Tuesday, May 22, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አርባ አንድ

ከክፍል አርባ የቀጠለ፦

ለዚች ዕለትና ለዚች ሰዓት ያደረሰን የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡

       የተከበራችሁ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ ልጆች!የመጨረሻው ዘመን የወለዳቸው የተለያዩ መናፍቃን ከውስጥም ከውጭም ሆነው  የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችንን እምነት፣ ሥርዓትና እንዲሁም ትውፊት ሳይቀር የሚያፋለሱ የስህተት ትምህርቶች በቤተ ክርስቲያናችን ስም እያሰራጩና ብዙዎችንም እያሳሳቱ መሆኑን ወቅታዊውን የቤ/ክ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተል ሁሉ ችግሩን በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡እኛም ይህችን "ወልድ ዋሕድ" የተሰኘች የጡመራ መድረክ የጀመርንበት ዋናው ምክንያት፤እነዚህን የጨለማ ሥራዎቻቸውን /የምንፍቅና ትምህርታቸውን/ ወደ ብርሃን በማምጣት ማለትም ስህተታቸውን በመግለጥና አቅማችንና እውቀታችን በሚፈቅድልን መጠን  መልስ በመስጠት፤ ትውልዱ እራሱንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑን ከስህተቱ ትምህርት እንዲጠብቅ የሚያስችለውን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡
       እነዚህ የስህተት ትምህርቶች በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በምሥጢረ ሥጋዌ (ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ሰውን ያዳነበት ምሥጢር) ትምህርት ላይ ነው፡፡ይህንንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ባስተማረው ትምህርት (ማቴ.24 በሙሉ ይመልከቱ)፤በመጨረሻው ዘመን ብዙ ሐሰተኞች አስተማሪዎች በስሙ እንደሚመጡና ብዙዎችንም እንደሚያስቱ፤እኛም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሁሉ ከስህተት ትምህርታቸው እንድንጠበቅ አስጠንቅቆናል፡፡በመቀጠልም ይህንን የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ "ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ" ብሎ እሱ በመረጣቸው በሐዋርያትና በእነሱ እግር በተተኩ መምህራንም በየዘመኑ ለተነሳው ትውልድ ትምህርቱና ማስጠንቀቂያው ሲነገር የነበረ ወደፊትም እስከ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሲነገር የሚኖር ነው፡፡ይሁን እንጂ ስንቶቻችን ይህንን ችግር ተረድተናል? ምን ያህልስ እራሳችንንም ሆነ ሌላውን ከስህተት ለመጠበቅ ተዘጋጅተናል? የሚለውን ጥያቄ እራሳችንን እየጠየቅን ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁዎች መሆን ይገባናል፡፡
       ወደ ዋናው ነገር እንመለስና፤ እነዚህን የስህተት ትምህርቶች ከሚያስተላልፉት የእምነት ድርጅቶች አንዱ እራሱን "የእውነት ቃል አገልግሎት"ብሎ የሚጠራው የመናፍቃን ድርጅት ሲሆን፤ከመጽሐፍቻቸው አንዱ በሆነው ‹‹የአዲስ ኪዳን መካከለኛ» በተባለው መጽሐፋቸው በምሥጢረ ሥጋዌ ላይ የሚሰጡትን የክህደት ትምህርት በዚችው ጡመራ መድረክ ከክፍል ሦስት እስከ ክፍል አምስት ከብዙው በጥቂቱ ለማሳየት ሞክረናል፡፡ ይህ ድርጅት ቀድሞ ከእኛ ዘንድ በነበሩ ነገር ግን ከእኛ ወገን ስላልነበሩ በራሳቸው ፈቃድ በወጡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እምነት አራማጆች የተመሠረተ ሲሆን ድርጅቱ በ2004 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘ ነው፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን፤

