ከክፍል ሰላሳ አንድ የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
"በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ"ማቴ.13፥34
ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ወደዚህ ዓለም የመጣበት አንዱና ዋነኛው ዓላማ የአዳምን ዘር ከወደቀበት ለማንሳት፣ ማለትም በኃጢአቱ ምክንያት ከተፈረደበት ሞት
ለማዳን ስለሆነ፤ ማንም ፍጡር ሊሳተፍበት በማይችለው የቤዛነት ሥራው አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ከሞት ወደ ሕይወት አሸጋግሮናል፡፡ መለኪያ
ለሌለው ለዚህ ፍቅሩ ምስጋና ይግባውና፤ ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ በአርአያነት ተግባሩ እኛም እንድንከተለው ምሳሌ ሆኖ ለማሳየት ነው፡፡
ሥግው ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ከኃጢአት በስተቀር
የሰውን ሥራ ሰርቶ፤ እኛም የእሱን ፈለግ ተከትለን፤እሱ በሚሰጠን ኃይልና አቅማችን የሚፈቅደው መጠን ተግተን እንድንሰራ፤ በዮሐ.14፥12
ላይ "እውነት እውነት እላችኋለሁ፤በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፡፡" በማለት በማይታበል ቃሉ አረጋግጦልናል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን በሚያስተምርበት ወቅት
በጣም ብዙ ሕዝብ፤ ለተለያየ ዓላማ ይከተለው እንደነበረ ቅዱስ ወንጌል ይመሰክራል፡፡የተወሰኑት ድንቅ የሆነ መልኩን ለማየት፣አንዳንዶቹ
ከበሽታቸው ለመፈወስ፣ ሌሎቹ ሕብስት አበርክቶ እንዲያበላቸው፣ግማሾቹ ደግሞ ሊያነግሱትም ይፈልጉ የነበረ ሲሆን፤ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን
ደግሞ ትምህርቱን ለማሰናከልና ቃሉን እያጣመሙ እሱን የሚከሱበት ምክንያት ለመፈለግ ነበር፡፡ይህ ብቻም አይደለም የሚከተለው ሕዝብ
የእውቀት ደረጃቸው፣የአኗኗር ዘይቤያቸው፣…እንዲሁ የተለያየ ነበር፡፡ሌላው ቀርቶ ሁሉን ትተው የተከተሉት ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል
እንኳን የተጠሩት ከተለያየ ሥራ በመሆኑ ይህ ልዩነት በእነርሱ መካከልም ይንጸባረቅ ነበር፡፡
የሁሉን ልብ መርምሮ የሚያውቅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ይህንን ሁሉ ሕዝብ ሲያስተምር፤ ቀድሞም በብሉይ ኪዳን እሱ የላካቸው ነቢያት በምሳሌ ይናገሩ እንደነበር፤ እሱም ይህንኑ የነቢያቱን
መንገድ ላለማፋለስና ትምህርቱንም ሁሉም እንዲረዳለት ለማድረግ ብዙ ጊዜ የሚያስተምረው በምሳሌ ነበር፡፡ለገበሬዎች በእርሻ በዘር፣
ለነጋዴዎች በዕንቁ በመክሊት፣ለሴቶች በቡሆ በእርሾ፣ እየመሰለ፤በእውቀታቸው ለሚመኩት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ደግሞ የሙሴን ህግ እየጠቀሰ፤ሊከራከሩት
ለሚመጡትም በመጡበት አኳኋን መልስ እየሰጠ በአጠቃላይ ለሁሉም እንደሚገባው አድርጎ አስተምሯል፡፡ከዚህ የምንረዳው ሰዎች እውነተኛውን
ትምህርት እንዲረዱና ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲገቡ ጥበብና ምሳሌን መጠቀም እንደሚገባ ነው፡፡
በመሆኑም "ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልን
ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ" ተብለው የተላኩት ቅዱሳን ሐዋርያትና በእግራቸው የሚተኩት ካህናትና መምህራን ይህንኑ የጌታችንን ፈለግ ተከትለው
ሲያገለግሉ፤እኛ ምእመናንም እንደ ተሰጠን ጸጋ መጠን በየተሰማራንበት መስክ የእውነተኛ ምእመንነት ሕይወት በመኖር አውደ ምሕረት
ላይ መቆም ሳይጠበቅብን ሌሎችን ማስተማር እንችላለን፡፡እዚህ ላይ አንድ ሊተኮርበት የሚገባው ነገር፤ ማስተማር ማለት፤በቃልም ይሁን
በመጽሐፍ ቃለ እግዚአብሔርን ለሰዎች ማድረስ ብቻ ሳይሆን፤ ለሌሎች የሚያስተምሩትን እውነተኛ ትምህርት በተግባርም እየፈጸሙ የሆነ
እንደሆን፤/ ለዓለም ብርሃን በመሆን/ የሚዘራው ቃለ እግዚአብሔር መልካም ፍሬ /ምእመናንን/ ያፈራል፡፡አገልጋዩም የሥራ ፍሬውን
ይዞ ሲቀርብ "አንተ በጎና ታማኝ አገልጋይ" ተብሎ ይሸለማል፤ፍሬዎቹም /ምእመናን/ ከመምህራቸው
ጋር ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይገባሉ፡፡ከአባቶቻችን በቃልም በሕይወትም ተማርነው እውነተኛ ትምህርት ይህ ነው፡፡
የተከበራችሁ የዚህ የመወያያ
መድረክ ተከታታዮች!
