Tuesday, November 14, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ አምስት

ከክፍል ሰላሳ አራት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? 
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       የተከበራችሁ የዚች የጡመራ መድረክ ተከታታዮች፤ በክፍል ሰላሳ አራት እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ብለው የሚጠሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤ እውነተኛ የተዋሕዶ አማኝ መስሎ ለመታየት የሚጠቀሙባቸውን የማሳሳቻ ስልቶች ለማሳየት መግቢያውን ጀምረን  በይቀጥላል ባቆየነውን መሠረት፤ እነሆ በዚህ ክፍል ዋና ዋናዎቹን ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!

       የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ስንመለከት፤ አንዲትና ቅድስት የሆነችው የተዋህዶ ሃይማኖት፤የፈተናው ዓይነትና ብዛት እንደየዘመኑ የተለያየ ይሁን እንጂ ያለ ፈተና የኖረችበት ጊዜ የለም፡፡የዛሬው ርዕሳችን ይህንን የቤ/ክ የብዙ ሺ ዓመታት ጉዞ ለመተረክ ስላልሆነ ያንን ለጊዜው አቆይተን፤ እኛ እራሳችን የዓይን ምስክር የሆንበትንና በቤተ ክርስቲያናችን በዕለት ተዕለት አገልግሎት ላይ፤ ከላይ የጠቀስናቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን  እያደረሱት ያለውን የጥፋት በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡
       እንግዲህ ቀደም ባለው በክፍል 34 እንዳየነው ራሳቸውን "ተሐድሶ" ብለው የሚጠሩት ክፍሎች እነሱም ሆኑ ሥራቸውም "ስውር" ከሆነ፤ የጥፋት ተልእኳቸውን የሚያራምዱትም በእኛው ቤ/ክ ውስጥ ሆነው፤ እኛኑ መስለውና ተመሳስለው ከሆነ፤ ከስህተት ትምህርታቸው ለመጠንቀቅ የምንችለው፤ እውነቱን ከሐሰት የምንለየውስ በምንድነው? የሚል ጥያቄ መነሳቱ የግድ ነው፡፡የዚህን ጥያቄ መልስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረንና ሐዋርያው ቅ/ማቴዎስ ከመዘገበልን የመጀመሪያው ወንጌል ላይ ቁልጭ ብሎ እናገኘዋለን፡፡"የበግ ለምድ ለብሰው ለሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኩላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፡፡ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ፡፡ለእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?"ማቴ.7፥15-20፡፡በዚህም በዚህ ኃይለ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤የማሳሳቻ ስልታቸውን፤"የበግ ለምድ ለብሰው" ማለት፤ የስህተት ትምህርታቸውን ደግሞ "ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ"በማለት በምሳሌያዊ አነጋገር አስተምሮናል፡፡እንዲሁም በዮሐ.10፥1 "እውነት እውነት እላችኋለሁ ወደበጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፡፡…"ብሎ አስተምሮናል፡፡
