Wednesday, September 14, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሰባት

 ከክፍል ሃያ ስድስት የቀጠለ

የተከበራችሁ  የዚች ጦማር ታዳሚዎች ምእመናን!

     ሁላችንም እንደምናውቀው ስለዚህ ስለ መጨረሻው ዘመን አስከፊነት አስቀድሞ በነቢያት፣ከዚያም በጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው፣እንዲሁም በጌታችን ደቀ መዛሙርትና ከነሱም በመቀጠል በየዘመኑ በተነሱ ቅዱሳን አባቶችና በሊቃውንት በሰፊው ሲነገር ኖርዋል፤አሁንም እየተናገሩ ነው፡፡በተለይም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ቁ.1-ፍጻሜ የተነገሩት የዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶች አሁን በእኛ እድሜ በስፋት እየተፈጸሙ እንመለከታለን፡፡የቀደሙት ቅዱሳን ከዚህ ዘመን እንዳይደርሱ፤ከእህል ውሃውም እንዳይቀምሱ፤ አጥብቀው በመጸለያቸው ምኞታቸው ተፈጸሞላቸው በሰላም ከዚህ ዓለም ተሰናብተዋል፡፡ ስለሆነም እኛም ክርስቲያኖች የዚህ የክፉ ትንቢት መፈጸሚያዎች እንዳንሆን ህገ እግዚአብሔርን ማወቅና ከክፉ ነገር መጠበቅ ብሎም የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

ክቡራን አንባብያን!

     ስለ ዘመኑ ፍጻሜ ምልክቶችና ጌታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማሳለፍ በሚመጣበት ጊዜ ስለሚሆነው ንውጽውጽታ "አክሊሉ ደበላ" የተባሉ ወንድማችን በማህበራዊ ደረ-ገጽ በግጥም ያስተላለፉትን እጅግ በጣም አስተማሪ ጸሁፍ ለሁላችንም ጠቃሚ ስለሆነ እንድተመለከቱ እንጋብዛለን፡፡

መልካም ንባብ!

Aklilu Debela

***ና ልበል: አትምጣ??***

ተልከው ነፋሳት - ምድርን ሲያናውጡ
የክፋት ነቢያት - ካሉበት ሲወጡ
መንግስት መንግስት ላይ - ህዝብም በህዝብ ላይ
ድንጋይም በድንጋይ - ተደርምሶ ሲታይ
የደስታ ካብ ሁሉ - ሲናድ ከሰዎች ልብ
የጸጥታ ስፍራ - በክፋት ሲከበብ
ያላሰብኩት ሆኖ - ያልኩት ሲቀርብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መቃረቡ ሲሆን - የትንቢት ፍጻሜ
ሰማይና ምድር - የሚያልፉበት እድሜ
የጸሃይዋ መጥለቅ
የብርሃኗ መራቅ
ይሆናል ያልተባለው - መሆኑ ሲታወቅ
ሰማይ ሲጠቀለል - ከዋክብት ሲረግፉ
የዓለም ኩሬዎች ሁሉ - ሲዘጉ ሲነጥፉ
“ዓለም!” “ዓለም!” ያሉት - ሲሆኑ መና ዎና
የምናያት ምድር - እንዳልሆነች ሆና
ባዶነት ሲወረኝ - ተስፋ ሲጠፋብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
የቁጣ ነፋሳት - ከአዜብ ሲለቀቁ
መድረሻ ጠፍቶአቸው - የቆሙት ሲወድቁ
ዙሪያው ሲጨላልም - ሲዘጋጋ መንገድ
ከምስራቅ ሲሰማ - አስፈሪው ነጎድጓድ
ሲያይሉ መባርቅት - መለከት ሲነፋ
የነበረው ሲተን - የሞለው ሲጠፋ
ሰላሜ ሲታወክ - ጭንቁ ሲመጣብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ኀሳዊያን ደቂቃን - ኀሳዊ መምህር
ኀሳዊ ክርስቶስ - የሀሰት ደቀመዝሙር
ሲበዛ በዓለም - ሲበረክት በደጅ
በተዓምር ጨረቃን - የጨበጠው በእጅ
በቅዱሱ ስፍራ - ሲፈስ የንጹህ ደም
ሽሽት ክረምት ሲሆን - የኃላው ሲቀድም
በሰንበት መሰደድ - ሲሆን መጨረሻ
በሀዘን ሊከበብ - የህይወት መድረሻ
ያ ግርማህ ሊገለጥ - ያኔ ልትፈርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
መዝገቡ ሲገለጥ ህይወቴ ሊነበብ
አንደበት ሲዘጋ አጽም ሲሰበሰብ
ዋይታ ዋጋ ሲያጣ ከንቱ ሲሆን ጩኸት
በጎቹ ከተድላ ፍየሎች ከእሳት
በሚጓዙበት ‘ ለት
በዚያ አስፈሪ ሰዓት
ኃጢአን በእንባ ብዛት - እጅግ ይጠቁራሉ
ጻድቃን ያለቅሳሉ - ክፉዎች ያነባሉ
ቅዱሳን መላእክት - ለሰው ልጆች ሲሉ
በዚያ ጭንቅ ሰዓት - ሁሉም ያለቅሳሉ፡፡
የሰማእታትን ደም - በከንቱ ያፈሰሱ
ጻድቃንን የገፉ - ንጹሃንን የከሰሱ
ስለነ አቤል ደም - መጥተህ ልትበቀል
ስለ ደሃ አደጎች - ሊሰማ የህይወት ቃል
ጉጉትና ፍርሃት - መንታ ሲሆንብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
ይህንን እያወቅሁ - ዛሬን በማበሌ
ሳልሰንቅ ለጉዞ - ለሚሻለኝ ክፍሌ
“ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!” - በሚል አንደበቴ
ሙሉ መስሎ ሲጓዝ - ባዶው እኔነቴ
“አይቴ ነበርከ?” ና “ምንተ ገበርከ” ስባል
ርዓዱን የሚያስተወኝ - ሳይኖረኝ አንድ ቃል
ሲታወሰኝ ዛሬ - ሲንቀጠቀጥ ጥርሴ - ልቤ እንዲርድብኝ
ቶሎ ና ልበልህ - ወይስ አትምጣብኝ?
(አክሊሉ ደበላ በሰንበተ ክርስቲያን በእለተ ደብረ ዘይት 2007 ዓ.ም የተጫረ)


ለወንድማችን ለአክሊሉ ደበላ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን፡፡

Sunday, July 31, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ስድስት

ከክፍል ሃያ አምስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
     በክፍል ሃያ አምስት የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ ባቀረብንላችሁ መሠረት ትልቅ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እንገምታለን፡፡
     ለዛሬው “ጌታሁን ደምፀ” የተባሉት የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ መምህር ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጻፉትንና፤July 29 2016 በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበኑንን ትምህርት በጣም ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘነው ለእናንተ ለተዋህዶ ልጆች ማካፈል ስለፈለግን፤ ጽሁፉ ለንባብ እንዲመች ከማስተካከል በስተቀር በሃሳቡ ላይ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡ይህ ጽሁፍ አጭር ግን ትልቅ ትምህርት ሰጪ በመሆኑና በተለይም በነሐሴ አንድ ቀን የእመቤታችንን የእርገቷን መታሰቢያ ጾም ለመጀመር በተዘጋጀንበት ወቅት የተላለፈ መልእክት በመሆኑ ከወዲሁ እራሳችንን እንድናዘጋጅ የሚያበረታታ ነው፡፡ጾሙን በተገቢው መንገድ ጾመን ከእመቤታችን በረከት እንድናገኝ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

Thursday, July 7, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ አምስት

“የቅብአት ምንፍቅና መደበቂያ ካባዎች”
ከክፍል ሃያ አራት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን›› በሚል በአራት ንዑሳን አርእስት ከፋፍለን ባቀረብነው አጭር ምላሽ፤የተሐድሶዎች የእምነት መግለጫ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ከገለባ ቀሎ የተገኘ፤ከንቱ የማጭበርበሪያ ሰነድ መሆኑን እንደተገነዘባችሁ እናምናለን፡፡በዚህ አጋጣሚ በነዚሁ አስመሳዮች (የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች) ከንቱ ስብከት ተወናብዳችሁ በየዋህነት እነሱን የምትከተሉ ሁሉ፤እባካችሁ የእግዚአብሔር ቃል መንፈስን ሁሉ መርምሩ እንጂ ዝም ብላችሁ አትመኑ ስለሚል ቆም ብላችሁ እንድታስቡና ወደ እውነተኛይቱ የተዋሕዶ ሃይማኖት እንድተመለሱ አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
ለዛሬው የምናቀርብላችሁ የ "ቅብአት" እምነትን በተመለከተ “መልካሙ በየነ” የተባሉ የተዋሕዶ ልጅ፤ ከእነዚሁ የ "ቅብአት"እምነት ተከታዮች ከሆኑት በአንዱ ለተዘጋጀ "ወልደ አብ" ለተባለው የክህደት መጸሐፍ የሰጡትን፤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያስነበቡንን፤ በአስር ክፍሎች የተዘጋጀ ምላሽ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አቅርበንላችኋል፡፡
ውድ አንባብያን! ምንም ጽሁፉ ረዘም ያለ ቢሆንም፤ ዓላማው እውነቱን ከሐሰት ለመለየትና ሁሉም እራሱን ከስህተት ትምህርት ለመጠበቅ እንዲችል ለማድረግ ስለሆነ፤መምህሩ ለመጻፍ ያልደከሙትን እኛ ለማንበብ መድከም ስለሌለብን፤ በትዕግስትና በጥንቃቄ አንብበን ክርስቲያናዊ ግዴታችንን እንድንወጣ በማለት እያሳሰብን ወደ ቀጣዩ ትምህርታዊ ምላሽ እንመራችኋለን፡፡

መልካም ንባብ!

