው ሰሩ በጥፋት ውኃ አጠፋቸው ከጥፋት ውኃም ስምንት ሰዎችን አዳነ ለነዚህ ወገኖች ኦሪትን፣ መጽሐፍትን፣ ነቢያትን ሰጠ እነርሱ ግን አልጠበቋቸውም በምንም በምን መዳን የማይቻል ቢሆን እርሱ ቅሉ አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ከክብርት እመቤታችን ያለ ዘርአብእሲ ተወለደ፡በሰላሳ ዘመን በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ተጠመቀ፡፡ ከዚያም ወጥቶ ወደገዳመ ቆሮንጦስ ገባ አርባ መአልትና አርባ ሌሊት ጾመ፡፡ የሰውነቱን ስራ ሁሉ ከጨረሰ በኋላ የጳንጦስ ሰው ጲላጦስ በተሾመበት ወራት ተሰቀለ መከራን ሁሉ ተቀብሎ ሞተ በሲኦል ላሉ ነፍሳት በአካለ ነፍስ ወርዶ ግዕዛንን ወይም ነፃነትን ሰበከላቸው፡፡ የዲያብሎስን ቁራኝነት አጥፍቶ በሶስተኛው ቀን ተነሳ፡፡ በተነሳ በአርባ ቀን በክብር በይባቤ አረገ፡፡ በአረገ በአስረኛው ቀን  ዛሬ እናንተ የከበራችሁበትን መንፈስ ቅዱስን ወደዚህ ላከላቸው፡፡" በማለት ስለ መንፈስ ቅዱስ ለማስተማር ከመጀመሪያው ጀምሮ ያለውን ታሪክ ነገሩን፡፡እንግዲህ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንዴት እንተወውና ነው ገድላት አያስፈልጉም የሚሉን?? ስለዚህ ገድል ላይ ያለው ትምህርት ክርስቶስን የሚሰብክ ነው።
4ኛ፦ ተአምር፦ ይህም ለጻድቁ የተደረገና ጻድቁ ያደረጉት ተአምር ነው ለምሳሌ፦ ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በተወለዱ በሶስት ቀናቸው እግዚአብሔር አምላካችንን "አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ" ብለው አመስግነዋል፣ በሰባት አመታቸው ደግሞ ወደ ክርስቶስ ፀልየው ውኃን አፍልቀዋል... ስለዚህ በገድሉ ላይ የተጻፈው አባታችን የሰሩት ተአምራት ነገረ ክርስቶስን ይሰብካል።
5ኛ፦ ፀሎት፦ ገድለ ተክለ ሃይማኖት እንዴት መፀለይ እንዳለብን የፀሎት ሥርዓትን ያስተምራል ለምሳሌ፦ አባታችን ሙታንን ለማስነሳት የፀለዩትን ፀሎት እንይ፦ "ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አልአዛርን ከሸተተ በኃላ በአራት ቀን ከመቃብር ያስነሳኸው አንተ ነህ፡፡ ናዪን በምትባል ሀገር የአንዲቷን ደሀ ልጅ እጁን ይዘህ ያስነሳኸው አንተ ነህ፡፡ ቀድሞም አንተ ነህ ዛሬም አንተ ነህ ሙታንን የምታስነሳ የኃያላን ፈጣሪ ሁሉንም ትችላለህ እንጂ የሚሳንህ የለም መግደልም ማዳንም ትችላለህና እነዚህ ሙታን ይነሱ ዘንድ ከሰማይ የቸርነትህን ዝናብ ላክ እያለ ለመነ" ይላል፡፡ ገድሉም እንደሚነግረን የዝናቡም ጠል ወረደ የሞቱትም ሰዎች ተነሱ ይለናል፡፡ ስለዚህ ይህ የአባታችን ፀሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነውና እኛም ኦርቶዶክሳውያን ገድላትን እንቀበላለን።
6ኛ፦ ቃል ኪዳን፦ ለቅዱሳን የሚደረገውን ቃል ኪዳንን መንቀፍ እግዚአብሔርን መንቀፍ ነው፡፡ ገድላቱ ላይ እግዚአቤሔር የገባውን ቃል ኪዳን ውሸት ነው ማለት እግዚአብሔር አያደርግም፣ ዋሽቷል ማለት ነው:: /ሎቱ ስብሐት/፡፡ ልናውቀው የሚገባው ነገር ክብር ይግባውን አምላካችን እግዚአብሔር ዋጋን የሚከፍለው በቅዱሳኑ ነው ምክንያቱም ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ መከራን የተቀበሉ ቅዱሳኑ ሊታወቁ ይገባልና ለምሳሌ፦ በገድለ ተክለሃይማኖት እንደምናነበው እግዚአብሔር አምላካችን "መታሰቢያህን ለሚያደርግ፣ ስምህን ለሚጠራ ሰው ሁሉ እኔ እስከ አስር ትውልድ እምረዋለው ብዬ በእውነት እነግርሃለው" አላቸው ይለናል:: ይህ አይነት ቃል ኪዳን ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም በዘፀ 20፥6 ላይ "ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና" ይላል:: ስለዚህ በእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር ለቅዱሳኑ የሚገባውን ቃል ኪዳን መቃወም ከፀረ ወንጌልነትም ባለፈ የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግስት እንዳይወርስ ምቀኝነትም ነው።
ስለዚህ ተወዳጆች ይህቺ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የማትታደስ እንደመሆኗ መጠን የተሃድሶ መናፍቃን ገድላት ነገረ ክርስቶስን አይሰብክም፤ ኦርቶዶክሳውያን ገድል የሚሉት የፈጠራ ወሬና ጥንቆላ ነው ከሚሉት ከሐሰተኛ ትምህርቶች እራሳችንን ጠብቀን በንጽህቷ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ነው የሚገባን፡፡ የትኛውንም የቅዱሳንን ገድል ብናነሳ ከክርስቶስ ወንጌል ውጪ የወጣ አንዳችም ነገር የለም የተሃድሶ መናፍቃኑም ልብ ገዝተው፣ ኑፋቄያቸውን ተረድተው ወደ እውነተኛዋ ኦርቶዶክሳዊ መንገድ ይመጡ ዘንድ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምኞት ነው።
የጻዲቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትና የሌሎቹም ቅዱሳን ረድኤት፣ በረከትና ምልጃ አይለየን!!! አሜን!!

 በወንድማችን ማቴዎስ ናታኒም--የህይወት ቃልን ያስማልን~!!!


No comments:

Post a Comment