       ሁላችንም እንደምናውቀው ማንኛውም ሌባ ለመስረቅ ከመሰማራቱ በፊት፤ የትኛው ቤት ጠቃሚ ነገር እንዳለ፤ በዚያ ቤት ገበቶ ንብረቱን ለመዝረፍ የሚመቸውን ጊዜና ሰዓት፤ሌላው ቀርቶ የቤቱ ባለቤት ኃይለኛ እንቅልፍ የሚተኛበትን ሰዓት ሳይቀር አስቀድም ያጠናል፡፡በዚሁ መሠረት ለሥርቆት ይሰማራል፤በጥናቱ መሠረት ከተሳካለት ያልደከመበትን ንብረት ጥርግርግ አድርጎ ይዞ ይሄዳል፡፡አጋጣሚ ሆኖ ውሻ ከጮሆበት፣ባለቤቱም ከነቃበት ግን በመጣበት እግሩ ባዶውን ይመለሳል፡፡ እንዲሁም የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች የተባሉት ተሐድሶዎችም በየተገኘው አጋጣሚ በግለሰብ ደረጃም ይሁን ቤ/ክ ደረጃ የጥፋት መረባቸውን ከመዘርጋታቸው በፊት በየትኛው ደካማ ጎን መግባት እንዳለባቸው አስቀድመው ያጠናሉ፤ ስልትም ይነድፋሉ፡፡
    በዚሁ መሠረት ከቤ/ክ ወቅታዊ ዘገባዎች እንደተረዳነው፤
1/ እስከ 1950 ዓ.ም ያለው ፦ ትክክለኛው ትምህርት የፕሮቴስታንቱ ብቻ እንደሆነ በማስተማር ነበር፤
2/ ከ1951 ዓ.ም እስከ 1990 ዓ.ም ፦ በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው የኦ/ተ/ቤ/ክ ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ማስተማር፤
3/ ከ1990 ዓ.ም እስከ አሁን ያለው፦ በቤ/ክ ውስጥ ሆኖ ፣የቤ/ክ የሆኑትን ሥርዓቶች ለማስመሰል ያህል እየፈጸሙ ከዚያው ጎን ለጎን የተለያየ ስልት በመጠቀም የስህተት ትምህርታቸውን ውስጥ ለውስጥ ማስፋፋት ነው፡፡
       ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ ስልቶች ይልቅ ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ያለው ስልት በመጠኑም ቢሆን ለጥፋት ተልእኳቸው የሰመረላቸው ይመስላል፡፡ስለዚህ ሁላችንም ከዚህ የጥፋት ስራ እራሳችንንም ሆነ ቤ/ክ ለመጠበቅ የምንችለው የማሳሳቻ ስልታቸውን ስናውቅ ስለሆነ ከብዙው በጥቂቱ ከዚህ በመቀጠል ለማሳየት እንሞክራለን፡፡

የማሳሳቻ ስልቶቻቸው

1/ ተሐድሶ የሚባል እንቅስቃሴ የለም በማለት፤
     በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ"ተሐድሶ" የሚባል ነገር እንደሌለ፤ እንዲሁ  የተወሰኑ ሰዎች በራሳቸው የፈጠሩት ነገር አንደሆነ አድርገው ያወሩ /ያስወሩ/  ነበር፡፡እነዚህ ክፍሎች አሁን ደግሞ መደበቅ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ክህደቱን አሻሽለው "የተሐድሶ እንቅስቃሴ" ቢኖርም አሁን በቤ/ክ ውስጥ ካለው የሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦት የበለጠ ችግር እያስከተለ አይደለም፡፡እንደውም "ነገሩ በአንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ጎልቶ ስለተወራና ነገሩን ከፍ አድርገው ስላጮሁት ነው እንጂ…." እያሉ ምእመኑ እራሱንም ሆነ ቤ/ክ ተግቶ እንዳይጠብቅ እያዘናጉት ይገኛሉ፡፡
