ከክፍል ሰላሳ ሁለት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
የተከበራችሁ
አንባብያን በክፍል ሰላሳ ሁለት "በቀጣይ ጽሁፋችን እነዚሁ አጽራረ
ቤተ ክርስቲያን / ተሐድሶ ተብዬዎቹ/ እውነተኛ መስሎ ለማሳሳት የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና ስልቶች በመጠኑ እንዳስሳለን፡፡ "ብለን በይደር አቆይተነው እንደነበር
ይታወሳል፡፡አሁንም ይህ የቤት ሥራችን እንዳለ ሆኖ ለዛሬው "አዘክሪ ድንግል"በሚል ርዕስ እመቤታችንን የምንማጸንበት ወቅታዊ መልእክት አቅርበንላችኋል፡፡
መልካም በዓል፡፡
አዘክሪ ድንግል!!!
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ
እምነትና ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ቀን እስከ ነሐሴ አስራ አምስት ቀን ድረስ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን
የእርገቷን ወይም የፍልሰቷን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ፤ በግልም ሆነ በማኅበር ማለትም በቤተ ክርስቲያን፤ ከሌላው ጊዜ ለየት
ባለ ሁኔታ የጾምና የጸሎት ሥርዓት ይከናወናል፡፡በዚህ ጾም መካከል ነሐሴ አስራ ሦስት ቀን ደግሞ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትን የደብረ ታቦርን በዓልም እናከብራለን፡፡ነሐሴ አስራ ስድስት ቀን ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ለሁለት መቶ አምስት ቀኖች በገነት በዕፀ ሕይወት ዛፍ ሥር በክብር ተቀምጦ የነበረውን የክብርት እመቤታችንን ሥጋዋን ከነፍሷ አዋህዶ፤ከገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ያሳረገበት ዕለት በመሆኑ በታላቅ
ድምቀት የከበራል፡፡/ልክ እንደ ልጇ ትንሣኤ/፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን ለሚወዷት ለሚያከብሯት
በስሟም ለሚማጸኑ ሁሉ፤ ከየካቲት አስራ ሰድስት ቀን ቀጥሎ የምሕረት ቃል ኪዳን የገባላትም በዚሁ ዕለት ነው፡፡
እንግዲህ ዘመናችን
የዓለም ፍጻሜ መቃረቡን የሚያመለክቱ ብዙ አስከፊ ነገሮች እየተፈጸሙ ያለበት ዘመን መሆኑን ሁላችንም እያየን እሰማንም ነው፡፡ሰይጣንና
ገንዘብ ጌትነታቸው ከፍ ብሎ ከዓለሙ አልፈው በሃይማኖት ጥላ ስር ያሉትን ሳይቀር በተቆጣጠረበት በዚህ ዘመን የምንኖር ክርስቲያኖች
እራሳችንን፣ቤተሰባችንን፣ቤተ ክርስቲያናችንንና አገራችንንም ከዚህ ከዓለሙ ርኩሰት ለመጠበቅ የምንችለው በጾም፣ በጸሎትና በሌሎቹም
ምግባረ ሰናያት ስንጸና ብቻ ነው፡፡ስለሆነም ጾም ጸሎታችን ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስልን፤የጎደለውን ወደምትሞላልን ወደ እመቤታችን
ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም፤ቅዱስ አባታችን አባ ሕርያቆስ ባመሰገነበት
ምሥጋናና በጸለየው ጸሎት መማጸን አለብን፡፡
እንዲህ እያልን፦
ድንግል! ከፈጠረው ፍጥረት ትንኝን ስንኳ ከማይዘነጋ ልጅሽ አሳስቢልን፡፡
ድንግል! በቁርና በብርድ ወራት
በቤተልሔም ከአንቺ የተወለደው መወለድ አሳስቢልን፡፡አንተማ የባሕርይ አምላክ አይደለህም? ምን መወለድ አለብህ ለእኛ ብለህ አይደለም
ብለሽ፡፡
ድንግል! በቤተልሔም በወለድሽው
ጊዜ በጨርቅ የተጠቀለለውን መጠቅለል አሳስቢልን፡፡አንተማ ብርሃንን እንደ ልብስ የምትጎናጸፍ አይደለህም? በጨርቅ መጠቅለልህ ለእኛ
ብለህ አይደለምን ብለሽ፡፡
ድንግል! ሄሮድስ ልጅሽን እንዳይገድለው
ከእስክንድርያ ወደ ደብረ ቁስቋም፤ ከደብረ ቁስቋም ወደ እስክንድርያ ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢልን፡፡አንተማ ዓለሙን
ሁሉ በመሐል እጅህ የያዝህ አይደለህም? መሰደድህ ለእኛ ብለህ ነው እንጂ ብለሽ፡፡
ድንግል! በልጅሽ በወዳጅሽ ፊት
የወረደውን ጽኑዕ እንባ አሳስቢልን፡፡
እመቤታችን ከዕለተ ዐርብ በፊት አራት ጸኑ ኀዘን አግኝቷት ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡የዕለተ
ዐርብ ኀዘንና ልቅሶዋ ግን በፍጡር ህሊና የሚታሰብ አይደለም፡፡
አንደኛው፦ አረጋዊው ስምዖን በቤተ መቅደስ "ይህ ብላቴና ለእስራኤል ለልማታቸውም ለጥፋታቸውም የተዘጋጀ ነው፤ አንቺን ግን እንደ ጦር ልብ የሚከፋፍል
ኀዘን ያገኝሻል" ብሎ በተናገረ ጊዜ፡፡
ሁለተኛው፦ እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ
ጌታን ይዘው በተሰደዱ ጊዜ "ዮሳ" የተባለው የዮሴፍ ልጅ እየተከተላችው ነበርና ሲያገኛቸው " እናንተ በዚህ ባለ ጤና ሆናችኋል፤
በዚህ ሕፃን ምክንያት ግን በገሊላ በክንዷ ልጅ የታቀፈች ሴት የለችም "ብሎ በተናገረ ጊዜ፡፡
ሦስተኛው፦ ሰብአ ሰገል ለጌታችን ያመጡለትን የወርቅ ጫማ ሌቦች በሰረቁባት ጊዜ፡፡
አራተኛው፦ በረሃ በረሃውን ሲሄዱ ሽፍቶች አግኝተዋቸው የጌታችንን ሥረወጽ (ስፌት ያልነካው) ልብሱን ገፈው ከሄዱ
በኋላ እልፍ ብለው ሲማከሩ አይታ "ወንበዴ አዩኝ አላዩኝ ብሎ የቀማውን ቀምቶ ይሄዳል
እንጂ ቆሞ ይማከራል? ልጄን ሊገድሉት ነው እንጂ" ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡
አምስተኛው፦ የወልድ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዕለተ ዐርብ ልጅሽ ተሰቀለ
ባሏት ጊዜ በጭንቅ በመከራ ወደ ቀራንዩ ተጓዘች፡፡ እንዲህ እያለች "ልጄ ወዳጄ ሆይ በሊቀ ካህናቱ በሀና ግቢ የተቀበልከውን ግፍ ወሬው
መራራ ነው፤ልጄ ወዳጄ ሆይ ዛሬ ከእኔ ላይ ነጻነቴን አስወገድክ፤ ስለ ልደትህ በናዝሬት መልካም የምሥራች ነገሩኝ ዛሬ ግን በኢየሩሳሌም
