Tuesday, August 8, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ አንድ

ከክፍል ሰላሳ የቀጠለ፦

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?

ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

      ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ፤ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረ እናስታውሳለን፡፡
     ዛሬ በዚች ክፍል የምናስነብባችሁ "ማቴዎስ ናታኒም" የተባሉ ወንድማችን በማህበራዊ ድረ-ገጽ ላይ "ነገረ ክርስቶስ በገድላት" በሚል ርዕስ ያስተላለፉትን ጠቃሚ ትምህርት ነው፡፡የመልእክቱ ይዘት  ለእኛ ለተዋሕዶ ልጆች ትምህርት፤ እንዲሁም ሳይገባቸውና ሳይገባቸው (" "ጠብቆ ይነበብ) ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ለሚተቹ ደግሞ ምላሽ የሚሰጥ ስለሆነ ሁላችን አንብበን እንድንጠቀምበት ማስተዋሉን ያድለን፡፡
ጽሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማድረግና አንዳንድ የፊደላት እርማት ከማድረግ በስተቀር የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡

Wednesday, August 2, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ


ከክፍል ሃያ ዘጠኝ የቀጠለ

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ?

ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

    ሁላችንም እንደምናውቀው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሳይሆኑ መስለውና ተመሳስለው የተዋሕዶ ሃይማኖታችንን ዶግማ፣ሥርዓትና ትውፊቷን የራሳቸው ልብ ወለድ በሆነ እንግዳ ትምህርት ለመለወጥና በመጨረሻም የፕሮቴስታንት ጥገኛ ለማድረግ የጥፋት ተልእኳቸውን  ተግተው በመፈጸም ላይ የሚገኙ፤ እራሳቸውን "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ" ብለው የሚጠሩ ክፍሎች ቤ/ክንን ምን ያህል እተፈታተኗት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
      ይህንኑ የክህደት ሥራቸውን ሳያፍሩና ሳይፈሩ "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  ብለው ባለ 43 ገጽ ክህደት መግለጫ ሲያወጡ፤እኛም "በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ…"/1ኛ ጴጥ.3፥15/ በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት፤ ቅዱሳን አባቶች ተገቢውን መልስ እስከሚሰጡ ድረስ ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልምና በዚሁ ድረ-ገጻችን ( ወልድ ዋሕድ) ላይ በክፍል 19፣22፣23፣24 መልስ መስጠታችን ይታወሳል፡፡
       ለእግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና የቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ጉባኤ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ከላይ ለተጠቀሰው የክህደት መግለጫቸው "ከውሾችና ከክፉ አድራጊዎች ተጠበቁ"(ፊል. ፫፥፪ ) በሚል ርዕስ ተገቢው ምላሽ ስለተሰጠ፤ አባቶቻችን ብዙ ደክመው ያዘጋጁት መጸሐፍ ሁላችንም የተዋህዶ ልጆች በመግዛትና በጥሞና በመመልከት  እራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከስህተት ትምህርት በመጠበቅ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን መወጣት ይገባናል፡፡

የመጽሐፉ የፊት ገጽታ
"ከውሾችና ከክፉ አድራጊዎች ተጠበቁ"
(ፊል.፫፥፪)
"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"
ለሚለው የመናፍቃን አስመሳይ መግለጫ
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የተሰጠ መልስ
በሊቃውንት ጉባኤ ተዘጋጅቶ በትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት አሳታሚነት ታተመ
                                                                                    ጥር ፳፻ወ፱

                                                                                     አዲስ አበባ 

Monday, April 10, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ዘጠኝ

ከክፍል ሃያ ስምንት የቀጠለ

የተከበራችሁ  የዚች ጦማር ታዳሚዎች ምእመናን!

     እንደምን ሰነበታቸሁ?  ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ብሎ የጾመውን ዐቢይ ጾም፤እኛም እንደ አቅማችን ጾመን እንድንፈጽመው የረዳን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
ከዚህ በመቀጠል የጌታችንን የሕማሙን፣የሞቱንና የትንሣኤውን ነገር  በመጠኑ ለማዘከር እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!