2/ በደካማ ጎን በመግባት፤
     አንድን ሰው ወደነሱ ዓላማ ለማስገባት የሚሸነፈው በምን ሁኔታ እንደሆነ ደካማ ጎኑ ይጠናል፡፡ ማለትም፤የእውቀት ማነስ የኢኮኖሚ እጥረት፣ የስጋ ድክመት ያለበትና በሥርዓተ ቤ/ክ ጸንቶ ለመኖር ያልቻለ፣ እንዲሁም በቤ/ክ አስተዳደር በደል የደረሰበትና ፍርድ የሚሰጠው አጥቶ ግራ የተጋባውን ……….ወዘተ፡፡ በመሳሰሉት ሁኔታዎች ሊሸነፍ የሚችለውን ካህን፣ መነኩሴ፣ ዲያቆን፣ ምእመን ሳይለዩ በሚሸነፉበት ደካማ ጎን በመያዝና የተለያየ ጥቅማ ጥቅም በመስጠት የእነሱ ተከታይ ማድረግ ነው፡፡
3/ በገዳማት፣ በአብነት ጉባኤ ቤቶችና በመንፈሣዊ ኮሌጆች በመግባት ከምንጩ መበከል ወይንም ጨርሶ ማድረቅ፤
     የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን ያለ አብነት ትምህርት ቤት ብቻዋን ማሰብ አይቻልም፡፡ይህንን የቤ/ክ ጀርባ አጥንት የሆነውን ትምህርት ቤት ተመሳስለው በመግባትና እንክርዳዳቸውን በመዝራት የነሱ የክህደት ትምህርት ሰለባ ሆኖ ቤ/ክ ሲያውክ እንዲኖር ወይም ገዳሙን (ት/ቤቱን) ጥሎ እንዲወጣ ማድረግ ነው ዓላማቸው፡፡በተለይም በመንፈሳዊ ኮሌጆች የሚሰጠው ትምህርት በዘመናዊ መልክ በመሆኑና ኮሌጆቹም የሚገኙት በከተሞች ውስጥ በመሆኑ የተለያዩ  የምንፍቅና መጸሕፍትን እንዲያነቡ እያደረጉና ወደተለያዩ የመናፍቃን አዳራሾች በድብቅ እየወሰዱ ለጥፋቱ ተልእኮ ስልጠና እንዲወስዱ ያደርጋሉ፡፡አጋጣሚ ሆኖ ሳይነቃባቸው ከተመረቁ እንደ መልካም አገልጋይ በየአድባራቱ ተመድበው የሚፈልጉትን የጥፋት ተልእኳቸውን ያራምዳሉ፡፡ 
4/ በልዩ ልዩ የአገልግሎት ሥልጣን ላይ በመቀመጥ፤
     ከታች ከአጥቢያ ቤ/ክ ጀምሮ እስከ መንበረ ፓትርያርክ ባሉት የአገልግሎት ክፍሎች ስልጣንና የአገልግሎት መድረክ በመያዝና እነሱን የመሳሰሉትን በማሰባሰብ፤ በተቃራኒው ስለ እውነተኛይቱ ቤ/ክ የሚሰሩትን በማግለልና በማሳደድ  ተበሳጭተው ከቤ/ክ እንዲወጡ ካደረጉ በኋላ ያለ ተቀናቃኝ የሚፈልጉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ይህ ሥልጣንን የመያዝ ጉዳይ  በሰበካ መንፈሣዊ ጉባዔ፣በሰ/ት/ቤት፣በልዩ ልዩ የአገልግሎት ክፍሎች ነጻ አገልግሎት በመስጠትም ጭምር የሚተገበር ነው፡፡
5/እውነተኛ የቤ/ክ ተቆርቋሪ መምሰል፤
     ይህ ስልታቸው ከሌሎቹ ስልቶቻቸው ጋር ሲነጻጸር ቶሎ ለመለየት ጊዜ የሚወስድ ከመሆኑ ሌላ በእውቀትም በሰል ያሉ መሆንን ይጠይቃል፡፡ምክንያቱም በማንኛውም እንቅስቃሴያቸው ቤ/ክንን በግልጽ አይነቅፉም፤ተአማኒነት ለማግኘትና ህዝቡ ልብ ውስጥ ለመግባት ማንኛውንም ነገር ይጠቀማሉ፡፡ ለምሳሌ የጽዋና የጉዞ ማህበራት በማቋቋም፣ ችግረኞች ሰዎችን በመርዳት፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናትን በመርዳት /ህንጻ ቤ/ክ እስከመስራት/፣ ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚል ስም ከደብራቸው አልፈው እልም ያለ ገጠር ድረስ እየሄዱ ጉባኤ በማካሄድ፣ሰንበት ት/ቤት በማቋቋምና በመሳሰሉት በአደባባይ በሚታይ አገልግሎት ፍጽም የቤ/ክ ሰው /ኦርቶዶክሳዊ/ ለመምሰል ይሰራሉ፡፡አካሄዳቸው ከእርዳታ ጋር የተያያዘ ስለሆነ አገልግሎታቸው ትክክል ይሁንም አይሁንም ትኩረት የሚሰጠው ስለሌለ እንክርዳዳቸውን በቀላሉ መዝራት ያመቻቸዋል፡፡ሆኖም ውሸት ተራራ እስከሚያክል ድረስ ቢገዝፍ እውነት ብቅ ያለችና የተጋለጡ ቀን፤ ከላይ በተገለጡት መንገዶች ያደራጁዋቸውን ምእመናን ይዘው በመውጣት የምንፍቅና ድርጅታቸውን ይከፍታሉ፡፡በ2004 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ያወገዛቸው የምንፍቅና ድርጅቶችና ግለሰቦች ድርጅታቸውን የመሠረቱት ከላይ በገለጽነው መንገድ እዚሁ ቤ/ክ ውስጥ ሆነው ያደራጁዋቸውን ደጋፊዎቻቸውን ይዘው ነው፡፡
6/ በትምህርትም ሆነ በዝማሬ ኦሮቶዶክሳዊ ላህዩን መቀየር፤
     ይህም ችግር በጣም ስር የሰደደ ነው፡፡እንኳን ምእመኑ ቀርቶ በመምህርነት ደረጃ ያሉት ሳይቀሩ ጥንቃቄና ሃላፊነት  በጎደለው አካሄድ ተራ ዓለማዊ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም የሚያስተምሩት ትምህርትና ዝማሬያቸው ምእመኑን ከማስጨብጨብና እልል ከማስባል አልፎ የደነደነውን ልብ ሰብሮ ለንስሃ የሚያበቃ ትምህርትና መዝሙር ሲተላለፍ ማየትና መስማት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሶዋል፡፡በተለይ በዝማሬው ዙሪያ ዜማው ከያሬዳዊ ዜማ እጅግ የራቀ መሆኑ ሳይበቃው አልፎ ተርፎም ዶግማና ቀኖና ሊያፋልሱ የሚችሉ ቃላትን በመጠቀም የሚቀርቡ "ዝማሬዎች" ከዕለት ዕለት እየጨመሩ ናቸው፡፡
7/ ለዘብተኛ/ ግዴለሽ/ እንዲሆኑ ማድረግ፤
     በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ኢየሱስ ክርስቶስ በትክክል እንዳልተሰበከ አድርጎ ከመናገር ጋር፤በማንኛውም አገልግሎት ማለትም በትምህርትም ሆነ በዝማሬ ስለ ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊት፣በአጠቃላይ ስለ ነገረ ቅዱሳንና ምግባረ ሰናያት  ባለ ማስተማር ማስረሳት /ምእመናን ለዘብተኛ እንዲሆኑ ማድረግ/፡፡ ትምህርታቸውም "በጌታ ሞት አንዴ ጸድቃችኋል፤ ድናችኋል፤ደስ ይበላችሁ"…ወዘተ፡፡በሚል ስብከት ብቻ ታጅቦ ምእመኑ የራሱን ኃጢአት እንዳያይና ንስሃም እንዳይገባ በተዘዋዋሪ በኃጢአት እንደ ተዘፈቀ እንዲኖር የማዘናጊያ ስብከት መስጠት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያንን ለሁለት ከፍሎ፤ከአጤ ዘርዓያዕቆብ በፊት ያለችው ቤ/ክ ትክክል እንደነበረች ከአጤ ዘርዓያዕቆብ በሁዋላ አላስፈላጊ ትምህርት እንደተጨመረባት አድርጎ በማሳየት በዚህም ካህኑም ሆነ ምእመኑ በሃይማኖቱ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
8/ የስም ማጥፋት ዘመቻ
