ከክፍል አርባ የቀጠለ፦
ለዚች ዕለትና ለዚች ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
የተከበራችሁ
የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ ልጆች!የመጨረሻው ዘመን የወለዳቸው የተለያዩ መናፍቃን ከውስጥም ከውጭም ሆነው የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እምነት፣ ሥርዓትና እንዲሁም
ትውፊት ሳይቀር የሚያፋለሱ የስህተት ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያናችን ስም እያሰራጩና ብዙዎችንም እያሳሳቱ መሆኑን ወቅታዊውን የቤ/ክ
ሁኔታ በቅርበት የሚከታተል ሁሉ ችግሩን በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡እኛም ይህችን "ወልድ ዋሕድ" የተሰኘች የጡመራ መድረክ የጀመርንበት ዋናው ምክንያት፤እነዚህን የጨለማ ሥራዎቻቸውን /የምንፍቅና ትምህርታቸውን/ ወደ
ብርሃን በማምጣት ማለትም ስህተታቸውን በመግለጥና አቅማችንና እውቀታችን በሚፈቅድልን መጠን መልስ በመስጠት፤ ትውልዱ እራሱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ከስህተቱ ትምህርት
እንዲጠብቅ የሚያስችለውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡
እነዚህ የስህተት ትምህርቶች በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በምሥጢረ ሥጋዌ (ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ
የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ሰውን ያዳነበት ምሥጢር) ትምህርት ላይ ነው፡፡ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው
ባስተማረው ትምህርት (ማቴ.24 በሙሉ ይመልከቱ)፤በመጨረሻው ዘመን ብዙ ሐሰተኞች አስተማሪዎች በስሙ እንደሚመጡና ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፤እኛም
በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሁሉ ከስህተት ትምህርታቸው እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡በመቀጠልም ይህንን የጌታችንን ትምህርት
መሠረት በማድረግ "ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት
ሁሉ ስበኩ" ብሎ እሱ በመረጣቸው በሐዋርያትና
በእነሱ እግር በተተኩ መምህራንም በየዘመኑ ለተነሳው ትውልድ ትምህርቱና ማስጠንቀቂያው ሲነገር የነበረ ወደፊትም እስከ እስከ ዓለም
ፍጻሜ ድረስ ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ይሁን እንጂ ስንቶቻችን ይህንን ችግር ተረድተናል? ምን ያህልስ እራሳችንንም ሆነ ሌላውን ከስህተት
ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል? የሚለውን ጥያቄ እራሳችንን እየጠየቅን ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች መሆን ይገባናል፡፡
ወደ ዋናው ነገር እንመለስና፤ እነዚህን የስህተት ትምህርቶች ከሚያስተላልፉት የእምነት ድርጅቶች አንዱ እራሱን "የእውነት ቃል አገልግሎት"ብሎ የሚጠራው የመናፍቃን ድርጅት
ሲሆን፤ከመጽሐፍቻቸው አንዱ በሆነው ‹‹የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» በተባለው መጽሐፋቸው በምሥጢረ ሥጋዌ
ላይ የሚሰጡትን የክህደት ትምህርት በዚችው ጡመራ መድረክ ከክፍል ሦስት እስከ ክፍል አምስት ከብዙው በጥቂቱ ለማሳየት ሞክረናል፡፡
ይህ ድርጅት ቀድሞ ከእኛ ዘንድ በነበሩ ነገር ግን ከእኛ ወገን ስላልነበሩ በራሳቸው ፈቃድ በወጡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት
አራማጆች የተመሠረተ ሲሆን ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘ ነው፡፡
የተወደዳችሁ አንባብያን፤
“ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” በማለት ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር
9 በሰፊው አስተምሮናል፡፡በዚሁ መሠረት ዝግጅቱ የእኛ ባይሆንም፤ትክክለኛውን
የተዋሕዶ ትምህርት የሚያስተምሩትን የሌሎች መምህራን ትምህርቶች ስናካፍላችሁ እንደነበር፤ዛሬም "ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልዳል"
(ሎቱ ስብሐት) እያሉ ለሚዘባርቁ የተለያዩ የውስጥም ሆነ የውጭ መናፍቃን ተገቢውን ምላሽ የሰጡበትንና "ፀረ-በጋሻው ደሳለኝ ፀረ-ተሀድሶ!" በተባለው የፌስ ቡክ ገጽ ለንባብ
የበቃውን የመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራውን ትምህርት እንዳለ አቅርበንላችሁዋል፡፡
መልካም ንባብ ከማስተዋል ጋር!