ይህንን የማይሻሻል፣የማይሻርና የማይለወጥ የወንጌል ቃል ይዘን፤አሁን
እኛ ወዳለንበት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ሁኔታ መለስ ብለን ስንመለከት ከወንጌሉ ቃል ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ
ነገር ጋር ተባበሩ” በማለት ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9 ባስተማረን መሠረት፤ ለዛሬው "አክሊሉ ደበላ" የተባሉት የሕክምና ባለሙያ ወንድማችን፤በዓለማዊው
ትምህርት ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው፤እንደ ቤ/ክ ልጅነታቸው ደግሞ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ያለችበትን
ሁኔታ ከላይ የገለጥነውን በምሳሌ የማስተማር ዘይቤ ተጠቅመው አሳይተውናል፡፡በሽታውን ብቻ ሳይሆን ለሥጋዊውም ሆነ ለመንፈሳዊው በሽታ
መድኃኒቱንም ከነአጠቃቀሙ፤ ቁልጭ አድርገው ነግረውናል፡፡ያውም ብዙ
ጊዜ ብዙ ገንዘብ ከፍለው ያገኙትን እውቀት በነጻ፡፡
ስለሆነም ሁላችንም እራሳችንን እየመረመርን ወይም እያስመረመርን፤በበሽታው ተይዘን ከሆነ ቶሎ ወደ ሕክምናው በመሄድ፤
በበሽታው አልተያዝን ከሆነ በሽታው ወደ እኛ እንደይመጣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ እንድንችል፤ ከላይ የጠቀስናቸው ወንድማችን፤እራሳቸውን
"ተሃድሶ" ብለው የሚጠሩና የተዋሕዶ ሃይማኖትን
አጥፍቶ በፕሮቴስታንት እምነት ለመቀየር ደፋ ቀና የሚሉትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች " ከነቀርሳ(ቲቢ)"በሽታ ጋር እያነጻጸሩ ያቀረቡልንን
ጽሁፍ፤ ለንባብ እንዲመች ከማድረግና አንዳንድ የፊደላት እርማት ከማድረግ በስተቀር የራሳችንን ሃሳብ ሳንጨምር አቅርበንላችኋል፡፡
መልካም ንባብ!
~~ተሃድሶ፣
ነቀርሳ(ቲቢ )ነው!~~
(አክሊሉ
ደበላ)
በሰው ላይ
እየተከሰቱ ካሉት በሽታዎች ውስጥ እንደ ቲቢ ሐራ ጥቃ ተሃድሶን የሚመስል አለ?
እስቲ ለሥጋም
ለነፍስም ጤንነት ይጠቅመናልና ስለበሽታው እንመልከት!