     ይህንን ተንኮላቸውን አውቀው የሚቃወሙዋቸውን ሰዎች ትልልቅ አባቶችን ሳይቀር የተለያየ የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ ምእመኑ አባቶቹን እንዲጠላቸውን በአግልግሎታቸው እንዳይጠቀም ከማድረጋቸው ሌላ  እውነተኞቹ ሰዎች ተበሳጭተውና ተስፋ ቆርጠው ከቤ/ክ እንዲሰደዱ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡
9/ የተበዳዩን አቤቱታ ተቀብሎ ለበደል ፈጻሚው መስጠት
     አንድ ሰው በሚያገለግልበት ቦታ በደል ደረሰብኝ ብሎ ለበላይ አካል አቤቱታ ያቀርባል፡፡ለእሱ የተቆረቆሩ በመምሰል በጽሁፍ ካቀረበው ሌላ በቃልም እንዲናገር እየኮረኮሩ ሃሳቡን ተቀብለው ይሸኙታል፡ተበዳዩ ጨርሶ ሲወጣ ለበደል አድራሹ የተባለው ነገር ሁሉ ይነገረዋል፡፡ፍርድ ይሰጠኛል ብሎ የሚጠብቀው ምስኪን ተበዳይ ወደ ቦታው ሲመለስ ከበፊቱ የባሰና ያልጠበቀው የበቀል እርምጃ ይወሰድበታል፡፡ይህ በግለሰብ ደረጃና በግል ጉዳይ ላይ የሚደረገው ሲሆን፤ሃይማኖትና ሥርዓት የሚያፋልስ እኩይ ተግባር እየተፈጸመ ነው ብሎ ስለ ቤተ ክርስቲያንም አቤቱታ የሚያቀርበውም እንዲሁ ነው፡፡ተፈጠረ ለተባለው ስህተት "ተጨባጭ ማስረጃ ካለማ በሃይማኖት ድርድር የለም፤እርምጃ ይወሰዳል" ተብሎ ከላይ በተጠቀሰው ዓይነት ማመልከቻውንም ማስረጃውንም ይቀበላሉ፡፡በሃይማኖት ድርድር የለም ያሉበት አንደበት ተለውጦ፤  ወዲያው ከስህተት ፈጻሚው ጋር ድርድር ምክክር ይጀመራል፡፡ፈጽሟል በተባለው ጉዳይ የቀረበው ማስረጃ ሁሉ ይነገረዋል፡፡ከዚያ ስለ ቤ/ክ እምነትና ሥርዓት መፋለስ ተቆርቁሮ አቤቱታ ያቀረበውን ሰው በተለያየ መንገድ በማገለልም ሆነ ጉዳዩን ሁለተኛ እንዳያነሳ በማድረግ ጥፋተኛው ስልት እየቀያየረ የዋሃንን ምእመናንን የሚያታልልበትን ድራማ አጠናክሮ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡
10/ ቤ/ክ ሐዋርያዊ ተልእኮ በአግባቡ እንዳትወጣ ማድረግ፤
     አጠቃላይ ቤ/ክ በማዕከላዊ አሰራርዋ ከአጥቢያ ቤ/ክ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ድረስ ያለው የግንኙነት መስመር ተጠብቆ፣ቤ/ክ የሚጠበቅባትን ሐዋርያዊ ተልእኮ በአግባቡ እንዳትወጣ የተለያዩ ችግሮችን እየፈጠሩ በቀላሉ የሚፈቱ ጉዳዮችን እያወሳሰቡና አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላ ችግር በመፍጠርና ሁከት በማብዛት እረፍት አልባ ማድረግ፡፡ይህም አንዱን  ከአንዱ ከሚያባላ ከተራ አሉባልታ ተነስቶ ቤ/ክ እስከ ማቃጠል፤ ጽላትንና በቀላሉ የማይገኙ መንፈሳዊ ቅርሶች እስከ መዝረፍ ፣በአጠቃላይ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንዳትወጣ ብሔራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ተአማኒነትዋን የሚያሳጣትና በየአደባባዩ የሕዝቡም የአሕዛቡም መሳቂያና መሳለቂያ እያደረጋት  ያለ ከፍተኛ አደጋ ነው፡፡

ተከበራችሁ አንባብያን በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታችሁ የተዋሕዶ ልጆች!
