ከክፍል ሰላሳ ሦስት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
የተከበራችሁ የዚች የጡመራ መድረክ ተከታታዮች፤ በክፍል ሰላሳ ሦስት "በቀጣይ ጽሁፋችን እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ብለው የሚጠሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤
እውነተኛ የተዋሕዶ አማኝ መስሎ ለመታየት የሚጠቀሙባቸውን የማሳሳቻ ስልቶች በመጠኑ እንዳስሳለን" ብለን በይደር ባቆየነውን መሠረት፤
እነሆ በዚህ ክፍል ዋና ዋናዎቹን ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
የዚህ መልእክት መሠረታዊ ዓላማ ሁላችንም ተዋሕዶ ልጆች፤ እንደ እስስት በሚቀያየረውና ተዘርዝሮ በማያልቀው የተሐድሶዎች
የማሳሳቻ ስልታቸው እንዳንጠመድ፤ እራሳችንንም ሆነ ሌላውን ለመጠበቅ /ለመጠንቀቅ/ እንድንችል ማድረግ ሲሆን፤ የጽሁፋችን መነሻም፤
‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› በተባለው የጡመራ መድረካቸው ላይ December 23, 2014 /በእኛ አቆጣጠር 2007 ዓ.ም/ የለጠፉት ጽሁፋቸው
ነው፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ለአንባብያን ግልጽ እንዲሆን፤
ከላይ በተጠቀሰው የጡመራ መድረካቸው ላቀረቡት ትችት መነሻ የሆናቸውን ጉዳይ በመጠኑ እንገልጻለን፡፡
ከልዑል እግዚአብሔር በተሰጠው መንፈሣዊ ሥልጣን መሠረት፤ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያንን
በበላይነት የሚመራው ቅ/ሲኖዶስ፤ በየዓመቱ በጥቅምት ወርና በርክበ ካህናት /ትንሣዔ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን/ መደበኛ ጉባዔ
በማካሄድ ለቤ/ክ አገልግሎት መቃናት ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፤ መግለጫዎችንም ያወጣል፡፡በዚሁ መሠረት በጥቅምት
2007 ዓ.ም ጉባዔው ላይ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች አንዱና ዋነኛው የዚሁ የተሐድሶዎች ጉዳይ ሲሆን፤ ብዙ የዋሃን
ምእመናን በገዛ ቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ እያሉ፤ ነገር ግን ከልዩ ልዩ መናፍቃን በተቃረመ የስህተት ትምህርት ለመሰነካከል ምክንያት
የሆነው የተሐድሶዎች እንቅስቃሴ፤ "ስልታቸውን መቀያየራቸውና ዓላማቸውን በስውር ማካሄዳቸው" መሆኑ በሲኖዶሱ ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ ከወሰናቸው ውሳኔዎች አንዱ "ተሐድሶ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲጠና" የሚል ነበር ፡፡
እውነቱን እውነት ማለት ስለሚገባ፤ ቅ/ሲኖዶስ ችግሩ እንዲጠና መወሰኑና
ኮሚቴም ማቋቋሙ ተገቢ ቢሆንም፤ ይህ ችግር ሥር እስከሚሰድና ለመንቀልም አስቸጋሪና ብዙ ትግል የሚጠይቅ ሆኖ እስከሚያድግ ድረስ
መዘግየት አልነበረበትም፡፡ለምሳሌ ተሐድሶዎቹ እዚሁ ቤ/ክ ውስጥ እያሉ ገና በ1990ዎቹ በጥፋት መረባቸው ያጠመዷቸውንና በማያውቁት
መንገድ የእነሱው ተከታይ ያደረጓቸውን የዋሃን ወጣቶችንና ምእመናንን ይዘው፣ለድርጅታቸውም በመንግሥት ደረጃ እውቅና አግኝተው ራሳቸውን
ችለው መሥራት የጀመሩትን የመናፍቃን ድርጅቶችና ግለሰቦችን ፤ቅ/ሲኖዶስ ያወገዛቸው በ2004 ዓ.ም መሆኑ፤"ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ " የሚለውን ዘይቤያዊ አነጋገር ያስታውሳል፡፡ሌላው ቀርቶ
እራሳቸው የተወገዙት መናፍቃን ሳይቀሩ ቤ/ክ መሳቂያና መሳለቂያ ያደረጓት፤ከአቅማቸው በላይ ተንጠራርተው "የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያንን የምታስተምረው የሐሰት ትምህርት ነው" እስከ ማለት
የደረሱት፤ ለስህተታቸው ወቅታዊ ምላሽ ባለመሰጠቱና ይህንንና የመሳሰሉትን
ሌሎች ክፍተቶች እየተጠቀሙ ነው፡፡
ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ፤ እነዚህ ተኩላዎች ልባቸውና ሥራቸው
ከፕሮቴስታንት ድርጅት ጋር ቢሆንም፤ በአካል ግን ከእኛው (ከተዋሕዶ ቤ/ክ) ውስጥ ስለሆኑና ውሳኔውንም ለማግኘት ስላልተቸገሩ፤
ከላይ በተገለጠው ድረ-ገጻቸው ላይ የቅ/ሲኖዶስን ውሳኔ ምፀት በተሞላበት አገላለጽ፤