ቲቢ የሳንባ("የሳንባ
ነቀርሳ") ተብሎ በተለምዶ ይታወቅ እንጂ በመሠረታዊነት የማይጎዳ
የሰውነታችን ክፍል የለም፣ ጥፍር ሳይቀር። የጎሉቱ:-
ጭንቅላት፣ አጥንት፣ አንጀት፣ ማህፀን፣ ንፍፊት፣ ኩላሊት፣ ልብ ...ይሁን እንጂ ከነቀርሳ እተርፋለሁ ብሎ የሚገኝ አንድም
የሰውነታችን ክፍል የለም።
=ተሃድሶም እንዲሁ ነው። በተሃድሶ ምንፍቅና የተያዘ መንፈሳዊ ሰውነት ካለ፣ ይተርፍልኛል ብሎ የሚተማመን አካል አይኖረውም። ፆሙ፣ ፀሎቱ፣
ስግደቱ፣ ምግባሩ፣ ፍቅሩ፣ ትውፊቱ፣ ሥርዓቱ፣ ብሎም ሃይማኖቱ በተሃድሶ ምንፍቅና ነቀርሳ በማንኛውም ጊዜ ለጉዳቱ የተጋለጠ ነው።
ደግሞም ቀድሞ የተጠቃው ማንኛውም አካል ቢሆንም፣ ዞሮ ዞሮ ሁሉንም መበከሉ አይቀሬ ነው።
ቲቢን የሚያመጣ
ጀርም በመሠረቱ ሰነፍ(Lazy Bacteria) ከሆኑት ውስጥ የሚመደብ ነው። የተሃድሶን ምንፍቅና የሚያስተምሩም ሰዎች በመሠረቱ
ከመንፈሳዊ እውቀት የራቁ፣ ምግባራቸው ያልቀና፣ በትዕቢት ብቻ የተሞሉ፣ እዚህ ግባ የሚባል የስብእና ልዕልናና መንፈሳዊ ክብር የሌላቸው
ተራ አለሌዎች ናቸው። ሆኖም፣ ይህ የቲቢ ባክቴሪያ በብልሃት ሰውነታችንን ይቆጣጠራል። ሰውነታችንን የሚያጠቃበት ዘዴ(Pathophysiology)
እንመልከት!!
ታዲያ ይህ Mycobacterium Tuberculosis የሚባለው በሸታ
አምጪ ጀርም፣ ሳንባችን ውስጥ እኛን ማጥቃት ከመቻሉ በፊት ብዙ ጊዜ
አድፍጦ ሊያሳልፍ ይችላል። አድፍጦ መጥፎ ጊዜን ማሳለፍ አንዱ ትልቅ የቲቢ ስልት ነው።
= ተሃድሶ
መናፍቃንም እንዲሁ!! ቤተክርስቲያን ውስጥ እኛን ከመምሰል እኛን የሆኑ እስኪመስለን ድረስ ተመሳስለውን በምዕመንነትና በክህነት
Hibernate ያረጋሉ።
ታዲያ ቲቢ
ይህን ሁሉ የተኛ ሲመስልም ተኝቶ አይደለም፤ አካባቢውን እየቃኘ፣ ሳያስነቃ እያጠቃ እንጂ!! እንዲህ እንዲህ እያለ ቲቢው ሳንባችንን አዳርሶ፣ የመከላከል አቅማችንን ( Immunity) እያዳከመ፣ ከሳንባ ወደ
ሳንባ ማቀፊያ፣ በደም ሥር አማካይነት ወደ ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች ይሰራጫል። በዚህ ጊዜ በሽኛው ምልክት ያሳያል። የቲቢ ጀርም ሰውነታችንን ከጥቃት የሚከላከሉትን(እነ Macrophageን) ከሳንባ ጀምሮ
ኢላማው እነሱንና እነሱን የመሰሉ ላይ አድርጎ ይነሳል።
=ተሃድሶዎችም
ለእቅበተ ሃይማኖት ከሚታትሩ ካህናትና መምህራን ጀምረው ነቀፋን፣ ስድብና ጥላቻን እየተፉ ወደሚፈልጉት ሥርዓት፣ትውፊትና ዶግማ ብክለት
ይሸጋገራሉ። ተሃድሶ መርዙን ወደ ተለያየ መንፈሳዊ ሕይወታችን እየረጨ
ከተወሰነ ጊዜ በኃላ ምልክቶቹን ያሳያል።
ሳል፣ ድካምና
አቅም ማጣት ፣ ለሊት የሚያይል ላብ፣ ክብደት መቀነስ፣ ከፍተኛ ምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የጎን ህመምና ውጋት፣ ወዘተ ይከተላል፤ በነቀርሳ
አካሄድ። አንድም ደግሞ የተሃድሶን ህመም በሽታ ምልክት ስናይ:-
ክብረ ክህነትን ማናናቅ፣ የማያውቁትን ክርስቶስ ለስም ብቻ "ኢየሱስ" "ኢየሱስ" ማለት፣ ድንግል ማርያምንና ቅዱሳንን መንቀፍ፣
ለኦርቶዶክሳዊ ዋጋዎች ስሜት ማጣት፣ ሥርዓት አልበኝነት፣ ሙሰኝነትና ሆድ አደርነት፣ በመንፈሳዊ እውቀት ግልብ ሆኖ በትዕቢት ብቻ
አውቃለሁ አውቃለሁ ባይነት.....ወዘተ ናቸው። ከሁሉ ከሁሉ በላይ ደግሞ ፕሮቴስታንታዊ ስብከት እየተፉ ድርቅ ብለው ኦርቶዶክሳዊ
ነው ማለት።
ልብ ያድርጉ!
እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት ከብዙ ቆይታ በኋላ ሊሆን ይችላል። ቲቢ ወባ አይደለም፡- በአንድ ቀን ይዤ ካልገደልኩ አይልም። ውጤቱ
የከፋ ነው እንጂ ሂደቱ አጣዳፉ አይደለም። እንደ ታይፈስና ታይፎይድ፣ ማጅራት ገትር፣ ወባ፣ ኮሌራ ... በአጭር ጊዜ ውስጥ
" ወይ ሞት ወይ ፈውስ!" የሚል አይደለም።
=ተሃድሶ
ምንፍቅናም እንዲሁ ነው። አሁን ላይ የሚታየውን ምልክት ለማየት ብዙ ዘመናትን ለፍተውበታል። ከምዕት ዓመታት በላይ አቅደው፣አስልተው፣
ሰርገው ግብተው፣ መቅደስ ተቀምጠው፣ አውደ ምህረት ይዘው፣ ዘምረውና ሰብከው.... ነው ለዛሬ የበሽታነት ምልክት የደረሱት። ስለዚህ የበሽታ አመጣጡ ሂደታዊና በዘዴ
እንደሆነ ሁሉ፣ ህክምናውም እንደዚያው መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ህክምና!
የቲቢ ህክምና
በአንድ መድሃኒት ሳይሆን ብዙ መድሃኒቶችን አንድ ላይ ለረጅም ጊዜ በመውሰድ ነው። ታዲያ በነዚህ የህክምና ወራት ውስጥ ጥብቅ ክትትል
ብቻ በቂ ካለመሆኑም የተነሳ መድሃኒቶቹም የሚወሰዱት በየቀኑ በህክምና ባለሙያ ፊት(DOT-Directly Observed
Treatment) ነው።
=የተሃድሶ
ምንፍቅና ህክምናም እንዲሁ ነው። አንድ መድሃኒት(በጉባኤ ገለፃ መስጠት)ብቻ በቂ አይደለም። ብዙ መንፈሳዊ መድሃኒቶችን በአንድ
ላይ ሊያውም መንፈሳዊ ሃኪም(መምህራንና ካህናት) እያዩት፣ መውሰድና በቅርበትም እየተከታተሉት፣ ለውጡን እየመዘኑት፣ የመድሃኒቶቹን
የጎንዮሽ ጉዳት(ለሱ የሚደረገው ትዕግስት፣ ይቅርታ .... ወደ ሌላ ጉዳይ እንዳያሸጋግረው) እየገመገሙት የህክምና ጊዜውን እስኪጨርስ
ማከሙን መቀጠል አለባቸው። ልብ እናድርግ:- ምልክቶቹ በሽተኛው በህክምና ላይ እያለ እየተሻለው ነው ካልን በኃላም ሊያገረሹ ይችላሉ።
አንድም~
በህክምና ላይ ያለ ቲቢ በሽተኛ መድሃኒቶቹን እየወሰደ፣ 'ራጅ'፣ አክታና ሌሎችም ምርመራዎች እየተደረጉለት በመጨረሻም ላይ ካልዳነ
ያለመዳኑ ምክንያት መታወቅ አለበት። መድሃኒቱን አቋርጦ ከሆነ፣HIV እና ሌሌች ተዛማጅ በሽታዎች እየጎዱት ከሆነ፣ መድሃኒት ተላምዶ
ከሆነ...ወዘተ
= ቲቢና
HIV እጅጉን እንደሚረዳዱ ሁሉ:- ተሃድሶና አማሳኝነት፣ ሙሰኝነትም ይረዳዳሉ፣ ይመጋገባሉ። ማንኛውም HIV ያለበት ሰው የቲቢን፣ቲቢ ያለበትም
ሰው የ'HIV'ን ምርመራ ማድረግ እንዳለበት ሁሉ:- ሙሰኞችንና አማሳኞችን ከተሃድሶ፣ ተሃድሶዎችን ከምግባረ ብልሹነትና ስግብግብነት ለይቶ ማየት አስቸጋሪ ነው።
የቲቢ አንዱ
ጠባይ መድሃኒት መላመዱ ነው። ባክቶሪያው እራሱን ለማኖር ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ እራሱን መለወጡ (Mutate ማድረግ) ነው። በዚህም የተነሳ
ያድናል የተባለው መድሃኒት ላያድነው ይችላል። እንዲህ ያለ ቲቢ
:- "መድሃኒት የተላመደ ቲቢ (MDR TB-
Multidrug resistant TB" ይባላል። ይህም ዓይነቱ