     ይህ ከዚህ በላይ በጥቂቱ ለማሳየት የሞከርነው ስልታቸው እስከ ዛሬ ድረስ ሲጠቀሙበት ከነበረውን ያውም ከብዙው በጥቂቱ ሲሆን ለነገ ደግሞ ያዘጋጁት ሌላ ስልት ሊኖር ይችላል፡፡ይህም ከላይ በክፍል 34 መግቢያችን ላይ ከራሳቸው ድረ-ገጽ በመውሰድ እንደገለጽነው፤ "ይህን የምናደርግበት ዋናው ምክንያትም /ስልት የምንቀያይረው/ ማኅበረሰብ በየጊዜው በተለያዩ ምክንያቶች አስተሳሰቡና አኗኗሩን ስለሚቀያይር …ነው፡፡" ብለዋልና፤ ነገ  የማኅበረሰቡ አስተሳሰቡንና አኗኗሩን በመከተል መለዋወጣቸው ስለማይቀር፤ ሁላችንም ነቅተን እንድንጠብቅ፤ብፁዕ አባታችን አቡነ ቀውስጦስ እንዳሉት"እራሳችንን እንዳናሰርቅ" ለማስገንዘብ ያህል ብቻ ነው፡፡
እንግዲህ የጠላት ሰይጣን ጆሮው ይደፈንና ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ሰልቶች በመጠቀም ጉዳዩ ከሰመረላቸው ግባችን ብለው የነደፉት ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ፤
1/ ተሐድሶ መሆኑን ያላወቀ ተሐድሶ የሆነ ትውልድ መፍጠርና ቤ/ክ ከነምእመኖቿ ሙሉ በሙሉ መረከብ፤
2/ ቤ/ክ ለሁለት በመክፈል ምእመኖችንም ንብረትዋንም በመካፈል የራሳቸውን ድርጅት በመፍጠር፤
3/ ሁለቱም ካልተሳካ ካህኑም ምእመኑም እርስ በርስ ሲነታረክ እንዲኖር ማድረግ፤
4/ የ"ተሐድሶ" የጥፋት ተልእኮ የመጨረሻው ጥግና ማጠቃለያው ትውልዱን ሃይማኖት አልባ አድርጎ ለሐሣዌ መሲሁ/ለሐሰተኛው ክርስቶስ/ /ለአውሬው/ ማስረከብ ነው፡፡
     
   እንግዲህ የጥፋት መልእክተኞቹ ጊዜያቸውን፣ገንዘባቸውን፣እውቀታቸውን፣ጉልበታቸውን ሁሉ መስዋዕት አድርገው፤የእያንዳንዱን ግለሰብ ደካማ ጎን አጥንተው፤ለዚያም ማሸነፊያ ስልት ነድፈው፣ከኋላ ሆነው ለሚነዷቸውና በገንዘብ ኃይል እንዲሰክሩ የሚያደርጓቸው የተለያዩ የፕሮቴስታንት ድርጅቶች የጥፋት ሪፖርታቸውን አቅርበው፣ ያውም "ካዩኝ እስቃለሁ፤ካላዩኝ እሰርቃለሁ" እንደሚለው ሌባ ድንገት ከተነቃብን ተወግዘን እንለያለን ከሚለው ስጋት ጋር ቀንና ሌሊት ሲደክሙ እያየን እየሰማን ነው፡፡   (አቤት ሲያሳዝኑ! ይህ ሁሉ ድካም ስለ እውነት ቢሆን ለነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ / ሥላሴን እስከማየት/ በደረሱ ነበር)

ከእኛ ከተዋሕዶ ልጆች ምን ይጠበቃል?