       “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ” በማለት ሐዋርያው ቅ/ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕ.12 ቁጥር 9  በሰፊው አስተምሮናል፡፡በዚሁ መሠረት ዝግጅቱ የእኛ ባይሆንም፤ትክክለኛውን የተዋሕዶ ትምህርት የሚያስተምሩትን የሌሎች መምህራን ትምህርቶች ስናካፍላችሁ እንደነበር፤ዛሬም "ኢየሱስ ክርስቶስ ያማልዳል" (ሎቱ ስብሐት) እያሉ ለሚዘባርቁ የተለያዩ የውስጥም ሆነ የውጭ መናፍቃን ተገቢውን ምላሽ የሰጡበትንና "ፀረ-በጋሻው ደሳለኝ ፀረ-ተሀድሶ!" በተባለው የፌስ ቡክ ገጽ ለንባብ የበቃውን የመልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራውን ትምህርት እንዳለ አቅርበንላችሁዋል፡፡

መልካም ንባብ ከማስተዋል ጋር!

Thursday, April 5, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አርባ

ከክፍል ሰላሳ ዘጠኝ የቀጠለ፦
ዐቢይ ጾምን በሰላምና በጤና አስፈጽሞ ለዚች ቀንና ሰዓት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች!
ከዚህ በመቀጠል፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ስለ ሰው ልጆች ሲል ለሞት ተላልፎ የተሰጠባትን   ምሴተ ሐሙስን  በማስመልከት በወንድማችን በ"አክሊሉ ደበላ" የተዘጋጀች ድንቅ ግጥም አቅርበንላችኋል፡፡

Saturday, February 24, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ ዘጠኝ

ከክፍል ሰላሳ ስምንት የቀጠለ፦

የተከበራችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ልጆች!

እንኳን ለእናታችን ለወላዲተ አምላክ ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የቃል ኪዳን በዓል አደረሳችሁ አደረሰን፡፡

     ከዚህ በመቀጠል ስለ እመቤታችን ክብር ተናግረው የማይጠግቡት፤በተለይም ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን በመተርጎምና የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሁላችንም በየቤታችን እንድንሰማውና እንድንማርበት እንድንቀደስበትም በሲዲ አዘጋጅተው ያበረከቱልን መምህራችን ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ፤ የእመቤታችንን የኪዳነ ምሕረት በዓል በማስመልከት በማሕበራዊ ድረ-ገጽ ያስተላለፉትን ትምህርት ከዚህ ቀጥሎ አቅርበንላችኋል፡፡

Sunday, February 11, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ ስምንት

ከክፍል ሰላሳ ሰባት የቀጠለ፦
     የተወደዳችሁ አንባብያን! እንኳን የካቲት አምስት ቀን 2010 ዓ.ም ለምንጀምረው ዐቢይ ጾም  በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን፡፡
     ከዚህ በመቀጠል ስለ ዐቢይ ጾም መጠነኛ ግንዛቤ የምናገኝበት ትምህርት፤እንዲሁም በዐቢይ ጾም ውስጥ በሚውሉት ስምንት ሰንበታት  /እሑዶች/ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡትን ምንባባት በተመለከተ በዝርዝር አቅርበንላችኋልና በጥሞና እንድትከታተሉት እንጋብዛለን፡፡