ቲቢ በሌላ ዘርፍ መድሃኒት (SLD-Second Line Anti-TB Drugs)ሊታከም ይገባዋል። ዳግም ይህንንም መድሃኒት ሊላመድ ከቻለ XDR TB ይባላል። ሁለተኛ ደረጃ መድሃኒቶችን
ተላምዷልና እንዲህ አይነቱ በሽተኛ ከማህበረሰቡ ጋር እንዳይቀላቀል ተደርጎ፣ እጅግ በከፍተኛ ጥንቃቄ በሀገሪቱ ውስጥ በተመረጡ ማዕከላት
በተመረጡ ሃኪሞች ብቻ ህክምና ይደረግለታል።
= ልክ
እንደ ነቀርሳው ሁሉ ተሃድሶ ምንፍቅናም መንፈሳዊ መድሃኑቱን ሊላመድ ይችላል። ጓዳውን የሚያውቁ፣
በቤ/ክ አስተዳደር ላይ ያሉት፣ ሁሌ ስለ ተሃድሶው አስጊነት ከኦርቶዶክሳውያን ጋር የሚመክሩ፣ ከእቅዱ ውስጥ ያሉበት፣ ለኛም ለነሱም
ወሳኝ የሆኑ፣ ከአንድ አጥቢያ እስከ ሊቃውንት ጉባኤ የሐራ ጥቃ ተሃድሶን ሠንሰለት የዘረጉ፣ ትምህርተ ሃይማኖታዊ መልስ የማይዋሃዳቸው
አውራ ተሃድሶዎች ናቸው።
ታዲያ ለነዚህ
የሚመከረው ህክምና ሎሎችን መድሃኒቱን በተላመደው ባክቴሪያቸው እንዳይበክሉ
አገልግሎታቸውን ማገድ፣ ከክህነት መሻር፣ ከምዕመን መለየት ይሆናል። ተለይተው እስኪወገዙ ድረስ ህዝቡን እንዲበክሉ እድሉን መስጠት
ተገቡ አይሆንም።
ለዚህ ሁሉ
ችግር ታዲያ መነሻው አፍንጫችንን ለሎች ሳል ማጋለጥ እንደሆነ ይታወቃል። እስከሞት ያለውን ችግሮቹን ለመከላከል ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይመከራል። አንድ ውጫዊ
ምንጩን ማራቅና ማድረቅ
ሁለት- ውስጣዊ በሽታን የመከላከል አቅምን(Immunity) ማዳበር።
ውጫዊውን መስኮት በመክፈት፣ በሽታው ያለበት ሰው አፍንጫውን እንዲሸፍን ማስደረግ፣ ከሰው ራቅ ብሎ ማሳል፣ ያልታፈነና
ሰው ያልተጠጋጋበት ቦታ ላይ መገኘት ሊሆን ይችላል።
=እንዲሁ
ደግሞ ተሃድሶአዊ ምንፍቅናን ለመከላከል ውስጣዊና ውጫዊ የመከላከያ መንገዶች ይጠቅማሉ። እራስን የተሃድሶ ትንፋሽ ካለበት ህብረት፣
ይህ ትንፋሽ ከነካው ስብከት፣ መዝሙር፣ ጓደኝነት፣ ቦታ መለየት ውጫዊ ዘዴ ሲሆኑ ውስጣዊው መከላከያ ዘዴ ደግሞ መንፈሳዊ የመከላከል አቅማችንን(Spiritual
Immunity) የሚያጎለብትልንን ኦርቶዶክሳዊ የነገረ ኃይማኖት እውቀት ደርጃችንን፣ ኦርቶዶክሳዊ እሴቶቻችንን፣ ምግባራችንን፣ መንፈሳዊ
ትሩፋቶቻችንን፣ ክርስቲያናዊ ማንነታችንን ማሳደግ ነው።
የተሃድሶ
ምንፍቅና ነቀርሳ ነው
ስለዚህ:-
"መስኮትን
በመክፈት" ቲቢ-ነቀርሳንና ሐራ-ጥቃ ተሃድሶን እንከላከል!!
ሐምሌ
2009ዓ.ም
ለወንድማችን
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡
በቀጣይ ጽሁፋችን እነዚሁ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን
/ ተሐድሶ ተብዬዎቹ/ እውነተኛ መስሎ ለማሳሳት የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና ስልቶች በመጠኑ እንዳስሳለን፡፡
ለዛሬው ይቆየን!
የነገ ሰው ይበለን፡፡
No comments:
Post a Comment