     አሁን ከመንፈሳዊ እንቅልፍ የምንነቃበት፣ከህሊናና ከታሪክ ወቀሳ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ፍርድ ለመዳን "እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብ የዋሆች ሁኑ" የሚለው አምላካዊ መመሪያ አንግበን፤ ከማንኛውም ዓለማዊ ጉዳያችን አስበልጠን  ለመንፈሣዊ ሥራ የምንነሳበት  ወሳኝ ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ቅድስት ቤ/ክ ከልጆችዋ አንድም ሰው እንዲጠፋባት እንደማትፈልግ ሁሉ፤ማንም ከሃዲ ሆነ መናፍቅ "ወልድ ዋሕድ"የሚለውን እምነትዋን እንዲነካባት እንዲያጠፋባት አትፈልግም፡፡ስለሆነም ከቅዱሳን አባቶቻችን የተረከብናት ርትዕት ሃይማኖታችን ዶጋማዋ፣ሥርዓትዋና ትውፊትዋ ሳይቀር ሳይበረዝና ሳይከለስ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍና እስከ ምጽዓተ ክርስቶስ ድረስ እንድትቀጥል የማድረግ ግዴታ ስላለብን፤ እንዲሁም አንዳንድ በመናፍቃኑ የስህተት ትምህርት የተወናበዱና ግራ የተጋቡት ምእመናን ካሉ በርግገው እንዳይጠፉ ጥንቃቄና ትዕግሥት በተሞላው አካሄድ እየመከርንና እያስተማርን በተዋሕዶ እምነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ የልጅነታችንን መንፈሣዊ ግዴታ መወጣት ይኖርብናል፡፡ይህንንም ለማድረግ፤
1/ ያለ ፈቃደ እግዚአብሔር ምንም ምን ማድረግ ስለማንችል፤አጥብቀን በመጾምና በመጸለይ ሌሎችንም ምግባረ ሠናያት መፈጸም፤
2/ እራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከስህተት መጠበቅ የምንችለው ሃይማኖታችንን ጠንቅቀን ስናውቅ ስለሆነ፤  የእውቀትና የሕይወት ምንጭ ወደሆነችው ቅድስት ቤ/ክ በመቅረብ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋትና ማጠናከር፤በየግላችንም ከእውነተኞቹ መምህራን ቀርበን መማር፤ይህንን የተረዳነውን እውነተኛ ትምህርት በተግባር በመተርጎም /በመንፈሳዊው ሕይወት በመኖር/ ለሌሎች አብነት መሆን፤
3/ ሌሎች ከላይ በተገለጡት የማሳሳቻ ስልቶች እንዳይጠለፉ አቅማችንና ሁኔታዎች በፈቀደልን መጠን ለሌሎች በማሳወቅ ከእሳት ነጥቀን ለማዳን በተመሳሳይ አቋም ላይ ካሉ ምእመናን ጋር በሕብረት መሥራት፤ትክክለኛ የሆነ መረጃም መለዋወጥ፤

ተከበራችሁ የተዋሕዶ ልጆች!
ከላይ እንደገለጥነው በእኛ ተሞክሮ፤ የ"ተሐድሶ" ነን ባዮቹን የተለያዩ እንቅስቃሴያቸውን በማየት፣በመስማትና በቅድስት ቤ/ክ ከሚሰጡ የግንዛቤ መስጨበጫ መርሀ ግብሮች ያገኘነውን ለእናንተ አካፍለናል፡፡የዚህ የጡመራ መድረክ ዋናው ዓላማም እርስ በርስ በመወያየት፣ አንዳችን ለአንዳችን አስተያየትና ጥቆማ በመስጠት የዘላለም ቤታችን የሆነችውን የተዋሕዶ ቤ/ክ በጋራ መጠበቅ እንድንችል ለማድረግ ስለሆነ ስለ ችግሩና ስለ መፍትሔው የሚሰማችሁን በማካፈል  እንድተተባበሩ ቤ/ክ በደሙ በመሠረታት በልዑል እግዚአብሔር ስም እናሳስባለን፡፡

ለዛሬው ይቆየን፡፡እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡







      


No comments:

Post a Comment