Sunday, February 5, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ስምንት

ከክፍል ሃያ ሰባት የቀጠለ

     የተከበራችሁ  የዚች ጦማር ተከታታዮች ምእመናን! እንደምን ሰነበታችሁ? ለዚች ዕለትና ለዚች ሰዓት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ከዓለም ዳርቻ እስከ ዓለም ዳርቻ የተመሰገነ ይሁን፡፡በአገልግሎት መብዛት ምክንያት ወቅታዊ መልእክቶችን ከማስተላለፍ ስለዘገየን አስቀድመን ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡
     ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.፲፪ ቁጥር ፱  “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” ብሎ ባስተማረን መሠረት፤ዓላማችን አንድ እስከሆነ ድረስ፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትና ሥርዓት ጠብቀው የሚያስተምሩትን የተለያዩ መምህራንን ትምህርቶች፤በዚች የመወያያ ጦማር ላይ እንድታነቡ ስናደርግ እንደነበረው፤በዚች ክፍል የምናስነብባችሁ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ “ሠለስቱ ደቂቅን ከእሳት ያዳናቸው መልአክ ማን ነው?”በሚል ርዕስ ያስተላለፉትን እጅግ ተቃሚ ትምህርት በድረ ገጻቸው በጊዜው ማንበብ ላልቻላችሁ ምእመናን አቅርበንላችኋል፡፡ሙሉው መልእክት የዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ነው፤ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማድረግ በስተቀር የራሳችንን ሃሳብ አልጨመርንም፡፡
መልካም ንባብ!

Wednesday, September 14, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሰባት

 ከክፍል ሃያ ስድስት የቀጠለ

የተከበራችሁ  የዚች ጦማር ታዳሚዎች ምእመናን!

     ሁላችንም እንደምናውቀው ስለዚህ ስለ መጨረሻው ዘመን አስከፊነት አስቀድሞ በነቢያት፣ከዚያም በጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው፣እንዲሁም በጌታችን ደቀ መዛሙርትና ከነሱም በመቀጠል በየዘመኑ በተነሱ ቅዱሳን አባቶችና በሊቃውንት በሰፊው ሲነገር ኖርዋል፤አሁንም እየተናገሩ ነው፡፡በተለይም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁ.1-ፍጻሜ የተነገሩት የዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶች አሁን በእኛ እድሜ በስፋት እየተፈጸሙ እንመለከታለን፡፡የቀደሙት ቅዱሳን ከዚህ ዘመን እንዳይደርሱ፤ከእህል ውሃውም እንዳይቀምሱ፤ አጥብቀው በመጸለያቸው ምኞታቸው ተፈጸሞላቸው በሰላም ከዚህ ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ስለሆነም እኛም ክርስቲያኖች የዚህ የክፉ ትንቢት መፈጸሚያዎች እንዳንሆን ህገ እግዚአብሔርን ማወቅና ከክፉ ነገር መጠበቅ ብሎም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

ክቡራን አንባብያን!

     ስለ ዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶችና ጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ስለሚሆነው ንውጽውጽታ "አክሊሉ ደበላ" የተባሉ ወንድማችን በማህበራዊ ደረ-ገጽ በግጥም ያስተላለፉትን እጅግ በጣም አስተማሪ ጸሁፍ ለሁላችንም ጠቃሚ ስለሆነ እንድተመለከቱ እንጋብዛለን፡፡

መልካም ንባብ!

Aklilu Debela

***ና ልበል: አትምጣ??***

ተልከው ነፋሳት - ምድርን ሲያናውጡ
የክፋት ነቢያት - ካሉበት ሲወጡ
መንግስት መንግስት ላይ - ህዝብም በህዝብ ላይ
ድንጋይም በድንጋይ - ተደርምሶ ሲታይ
የደስታ ካብ ሁሉ - ሲናድ ከሰዎች ልብ
የጸጥታ ስፍራ - በክፋት ሲከበብ
ያላሰብኩት ሆኖ - ያልኩት ሲቀርብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መቃረቡ ሲሆን - የትንቢት ፍጻሜ
ሰማይና ምድር - የሚያልፉበት እድሜ
የጸሃይዋ መጥለቅ
የብርሃኗ መራቅ
ይሆናል ያልተባለው - መሆኑ ሲታወቅ
ሰማይ ሲጠቀለል - ከዋክብት ሲረግፉ
የዓለም ኩሬዎች ሁሉ - ሲዘጉ ሲነጥፉ
“ዓለም!” “ዓለም!” ያሉት - ሲሆኑ መና ዎና
የምናያት ምድር - እንዳልሆነች ሆና
ባዶነት ሲወረኝ - ተስፋ ሲጠፋብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
የቁጣ ነፋሳት - ከአዜብ ሲለቀቁ
መድረሻ ጠፍቶአቸው - የቆሙት ሲወድቁ
ዙሪያው ሲጨላልም - ሲዘጋጋ መንገድ
ከምስራቅ ሲሰማ - አስፈሪው ነጎድጓድ
ሲያይሉ መባርቅት - መለከት ሲነፋ
የነበረው ሲተን - የሞለው ሲጠፋ
ሰላሜ ሲታወክ - ጭንቁ ሲመጣብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ኀሳዊያን ደቂቃን - ኀሳዊ መምህር
ኀሳዊ ክርስቶስ - የሀሰት ደቀመዝሙር
ሲበዛ በዓለም - ሲበረክት በደጅ
በተዓምር ጨረቃን - የጨበጠው በእጅ
በቅዱሱ ስፍራ - ሲፈስ የንጹህ ደም
ሽሽት ክረምት ሲሆን - የኃላው ሲቀድም
በሰንበት መሰደድ - ሲሆን መጨረሻ
በሀዘን ሊከበብ - የህይወት መድረሻ
ያ ግርማህ ሊገለጥ - ያኔ ልትፈርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መዝገቡ ሲገለጥ ህይወቴ ሊነበብ
አንደበት ሲዘጋ አጽም ሲሰበሰብ
ዋይታ ዋጋ ሲያጣ ከንቱ ሲሆን ጩኸት
በጎቹ ከተድላ ፍየሎች ከእሳት
በሚጓዙበት ‘ ለት
በዚያ አስፈሪ ሰዓት
ኃጢአን በእንባ ብዛት - እጅግ ይጠቁራሉ
ጻድቃን ያለቅሳሉ - ክፉዎች ያነባሉ
ቅዱሳን መላእክት - ለሰው ልጆች ሲሉ
በዚያ ጭንቅ ሰዓት - ሁሉም ያለቅሳሉ፡፡
የሰማእታትን ደም - በከንቱ ያፈሰሱ
ጻድቃንን የገፉ - ንጹሃንን የከሰሱ
ስለነ አቤል ደም - መጥተህ ልትበቀል
ስለ ደሃ አደጎች - ሊሰማ የህይወት ቃል
ጉጉትና ፍርሃት - መንታ ሲሆንብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ይህንን እያወቅሁ - ዛሬን በማበሌ
ሳልሰንቅ ለጉዞ - ለሚሻለኝ ክፍሌ
“ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” - በሚል አንደበቴ
ሙሉ መስሎ ሲጓዝ - ባዶው እኔነቴ
“አይቴ ነበርከ?” ና “ምንተ ገበርከ” ስባል
ርዓዱን የሚያስተወኝ - ሳይኖረኝ አንድ ቃል
ሲታወሰኝ ዛሬ - ሲንቀጠቀጥ ጥርሴ - ልቤ እንዲርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
(አክሊሉ ደበላ በሰንበተ ክርስቲያን በእለተ ደብረ ዘይት 2007 ዓ.ም የተጫረ)


ለወንድማችን ለአክሊሉ ደበላ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

Sunday, July 31, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ስድስት

ከክፍል ሃያ አምስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
     በክፍል ሃያ አምስት የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ ባቀረብንላችሁ መሠረት ትልቅ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እንገምታለን፡፡
     ለዛሬው “ጌታሁን ደምፀ” የተባሉት የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ መምህር ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጻፉትንና፤July 29 2016 በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበኑንን ትምህርት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው ለእናንተ ለተዋህዶ ልጆች ማካፈል ስለፈለግን፤ ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡ይህ ጽሁፍ አጭር ግን ትልቅ ትምህርት ሰጪ በመሆኑና በተለይም በነሐሴ አንድ ቀን የእመቤታችንን የእርገቷን መታሰቢያ ጾም ለመጀመር በተዘጋጀንበት ወቅት የተላለፈ መልእክት በመሆኑ ከወዲሁ እራሳችንን እንድናዘጋጅ የሚያበረታታ ነው፡፡ጾሙን በተገቢው መንገድ ጾመን ከእመቤታችን በረከት እንድናገኝ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

Thursday, July 7, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ አምስት

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች”
ከክፍል ሃያ አራት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን›› በሚል በአራት ንዑሳን አርእስት ከፋፍለን ባቀረብነው አጭር ምላሽ፤የተሐድሶዎች የእምነት መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ከገለባ ቀሎ የተገኘ፤ከንቱ የማጭበርበሪያ ሰነድ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ እናምናለን፡፡በዚህ አጋጣሚ በነዚሁ አስመሳዮች (የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች) ከንቱ ስብከት ተወናብዳችሁ በየዋህነት እነሱን የምትከተሉ ሁሉ፤እባካችሁ የእግዚአብሔር ቃል መንፈስን ሁሉ መርምሩ እንጂ ዝም ብላችሁ አትመኑ ስለሚል ቆም ብላችሁ እንድታስቡና ወደ እውነተኛይቱ የተዋሕዶ ሃይማኖት እንድተመለሱ አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ለዛሬው የምናቀርብላችሁ የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡
ውድ አንባብያን! ምንም ጽሁፉ ረዘም ያለ ቢሆንም፤ ዓላማው እውነቱን ከሐሰት ለመለየትና ሁሉም እራሱን ከስህተት ትምህርት ለመጠበቅ እንዲችል ለማድረግ ስለሆነ፤መምህሩ ለመጻፍ ያልደከሙትን እኛ ለማንበብ መድከም ስለሌለብን፤ በትዕግስትና በጥንቃቄ አንብበን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ በማለት እያሳሰብን ወደ ቀጣዩ ትምህርታዊ ምላሽ እንመራችኋለን፡፡

መልካም ንባብ!