ከክፍል ሰላሳ አምስት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
የተከበራችሁ የዚች የጡመራ መድረክ ተከታታዮች፤ በክፍል ሰላሳ አምስት እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ብለው የሚጠሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤
እውነተኛ የተዋሕዶ አማኝ መስሎ ለመታየት የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና የማሳሳቻ ስልቶች ማሳየታችን ይታወሳል፡፡በዚህ ክፍል ደግሞ የዘመነ
ጽጌን ፍጻሜ ምክንያት በማድረግ ጥቂት
ትምህርታዊ መልእክት አለችን፡፡
መልካም ንባብ!
"ከገነት
በተሰደደ ጊዜ የአዳም ተስፋው አንቺ ነሽ"፡፡ ቅዳሴ ማርያም፡፡
ይህንን የተናገረው አባታችን አባ ሕርያቆስ ሲሆን፤ በዚህ አጭር ዓረፍተ
ነገር የሰው ልጆች ሁሉ አባት ከሆነው ከአዳም ጀምሮ ጌታችን ለቤዛ ዓለም እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ያለውን ረጅም የተስፋና የደጅ
ጥናት ዘመንን ያስቃኘናል፡፡አዎ አዳም አታድርግ የተባለውን በማድረጉ እግዚአብሔር የሞት ሞት ቢፈርድበትና ከገነት እንዲሰደድ ቢያደርገውም፤
አዳም በጥፋቱ ተጸጽቶ ንስሃ ቢገባ ከቁጣ ተመላሽ የሆነው እግዚአብሔር ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ
አድንሃለሁ በማለት የተስፋ ስንቅ ሰጥቶት ነበር፡፡እግዚአብሔር ለራሱ ለአዳም ቃል በቃል የሰጠውን ተስፋ፣ከዚያም በየዘመናቱ በተነሱት
በቅዱሳን አበውና በቅዱሳን ነቢያት በኩል ተስፋውን ያድስና ሕዝቡን ያጽናና እንደነበር ቅዱሳት መጸሕፍት ያስረዱናል፡፡
ስለሆነም እግዚአብሔር ወልድ የአዳምን ሥጋ ለብሶ የአዳምን የሞት
ዕዳ ለመክፈል ወደዚህ ምድር ሲመጣ፤ማለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል የምሥራቹን በሰማችበትና
"እንደ ቃልህ ይደረግልኝ" ብላ በተናገረችበት ቅጽበት ጌታችን
የዕለት ጽንስ ሆኖ በማህፀኗ አደረ፡፡(ሉቃ.1፥26 ጀምሮ ይመልከቱ) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራውን የጀመረው በጽንስ
በመሆኑ፤ አስቀድሞ በዘመነ ፍዳ /ኩነኔ/ ሰዎችን ገና ሲጸነሱ ጀምሮ በእናታቸው ማህፀን ሲቆራኝ የነበረው ዲያብሎስ ጌታችን ከእመቤታችን
በድንግልና በተጸነሰ ጊዜ ሥልጣኑ ተሽሯል፡፡የጽንሷም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በድንግልና የፀነሰችውን አምላክ በድንግልና ወለደችው፡፡/ክብር
ምሥጋና ለስሙ ይሁን፡፡/
ጌታችን በተወለደ በሁለት ዓመቱ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም
ጋር ከገሊላ ወደ ግብጽ በረሃ ተሰደደ፡፡የተሰደደውም ለጊዜው አረመኔው ንጉሥ ሄሮድስ እንዳይገድለው ይሁን እንጂ በዋናነት ከገነት
ወደ ምድረ ፋይድ የተሰደደውን አዳምን ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ ነው፡፡ይህ ስደት ተራ ስደት አይደለም፡፡ጭንቀት፣ሰቆቃ፣ረሃብ፣ጥማት፣እንቅልፍ
ማጣት፣ማደሪያ ማጣት፣በጥፊ መመታት፣ቅስም የሚሰብር የሰዎች ስድብና ሽሙጥ፣የሽፍቶች ዘረፋ፣የቀን ሀሩርና የሌሊት ቁር፣በመሳሰሉት
ተደራራቢ ችግሮች የታጀበ ነበር፡፡በዚህ ሁኔታ የሦስት ዓመት ከመንፈቁ የስደቱ ዘመን ተፈጽሞ ጌታችንና እመቤታችን ወደ አገራቸው
ወደ ገሊላ ተመልሰዋል፡፡"ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ህግ ሁሉ ፈጸመ" ተብሎ የተነገረለት ጌታችን ለእናቱ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምና
ለአረጋዊው ዮሴፍ እየታዘዘ በናዝሬት አደገ፡፡በሰላሳ ዓመቱ ተጠምቆ
ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን አስተምሮ በመጨረሻም በእለተ ዓርብ በመስቀል ተሰቅሎ በጽንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በመስቀል
ፈጽሞ፤ጠላት ዲያብሎስን ድል ካደረገ በኋላ፤ አዳምን ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶታል፡፡ከዚህ በኋላ የሰው ልጆች ሁሉ በራሳቸው
ኃጢአት ካልሆነ በስተቀር በአዳምና በሔዋን ምክንያት በመጣው ኃጢአት አይጠየቁም፡፡
ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም
ልዑል እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ የሚበልጠውን ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበትን ጥበቡን፤ ማለትም በጽንሰቱ፣በልደቱ፣በስደቱ፣በጥምቀቱ፣በጾሙ፣
በጸሎቱ፣በመራቡ፣ በመጠማቱ፣ወንጌልን በማስተማሩና ተአምራት
ማድረጉ በመጨረሻም በመስቀል ተሰቅሎ የፈጸማቸውን የቤዛነት ሥራዎች ዕፁብ ድንቅ በማለት በእምነት ተቀብላ ፈጣሪዋን ታገለግላለች፤ለዓለምም
ትመሰክራለች፡፡አሁን ባለንበት የመጨረሻው ዘመን የተነሱና "የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ስለ ክርስቶስ አትሰብክም" እያሉ በድፍረት ሲናገሩ የሚሰሙት
አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤/በተለይ ተሐድሶዎች/ ግን ጌታችን በዘመነ
ሥጋዌው ከዕለተ ዓርብ በፊት የፈጸማቸውን የቤዛነት ሥራዎች አይቀበሉም፡፡የዕለተ ዓርቡንም ቢሆን እንዲሁ በደፈናው ክርስቶስ ያዳነን፤በሞቱ ብቻ ፣በመስቀሉ ብቻ፣ በደሙ ብቻ፣ በጸጋው ብቻ፣ በማለት በ"ብቻ" አባዜ ተተብትበው፤ ከዚያም አልፈው
ክርስቶስን /ሎቱ ስብሐት/ እንደ ግል ጓደኛቸው በመቁጠር፤ሞገሳችን፣ክብራችን፣የጽድቅ ልብሳችን፣ ውበታችን፣ ጌጣችን፣ ወዳጃችን፣
ዓለታችን፣ አክሊላችን፣ግርማችን..….ነው፤ እያሉ ጸጋ እግዚአብሔር በተለየው ጩኸት ሰውን ሲያደነቁሩ ይሰማሉ፡፡ይህም በመጨረሻው
ዘመን ብዙ አሳሳቾች በክርስቶስ ስም ይመጣሉ የሚለው ትንቢት ፈጻሚዎች መሆናቸውን ከማስመስከር በቀር ሌላ ቁም ነገር የለውም፡፡
ወደ ቀደመው ነገር እንመለስና፤ ይህንን የጌታችንንና የእመቤታችንን
ስደት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም ሃያ ስድስት ቀን እስከ ህዳር ስድስት ቀን ድረስ
ያለው ዘመን፤ ዘመነ ጽጌ ወይንም ወርሃ ጽጌ ብላ በመሰየም፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስን ይዛ ከጻድቁ አረጋዊ ዮሴፍና ከቅድስት ሰሎሜ ጋር በስደት የተንከራተተችበትን የሦስት ዓመት ከመንፈቅ የሰቆቃ ጊዜ፤እንዲሁም
የስደቱ ዘመን አልፎ ወደ አገሯ የተመለሰችበትን ወቅት በማሰብ፤በማሕሌትና በቅዳሴ ታከብረዋለች፡፡በዚህ በዘመነ ጽጌ በቤ/ክ የሚደረሰው
ጸሎት ማሕሌቱ "ማሕሌተ ጽጌ እና ሰቆቃወ ድንግል" ቅዳሴው ደግሞ "ቅዳሴ ማርያም" ይባላል፡፡
እንግዲህ ዘመናችን የዓለም ፍጻሜ መቃረቡን የሚያመለክቱ ብዙ አስከፊ
ነገሮች እየተፈጸሙ ያለበት ዘመን መሆኑን ሁላችንም እያየን እየሰማንም ነው፡፡ሰይጣንና ገንዘብ ጌትነታቸው ከፍ ብሎ ከዓለማውያኑ
አልፎ በሃይማኖት ጥላ ስር ያሉትን ሳይቀር በተቆጣጠረበት በዚህ ዘመን የምንኖር ክርስቲያኖች እራሳችንን፣ቤተሰባችንን፣ቤተ ክርስቲያናችንንና
አገራችንንም ከዚህ ከዓለሙ ርኩሰት ለመጠበቅ የምንችለው በጾም፣ በጸሎትና በሌሎቹም ምግባረ ሰናያት ስንጸና ብቻ ነው፡፡ስለሆነም
ጾም ጸሎታችን ቅድመ እግዚአብሔር እንዲደርስልን፤የጎደለውን ወደምትሞላልን ወደ እመቤታችን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም፤ቅዱስ አባታችን አባ ሕርያቆስ ባመሰገነበት ምሥጋናና በጸለየው ጸሎት መማጸን አለብን፡፡ እንዲህ እያልን፦
አዘክሪ ድንግል!!!