‹‹“ታላቅ ዜናˮ “ተሐድሶ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲጠና ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑ ተሰማ፡፡ˮ››
በሚል ርእስ አቅማቸው የቻለውን
ያህል ለመተቸት ምክረዋል፡፡ ከዚሁ ትችታቸው መካከል አንዱ "ስልታቸውን ይቀያይራሉ፤ዓላማቸውን
በስውር ያካሂዳሉ.. " ስለመባላቸው ሲሆን፤ለዚህ መልስ ሲሰጡ፤
"ይህን የምናደርግበት ዋናው ምክንያትም ማኅበረሰብ
በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች አስተሳሰቡና አኗኗሩን ስለሚቀያይር …ነው፡፡" ብለዋል፡፡እንዲሁም ዓላማቸውን በስውር ስለማካሄዳቸው
ደግሞ፤ "ተሐድሶ ስውር ዓላማ አይደለም፤አገልግሎቱ ስውር የሆነበት ምክንያት የተሐድሶ አገልግሎት
አራማጆች እንደ ክፉ አድራጊዎች ተቆጥረው መሰደድ ስለበዛበቸው እንጂ፡፡ አባቶች ለወንጌል ቢደሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰት ትምህርት
ነፃ ለማድረግ ቢሰሩ ተሐድሶ ስውር ሊሆን አይችልም፤የተሐድሶ አራምጆችም በግልጽ መሥራት በቻልን ነበር፤ በግልፅ የተሐድሶ ጥያቄ
ያቀረቡ መናፍቃን እየተባሉ ሲፈረጁና ሲሰደዱ እያየን እንዴት አላማችንን ልንገልጽ እንችላለን? ይህ የብልህ ሰው ስልት አይደለም…፡፡" ብለዋል፡፡
እንግዲህ ከብዙ ሐተታቸው ውስጥ ማንነታቸውም ለማሳየት ያህል ከላይ
ቀንጨብ አድርገን ያቀረብነውን ሃሳባቸውን ስንመለከት የቤ/ክ አምላክ ፊታቸውን ጸፍቶ፤አፋቸውን ከፍቶ ስውር ዓላማቸውን በአደባባይ
ያውም በራሳቸው አንደበት እንዲናዘዙ አድርጓቸዋል፡፡"ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ" እንደሚባለው፤ እነሱ ስውር የሆነውን ዓላማቸውን
ለማሳካት የተለያየ ስልት በመጠቀም መሥራታቸውን እንደ ጽድቅ ቢቆጥሩትም ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ ግን እነዚህን የበግ ለምድ የለበሱ
ተኩላዎች እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል፡፡ "እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች የክርስቶስን ሐዋርያት እንዲመስሉ ራሳቸውን እየለወጡ፤ውሸተኞች
ሐዋርያት ተንኮለኞች ሠራተኞች ናቸውና፡፡ይህም ድንቅ አይደለም፤ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና፡፡2ኛ
ቆሮ. 11፥13-14፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ ለስሙ ክብር ምሥጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት፤ብሎም
ለተከታዮቹ ሁሉ /ለሁላችንም / ከሰጠን የወንጌል መመሪያ ጋር፤እንዲሁም ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችንን ተከትለው ካስተማሩን ትምህርት
ጋር ሲነጻጸር የተሐድሶዎቹ ትምህርት ምን ያህል ከእውነት የራቀ እንደሆነ ለአብነት ያህል ጥቂት ጥቅሶችን እንመልከት፤
- "በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ፡፡ "ማቴ.10፥27
- "ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡"…ማቴ.10፥32-33
- "እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም፡፡" ማቴ.5፥14
- "መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡" ማቴ.5፥16
- "ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብንል በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን እውነትንም አናደርግም፤"1ኛ ዮሐ.1፥6
- "አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፤ መከራን ተቀበል፤ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፤አገልግሎትህን ፈጽም፡፡"2ኛ ጢሞ. 4፥5
- "ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፡፡"ኤፌ. 6፥19
የተከበራችሁ አንባብያን! አሁንም ወደ ዋናው ጉዳቸው አልገባንም፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ
በሌላ ጊዜ እንቀጥላለን፡፡
"በጾምና ጸሎት እንትጋ" የዘወትር መልእክታችን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment