Wednesday, January 17, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ ሰባት

ከክፍል ሰላሳ ስድስት የቀጠለ፦

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ መታሰቢያ በዓላት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን፡፡
     ሁላችንም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እንደምናውቀው፤ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፤ ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤በዚህ ዓለም በቆየባቸው ሰላሳ ሶስት ዘመናት ማለትም በመዋዕለ ሥጋዌው የፈጸማቸው ሥራዎች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡አንዱና ዋነኛው አዳምና ልጆቹ የተያዙበትን የበደል ዕዳ ዋጋ ከፍሎ /ቤዛ ሆኖ/ ነጻ ለማውጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለአብነት /ለአርአያነት/ ነው፡፡በቤዛነት ሥራው የሰው ልጅ ሊሳተፍበት ስለማይችል እሱ ብቻ የፈጸማቸው ናቸው፡፡ከነዚህ ውስጥ ከእመቤታችን በድንግልና መወለዱ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ በዚያ ተቀብሮ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን መደምሰሱ፣ በመጨረሻም በጽንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በመስቀል ላይ በመፈጸም የከፈለው ካሳ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡በሌላ በኩል እሱ ጾሞ እንድንጾም፣እሱ ጸልዮ እንድንጸልይ፣እሱ ሰግዶ እንድንሰግድ፣ እሱ ለችግረኞችና ለበሽተኞች እንደ አዘነላቸውና እንደረዳቸው እኛም እንዲሁ እንድናደርግ፤ በአጠቃላይ ተከተሉኝ ባለን መንገድ ሁሉ እንድንከተለው፤በአምላካዊ ቃሉ እንዲህ ሲል አስተምሮናል፤"….ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ…..! /ዮሐ.14፥15/ "....እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት…..."!  / ዮሐ.15፥12/፡፡አኛም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች እስከሆንን ድረስ ትእዛዙን መፈጸም ይገባናል፡፡
     የተወደዳችሁ አንባብያን! የጌታችንን የልደቱን መታሰቢያ በዓል ታሕሳስ ሃያ ዘጠኝ ቀን አክብረን የጥምቀቱን በዓል ለማክበር እየተዘጋጀን ባለንበት ሰዓት፤ሁለቱንም በዓላት በማስመልከት ከማሕበራዊ ድረ-ገጽ ያገኘነውንና ለብዙዎቻችን ጥያቄ መልስ የሚሰጡንን ትምህርቶች ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡ልደቱን በተመለከተ "Ydidya Mesgana"የተባሉ፤ ጥምቀቱን በተመለከተ ደግሞ "ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ" የተባሉት መምህር የሰጡትን ትምህርት፤ ጸሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡

መልካም ንባብ! መልካም በዓል!

"በመጀመሪያ ቃል ነበረ ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ ። ዮሐ ፩"

Ydidya Mesgana added a new photo.

 “ነገረ ሰብዓ ሰገል”

"ስብዓ_ሰገል_መጡ ።"

     ሰብዓ ሰገል ማለት ምን ማለት ነው ቢሉ፡-ሰብዓ ጥበብ ፣ ጥበብ ያላቸው ሰዎች ማለት ነው ፣ አንድም ጥበበኞች ሰዎች ማለት ነው አንድም የስነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ማለት ነው ፡፡ አባታቸው ዠረደሽት ሲባል ስማቸውም ማልኮ ፣ ማንቱሲማር እና በዲዳስፋ ይባላሉ፡፡ የመጡት ከፋርስ ባቢሎን እና ከኢትዮጵያ ነው፡፡ልደቱንም በኮከብ ተረድተው ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ስማቸውም ማንቱሲማር፣ ሜልኩ በዲዳስፋ የተባሉ የፋርስ ነገሥታት ከገነት የተገኘ ወርቅ፣ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ገብረውለታል። ከምን አገኙት? ቢሉ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤል ወርቅ ዕጣን ከርቤ አምጥተው ሰጡት። እርሱ ለሔዋን ሰጣት። ሔዋን ለሴት ሰጠችው። ከሴት ሲወርድ ሲዋረድ ከኖኅ ደረሰ። ኖኅ ከመርከብ ከወጣ በኋላ ለሴም ሰጠው። ሴም መልከጼዴቅን አስጠበቀው፤ መልከጼዴቅ ለአብርሃም ሰጠው።ከአብርሃም ሲወርድ ሲዋረድ በዳዊት በሰሎሞን አድርጎ ከአካዝ ደረሰ። በሱ ዘመን ቴልጌልፌልሶር ማርኮ ወስዶ ከቤተ.መዛግብቱ አኑሮታል።አባታቸው ዥረደሽት ይባላል፤ ፈላስፋ ነበር። አንድ ቀን በቀትር ከውኃ ዳር ሆኖ ሲፈላሰፍ በሰሌዳ ኮከብ ድንግል ሕፃን ታቅፋ አየ። ያየውን በሰሌዳ ቀርጾ አስቀመጠው።ሲሞት ልጆቼ እንዲህ ያለ ኮከብ ሲወጣ ባያችሁ ጊዜ ሰማያዊ ንጉሥ ይወለዳልና ይህን ወስዳችሁ እጅ ንሱ ብሎ ሰጥቷቸዋል። አንድም በለዓም “ከያዕቆብ ቤት ኮከብ ይወጣል” ያለውን ሰምተው ይዘው መጥተዋል። (ዘኅ. 20፡17)። አንድም ትሩፋን በባቢሎን ሳሉ ነገሥተ ተርሴስ ወደ ስያት ስጦታ (ገጸ በረከት) አመጡ፤ ንግሥተ ሳባ ወዓረብ እጅ መንሻ ያመጣሉ እያሉ ሲጸልዩ ይሰሙ ነበረና ይኸን ይዘው መጥተዋል። አንድም ባሮክ አቴና ወርዶ ነበር። ያን ጊዜ ዛሬ የሀገራችሁን ንጉሥ የሚገብረውን ወርቅ ኋላ ከእኛ ወገን ንጉሥ ሲወለድ ይገብረዋል ብሎ የነገራቸውን ይዘው ነው። የተወለደ ዕለት ኮከቡን አይተው አባታችን የነገረን ደረሰ ብለው 12 ሆነው ሠራዊቶቻቸውን አስከትለው ተነሱ።
     ሰብዓ ሰገል ከአገራቸው ሲነሡ 12 የነበሩ ሲሆን እያንዳንዳቸውም ብዙ ሺህ ሠራዊቶች አስከትለው ነበር ነገር ግን በጉዞ ላይ ሳሉ ድንገት ጦርነት ተነሥቶ አብዛኞቹ ሲያልቁ ገሚሶቹ ደግሞ ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኤፍራጥስ ወንዝ አካባቢ ሲደርሱ ስንቅ አልቆባቸቸው ብዙዎቹ ተመልሰዋል የሚል ታሪክም አለ፡፡ ሆኖም ሦስቱ ብቻ ቀርተው አብዛኛዎቹ የመመለሳቸው ምክንያት የጌታን ልደት ለማየት ፈቃደ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስላልነበረ ነው፡፡ ነገር ግን ሦስቱ የተገባላቸውን ቃል ለመፈጸም ሁለት ዓመታትን ተጉዘው ቤተልሔም ከተማ ደርሰዋል፡፡እኒህ ሦስቱ ኮከቡ እየመራቸው ኢየሩሳሌም ደርሰው በሄሮድስ በኩል አድርገው ቤተልሔም ወርደው አግኝተው አባታቸው ዠረደሽት ያስተላለፈላቸውንም ወርቅ ፣ ዕጣንና ከርቤ ለጌታ ገብረውለታል፡፡ ›
ምሥጢሩም፡-
ወርቅ_መገበራቸው ፡ 
ይኸን የምንገብርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ነህ፤ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ፤አንድም ወርቅ ጽሩይ ነው፤ ጽሩየ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ እንዲሁም በአንተ ያመኑ ምዕመናንም ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ወርቅ የሃይማኖት ምሳሌ ነው። የሃይማኖት ጽሩይነቱና ግብዝነቱ የሚታወቅ መከራ ሲቀበሉበት ነውና።
ዕጣን_መገበራቸው ፡ 
ይኸንን የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኀላፍያን ናቸው። አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ ሲሉ። አንድም ዕጣን ምዑዝ ነው፤ አንተም በባሕርይ ምዑዝ ነህ ሲሉ እንዲሁ ደግሞ በአንተም የሚያምኑ ምእመናንን ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው ሲሉ። አንድም ዕጣን የተስፋ ምሳሌ ነው። ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋ ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና።
ከርቤ_መገበራቸው ፡ 
ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ በኋላም የማታልፍ ብትሆንም በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀበላለህ ሲሉ፤ አንድም ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለየውን አንድ ያደርጋል። አንተም ከማኅበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ ሲሉ። አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት። ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው። በፍቅር አንድ ይሆናሉና። ከርቤ የፍቅር ምሳሌ ነው። ከርቤ አንድ እንዲያደርግ ፤ ፍቅርም አንድ ታደርጋለችና። በአጠቃላይ ሰብአ ሰገል ወርቅ፣ እጣን ከርቤ የገበሩለት ሃይማኖት፣ ፍቅር፣ ተስፋ፣ ገንዘቦችህ ናቸው ሲሉ ነው። በሌላ መልኩ ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለመለኮቱ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ ናቸው።
     እጅ ነስተው ከወጡ በኋላ አንዱ እንዴት ያለ ሽማግሌ ነው ብሎ አደነቀ። ሁለተኛው የምን ሽማግሌ ጎልማሳ ነው እንጅ አለ። ሦስተኛው ደግሞ ሕፃን ነው እንጂ አለ። ገብተን እንይ ተባብለው ቢገቡ ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ፤ ጎልማሳ መለስሎ ለታየው ሕፃን፤ ሕፃነ መስሎ ለታየው ሽማግሌ መስሎ ታያቸው። ወጥተው እንዳንተ ነው እንዳንተ ነው ይባባሉ ጀመር። መልአኩ መጥቶ እንደሁላችሁም ነው አላቸው። በጆሮ የሰሙትን በዓይን ቢያዩት ይረዳል ብለው ለሦስተኛ ጊዜ ገቡ። ሽማግሌ ጎልማሳ መስሎ ለታየው ሕፃን፤ ጎልማሳ ሕፃን መስሎ ለታየው ሽማግሌ፤ ሕፃን ሽማግሌ መስሎ ለታየው ጎልማሳ መስሎ ታያቸው። እጹብ እጹብ ብለው አመስግነው፤ አምላክነቱን ተረድተዋል።
     በሌሎች የታሪክ ድርሳናት እንደተመዘገበው ደግሞ በጦርነቱ ወቅት ተበታትነው ከነበሩት(ስንቅ አልቆባቸው ከተመለሱት) 12ቱ ነገሥታት መካከል አንዱ የጌታን ልደት ለማየት ሽቶ ሦስቱን ነገሥታት (ሰብዓ ሰገልን) እንደተከተላቸውና መንገድ ጠፍቶበት ብዙ ዓመታትን ከፈጀ በኋላ ኢየሩሳሌም ከተማ የደረሰው ጌታ በተሰቀለበት ቀን ዕለተ አርብ ላይ ነበር፡፡ ቀራንዮም እንደደረሰ በጌታ መስቀል ራስጌ(አናት) ላይ ‹‹ይህ የአይሁድ ንጉሥ ነው›› የሚለውን ጽሕፈት ተመልክቶ አስቀድሞ ይወለዳል ተብሎ የተነገረለት ‹‹የአይሁድ ንጉሥ›› መሆኑን ዐወቀ፡፡ አንድም በመንገዳቸው ሁሉ ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው›› እያሉ ስለመጡ ይህ የተሰቀለው ጌታ ያ ይወለዳል ተብሎ የተነገረለት የአይሁድ ንጉሥ መሆኑን ተረዳ፤በልደቱ ተጠርቶ በሞቱ ደረሰ ጌታንም እንዳየ በዚያው በቀራንዮ ዐርፏል፡፡
     ሰብዓ ሰገል ከሩቅ ምስራቅ ወደ ቤተልሔም ሲመጡ ሁለት ዓመት የፈጀባቸው ሲሆን ወደ አገራቸው ሲመለሱ ግን 40 ቀናት ብቻ ነበር የፈጀባቸው፡፡ ለጌታ አምሐ(ስጦታ) አቅርበው ሲመለሱም እመቤታችን ለመንገድ የሚሆናቸውን ማዕድ(ስንቅ) ሰጥታቸው ስለነበር 40 ቀን ሙሉ ከነ ሠራዊቶቻቸው ተመግበውት አላልቅ ስላላቸው ‹‹ይህን ከጌታ እናት የተሰጠንን የከበረ ማዕድ ወደ ከተማ ይዘን አንገባም!›› ብለው ከሩቅ ትተውት ሄዱ፡፡ ይህን የሰሙ የከተማው ሰዎች(ነዋሪዎች) እስኪ አሳዩን ብለዋቸው ቢሄዱ ሲቃጠል(ሲነድ) አገኙት፡፡ ኋላም ‹‹እሳትን አምልኩ ቢለን እንጂ ይህ ባልሆነ ነበር›› ብለው የአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዚያን ቀን ጀምሮ እሳትን ማምለክ ጀመሩ፡፡ ሆኖም ከብዙ ዓመታት በኋላ ጌታ ሐዋርያቱን በዓለም ዞረው ወንጌልን እንዲያስተምሩ በላካቸው ጊዜ ሐዋርያው ናትናዔል አገረ ስብከቱ እዚያ ስለነበር ‹‹ይህ እሳት ለተዓምራት የተደረገ እንጂ እንድታመልኩት አይደለም! ማመን ያለባችሁ ሰማዩን ምድሩን ፣ ባሕሩን ጠፈሩን በፈጠረ በእግዚአብሔር ነው›› ብሎ አጥምቋቸዋል፡፡
     ሰብዓ ሰገል የጌታን ልደት ለማየትና እጅ መንሻን ለመስጠት እንዴት ከሩቅ አገር ድረስ መጡ? ቢሉ ትንቢተ ነቢያት ይፈጸም ዘንድ ነው “ልጆችሽን ከሩቅ ከእነርሱም ጋር ብራቸውንና ወርቃቸውን ያመጡ ዘንድ ደሴቶች የተርሌስ መርከቦችም አስቀድመው ይጠባበቁኛል”(ኢሳ 60÷9)፡፡ ከእነዚህ ሦስት የምሥራቅ ነገሥታት መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊ ነበር እርሱም ንጉሥ ባዜን (ንጉሥ አርማዕ) ይበላል፡፡ ለዚህም ማስረጃዎች አሉ “ከሳባ ይመጣሉ ወርቅና ዕጣንን ያመጣሉ የእግዚአብሔርንም ምስጋና ያወራሉ የቄፋር መንጐች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ የነቢያትም አውራ በጐች ያገለግሉሻል” (ኢሳ 60÷6-7) አንድም “በፊቱም ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ” ይላልና (መዝ72፡9)፡፡ በረከታቸው ይደርብን፡፡

ለYdidya Mesgana ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

ቀጥሎ የምናቀርበው "የሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ" ትምህርት ነው፡፡

"ከሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ"

"ከተራ ማለት ምን ማለት ነው?"

     1ኛ ከተራ ማለት “ከተረ” ከበበ ዙሪያውን ያዘ ካለው ከግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፡፡ከተራ ማለት ከበባ እጀባ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ታቦተ ሕጉ በጳጳሳት፣ በሊቃውንት፣ በቀሳውስት፣ በዲያቆናት እንዲሁም በምእመናን ተከቦ ታጅቦ መጓዙን የሚያመለክት ገላጭ ቃል ነው፡፡
     2ኛ ከተራ ማለት ከተረ ሰበሰበ ዐጠረ ማለት ሲሆን ይኸውም ወራጁን ውኃ ሰብስበው ወይም ገድበው በየሰበካው ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው ሚከተሩበት ስለሆነ ነው፡፡ ይህም ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት›› ወይም ‹‹የታቦት ማደሪያ›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ውኃ መሰብሰቢያ ምቋመ ማይ ማለት ነው፡፡

ከተራ መቼ ተጀመረ?

     የጥምቀት አከባበር በሀገራችን ኢትዮጵያ ታቦት ተሸክሞ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሲሆን ይበልጥ ተጠናክሮ መከበር በሜዳና በውኃ አካላት ዳር ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት (530-544 ዓ.ም) እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኸውም ከማኅሌታዊው ቅዱስ ያሬድ (507-572 ዓ.ም) ዜማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ታቦታቱ በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ጠዋት ወደ ወንዝ ወርደው ማታ ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ይደረግ ነበር፡፡ከዚህም ባሻገር በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውናና በስብከተ ወንጌል ተግተው ያገልግሉ የነበሩ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡ ንጉሥ ላልይበላ ከ1140-1180 ዓ.ም ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው በተናጠል ሲፈጽሙት የነበረውን ክብረ በዓል አስቀርቶ በምትኩም በአንድ አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአንድነት ተሰባስበው በአንድ ጥምቀተ ባሕር እዲያከብሩ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
     ይህም ተግባራዊ በመኾኑ የበዓሉ አከባበር ሥነ ሥርዓት ቅንጅትና ድምቀት ባለው ሁኔታ እንዲከበር አድርገዋል፡፡ በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት ከ1203-1304 ዓ.ም ድረስ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዓተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በአዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡በመቀጠል አጼ ናኦድም ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ታቦተ ሕጉ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ በሚወርደበት ጊዜና ከጥምቀተ ባሕር ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ እንዲመለስ አዋጅ ነግረው በአዋጁ መሠረትም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ታቦተ ሕጉን በማጀብ በሆታና በዕልልታ ሲያከብር ኖሯል፡፡
     በመንፈሳዊነታቸውና በደራሲነታቸው መጻሐፍትን ጽፈው ሥርዓትን ሠርተውለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም) ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር ፲ ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ ሀገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በአዋጅ ወሰኑ፡፡ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡ አከባበሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ አድማሱም ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ፡፡ ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድሩ ጀመር፡፡የከተራ በዓል ጥንት ከነገሥታቱ ጀምሮ የሀገር መሪዎች በቀዳሚነት ተሰልፈው የሚያከብሩት ብሔራዊ በዓል ከመሆኑ የተነሣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ የአከባበር ሥነ ሥርዓት አለው፡፡ ይኸውም ባህላዊው ከሃይማኖታዊው ሥርዓት በመነሣት የሚከናወን ሆኖ ማህበረ ሰቡ ደስታውን ፍቅሩን የሚገልጥበት የአለባበስ የአጨዋወት ሥርዓት አለው፡፡

ባሕላዊ አከባበሩ

     ሀገሬ ታቦት እዩት እዩት ሲያምር የበአታ ደብር፤ እያሉ የደብራቸው ስም እየጠሩ ያመሰግናሉ፡፡ ‹‹እንኳን ለታቦት ለደጉ ጌታ ይጨበጨባል ለጋለሞታ፡፡ ሁሉም ያምረኛል በመር በመሩ፤ እነ መምሬ ቅኔ ሲመሩ፡፡ ‹‹በሕይወት ግባ በሕይወት፤ የአገሬ ታቦት፡፡ ሲያምር ዋለ ሲያምር፤ የሀገራችንደብር፡፡ እየው ወሮአት ሲገባ፤ ጌታ ባለአበባ፡፡ አለው አለው አበባ፤ የአገሬ ታቦት ሲገባ፡፡ ርግቤ በቀሚሱ ላይ፤ ርግቤ በካባው ላይ፤ የሰላም ምልክት ይዛ ልትታይ፡፡ ልብሱ አረፈረፈ ልብሱ አረፈረፈ፤ ርግብ በራሱ ላይ ዐረፈ፡፡በዚህ መልኩ ታቦቱን በልዩ ልዩ ቃላት ያሞግሳል፡፡ ሴቶችም እንደዚሁ በበኩላቸው ከወላጆቻቸው ሲዋረስ በመጣው መሠረት ነጫጭ የሀገር ልብሳቸውን ለብሰው ከዋክብት መስለው መቀነታቸውን በወገባቸው ሸብ አርገው የታቦት ዜማ ያሰማሉ፡፡

ሃይማኖታዊ አከባበሩ

     ጥር ፲ ቀን ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዋዜማ ይቆማል፡፡ ከሰዓት በኋላ ታቦታቱ በተለያየ ሕብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከአብያተ ክርስቲያናት ወደ አብሕርተ ምጥማቃት ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በነቂስ ወጥተው በአጸደ ቤተ ክርስቲያንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ይሰባሰባሉ፡፡

መንፈሳዊ ምሥጢሩ

     ቃል ኪዳኑን ታቦት ይዞ አክብሮ ወደ ወንዝ መውረድ በብሉይ ኪዳን የነበረ ሥርዓት ነው፡፡ይኸውም ኢያሱ በሙሴ ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን ሲመራ ታቦቱን አሸክሞ ሲሔድና ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ወራጁም ይቆም እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ ይናገራል፡፡ እስራኤል ወደ ምድረ ርስት ሲገቡ ታላቁን የዮርዳስ ወንዝ ሲሻገሩ ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳን ታቦት ድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ ዙሪያውን ካህናቱ በውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንደተሻገሩ ዛሬም እንደ ዮርዳኖስ ከጉስቁልና ወደ ብልጽግና ከደዌ ወደ ጤና አላሻግር ያለን ባሕረ ኀጢአት በቃል ኪዳኑ አማካኝነት በጥምቀቱ በረከት ያደርቅልናል ስንል ነው፡፡ኢያሱ 1 ፥ 13 ፣ ኢያሱ 3፥8፡፡አንድም ሐዋርያው ፊሊጶስ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባውን ሊያጠምቀው ወደ ወንዝ የመውረዱ ምሳሌ ነው፡፡           ሐዋ.ሥራ 8 ፥34
     ዋናው ምስጢሩ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን አስከትሎ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመሄዱ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቱ የጌታችን፤ ታቦቱን ተሸክሞ የሚሄደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሄዱት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩ ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው በዚያው ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱ የመቃብሩ አምሳል ነው፡፡ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያ ዘንድ የዝናም፣ የበረዶ ወራት ነው፤ እንኳንስ ከወንዝ ዳር ከማናቸውም ቦታ ቢሆን ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፤ በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ በድንኳኖች የተከለሉ ዳሶች ይጣላሉ፡፡
     ስለዚህ ከጥንት ጀምሮ የቃል ኪኑን ታቦት ይዘን ወደ ወንዝ ወርደን በዓለ ጥምቀትን የምናከብረው ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር ፲ ቀን ተቀራራቢ የሆኑትን ታቦታት በየአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ወንዝ በአንድነት እያወረደች ከከተራ ዕለት ጀምሮ የጥምቀትን በዓል በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ታከብራለች፡፡ ሌሉቱን ከሚያነጋው ሕዝበ ክርስቲያን ጋር በመሆን የማኅሌትና የወንጌል ጉባኤ ተዘርግቶ በመምህራን ወቅታዊ ትምህርት ሲሰጥ ይታደራል ይዋላል፡፡

ለሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ፤ ቃለ ሕይወት ያሰማልን፡፡

ውድ አንባብያን! እኛ ያገኘነውን መልካም ነገር ለሌሎች ማካፈል፤የክርስቲያንነታችን እና የኢትዮጵያዊነታችን መገለጫዎች ስለሆኑ ለሌሎች ማካፈልን አንርሳ፡፡

ለዛሬው ይቆየን፡፡እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ በሌላ ርዕስ እንገናኛለን፡፡


No comments:

Post a Comment