Monday, June 27, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ አራት

"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል አራት)
ከክፍል ሃያ ሦስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሦስት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሦስተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡በገባነው ቃል መሠረት አሁን አራተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሦስት

"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሦስት)
ከክፍል ሃያ ሁለት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
     ‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል ሃያ ሁለት ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ ሁለተኛውን ክፍል ተመልክተን በይደር አቆይተነው እንደነበር ይታወሳል፡፡አሁን በገባነው ቃል መሠረት ሦስተኛውን ክፍል እንቀጥላለን፡፡በመግቢያችንና ቀደም ባሉት ክፍሎች እንደገለጽነው “የእምነት መግለጫ” ሰነዳቸው ብዙ የዋሃን ምዕመናንን ለማሳሳት  በተንኮል የተቀናበረ በመሆኑ ከቃላት አጠቃቀማቸው ጀምሮ ለእያንዳንዱ አንቀጽ መልስ ያስፈልገው ነበር፡፡ሆኖም የእነሱን አካሄድ ተከትለን ብንሄድ፤የእኛንም ሆነ የአንባብያንን ብዙ መልካም ሥራዎችን የምንሰራበትን ጊዜና አእምሮ በከንቱ ማባከን ስለሆነ በጣም ጎላ ብለው የሚታዩት ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡

የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሁላችንም እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡

Monday, June 13, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ ሁለት

  "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!(ንዑስ ክፍል ሁለት)
ከክፍል ሃያ አንድ የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
     ‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር በክፍል አስራ ዘጠኝ ‹‹"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ"  በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን››በሚል ንኡስ ርዕስ መግቢያውን ተመልክተን በይደር አቆይተን፤ በክፍል ሃያ ደግሞ "ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ" የተባለች እህታችን ስለ ተሐድሶ መጠነ ሰፊ ስህተቶች የጻፈችውን አስነብበናችሁ፤እንዲሁም በክፍል ሃያ አንድ "እምነ ጽዮን" ከተባለው ብሎግ ያገኘነውን ጠቃሚ ዘገባ አስነብበናችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡
     ሁላችንም የተዋህዶ ልጆች እንደምናውቀውና እኛም ይህንን የመወያያ መድረክ(ወልድ ዋሕድን)ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ለማስገንዘብ እንደሞከርነው፤ እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ›› ብለው የሚጠሩት መናፍቃን፤ኑፋቄያቸው ከተለያዩ የፕሮቴስታንት የእምነት ድርጅቶች የተውጣጣ መሆኑ እየታወቀ፤ ልክ ጠላታችን ሰይጣን ሰውን ለማሳሳት የብርሃን መልአክ መስሎ እንደሚታይ ሁሉ፤እነሱም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ ለመምሰል የማያምኑበትን የተለያየ ሥርዓት ሲፈጸሙ ይታያሉ፡፡(በእምነት ለሚቀበሉት የሚያድን እሳት፤ሳያምኑበት ለሚቀበሉት የሚባላ እሳት የሆነውን ቅዱስ ቁርባንን በድፍረት እስከ መቀበል ድረስ!)
አሁን ወደ ጥንት ነገራችን ተመልሰን፤ ስለ "ተሐድሶ የእምነት መግለጫ" ቀጣዩን  ክፍል  እንዳስሳለን፡፡(ክፍል ሁለት)
     ቀደም ብለን በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፤ የዚህ መልእክታችን ዋና ዓላማ እነዚህ ተኩላዎች የለበሱትን የበግ ለምድ ገፎ ተኩላነታቸውን ለማሳየት ያህል እንጂ እነርሱ ሥራ ፈትተው ሌላውን ሥራ ለማስፈታት ለጻፉት እርስ በርሱ ለሚጣረስ "መግለጫቸው"ለእያንዳንዱ አንቀጽ መልስ ለመስጠት ባለመሆኑ አለፍ አለፍ እያልን የተወሰኑትን ብቻ እንመለታለን፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር እውነትን እንድናስተውል አእምሯችንን ያብራልን፡፡

የ"ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" አጠቃላይ ይዘት፤

ሀ/ የእምነት መግለጫቸውን እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ለማስመሰል የተጠቀሙባቸው የማጭበርበሪያ ስልቶች፤
1/ በአሁኑ ዘመን ለቋንቋ ጥናትና ለምርምር ሥራ ካልሆነ በስተቀር ከኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ውጪ የግዕዝ ቋንቋ የሚጠቀምበት እንደሌለ ማንም የማይክደው ሲሆን እነሱ ግን  ይህንን የግዕዝን ቋንቋ መጠቀማቸው አንዱ የዋሃንን የማደናገሪያ ስልት ነው፡፡
2/ "መክሥተ አርእስት" ብለው የጠቀሱት፦ጸሎተ ሃይማኖት፣አመክንዮ ዘሐዋርያት፣የተለያዩ ቅዱሳን አባቶች የሃይማኖት ውሳኔዎች፣የቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤያት፣የቤ/ክ ታሪክ፣አዋልድ መጻሕፍት፣መጻሕፍተ ሊቃውንት፣ገድላት ድርሳናትና ተአምራት፣ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን፣ነገረ ቅዱሳን፣ነገረ ማርያም፣…በማለት በአርእስትነት የተጠቀሙባቸው ቃላትና ክፍለ ትምህርቶች በሙሉ ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤ/ክ በስተቀር ተሐድሶን ጨምሮ በየትኛውም የእምነት ድርጅት የማይታመንባቸው መሆኑ እየታወቀ፤ እነሱ ግን ያው ዓላማቸው መስሎ ለማሳሳት ስለሆነ እነዚህን ቃላት ተጠቅመው ጽፈዋል፡፡ሆኖም በእያንዳንዱ ርእስ ሥር የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ ምን ያህል የተሳሳተ እንደሆነ ወደ ዝርዝሩ ስንገባ የምናየው ይሆናል፡፡
3/ ተሐድሶዎች የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክንን እምነት፤ሥርዓትና ትውፊት እየተቃወሙ፤ነገር ግን "እናት ቤተ ክርስቲያናችን" እያሉ ስሟን ያለ አገባብ /ለማስመሰል/ እየጠቀሱ መጻፋቸው ነው፡፡
     እዚህ ላይ አንባቢ እንዲፈርድ፤ እነሱ በዚሁ የእምነት መግለጫቸውም ሆነ በየ ድረ-ገጾቻቸው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚሳደቡበትን አጸያፊ ቃላት መጥቀስ ይቻል ነበር፡፡እኛ ግን ለቤተ ክርስቲያናችን ክብር ስንል መጻፍ አንፈልግም፡፡ስድብን በተመለከተ በመጨረሻው ዘመን የሚነሱ አሳቾች በአውሬ በተመሰለው በዲያቢሎስ መንፈስ እየተመሩ እግዚአብሔርንና ማደሪያውን እንደሚሳደቡ በወንጌላዊው ዮሐንስ የተነገረውን ትንቢት በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 13 የተመዘገበውን ስንመለከት፤ተሐድሶዎቹ በገዛ እራሳቸው የዲያቢሎስ የግብር ልጆች መሆናቸውን መስክረዋል፡፡

ለ/ የእምነት መግለጫቸውን ያዘጋጁበት ምክንያት፦

ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 11 መግቢያ የተወሰደ፦"በልዩ ልዩ ምክንያቶች በማንነት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው የተሐድሶ አገልግሎት አንዱ ጉድለትም ይህ ነው የሚባልና ወጥ የሆነ ኹሉም በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ የሚቀበሉት የእምነት መግለጫ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ይህንን ክፍተት ለመሙላት በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ይህንን የእምነት መግለጫና በዚያ ላይ የተመሰረተውን አስተምህሮና ሌሎች ከእንቅስቃሴው ጋር ሊገናኙ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ የያዟቸውን አቋሞች ያካተተውን ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓቸዋል፡፡"
የተዋህዶ ልጆች እዚህ ላይ ልብ በሉልኝ!
ከዚህ በላይ በተመለከትነው የእምነት መግለጫቸው እንደገለጹት፦
1/ እነሱ ለእራሳቸው የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጥተው አእምሯቸው /አስተሳሰባቸው/ የተቃወሰባቸው መሆኑን እየነገሩን ነው፡፡ ታዲያ "እራሷ ክርስትና ሳትነሳ ልታቋቁም ሄደች" የሚለው ተረት  አይስማማቸውም?
2/ እንደነሱ አባባል፤ በማንነት ቀውስ ውስጥ ከሚገኘው የተሐድሶ  እንቅስቃሴ ከብዙ ጉድለቶቹና ክፍተቶቹ አንዱ የእምነት መግለጫ ያልነበረው መሆኑ ሲሆን፤ይህም የተዋህዶን ሃይማኖት ከማጥፋት በስተቀር  እውነተኛና ጠቃሚ መንፈሳዊ ትምህርት ይዘውና አቅደው እንዳልተነሱ ያረጋግጣል፡፡ለመሆኑ በራሱ ጉደለትና ክፍተት ያለበት "እምነት" ይዘው ነው ስንዱዋን እመቤት  ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚቹት? በእውነቱ እራስን አለማወቅ ትልቅ ድንቁርና ነው!
3/ ከአሁን በፊት "ተሐድሶ የሚባል የለም እነ እንትና የፈጠሩት ወሬ ነው" ሲሉ እንዳልነበር፤ዛሬ ማጣፊያው ሲያጥራቸው የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን በራሳቸው አንደበት መናገራቸው፤ ከጥንቱም የድርጅታቸው መሠረቱ ሐሰት/ውሸት/ መሆኑንና ዓላማቸውም ከግብር አባታቸው ከሐሰት አባት ከዲያቢሎስ የተወረሰ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡
4/  "ኹሉም በእንቅስቃሴው ውስጥ የሚገኙ …"የሚለው አባባል በመካከላቸው የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች እንዳሉ ያመለክታል፡፡ነገር ግን እንደ ወንጌሉ ቃል እርስ በእርሱ የተለያየ መንግስት አይጸናም፡፡

ሐ/ እነዚህ የውስጥ መናፍቃን /ተሐድሶዎች/ ከነባሮቹም ሆነ በየጊዜው ከሚፈበረኩት የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ጋር ተባባሪ ስለመሆናቸው፤

ማስረጃ፦ ከሰነዳቸው ገጽ 5/የተወሰደ፦ "……ቤተ ክርስቲያን ራሷን በእግዚአብሔር ቃል እንድትመረምርና ከዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድትወጣ በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጭም ልዩ ልዩ ተሐድሷዊ ጥሪዎች ሲተላለፉ ኖረዋል፡፡አሁንም እየተላለፉ ይገኛሉ፡፡በታሪክ ከሚጠቀሱት መካከልም በዋናነት ከውስጥ በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ፤ ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን ቀርቦ የነበረውን ትችት መጥቀስ ይቻላል፡፡…"

ማስገንዘቢያ፤አንባብያን እዚህ ላይ ልብ እንበል!

1/ ከውስጥ በአባ እስጢፋኖስና በደቀ መዛሙርቱ የተላለፈውን የተሐድሶ ጥሪ መቀበል ነበረባት፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ  ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ ገጽ 49 እንዲህ ይነበባል፦
 "የቤተ ክርስቲያናችን ስነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብን ያስፋፉት፣አምልኮ ጣኦትን ከምድረ ኢትዮጵያ ጨርሶ ለማጥፋት የታገሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ናቸው፡፡ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የነገሡት በ1444-1468 ዓ.ም ነው፡፡ከዚህም ሌላ በዘመናቸው ዜና መዋዕላቸው እንደሚለው ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ስግደት አይገባም የሚሉ መናፍቃን እንደ ተነሱ ይጽፋል፡፡ይኸው ዜና መዋዕል እንደሚለው እነዚህን መናፍቃን ንጉሡ ባሉበት ሊቃውንቱ ተከራክረው ረቷቸው፡፡……"
 2/ከውጭ ደግሞ በኢየሱሳውያን የቀረበውን ትችት መቀበል ነበረባት፤ ፤ ስላሉት
መልስ፦በብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ  ካልዕ የተዘጋጀው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ" መጸሐፍ ገጽ 57-59 እንዲህ ይነበባል፦
"ኢየሱሳውያን የሚባሉት ካቶሊኮች ተንኮል ውስጥ ውስጡን ሲሔድ ቆይቶ በይፋ የተከሰተው በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡/1607-1632/ ጴጥሮስ ፓኤዝ እንደ አንድርያ ኦቢያዶ ግትር ሳይሆን በጣም ፈሊጠኛ ነበር፡፡የሀገሪቱን የአምልኮት ማቅረቢያ ቋንቋ ግዕዝ ተምሮ ይሰብክ፤ ይቀድስ ነበር፡፡ወደ ንጉሡ እየቀረበ የሮማ ካቶሊክን እምነት ቢቀበሉ የፖርቱጋል መንግሥት የጦር መሣሪያ ያስታጥቅዎታል እያለ ይሰብካቸው ነበር፡፡…ዐፄ ሱስንዮስ በ1622 ዓ.ም በጴጥሮስ ፓኤዝ እጅ ከነቤተሰቦቻቸው በሮማ ካቶሊክ ሥርዓት ተጠምቀው ካቶሊክነታቸውን አስታወቁ፡፡ (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 57)…ዐፄ ሱስንዮስ በነገሡ በ27ኛው ዓመት ታመው አንደበታቸው ተዘጋ፤…የገዳማቸው መነኮሳት….ሦስት ሱባኤ በጸሎት በምህላ ቆይተው ጸበል አጠመቋቸው በዚህ ጊዜ የተዘጋ አንደበታቸው ተፈታ…፡፡" (የኢ/ቤ/ክ ታሪክ ገጽ 59)
     እንግዲህ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መቀበል ነበረባት እያሉ እንደ አብነት የጠቀሷቸው ከላይ የተመለከትናቸውን "ለእመቤታችንና ለቅዱስ መስቀል ስግደት አይገባም" ይሉ የነበሩትን የውስጥ መናፍቃን ደቂቀ እስጢፋን/እስጢፋኖስን/፤ ከውጭ ደግሞ ኢየሱሳውያን የተባሉትን የካቶሊክ መልክተኞችን ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ሃይማኖትን ብቻ ሳይሆን አገርንም ጭምር ለማጥፋት የተሰለፉ ነበሩ፡፡እንግዲህ የዛሬዎቹ "ወንጌላውያን" ነን ባዮች /ተሐድሶዎች/ በጥቂቱ 500 አመታትን ያስቆጠረውን፤ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ኩራት፤ለመናፍቃን እፍረት፤የሆነውንና በዚያን ጊዜ ቅዱሳን አባቶች በቂ መልስ ሰጥተውና በእግዚአብሔር ቃል እረትተዋቸው የዘጉትን ታሪክ እያስታወሱ፤ አሁንም በድፍረት ይህንኑ የጥፋት መልእክት ተቀበሉ እያሉ የሚወተውቱት፤ እውነትም በማንነት ቀውስ ውስጥ ቢሆኑ አይደል እንዴ?
ሌላው ቢቀር!
1/ ዐፄ ሱስንዮስ በካቶሊክ ሥርዓት ሲጠመቁና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን ሲያውጁ አንደበታቸውን የዘጋውን፤
2/ ተጸጽተው ንስሃ ሲገቡ ደግሞ በአባቶች ጸሎትና በጸበል ተጠምቀው ወደ ቀደመ ጤንነታቸው የመለሳቸውን፤
3/ በዚህም የተዋህዶ ቤ/ክ በእግዚአብሔር ወልድ ደም የተመሰረተች በመሆኗ ያረጋገጠበትን፤
4/ በአጠቃላይ ከዚችው ከአንዲቱ ተዋህዶ በስተቀር ሌላው ሁሉ ከንቱ መሆኑ፤/በክርስትናው ዓለም ውጭ ያሉትን አይጨምርም/

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በድንቅ  ተአምራት የመሰከረውን እውነት መቀበል አለመቻላቸው፤ አይነ ህሊናቸው የታወረና "እምነት" ብለው የያዙትም መንገድ/ተሐድሶ/ ከእውነት የራቀ ለመሆኑ ሌላ ምስክር አያሰፈልገውም፡፡

ውድ አንባብያን! የተሐድሶ ጉድ በዚህ ብቻ አያበቃም ገና ብዙ አስቂኝ ነገር አለ፡፡!
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በሌላ ጊዜ እንቀጥላለን፡፡
እናንተም ከጾምና ከጸሎት ጋር በትዕግስት ጠብቁን፡፡
"ንቁ ! በሃይማኖት ቁሙ!"
የዘወትር መልእክታችን  ነው፡፡!

Monday, June 6, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ አንድ

     የተከበራችሁ የዚህ ድረ ገጽ (ወልድ ዋሕድ) ተከታታዮች! እንደምታውቁት የእኛ ዓላማ  የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት ጠብቀን ሌላውም እንዲጠብቅ የአቅማችንን መልእክት ማስተላለፍ ነው፡፡ስለሆነም ለዛሬው www.emenetsion.blogspot.com በተባለው ድረ ገጽ ላይ ያገኘነውን ጥልቅ መልእክት ያዘለ ጽሁፍ በማስተዋል እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡
መልካም ንባብ!!!
 ን ዝም አልልም ”  ክፍል ሰባት
ክፍል ስድስት የቀጠለ
የተወደዳችሁ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች፣
     ይህንን "እምነ ጽዮን" ብለን የሰየምነውን የመወያያ መድረክ ስንጀምር “ጆሮ ያለው መሰማትን ይስማ”  በሚል ርዕስ ፤በአራት ተከታታይ ክፍሎች፤ እንዲሁም "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በስድስት ተከታታይ ክፍሎች፤ ባቀረብነው ጽሁፍ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ሃይማኖታችንን በበላይነት የሚመሩት ክፍሎች እያደረሱ ያለውን ጥፋት በማሳየት ከእኛስ ምን ይጠበቃል በሚል ማጠቃለያ ሰፊ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡አንባብያን ሀሳቡን በጥሞና እንድትከታተሉት በማሰብና ዛሬ ለምንወያይበት ርዕስም አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው "ማንም እንዳያስታቸሁ ተጠንቀቁ"በሚለው ርዕስ በክፍል አራት ያቀረብነው ጥሁፍ እንዳለ አምጥተነዋል፡፡

Saturday, May 21, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል ሃያ

የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
በክፍል አስራ ዘጠኝ ጽሁፋችን "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን! በሚል ርዕስ ጀምረን በይቀጥላል እንዳቆየነው ይታወሳል፡፡ ክፉውን ነገር እንድንጸየፍ ከበጎ ነገር ጋር እንድንተባበር ከቅዱሳት መጻሕፍት በተማርነው መሠረት ‹‹ቲጂ የተዋህዶ ልጅ ተዋህዶ››የተባለች እህታችን በface book ያስተላለፈችው ትምህርት የእኛም መልእክት ስለሆነ ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡

Sunday, May 1, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤16 ክፍል አስራ ዘጠኝ

   “ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡ማቴ.716 ክፍል አስራ ዘጠኝ
 "ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ የእምነት መግለጫ" በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን!
ከክፍል አስራ ስምንት የቀጠለ
የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር ከክፍል አንድ እስከ ዘጠኝ ባስነበብነው ጽሁፍ፤የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ፈተና የሆኑትን እራሳቸውን ‹‹ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ››ብለው የሚጠሩትን የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን የጥፋት ተልእኮ ለማሳየት ሞክረናል፡፡የእኩይ ሥራቸው መራራ ፍሬዎች ከሆኑት መጻሕፍቶቻቸውም መካከል ‹‹የአዲሰ ኪዳን መካከለኛ» የተባለው መጽሐፍ በመጽሐፍ ቅዱስ ሲመዘን ቀሎ የተገኘ /ከፍሬው ገለባ/ መሆኑንም መጽሐፍ ቅዱስን ምስክር አድርገን አሳይተናል፡፡እንዲሁም

Friday, April 29, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ ስምንት

ከክፍል አስራ ሰባት የቀጠለ

የተከበራቸሁ አንባብያን!
     በዚህ የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡እንዲሁም በክፍል አስራ ስድስትና አስራ ሰባት ደግሞ "Bini Zelideta" ከተባሉ ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ የእኛም ሃሳብ ስለሆነና ትልቅ መልእክት የሚያስተላልፍ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አስነብበናችኋል፡፡አሁንም ከዚህ በመቀጠል "Blni Zelideta" መዝሙርን በተመለከተ የጻፉትን ክፍል ሦስትና ማጠቃለያውን እንድታነቡ እየጋበዝን፤ጉዳዩ ይመለከተናል የምንል ሁላችንም በዚህ ጽሁፍ ላይ በምናገኘው መልእክት መሠረት ችግሩን ከማስወገድ አኳያ የየድርሻችንን መልካም ስራ እንድናበረክት ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
መልካም ንባብ!

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ ሰባት

ከክፍል አስራ ስድስት የቀጠለ

የተከበራቸሁ አንባብያን!
በዚህ የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡እንዲሁም በክፍል አስራ ስድስት ደግሞ "Bini Zelideta" ከተባሉ ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ ጥሩ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ አስነብበናችኋል፡፡አሁንም ከዚህ በመቀጠል  ደግሞ የ"Blni Zelideta"ን ክፍል ሁለት መዝሙር ነክ ጽሁፍ አቅርበንላቸኋል!!!
መልካም ንባብ!

Sunday, March 27, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ ስድስት

ከክፍል አስራ አምስት የቀጠለ
የተከበራቸሁ አንባብያን!
በዚህ የመወያያ መድረክ (ወልድ ዋሕድ) ክፍል ስድስትና ሰባት ቤተ ክርስቲያናችን በመዝሙር በኩል እየገጠማት ያለውን ፈተና በማስመልከት ባቀረብነው ጽሁፍ መጠነኛ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ እናምናለን፡፡ከዚህ በመቀጠል ደግሞ "Bini Zelideta" ከተባሉ ወንድማችን ከፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያገኘነውን ጽሁፍ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘነው እንድታነቡት እንጋብዛለን፡፡
መልካም ንባብ!
Bini Zelideta
የተሃድሶ መናፍቃን መዝሙራት ሥውር ተልዕኮ!”
ክፍል-1 (ስለ ነገረ ክርስቶስ) /መልዕክቱ የረዘመው ግጥሞች ስለበዙበት ነው/
መግቢያ
ቅድስት፤ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖታችን ዕረፍት አልባ ዘመናትን ስታሳልፍ ዛሬ 2008 ዓመቷ ነው፡፡ ፈተናዎቿም እንደየ አዝማናቱና እንደፈታኞቿ የተለያዩ ነበሩ፡፡ ሠይፍ፣የዐላውያን መከራ፣የአናብሥት ትግል፣የክርስቲያኖች ስቃይ የሮም ኮሎሲየም አምፊ ቴአትር ትርዒት፣የቁም እሳት ቃጠሎ፣የካታኮምቡ ሕይወት፣የሠንሠለት ኑሮ እና የመንኩራኩር ስቃይ የመጀመሪያው እልህ አስጨራሽ ፈተናዋ ሲሆን እግር ተከትሎ፤ዓይነቱን ቀይሮ የመጣው የአርዮሳውያን ሃይማኖትን የመቀየር፣አስተምሕሮዋን የመበረዝ እንቅስቃሴ ጣሯን፣ሰቀቀኗን፣መከራዋን አብዝቶባት ቆይቷል፡፡ ዮዲት ጉዲት፣የካቶሊክ ሚሲዮናውያን፣ጽንፈኛ አሕዛቦችና የሉተር ርዝራዦች ዞረው ዞረው ሲሻቸው አንድ ላይ ሲሻቸው ደግሞ በፍርርቅ በመከረኛይቱ ሃይማኖት ላይ ቀንበር ሲጭኑ ኖረዋል ዛሬም ዕረፍት የላትም! የገሃነም ደጆች አይችሉአትም ተብሎ ስለተጻፈው አማናዊ ቃል ሁሉን አልፋ ዛሬ ብትደርስ ለሆዳቸው ያደሩ ሥጋውያን አስተምህሮዋን እናድሳለን ብለው ተነሡባት፡፡ ይህ ከቀደምት ዘመናት በዓይነትም በቅርጽም አካሄዱን ቀይሮ ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ሥልት ይዞ የተነሣው ፕሮቴስታንታዊ ቡድን ስውር ተልዕኮውን በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ በመሰንዘር ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል አሁንም በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ቅብ ይዘው፣ተቆርቋሪ መስለው መንገዷን ስታለች፣አስተምህሮዋ ልክ አይደለም፣አርጅታለች፣እናድሳታለን ባዮች ሲሆኑ በትምርቶቻቸው እና ከዘፈን በተቃኙ መዝሙሮቻቸው ትውልድን መበረዝ የዕለት እንጀራቸው አድርገውታል፡፡ በተለይም መዝሙሮቻቸው በአንድ ሌሊት ተደርሰው ንጋቱን ለጆሮ ስለሚበቁ ኑፋቄን ለማሰራጨት ደገኛ መሣሪያቸው ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ አምስት