ይህቺን ክፉ መርዶ አረዱኝ፤ በዮሴፍ ቤት መልካም ዜና ደረሰኝ በዮሐንስ ቤት ግን የሞት ዜና መጣብኝ፤ ልጄ ወዳጄ ሆይ በእንባና
በኀዘን በዓሌ ወደ ልቅሶ ተመለሰ፤ፋሲካም ወደ ልብ ኀዘን፡፡፡" እመቤታችን እንዲህ እያነባች እወደቀችና እየተነሳች ከመስቀሉ አጠገብ
ደረሰች፡፡ከተሰበሰቡት የአይሁድ ብዛት
የተነሳ ታላቅ መጨናነቅ ነበርና የምትወደውን ልጅዋን ማየት አልቻለችም፡፡ድንግልም ስለ ጽኑ መከራዋ ስለ ልቅሶዋ ስለ ብዙ እንባዋም
አንገቷን ወደ መሬት ደፍታ ነበር፡፡ጌታችንም እናቱንና ደቀ መዝሙሩን ዮሐንስን ባያቸው ጊዜ፤ ዮሐንስን "አነኋት እናትህ" እሷንም "እነሆ ልጅሽ" አላቸው፡፡ዮሐንስም ወደ ቤቱ ሊወስዳት ባለ ጊዜ እመቤታችን "ዮሐንስ
ሆይ በልጄ ላይ አለቅስ ዘንድ ተወኝ፣ከእርሱ ፈጥነህ አትለየን፣" እያለች ከልጅዋ መስቀል ቀኝ ቆማ ሳለች ድንግል ኀዘኑ ጸንቶባት ነበርና፤
ልቡዋን በኀዘን እጅግ ስለተነካ ከብቻው ለቅሶ በቀርም ያንን ታላቅ ጉባኤ መለስ ብላ አታይም ነበር፡፡ ዮሐንስም ወደቤት እንድትሄድ
ግድ ባላት ጊዜ ልጅዋን እንዲህ እያለችው ወደ ሀገር ተመለሰች፡፡"ልጄ ሆይ በላዩ በሰቀሉህ መስቀል ላይ እያለህ በፍቅር እሰናበትሃለሁ፣
ብርሃንን ስለተመላው ምራቃቸውንም ስለተፉበት ፊትህ እሰናበተሃለሁ፣ በሁለት ወንበዴዎች መካከል የሰቀሉህ ንጉሥ ሆይ ለመራቆትህ እጅ
እነሳለሁ፤ ሰላምታም አቀርባለሁ፤ ልጄ ሆይ በጠላቶችህ እጅ ላለው ለከበረው ልብስህ እጅ እነሳለሁ ሰላምታ አቀርባለሁ፤ ልጄ ሆይ
ከራስህ በላይ ለተደፋው የእሾህ ዘውድ እጅ እነሳለሁ፤ሰላምታ አቀርባለሁ…."፤ይህንንና ይህንን የመሰለ ለቅሶ እያለቀሰችና እየጮኸች ወደ ዮሐንስ
ቤት አደረሱዋት፡፡እስዋም ከመጮህና ከማልቀስ ዝም አላለችም፤ ከለቅሶዋና ከኀዘንዋ ብዛት የተነሳ ለዓይኖችዋ ሽልብታ አልሰጠችም፤
የልጇን ትንሣኤ እንከምታይ ድረስ እህል ውሃ አልቀመሰችም፡፡
ድንግል! የተራብሽውን መራብ የተጠማሽውን መጠማት፤ያዘንሽውን ኀዘን፤ከእርሱ
ጋር ያገኝሽን ጭንቅ ሁሉ አሳስቢልን፡፡
ድንግል! ጥፋትን ያይደለ ይቅርታ አሳስቢልን፡፡
ድንግል! ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥአን አሳስቢልን፡፡ጻድቃንንስ ሃይማኖት
ምግባራቸውን ምክንያት አድርጎ ይምራቸዋል፤ኃጥአንን ግን በምን ምክንያት ይምራቸዋል እያለች ታዝናለችና፡፡ /ምንጭ፦ ቅዳሴ ማርያምና
ድርሳነ ኪዳነ ምሕረት/
የመለኮት እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ምክንያት ያገኛትን ይህንን ሁሉ መከራና ኀዘን ተመልክቶ ልጇ
ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጣት የማይታበል ቃል ኪዳን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር በቸርነቱ የእመቤታችን አማልጅነቷ ከነፍስም ከሥጋም
መከራ ይጠብቀን፡፡አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment