ከክፍል አስራ አራት የቀጠለ
"እያወቁ ማለቅ"
"ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ፡፡"
በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ሁሉን ቻይ ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር እውቅና
እና ፈቃድ ውጪ የሚከናወን ምንም ነገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ይታመናልም፡፡ይሁን እንጂ ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን ከሌሎች ፍጡራን
ለይቶ በመልኩና በምሳሌው ሲፈጠረው የማሰብ፣የመናገርና ሕያው ሆኖ የመኖር ዕድል ሰጥቶታል፡፡የሰው ልጅ በዚህ በተሰጠው አእምሮ መመራት
አቅቶት በኃጢአት ቢወድቅ፤ይህንን አድርግ ይህንን አታድርግ የሚል የተጻፈ ህግ /ህገ ኦሪትን/ ሰጠው፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም፤እራሱ
እግዚአብሔር ወልድ ወደዚች ምድር መጥቶ ለሰው ልጅ የቤዛነቱንና የአርአያነት ሥራውን ፈጸሞለታል፡፡ ጌታችን መድሐኒታችን በኢየሱስ
ክርስቶስ በጽንስ ጀምሮ በመሰቀል የፈጸመውን የቤዛነቱን ሥራ እፁብ! ድንቅ! ብሎ ከማመስገን በስተቀር በዚች አጭር ጽሁፍ የምንለው
ነገር አይኖረንም፡፡በአርአያነት/በምሳሌነት/ ሥራው ግን ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ህግ ሁሉ ፈጽሞ እኛም እንድንከተለው አዝዞናል፡፡በእኔ
ያመነ እኔ የምሰራውን ሁሉ ያደርጋል፤እንደውም የበለጠ ያደርጋል ብሎ፡፡ዮሐ.14፥12፡፡