- ድንግል! ከፈጠረው ፍጥረት ትንኝን ስንኳ ከማይዘነጋ ልጅሽ አሳስቢልን፡፡
- ድንግል! በቁርና በብርድ ወራት በቤተልሔም ከአንቺ የተወለደው መወለድ አሳስቢልን፡፡አንተማ የባሕርይ አምላክ አይደለህም? ምን መወለድ አለብህ ለእኛ ብለህ አይደለም ብለሽ፡፡
- ድንግል! በቤተልሔም በወለድሽው ጊዜ በጨርቅ የተጠቀለለውን መጠቅለል አሳስቢልን፡፡አንተማ ብርሃንን እንደ ልብስ የምትጎናጸፍ አይደለህም? በጨርቅ መጠቅለልህ ለእኛ ብለህ አይደለምን ብለሽ፡፡
- ድንግል! ሄሮድስ ልጅሽን እንዳይገድለው ከእስክንድርያ ወደ ደብረ ቁስቋም፤ ከደብረ ቁስቋም ወደ እስክንድርያ ስትሸሺ ከአንቺ ጋር መሰደዱን አሳስቢልን፡፡አንተማ ዓለሙን ሁሉ በመሐል እጅህ የያዝህ አይደለህም? መሰደድህ ለእኛ ብለህ ነው እንጂ ብለሽ፡፡
- ድንግል! በልጅሽ በወዳጅሽ ፊት የወረደውን ጽኑዕ እንባ አሳስቢልን፡፡
- አንደኛው፦ አረጋዊው ስምዖን በቤተ መቅደስ "ይህ ብላቴና ለእስራኤል ለልማታቸውም ለጥፋታቸውም የተዘጋጀ ነው፤ አንቺን ግን እንደ ጦር ልብ የሚከፋፍል ኀዘን ያገኝሻል" ብሎ በተናገረ ጊዜ፡፡
- ሁለተኛው፦ እመቤታችን ዮሴፍና ሰሎሜ ጌታን ይዘው በተሰደዱ ጊዜ "ዮሳ" የተባለው የዮሴፍ ልጅ እየተከተላችው ነበርና ሲያገኛቸው " እናንተ በዚህ ባለ ጤና ሆናችኋል፤ በዚህ ሕፃን ምክንያት ግን በገሊላ በክንዷ ልጅ የታቀፈች ሴት የለችም "ብሎ በተናገረ ጊዜ፡፡
- ሦስተኛው፦ ሰብአ ሰገል ለጌታችን ያመጡለትን የወርቅ ጫማ ሌቦች በሰረቁባት ጊዜ፡፡
- አራተኛው፦ በረሃ በረሃውን ሲሄዱ ሽፍቶች አግኝተዋቸው የጌታችንን ሥረወጽ (ስፌት ያልነካው) ልብሱን ገፈው ከሄዱ በኋላ እልፍ ብለው ሲማከሩ አይታ "ወንበዴ አዩኝ አላዩኝ ብሎ የቀማውን ቀምቶ ይሄዳል እንጂ ቆሞ ይማከራል? ልጄን ሊገድሉት ነው እንጂ" ብላ ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡
- አምስተኛው፦ የወልድ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዕለተ ዐርብ ልጅሽ ተሰቀለ ባሏት ጊዜ በጭንቅ በመከራ ወደ ቀራንዩ ተጓዘች፡፡ እንዲህ እያለች "ልጄ ወዳጄ ሆይ በሊቀ ካህናቱ በሀና ግቢ የተቀበልከውን ግፍ ወሬው መራራ ነው፤ልጄ ወዳጄ ሆይ ዛሬ ከእኔ ላይ ነጻነቴን አስወገድክ፤ ስለ ልደትህ በናዝሬት መልካም የምሥራች ነገሩኝ ዛሬ ግን በኢየሩሳሌም ይህቺን ክፉ መርዶ አረዱኝ፤ በዮሴፍ ቤት መልካም ዜና ደረሰኝ በዮሐንስ ቤት ግን የሞት ዜና መጣብኝ፤ ልጄ ወዳጄ ሆይ በእንባና በኀዘን በዓሌ ወደ ልቅሶ ተመለሰ፤ፋሲካም ወደ ልብ ኀዘን፡፡፡" እመቤታችን እንዲህ እያነባች እወደቀችና እየተነሳች ከመስቀሉ አጠገብ ደረሰች፡፡ከተሰበሰቡት የአይሁድ ብዛት የተነሳ ታላቅ መጨናነቅ ነበርና የምትወደውን ልጅዋን ማየት አልቻለችም፡፡ድንግልም ስለ ጽኑ መከራዋ ስለ ልቅሶዋ ስለ ብዙ እንባዋም አንገቷን ወደ መሬት ደፍታ ነበር፡፡ጌታችንም እናቱንና ደቀ መዝሙሩን ዮሐንስን ባያቸው ጊዜ፤ ዮሐንስን "አነኋት እናትህ" እሷንም "እነሆ ልጅሽ" አላቸው፡፡ዮሐንስም ወደ ቤቱ ሊወስዳት ባለ ጊዜ እመቤታችን "ዮሐንስ ሆይ በልጄ ላይ አለቅስ ዘንድ ተወኝ፣ከእርሱ ፈጥነህ አትለየን፣" እያለች ከልጅዋ መስቀል ቀኝ ቆማ ሳለች ድንግል ኀዘኑ ጸንቶባት ነበርና፤ ልቡዋን በኀዘን እጅግ ስለተነካ ከብቻው ለቅሶ በቀርም ያንን ታላቅ ጉባኤ መለስ ብላ አታይም ነበር፡፡ ዮሐንስም ወደቤት እንድትሄድ ግድ ባላት ጊዜ ልጅዋን እንዲህ እያለችው ወደ ሀገር ተመለሰች፡፡"ልጄ ሆይ በላዩ በሰቀሉህ መስቀል ላይ እያለህ በፍቅር እሰናበትሃለሁ፣ ብርሃንን ስለተመላው ምራቃቸውንም ስለተፉበት ፊትህ እሰናበተሃለሁ፣ በሁለት ወንበዴዎች መካከል የሰቀሉህ ንጉሥ ሆይ ለመራቆትህ እጅ እነሳለሁ፤ ሰላምታም አቀርባለሁ፤ ልጄ ሆይ በጠላቶችህ እጅ ላለው ለከበረው ልብስህ እጅ እነሳለሁ ሰላምታ አቀርባለሁ፤ ልጄ ሆይ ከራስህ በላይ ለተደፋው የእሾህ ዘውድ እጅ እነሳለሁ፤ሰላምታ አቀርባለሁ…."፤ይህንንና ይህንን የመሰለ ለቅሶ እያለቀሰችና እየጮኸች ወደ ዮሐንስ ቤት አደረሱዋት፡፡እስዋም ከመጮህና ከማልቀስ ዝም አላለችም፤ ከለቅሶዋና ከኀዘንዋ ብዛት የተነሳ ለዓይኖችዋ ሽልብታ አልሰጠችም፤ የልጇን ትንሣኤ እንከምታይ ድረስ እህል ውሃ አልቀመሰችም፡፡
- ድንግል! የተራብሽውን መራብ የተጠማሽውን መጠማት፤ያዘንሽውን ኀዘን፤ከእርሱ ጋር ያገኝሽን ጭንቅ ሁሉ አሳስቢልን፡፡
- ድንግል! ጥፋትን ያይደለ ይቅርታ አሳስቢልን፡፡
- ድንግል! ለጻድቃን ያይደለ ለኃጥአን አሳስቢልን፡፡ጻድቃንንስ ሃይማኖት ምግባራቸውን ምክንያት አድርጎ ይምራቸዋል፤ኃጥአንን ግን በምን ምክንያት ይምራቸዋል እያለች ታዝናለችና፡፡ /ምንጭ፦ ቅዳሴ ማርያምና ድርሳነ ኪዳነ ምሕረት/
የመለኮት እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ምክንያት ያገኛትን ይህንን ሁሉ መከራና ኀዘን ተመልክቶ ልጇ
ወዳጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰጣት የማይታበል ቃል ኪዳን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር በቸርነቱ የእመቤታችን አማልጅነቷ ከነፍስም ከሥጋም
መከራ ይጠብቀን፡፡አሜን፡፡
ለዛሬው ይቆየን፡፡እንደ
እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡
No comments:
Post a Comment