Wednesday, January 17, 2018

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ ሰባት

ከክፍል ሰላሳ ስድስት የቀጠለ፦

የተወደዳችሁ አንባብያን! እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ መታሰቢያ በዓላት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ አደረሰን፡፡
     ሁላችንም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እንደምናውቀው፤ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፤ ንጽሕት ቅድስት ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፤በዚህ ዓለም በቆየባቸው ሰላሳ ሶስት ዘመናት ማለትም በመዋዕለ ሥጋዌው የፈጸማቸው ሥራዎች በሁለት ዐበይት ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡አንዱና ዋነኛው አዳምና ልጆቹ የተያዙበትን የበደል ዕዳ ዋጋ ከፍሎ /ቤዛ ሆኖ/ ነጻ ለማውጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለአብነት /ለአርአያነት/ ነው፡፡በቤዛነት ሥራው የሰው ልጅ ሊሳተፍበት ስለማይችል እሱ ብቻ የፈጸማቸው ናቸው፡፡ከነዚህ ውስጥ ከእመቤታችን በድንግልና መወለዱ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ በዚያ ተቀብሮ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤያችንን መደምሰሱ፣ በመጨረሻም በጽንስ የጀመረውን የቤዛነት ሥራ በመስቀል ላይ በመፈጸም የከፈለው ካሳ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡በሌላ በኩል እሱ ጾሞ እንድንጾም፣እሱ ጸልዮ እንድንጸልይ፣እሱ ሰግዶ እንድንሰግድ፣ እሱ ለችግረኞችና ለበሽተኞች እንደ አዘነላቸውና እንደረዳቸው እኛም እንዲሁ እንድናደርግ፤ በአጠቃላይ ተከተሉኝ ባለን መንገድ ሁሉ እንድንከተለው፤በአምላካዊ ቃሉ እንዲህ ሲል አስተምሮናል፤"….ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ…..! /ዮሐ.14፥15/ "....እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት…..."!  / ዮሐ.15፥12/፡፡አኛም የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች እስከሆንን ድረስ ትእዛዙን መፈጸም ይገባናል፡፡
     የተወደዳችሁ አንባብያን! የጌታችንን የልደቱን መታሰቢያ በዓል ታሕሳስ ሃያ ዘጠኝ ቀን አክብረን የጥምቀቱን በዓል ለማክበር እየተዘጋጀን ባለንበት ሰዓት፤ሁለቱንም በዓላት በማስመልከት ከማሕበራዊ ድረ-ገጽ ያገኘነውንና ለብዙዎቻችን ጥያቄ መልስ የሚሰጡንን ትምህርቶች ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡ልደቱን በተመለከተ "Ydidya Mesgana"የተባሉ፤ ጥምቀቱን በተመለከተ ደግሞ "ሊቀ ጉባኤ ጌታሁን ደምፀ" የተባሉት መምህር የሰጡትን ትምህርት፤ ጸሁፉን ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡

መልካም ንባብ! መልካም በዓል!

Friday, November 17, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ ስድስት

ከክፍል ሰላሳ አምስት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? 
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       የተከበራችሁ የዚች የጡመራ መድረክ ተከታታዮች፤ በክፍል ሰላሳ አምስት እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ብለው የሚጠሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤ እውነተኛ የተዋሕዶ አማኝ መስሎ ለመታየት የሚጠቀሙባቸውን ዋና ዋና የማሳሳቻ ስልቶች ማሳየታችን ይታወሳል፡፡በዚህ ክፍል ደግሞ የዘመነ ጽጌን ፍጻሜ ምክንያት በማድረግ ጥቂት ትምህርታዊ መልእክት አለችን፡፡

መልካም ንባብ!

Tuesday, November 14, 2017

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሰላሳ አምስት

ከክፍል ሰላሳ አራት የቀጠለ፦
የተወደዳችሁ አንባብያን! እንደምን ሰነበታችሁ? 
ለዚህ ዕለት ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ስሙ ይመስገን፡፡
       የተከበራችሁ የዚች የጡመራ መድረክ ተከታታዮች፤ በክፍል ሰላሳ አራት እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ›› ብለው የሚጠሩት አጽራረ ቤተ ክርስቲያን፤ እውነተኛ የተዋሕዶ አማኝ መስሎ ለመታየት የሚጠቀሙባቸውን የማሳሳቻ ስልቶች ለማሳየት መግቢያውን ጀምረን  በይቀጥላል ባቆየነውን መሠረት፤ እነሆ በዚህ ክፍል ዋና ዋናዎቹን ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
መልካም ንባብ!