ከክፍል አስራ አራት የቀጠለ
"እያወቁ ማለቅ"
"ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፤
እያወቁ ማለቅ መጣ በሰዓቱ፡፡"
     በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ሁሉን ቻይ ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር እውቅና እና ፈቃድ ውጪ የሚከናወን ምንም ነገር እንደሌለ ይታወቃል፡፡ይታመናልም፡፡ይሁን እንጂ  ለስሙ ክብር ምስጋና ይግባውና አምላካችን እግዚአብሔር ሰውን ከሌሎች ፍጡራን ለይቶ በመልኩና በምሳሌው ሲፈጠረው የማሰብ፣የመናገርና ሕያው ሆኖ የመኖር ዕድል ሰጥቶታል፡፡የሰው ልጅ በዚህ በተሰጠው አእምሮ መመራት አቅቶት በኃጢአት ቢወድቅ፤ይህንን አድርግ ይህንን አታድርግ የሚል የተጻፈ ህግ /ህገ ኦሪትን/ ሰጠው፡፡በዚህ ብቻ አላበቃም፤እራሱ እግዚአብሔር ወልድ ወደዚች ምድር መጥቶ ለሰው ልጅ የቤዛነቱንና የአርአያነት ሥራውን ፈጸሞለታል፡፡ ጌታችን መድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በጽንስ ጀምሮ በመሰቀል የፈጸመውን የቤዛነቱን ሥራ እፁብ! ድንቅ! ብሎ ከማመስገን በስተቀር በዚች አጭር ጽሁፍ የምንለው ነገር አይኖረንም፡፡በአርአያነት/በምሳሌነት/ ሥራው ግን ከኃጢአት በስተቀር የሰውን ህግ ሁሉ ፈጽሞ እኛም እንድንከተለው አዝዞናል፡፡በእኔ ያመነ እኔ የምሰራውን ሁሉ ያደርጋል፤እንደውም የበለጠ ያደርጋል ብሎ፡፡ዮሐ.14፥12፡፡

Sunday, March 6, 2016

“ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ ፡፡” ማቴ.7፤15 ክፍል አስራ አራት

የተወደዳችሁ አንባብያን!
እንደምን ሰነበታችሁ ?
‹‹ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ›› በሚለው ዐቢይ ርዕስ ሥር፤ በክፍል አስራ አንድና አስራ ሁለት ላይ ወቅታዊ የሆነውን የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን  የውስጥና የውጪ መናፍቃን/ተሐድሶዎች/ ችግር በማስመልከት ማህበረ ቅዱሳን በድረ-ገጹ (www.eotcmk.org) ያቀረበውን ዘገባ ተመልክታችሁ ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኛችሁ በመገመት፤በመቀጠል ደግሞ "አምልኮተ ሰይጣን - ፍጻሜ “ተሐድሶ”?"
በሚለው ርዕስ ከማህበረ ቅዱሳን ድረ-ገጽ ያገኘነውን በማስረጃ የተደገፈ ዘገባ እነሆ ብለናል፡፡

መልካም ንባብ!